Skip to main content
x
ሶማሊያ ከመዳረሻ አገሮች አውራ በሆነችበት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የ1.35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተመዘገበ

ሶማሊያ ከመዳረሻ አገሮች አውራ በሆነችበት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የ1.35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተመዘገበ

በዚህ ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ዘርፉ የ1.35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ከአሥሩ ዋና ዋና መዳረሻ አገሮች ውስጥ ሶማሊያ በቻይና ተበልጣ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የወጪ ንግድ መዳረሻ አገር ተብላለች፡፡

ምንም እንኳ ከሌሎች ጊዜያት በተለይም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የዘንድሮው ገቢ መጠነኛ መሻሻል እንደታየበት የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ያመላክታል፡፡ ይኸውም የ9.3 በመቶ ወይም የ114 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ የታየበት በመሆኑ ነው፡፡ በአንፃሩ ዓምና የተገኘው ጠቅላላ ገቢ 2.23 ቢሊዮን ዶላር እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ከታቀደው አኳያ ሲታይ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ አፈጻጸም ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራትም ይገኛል ተብሎ ከታሰበው ገቢ በ855 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ገቢ ተመዝግቧል፡፡ ይጠበቅ የነበረው ገቢ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ሆኖም በ1.35 ቢሊዮን ዶላር ተወስኗል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንደ ወትሮው ማሽቆልቆሉ አልቀረም፡፡ በንግድ ሚኒስቴር የተጠቀሰው ምክንያት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ያስከተለው ጫና በወጪ ንግዱ እንቅስቃሴ ላይ ጎልቶ መታየቱን ነው፡፡ ይሁንና ከፍተኛ ማሽቆልቆል ካስመዘገቡት ንዑስ ዘርፎች ውስጥ የማዕድን ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ከዚህ ዘርፍ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ከ58 ሚሊዮን ዶላር አልዘለለም፡፡

ከማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች የተገኘውም ቢሆን ከሚጠበቀውና በመንግሥት ሲገለጽ ከነበረው አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በስድስቱ ወራት ከ224 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ገቢ በማስገኘት ግማሽ ዓመቱን አገባዷል፡፡ ይሁንና ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በተለይም ከጨርቃ ጨርቅና አልበሳት የሚጠበቀው ዓመታዊ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ለዚህም ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በዓመት እንደሚገኝ ሲገለጽ መቆየቱ አንዱ ዋቢ ነው፡፡

ከሌሎቹ ዘርፎች ይልቅ ሳያቋርጥ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ በመደገፍ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚገኘው የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ከ71 በመቶ በላይ በማስመዝገብ ከታቀደለት የ1.43 ቢሊዮን ዶላር የገቢ መጠን ውስጥ የ1.03 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘው ግብርናው ነው፡፡ ቡና ትልቁን ገቢ ሲያስመዘግብ፣ የቅባት እህሎች፣ ሻይ ቅጠል፣ ያለቀለት ቆዳና ጫት ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምርቶች የሚቀበሉ 137 የተመዘገቡ አገሮች እንዳሉ የንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ግንባር ቀደምት በመሆኑ አሥር አገሮች ሲመደቡ፣ ሶማሊያ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ተቀባይ አገር ነች፡፡ በቻይና የተቀደመችው ሶማሊያ፣ ዋናው የገቢ ሸቀጧ ጫት ነው፡፡ ከጫት ባሻገር ግን ፍራፍሬና አትክልት፣ የቁም እንስሳት፣ ኬሚካልና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ ቅመማቅመም፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች፣ ባህር ዛፍ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦና የመሳሰሉት ምርቶች ወደ ሶማሊያ ተልከዋል፡፡ በዚህም ከ97 ሺሕ ቶን በላይ ግምት ያላቸው ምርቶች 120 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማስገኘታቸው ታውቋል፡፡ ሶማሊያ ባለፈው ዓመት ከአሥሩ አገሮች ቀዳሚዋ እንደነበረች ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአንፃሩ ወደ ቻይና ከተላኩት የቅባት እህሎች፣ ያለቀለት ቆዳ፣ ጫማ፣ ታንታለም፣ ቡና እና ሌሎችም ምርቶች ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ በመጠን ረገድም 106 ሺሕ ቶን ገደማ ግምት ያላቸው ምርቶች ወደ ቻይና ሔደዋል፡፡ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመን፣ ጂቡቲ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ እስራኤልና ጃፓን፣ ከቻይናና ሶማሊያ በመከተል እንደቅደም ተከተላቸው እስከ አሥር ያለውን ደረጃ በመያዝ ዋና ዋና የኢትዮጵያ ሸቀጦች መዳረሻዎች ሆነዋል፡፡