Skip to main content
x

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ራስ ምታት

መስረከም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪ ዋጋን የሚያመለክተው የባንኮች ሰንጠረዥ አንድ ዶላር በ23 ብር ከ85 ሳንቲም በሚመነዘርበት ወቅት፣ የጥቁር ገበያ ከፍተኛ የምንዛሪ ዋጋ ከ27 ብር ከ50 ሳንቲም አልበለጠም ነበር፡፡ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ የብር የምንዛሪ ለውጥ ስለመደረጉ የሚያመለክተው አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ፣ ባንኮች አንዱን ዶላር በ26.70 ብር በመመንዘር በአዲሱ የምንዛሪ ለውጥ ግብይት ማድረግ እንደጀመሩ የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ ወደ 30 ብር ከፍ ሊል ችሏል፡፡

በ26.70 ብር የተጀመረው የባንኮች ግብይት ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የባንኮች የምንዛሪ ዋጋ እንደሚያሳየው የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ 27 ብር ከ22 ሳንቲም ሲደርስ፣ የመሸጫ ዋጋው ደግሞ 27 ብር ከ77 ሳንቲም ሆኗል፡፡ በአንፃሩ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር እስከ 34 ብር ከ10 ሳንቲም እየተመነዘረ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ብቻ በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የዶላር ምንዛሪ ዋጋ እየሰፋ መምጣቱን አመላክቷል፡፡ ይህ መረጃ የሚያመለክተው ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ እስከ እዚህ ሳምንት አጋማሽ ድረስ በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ከሦስት ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ነው፡፡ በባንኮች በኩል ደግሞ ከጥቅምት 1 ቀን ወዲህ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ያሳየው ጭማሪ ከአንድ ብር ያነሰ ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት በጥቁር ገበያና በባንኮች መካከል ያለውን የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ከሰባት ብር በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የብር የምንዛሪ ለውጡ ከመደረጉ በፊት በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ከአምስት ብር ያነሰ ሲሆን፣ አሁን የታየው ልዩነት በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ እየጨመረ በባንኮች ግን ዕድገቱ አነስተኛ ሆኖ መቀጠሉን ነው፡፡ ይህ ጤናማ አካሄድ መሆኑ ቢታመንም፣ በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ጤናማ ያለመሆኑን ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡

በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄዱ ምን ያሳያል? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ ቆስጠንጢኖስ በረሃ (ዶ/ር)፣ በባንኮችና በጥቁር ገበያ ያለው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ዋነኛ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ነው ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የባንክ ባለሙያ በባንኮችና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት ባንኮች በቂ የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ ያለመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ እያደገ በመጣ ቁጥርና ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎችን በጥያቄያቸው መሠረት ማስተናገድ አለመቻል፣ ፊታቸውን ወደ ጥቁር ገበያ እንዲያዞሩ የሚያስገድዳቸው በመሆኑ የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ዋጋ ከፍ እያለ ልዩነቱ እንዲሰፋ አድርጎታል፡፡

በጥቁር ገበያ ያለው የምንዛሪ ዋጋ በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት በፍጥነት እያደገ የመጣውም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በማደጉ ብቻ ሳይሆን፣ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ላይ የወጣው መመርያ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች በቶሎ ባለማስተናገዳቸው ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደውን እንዲጨምር በማድረጉ ይህንን የተመለከቱ የጥቁር ገበያ ተዋንያኖች ዋጋውን እያሳደጉ ሄደዋል የሚል ግምት አላቸው፡፡

አሁንም ችግሩን ለማቃለልና በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ካልተቻለ የጥቁር ገበያው ዋጋ ከፍ ሊል የሚችለበት ዕድል እንደሚኖርም ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

ባንኮች አሁን አላቸው የሚባለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያለውን ፍላጎት ለመሙላት ቀርቶ መሠረታዊ የሚባሉ እንደ መድኃኒት ያሉ ዕቃዎችን እንኳን በአግባቡ ለማስመጣት ባለማስቻሉ፣ የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያሳይም እኝሁ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

ሰሞኑን የተለያዩ የአገር ውስጥ የመድኃኒት የአምራቾችም ለመድኃኒት ማምረቻ የሚሆኑትን ጥሬ ዕቃዎች ለማስገባት ባጋጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ፣ ማምረት የሚገባቸውን ያህል ባለማምረታቸው ምክንያት የአንዳንድ መድኃኒቶች እጥረት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አሁን የገጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቶሎ የማይፈታላቸው ከሆነም፣ በመድኃኒት አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው እየጎላ እንደሚመጣ ያላቸውን ሥጋት እየጠቀሱ ነው፡፡ በመድኃኒት ዙሪያ ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ነው የተባለው ችግር፣ በአገር ውስጥ አምራቾች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ከውጭ በሚያስገቡት ላይ ጭምር እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡

 አሁን ከአቅማቸው በታች እያመረቱ እንደሚገኙ የሚገልጹት እነዚህ ፋብሪካዎች፣ ሌላው ቀርቶ ውለታ የገቡበትን መድኃኒት ለማቅረብ እንዳላስቻላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመንተራስ ብሔራዊ ባንክ ለእነዚህ ምርቶች የሚሆን ጥሬ ዕቃ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችላቸውን የውጭ ምንዛሪ ሊፈቅድ ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን በተመለከተ በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው መመርያ ላይ ግን ባንኮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያስተናግዷቸው ከጠቀሳቸው ገቢ ምርቶች ውስጥ አንዱ መድኃኒት እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም፡፡  

