Skip to main content
x
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና አሳሳቢ ችግሮች ላይ ያተኩራል
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርና አሳሳቢ ችግሮች ላይ ያተኩራል

  • ከግጭት እስከ ቻይና ብድር ዕዳ ያሉ ጉዳዮችም እንደሚቃኙ ይጠበቃል

ከረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን፣ በጉብኝታቸው ወቅት ትኩረት ከሚያደርጉባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሽግግር ሒደቱን የተመለከተውና ከወቅቱ አሳሳቢ ችግሮች ከዋና ዋና ነጥቦች መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ሰኞ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በስልክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተናሩት፣ ሬክስ ቲለርሰን ትኩረት ከሚያደርጉባቸውና ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ከሚነጋገሩባቸው ነጥቦች መካከል በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም የሚደረገው እንቅስቃሴና የሽግግር ሒደቱን የሚመለከት ይሆናል፡፡ ‹‹በኢትየጵያ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሽግግር ሒደቱን የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ጨምሮ ተቋማትን ማጠናከርም በትኩረት የምንመለከተው ጉዳይ ነው፤›› ያሉት ያማማቶ፣ በአሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተፈጠሩትን ችግሮችን መንግሥታቸው እየተመለከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሥልጣን ለመልቀቅ ከተገደዱባቸው ምክንያቶች ውስጥ በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣው የፖለቲካ ቀውስ፣ ቀውሱን ተከትሎም በየአካባቢው የሚታየው ግጭት ዋናው መንስዔ ነው፡፡ አምባሳደር ያማማቶም በኢትዮጵያ የተከሰተው ፖለቲካዊ ሁኔታ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት በአሜሪካ መንግሥት ትኩረት እንደተሰጠው፣ በተለይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ሁኔታ መንግሥታቸውን እንደሚያሳስበው አምባሳደር ያማማቶ አስታውቀዋል፡፡ 

‹‹ምናልባትም እስከ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የተፈናቀሉበትን ጉዳይ እያየን ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ የተፈጠሩትን ውጥረቶች ለማርገብ አሜሪካ እንዴት ድጋፍ ልታደርግ ስለምትችልበት ጉዳይም እየመከረች እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኃላፊነታቸውን እንደለቀቁ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከመሀላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም ላይ ታች እያሉ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ተመሳሳይ ችግሮች በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እንደሚታዩ ያስታወሱት ያማማቶ፣ ከመሬት ልማትና ከመሬት ባለመብትነት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የሰብዓዊ መብት አንዱ እንደሆነም አውስተዋል፡፡  በመሆኑም የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ሥራ እንዲከናወን መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

የሬክስ ቲለርሰን ጉብኝት ከሩስያ ውጭ የጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መገጣጠሙ የአጋጣሚ ወይም በሁለቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ስለመኖሩ አመላካች ነው ወይ? በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ያማማቶ በሰጡት ምላሽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በተመሳሳይ ወቅት በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ እግረ መንገዳቸውን በማስታወስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሻቸውም የሬክስ ቲለርሰን ጉብኝት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ከአፍሪካ ኅብረት ኃላፊዎች ጋር መነጋገር ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ አጽንኦት የሰጡበት ጉዳይ ግን በኢትዮጵያ በሚደረገው ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሰየም ሽግግር ሒደት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ፣ በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው መጪው መንግሥት ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችልና አዲሱን አስተዳደር አሜሪካ እንዴት ልታግዘው ትችላለች በሚሉት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ብለዋል፡፡

የሽግግር ሒደቱን በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት የጠቀሱት አምባሳደር ያማማቶ ሌሎች አገሮችም በዚህ ሒደት ውስጥ እንደሚገኙ፣ እንዲህ ባሉት የሽግግር ሒደቶች ለውጥና ተቋማት ላይ ማሻሻያ በማድረግ እንዲጠናከሩ የሚያስችል ምልክት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ወይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ምን ሊያደርጉ ይመጣሉ የሚለው ሳይሆን፣ የአሜሪካ ትኩረት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ብሎም ኢትዮጵያ በቀጣናው በምትጫወተው ሚና ላይ እንደሚያጠነጥን አስታውቀዋል፡፡ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተግባራት ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሠራዊት ቁጥር በማዋጣት ጭምር ግንባር ቀደም ሚና እንዳላትም አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሌሎች ጉብኝት በሚደረግባቸው አገሮች ውስጥ እየታየ ካለው ውጥረትና የእርስ በርስ ግጭት በተጨማሪ ቻይና በአፍሪካ ያላት ሚናም ትኩረትን ስቧል፡፡ አሜሪካ ቻይና በምታለምደው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ጥያቄዎች እንዳሏት ያስረዱት ያማማቶ፣ በተለይ በቻይና የሚፈጸሙ ‹‹ብዝበዛዎችና የሀብት ሽሚያዎች›› መንግሥታቸውን እንደሚያሳስብ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቻይና ብድር የሚያገኙ አገሮች ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ መዘፈቃቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ሲያብራሩም አንዳንድ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ከሚችለው በላይ እስከ 200 በመቶ በዕዳ ውስጥ መዘፈቃቸው እየታየ ስለሆነ ስለዚህ ጉዳይ ከቻይና መንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ፕሮጀክቶች ከቻይና በሚገኝ ብድር ፋይናንስ ይደረጋሉ፡፡ በዚህ ሳቢያም ከፍተኛ የብድር ዕዳ ክምችት በመፈጠሩ እንደ መርከብ ድርጅት ያሉ ተቋማት ውስጥ ድርሻ ለመያዝ ከቻይና ጥያቄ እየቀረበ እንደሚገኝ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ወርቅነህ ገበየሁን (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ኃላፊዎችንና ሌሎች በስም ያልጠቀሷቸውን አካላት እንደሚያነጋግሩ ታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬንያን፣ ጂቡቲን፣ ቻድን እንዲሁም ናይጄሪያን እንደሚጎበኙ ሲገለጽ፣ በተለይ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ናይጄሪያ አሜሪካ ቁልፍ የምትላቸው አገሮች ስለመሆናቸውም አምባሳደር ያማማቶ አስታውሰዋል፡፡