Skip to main content
x
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓምና እና ዘንድሮ
የመከላከያ ሚኒስትርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓምና እና ዘንድሮ

ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በልማትና በማኅበራዊ ጉዳዮች አበረታች ስኬት እንዳስመዘገበች ሲነገር ቢሰማም፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት አያያዝ በርካታ ችግሮች እንዳሉባት በስፋት የመነጋገሪያ አጀንዳ ነበር፣ አሁንም ነው፡፡

በደርግ ሥርዓት ወቅት ከነበረው የጦርነት አባዜ ወጥታ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባት አገር እንደሆነች ሲነገር ቢሰማም አሁንም የዴሞክራሲ ሥርዓትን ከማጎልበት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማክበርና ከማስከበር፣ እንዲሁም በአገሪቱ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ከመሥራት አኳያ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ችግሮቹም እየተደራረቡ እዚህ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ፣ በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ተስተውሏል፡፡ ለጥያቄዎቻቸው መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ ሳቢያም ወጣቶች ተቃውሟቸውን ወደ አደባባይ ይዘው በወጡበት ወቅት፣ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በሚፈጠር ግጭት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ 

ከቅማንት የማንነት ጥያቄ እስከ ‘ጠገዴና ፀገዴ’ ይገባኛል፣ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንና ልዩ ጥቅም እስከ የታሰሩ ዜጎች ይፈቱ፣ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እስከ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ፖለቲካዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ በተነሱ ጥያቄዎች በአገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ተከስቷል፡፡ ቀውሱ አሁንም ድረስ አልበረደም፡፡

በ2008 ዓ.ም. አጋማሽ አካባቢ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ሳቢያ በተቀሰቀሰ ቀውስ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በወጣቶች በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ የዜጎች ንብረት ከመውደሙም በላይ የሕይወትና የአካል ጉዳት አስከትሏል፡፡ በወቅቱ የነበረው ግጭት ወደ 2009 ዓ.ም. ተሻግሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሎ አልፏል፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ከላይ ታች እያልኩ ነው ቢልም፣ መፍታት ባለመቻሉ በ2009 ዓ.ም. መግቢያ አካባቢ የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡

በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት ከጎንደር እስከ ባህር ዳር፣ ከአዳማ እስከ ወለጋና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በነበረው ቀውስ ሳቢያ በርካቶች ሞተዋል፡፡ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችና ፋብሪካዎች ለውድመት ተዳርገዋል፡፡

በርካታ የመንግሥት ተቋማትና ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ ወደ አመድነት ተቀይረዋል፡፡ ይህን ችግር ለማስቆምና በአገሪቱ መረጋጋት ለመፍጠር ተብሎም፣ መንግሥት መደበኛውን ሕግ ማስከበር፣ በመተው ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጣ፡፡

በ2009 ዓ.ም. መስከረም መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ክልከላ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ጽሑፎችን ማተም፣ ማባዛትና ማሠራጨት፣ በቡድን መደራጀት፣ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ አለመንቀሳቀስ፣ ስለታም ነገሮችን ይዞ አለመንቀሳቀስ፣ የተጠረጠረን ሰው በኮማንድ ፖስቱ አማካይነት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈተሽ፣ ዘርን፣ ቋንቋንና ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸም፣ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖችና ድርጅቶች ጋር ማበር፣ የሕግ አስከባሪዎችን እንቅስቃሴ ማወክ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማወክ፣ ያልተፈቀደ ሠልፍ ማካሄድ፣ የአደባባይ ስብሰባና ሌሎች ተግባራትን ማካሄድ፣ ወዘተ የተከለከሉ ጉዳዮች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ደግሞ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

በወቅቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ታይቶ ነበር፡፡ በዋናነት ደግሞ ትልልቅ ፋብሪካዎችንና ኢንቨስትመንቶችን በእሳት ከመውደም መታደግ እንደተቻለ ተነግሯል፡፡ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ የመለቀቅ መጠንም ቀንሶ ተስተውሏል፡፡ መንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎትን በከፊል ያቋረጠበት ጊዜም እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ለስድስት ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ፣ እንደገና ለአራት ወራት ተራዝሞ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለአራት ወራት ባራዘመበት ወቅት የመከላከያ ሚኒስትሩና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባቀረቡት ሪፖርት፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በአገሪቱ የነበረው የፀጥታ ችግር መፈታት መቻሉን ጠቁመው ነበር፡፡ ነገር ግን የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ለምክር ቤቱ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ጥያቄው ተቀባይነት እንዳገኘና ለተጨማሪ አራት ወራት እንደተራዘመ አይዘነጋም፡፡  

