Skip to main content
x
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት መሬት የሚቀርብበትን መንገድ እንደሚወስን ይጠበቃል
አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት መሬት የሚቀርብበትን መንገድ እንደሚወስን ይጠበቃል

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣውን አዋጅ በድጋሚ ለማሻሻል ባዘጋጀው ረቂቅ፣ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሬት የሚያገኙበትን መንገድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲወስን ክፍቱን መተውን አመለከተ፡፡ ከዚህ ጋር ነባር ባለይዞታዎች በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው አካባቢያቸውን ለማልማት ሲጠይቁ መስተናገድ እንዲችሉ ማካተቱን አስታውቋል፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዙ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 7 እና ይህንኑ ተከትሎ በወጣው የሊዝ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 11/2004 አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 2 በግልጽ እንደተደነገገው፣ የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ ነው፡፡

ነገር ግን በሊዝ አፈጻጸም መመርያ አንቀጽ 34 በከተማ አስተዳደር ከንቲባ እየታየ ለካቢኔ ለሚመሩ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚውሉ ቦታዎች፣ በዝርዝር መሥፈርቱና በቦታ አመዳደብ ሒደቱ ራሱን በቻለ መመርያ የሚወስን መሆኑ በተደነገገው መሠረት ልዩ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች ተብሎ መመርያ ቁጥር 15/2005 ቢወጣም፣ መመርያው ግን ከሊዝ አዋጁ ጋር ተጣርሷል፡፡

በዚህ ምክንያት በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ከኀዳር 2004 ዓ.ም. ወዲህ ላሉት ስድስት ዓመታት የባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ ልዩ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች የገበያ ማዕከላት ግንባታ የመሬት ጥያቄዎች አላስተናገደችም፡፡

ይህ የአሠራር ክፍተት ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየ ሲሆን፣ አስተዳደሩም ፕሮጀክቶቹ በልዩ ጨረታ ይስተናገዱ ሲል ከርሟል፡፡ ነገር ግን ባለፉት ስድስት ዓመታት ልዩ ጨረታ የወጣው አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ አሠራሩ የዘርፉን ተዋናዮች ሲያሳዝን ነበር፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የመሬት አቅርቦት አንፃራዊ ገጽታ አለው፡፡ ለትልልቅ ከተሞችና ለትንንሽ ከተሞች የተለየ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

‹‹እነዚህ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሊዝ አዋጁ የሚስተናገዱበት በር ሊኖር ይገባል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ይኼ ሐሳብ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተነጋግሮ የሚቀበለውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያፀድቀው ሐሳብ ገዥ ይሆናል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው ሌላው ጉዳይ በአክሲዮን የተደራጁ ነባር ነዋሪዎች ይዞታቸውን አንድ ላይ አድርገው ለማልማት ጥያቄ ቢያቀርቡም መስተናገድ አለመቻላቸው ነው፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ነጋዴዎች በያሉበት የገበያ ሥፍራ በአክሲዮን ተደራጅተው፣ አሥር የሚጠጉ ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት የመሬት ጥያቄ ቢያቀርቡም ሊስተናገዱ አልቻሉም፡፡

ማኅበራቱ ይህንን ችግር ከመንግሥት ጋር ተወያይተው ለመፍታት የአክሲዮን ማኅበራት ኅብረት በማቋቋም፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በዝግ ሒሳብ ማስቀመጣቸውን በመግለጽ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቢቆዩም ሊስተናገዱ ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ነገር ግን በረቂቅ አዋጁ አቅም ያላቸው ነባር ባለይዞታዎች ማልማት ከቻሉ እንዲስተናገዱ የሚደነግግ አንቀጽ ማካተቱን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ የሊዝ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከገባ የቆየ ቢሆንም፣ እስካሁን ለውይይት አልቀረበም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተፈጠረው አገራዊ ችግር በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በረቂቅ የሊዝ አዋጁ ላይ ከሕዝብ ጋር ውይይት ስላልተደረገበት እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