Skip to main content
x

ኢኮኖሚውም የፖለቲካውን ትኩረት ይሻል

በሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ታውጀዋል፡፡ ይህም መረጋጋት እንደሌለ ያመላክታል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው አዋጅ ሥራ ላይ መዋሉ ከተነገረ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል፡፡ የቀደመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፈጠረው ውጥረት ሳቢያ ኢኮኖሚው ከደረሰበት ተፅዕኖ ሳያገግም፣ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ ላይ መዋሉ ሊፈጥር የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡

በእርግጥ በመጀመርያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ በቆየባቸው አሥር ወራት ውስጥ ኢኮኖሚው የተፈራውን ያህል ተፅዕኖ አልደረሰበትም የሚል መረጃ መንግሥት ሲቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህንን አባባል አምኖ መቀበል ግን አዳጋች ነበር፡፡ ከመንግሥት በኩል የተባለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠንካራ ስለነበር በአዋጁ ኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አላሳረፈም፡፡

ይህም ቢባል ግን የዓምናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን ማቀዛቀዙ አልቀረም፡፡ እንደልብ ለመሥራት የማያስችሉ ድባቦችንና ሥጋቶችን ፈጥሮ ስለነበር፣ ኢኮኖሚው ላይ የነበረው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ ወደ ተግባር እንዲገቡ የታቀዱ የተለያዩ የቢዝነስ ስምምነቶች ቁርጡ ይታወቅ በሚል ሥጋት ለይደር የተባሉበትን አጋጣሚ መፍጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም ሊባል አይችልም፡፡

ሌላው ቀርቶ አዋጁን ለመተግበር ሲባል ለአስፈጻሚ አካላት በአበል ሰበብ፣ ለተለያዩ ሥራ ማስኬጃዎች እየተባለ የወጣው ወጪም ስሌት ውስጥ ቢገባ ያልታሰበ ወጪ ነው፡፡ ያልታሰቡ ወጪዎች ለኢኮኖሚው መዋል የነበረበት ሀብትና ገንዘብ አዋጁን ለማስተግበር ሲባል ወደዚህ እንዲያዘነብል በመደረጉ ነው፡፡ ባለሙያዎችም ይህንኑ ይተነትናሉ፡፡ ለልማት መዋል ያለበት ሀብት ብጥብጥ ለማስቆም፣ ሰላም ለማስፈን እየተባለ ወደዚህ አቅጣጫ እንዲሄድ መደረጉ አይቀሬ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ዜጎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ አዋጁ ጥበቃ የሚያደርግ፣ ሥጋት ውስጥ እንዳይገቡ በማሰብ መውጣቱ ቢታወቅም፣ ዜጎች እንደቀድሞው ባለ የሥራ መንፈስ የዕለት ተግባራቸውን ለመወጣት አይቸገሩም ብሎ ማመን ይቸግራል፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ አላደረሰም ብሎ መደምደም   አይቻልም፡፡

የአዲሱ አዋጅ መታወጅ፣ ዜጎች ያለ ፀጥታ ሥጋት የዕለት ተግባራቸውን እንዲከናውኑ የሚደግፍ ነው በሚለው ላይ መስማማት ቢቻል እንኳ፣ ኢኮኖሚውና ቢዝነሱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሳያሳርፍ ለስድስት ወራት ይቆያል ማለት አዳጋች ነው፡፡ ምክንያቱም ገና ከአሁኑ የምናያቸው ምልክቶች ስላሉ ነው፡፡ አንዳንድ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ ነው፡፡ ለዜጎችም ሆነ ለንግድ ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማቶችና ለመሳሰሉት አዋጁ ጥበቃ እንደሚያደርግ ቢገለጽም፣ ቢዝነሶች ግን ከሥጋት አልዳኑም፡፡ ተፅዕኖ አለ፡፡ ለምሳሌ ዕቃዎችን ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ሥራ ስለመቀዝቀዙ ይናገራሉ፡፡