በአገሪቱ ለስድስት ወራት ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጨማሪ አራት ወራት ታክሎበት ወደ አሥር ወራት ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው አዋጅ የተነሳው ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ አቶ ሲራጅ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አሁን በአገራችን አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የሚቀሩ ትናንሽ ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በመደበኛው የሕግ አግባብ ማስተካከል ይቻላል፤›› ብለው ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም ምክር ቤቱ ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲነሳ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ አገሪቱ በሰላም መቆየት የቻለችው ለጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ2010 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት አገሪቱ እንደገና ወደ ሌላ ቀውስ ውስጥ ገባች፡፡ በዚህ ቀውስ ሳቢያም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የአገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እንደተናገሩ ይታወሳል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች በምግብና በውኃ እጥረት ከመቸገራቸውም በላይ፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከዚህ ግጭት ጋር በተያያዘም በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር፡፡ በዚህ ተቃውሞ ሳቢያም በርካታ ወጣቶች ለሕልፈተ ሕይወትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ ሌላም በአገሪቱ ባሉ አሥራ ዘጠኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚማሩ ተማሪዎች መካከል ብሔር ተኮር ግጭት ተከስቶ የአራት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡ አንዴ ረገብ አንዴ ደግሞ ጋል የሚለውን የአገሪቱን ቀውስ ማስቆም ባለመቻሉ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባ በማካሄድ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የስድስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደታወጀ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ አቶ ሲራጅ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ አቶ ሲራጅ እንደተናገሩት፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ አዋጁ በአጠቃላይ 18 ክልከላዎችን አካቷል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈጸም፣ የሕዝቦችን መቻቻልና አንድነት የሚጎዳ ተግባር መፈጸም፣ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች፣ አመራሮችና ፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ፣ የአሸባሪ ድርጅቶችን ዓላማ ማስፈጸም፣ ጽሑፎችን መያዝ፣ ማስተዋወቅ፣ የትራንስፖርትን እንቅስቃሴ ማወክ፣ መንገድ መዝጋት፣ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ታሪፍ መጨመር፣ የሕዝብ አገልግሎትን ማቋረጥ፣ የንግድ ተቋማትን መዝጋት፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ሕገ አስከባሪዎች የሚሰጡትን ትዕዛዝ አለማክበር፣ ለፍተ አለመተባበር፣ በሕግ አስከባሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸም፣ ያልተፈቀደ ሠልፍ ማድረግ፣ ዓድማ ማድረግ፣ በአደባባይ ሠልፍና ተቃውሞ ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማት ዓድማ ማድረግ፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች ዓድማ ማድረግ፣ ባህላዊ፣ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን ማወክ፣ ከሰዓት ዕላፊ በኋላ መንቀሳቀስ፣ ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ ዜጎች ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እነዚህን ተግባራት ከመፈጸም እንዲቆጠቡና በአስቸኳይ አዋጁ ኮማንድ ፖስት የወጣውን መመርያ እንዲያከብሩ ተደንግጓል፡፡

የዓምናውና የዘንድሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ያካተቷቸው ክልከላዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት ያላቸው እንደሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ዘለዓለም ብዙነህ ያለፈውና የዘንድሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተመሳሳይ ናቸው ይላሉ፡፡

ልዩነታቸው የዓምናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኢሕአዴግ በራሱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ውዝግብ ባልገባበት ጊዜ የታወጀ እንደነበር ጠቁመው፣ የአሁኑ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልቀቂያ ጥያቄ ባቀረቡበትና የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሽኩቻ ውስጥ በገቡበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአሥራ አምስት ቀናት መፅደቅ እንዳለበት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ላይ ተደንግጓል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በሥራ ላይ ከሆኑ ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአርባ ስምንት ሰዓት መፀደቅ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ቀርቦ ፀድቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በቀናት ውስጥ፣ በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ተስተውለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በነቀምቴና በደምቢዶሎ ከተሞች በተነሳ ግጭት የአንድ ሰው ሕይወት እንዳለፈ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ ከዚህ ግጭት ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ወጣቶች በፀጥታ አካላት ላይ ጥቃት ለማድረስ ቦምብ ወርውረዋል ብሏል፡፡ መግለጫው አክሎ እንደጠቆመው፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉ መመርያዎችን በሚጥሱ ኃይሎች ላይ የፀጥታ አካላት ዕርምጃ እንዲወስዱ መመርያ ተላልፏል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎትን ማቋረጥ በአስቸኳይ አዋጁ ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

አቶ ሲራጅ በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ የቻለበት ምክንያት አገሪቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስተዳደር ባለመቻሉ እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ሊጎዳው እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

በአገሪቱ ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች የተቃውሞ መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ይህን መሰል መግለጫ ማውጣት ገንቢም ጠቃሚም አይደለም፤›› ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