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽ ሲሆን፣ በተለይ የብር ምንዛሪ ለውጡ ሲደረግ ዋነኛ ዓላማ ያደረገው የወጪ ንግዱን ለማበረታታት እንደሆነ ያስታወሱት ቆስጠንጢኖስ፣ አሁን እንደምናየው ግን የምንዛሪ ለውጡን ዋነኛ ምክንያት ያሳካ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2010 ላይ ተመሳሳይ ምክንያት ተሰጥቶ የብር የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ የወጪ ንግዱ ለውጥ አላመጣም፡፡ አሁንም የሚታየው ይህ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ የተፈለገውን ግን መትቷል ለማለት እንደሚያስቸግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ አሁንም የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲው ሊፈተሽ የሚገባ መሆኑን ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዶላር እየወደቀ በኢትዮጵያ ደግሞ የዶላር ምንዛሪ እያደገ መምጣቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የብር ምንዛሪ ለውጡ ሲደረግ በሕጋዊና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ያስችላል ቢባልም፣ በተቃራኒው ከቀድሞው በበለጠ ልዩነቱ መስፋቱ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጡ የታሰበለትን ዓላማ ያለማሳከቱን ያሳያል ተብሏል፡፡

ከዚህም ቀደም የብር የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ ዓላማ ያደረገው የወጪ ንግዱን ለማበረታታት ነበር፡፡ አሁንም በተመሳሳይ ይህ ተገልጿል፡፡ ለውጡ ምን ያህል ነው ሲባል ግን በተጨባጭ አለመታየቱ፣ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥና የወጪ ንግድ የሚተሳሰሩበት ምክንያት ውጤታማ አለመሆኑን ይጠቁማል፡፡  

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በሌላም መንገድ እየተገለጸ ሲሆን፣ አሁን እየተሰማ እንዳለው ባንኮች ለውጭ ተጓዦች ይሰጡ የነበሩትን የገንዘብ መጠን መቀነሳቸው ነው፡፡ በመሆኑም ተጓዦች ፊታቸውን ወደ ጥቁር ገበያ በማዞራቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋን ከፍ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

ሌላው ለውጭ ተጓዦች ተቀናንሶ የሚፈቀደውንም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባንኮች እየጠየቁ ያሉት ቅድመ ሁኔታዎችም ሁኔታውን አባብሶታል፡፡ የባንኩ ደንበኛ መሆን የባንኩ ተበዳሪና አስቀማጭ እንደሆነ መጠየቃቸውም ለጥቁር ገበያው የተመቸ ሆኗል፡፡ እንዳነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያ ገለጻ ለውጭ ተጓዦች የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ አቅም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለተለያዩ ጉዞዎች የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁትን ሁሉ ለማስተናገድ ስለማይቻል፣ የግድ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመለየት ሥራም ይጠይቃል፡፡ ለሕክምናና በጣም ለአሳማኝ ጉዳዮች በመለየት ይሰጣል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የሚፈቀደው ጣራ ድረስ መስጠት አይቻልም፡፡ በርካታ ባንኮች ወደ 1,000 ዶላር አካባቢ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያም ያነሰ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ካለ ለውጭ ተጓዦች እስከ 4,000 ዶላር ይሰጥ እንደነበር ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ ለአንዳንድ ተጓዦች የሚፈቅዱት እስከ 200 ዶላር ብቻ ሲሆን፣ ለተለያዩ ቢዝነሶች የሚጓዙ መንገደኞች ሁኔታው እያሳሰባቸው እንደሆነ እየገለጹ ነው፡፡ ይህ አሠራር የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ለመጠቀምና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ባንኮች በዚሁ አግባብ መሠረት እንዲሠሩ ለማድረግ ነው ቢባልም፣ ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ ሊሰጣቸው የሚገቡና እንደ መድኃኒት ፋብሪካዎች የገጠማቸው ችግር አንዳንድ መድኃኒቶች በገበያ ውስጥ እንዳይገኙ ምክንያት እየሆነ ስለመምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ እንዳመለከቱት በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሳቢያ፣ አንድ መድኃኒት ገበያ ላይ ማግኘት አልተቻለም መባሉና አንድ የቢራ ፋብሪካ ማስፋፊያ ተፈቀደ የተባለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ግርታ ፈጥሮባቸዋል፡፡ የትኛው ነው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው? በማለትም ይጠቅሳሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ አዳዲስ አሠራሮችን መተግበር  እንደ አንድ አማራጭ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ከዶላር እጥረቱ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰድ እንዳለበት የጠቀሱት ቆስጠንጢኖስ፣ አንዱ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ገታ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡

ከህዳሴ ግድብ ሌላ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ተቀዛቅዘው፣ የውጭ ምንዛሪው መሠረታዊ ለሆኑ ዕቃዎች እንዲውል በማድረግ ችግሩን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው፣ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆንም ገልጸዋል፡፡