ይህ ከሆነ በቂ ምርት ወደየሚፈለገው ቦታ አይደርስም ወይም እየደረሰ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ከፀጥታ ሥጋት ቢድን እንኳ ከምርት እጦትና ከዋጋ ንረት ሥጋት ሊድን አልቻለም ማለት ነው፡፡ ነገ የሚመጣውና የሚሆነው አይታወቅም እየተባለ በየቦታው የቆሙ ከባድ ተሽከርካሪዎች አዋጁ ከወጣ በኋላም ሆነ ከአዋጁ በፊት ከእንቅስቃሴ ለመቆጠብ ሲገደዱ መታየታቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አለው፡፡

በጥቅሉ ሲታይ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ለአዋጁ መውጣት መንስዔ የሆኑ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች የዚህችን አገር ኢኮኖሚና የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች እየኮረኮሙ ስለመሆናቸው ሌላው ማስረጃ የቱሪዝም ዘርፉ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ አገሮች የጉዞ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል፡፡ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ማስጠንቀቃቸው አስጊ ነው፡፡ በሥጋት ወረዳ የተፈረጁ አካባቢዎችን የሚጎበኝ ቱሪስት አይኖርም፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው፤›› እንዲሉ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከልክ በላይ በማግነን ውስጣዊም ውጫዊም ሥጋቶችን የሚያባብሱ በርካታ ኩነቶች እየታዩ ነው፡፡  

በአዲስ አበባ ከተማ በሚሰናዳው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ለመሳተፍ ቃል የገቡ ኩባንያዎች የአሪቱን ሁኔታ በማየት ከተሳትፎ መቅረታቸውም የችግሩ ማሳያ ነው፡፡ በተለያዩ ቢዝነሶች ውስጥ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ኩባንያዎች ወቅታዊውን ችግር ከግምት በማስገባት ፕሮግራማቸውን ለመቀየር የሚያስገድድ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱ ይገመታል፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ቀስ በቀስ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ቀላል እንደማይሆን ያሳየናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ከአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተያይዟል፡፡ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ከአገር ውስጥ ባሻገር ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በጓሮ እየሾለኩ በገፍ የሚወጡትም እንዲህ ባለው ወቅት ለመሆኑ የዓምናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይረሴ ነው፡፡ የወጪ ንግዱ ከሚጠበቀው በታች ወርዶ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ላይ ለመገታቱ አዋጁ አስተዋጽኦ አልነበረውም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህም ሌላ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ወሳኝ የተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመግባት የሚያመርቱ ኩባንያዎች በሚፈለገው ቁጥር ልክ አለመምጣታቸው ከዚሁ ለአዋጁና ካለመረጋጋቱ ጋር ይያያዛል፡፡

የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ይመረቃሉ ተብለው ሲጠበቁ፣ ያለመመረቃቸው ከዚሁ ችግር ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ አለመረጋጋቱም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ላይ ውሳኔ ሰጪ ባለሥልጣናት በልማት ሥራዎች ላይ ጊዜያቸውን ከማጥፋት እየቦዘኑ በፀጥታው ችግር ላይ እየተሰበሰቡ የሚያባክኑት ጊዜ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደፈጠረ ሲታሰብ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት እንደቀደመው ጊዜ ይህንን ያህል በመቶ እያደገ ነው የሚሉበት አንደበት ሊቸግራቸው እንደሚችል አመላካች ነው፡፡

መንግሥት በውስጡ ያሉበትን ችግሮች፣ በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድም የሚነሳውን የፖለቲካ ጥያቄ በወቅቱ በመመለስ  የኢኮኖሚውን አያያዝ እንዲያስተካክል ይመከራል፡፡ ወደ ኋላ መመለስ አሁን ከሚታየውም ፖለቲካዊ ችግር በላይ የባሰ ቀውስ ሊያስከትል ስለሚችል፣ ለፖለቲካው የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለኢኮኖሚውም አይንፈገው፡፡