Skip to main content
x
ኢትዮጵያውያን ከፍ ያሉበት የበርሚንግሃም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ኢትዮጵያውያን ከፍ ያሉበት የበርሚንግሃም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሠለፈችባቸውን ወርቃማ ድሎች ያጎናጸፏት ጥቂት አትሌቶች መሆናቸው መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ከተመሠረተ ከሦስት አሠርታት በላይ ባስቆጠረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ስማቸው የሚጎላው አትሌቶች ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ መሠረት ደፋር፣ ገለቴ ቡርቃ  እንዲሁም የአሁኖቹ ገንዘቤ ዲባባ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻና ሳሙኤል ተፈራ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከአሜሪካና ከሩሲያ በመከተል እስከ በርሚንግሀሙ ድረስ በዓለም ሦስተኛዋ ባለብዙ ሜዳሊያ እንድትሆን ያበቋት እነዚህና ሌሎችም ጥቂት አትሌቶች ሲሆኑ፣ እስካሁንም በ27 ወርቅ በ10 ብርና በ13 ነሐስ በድምሩ በ50 ሜዳሊያዎች ሁለቱን ኃያላኖች ትከተላለች፡፡ አሜሪካ በ272 ሜዳሊያ ግንባር ቀደምትነቱን ስትቆጣጠር፣ ሩሲያ በ145 ሜዳሊያዎች ትከተላታለች፡፡

ቀደምቱ ኢትዮጵያውያን በ1,500 ሜትርና በ3,000 ሜትር ርቀቶች በመወዳደር ሲያስመዘገቡት የቆዩትን ድል ተተኪዎች ከሰሞኑም ተክነውበት ታይተዋል፡፡ በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ ከየካቲት 22 እስከ የካቲት 25 ለተከታታይ አራት ቀናት በተካሄደው በዚሁ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ገንዘቤ ዲባባ፣ በ1,500 እና በ3,000 ሜትሮች ድርብ ድል በማስመዝገብ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝታለች፡፡ በወንዶች በኩል ቁመተ መለሎው ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3,000 ሜትር እንዲሁም ባለተስፋው ሳሙኤል ተፈራ በ1,500 ሜትር ከተፎካካሪዎቻቸው ልቀው ሦስተኛውንና አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች ናቸው፡፡ ሌላው በወንዶች 3,000 ሜትር ሁለተኛ በመውጣት ሰለሞን ባረጋ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ኢትዮጵያውያን ከፍ ያሉበት የበርሚንግሃም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መከናወን ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከ1985 እስከ 2018 ባለው የውድድር መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት የበርሚንግሃም ተሳትፎዋ ከፍተኛው ሆኖ እንዲጠቀስ አስችሎታል፡፡ ይህም በአገሪቱ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የድል ጥማት ማርካት የተቻለበት አጋጣሚ ሆኗል፡፡ በአራት ወርቅና በአንድ የብር በድምሩ በአምስት ሜዳሊያ ኢትዮጵያ ከዓለም ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ የአንደኛነት ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀች ምሥራቅ አፍሪካዊት አድርጓታል፡፡

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ገለቴ ቡርቃ እ.ኤ.አ. በ2008 በተካሄደው ውድድር፣ በ1,500 ሜትር ያስመዘገበችው 3፡59.75 የርቀቱ ክብረ ወሰን እንደተጠበቀ ይገኛል፡፡ በወንዶች በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሸኑን በፕሬዚዳንትነት እያስተዳደረ የሚገኘው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እ.ኤ.አ. በ1997 በ3,000 ሜትርና በ1999 በ1,500 ሜትር አሸናፊ ሆኖ በርቀቶቹ ያስመዘገበው 7፡37.71 እና 3፡33.77 እንደ ገለቴ ቡርቃ ሁሉ በክብረ ወሰንነታቸው እንደተጠበቁ ናቸው፡፡ ኃይሌ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3,000 እና በ1,500 ሜትሮች በድምሩ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በሴቶች በተመሳሳይ አራት የወርቅ፣ አንድ የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ መሠረት ደፋር ስትጠቀስ፣ ገንዘቤ ዲባባ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታ አንፀባራቂ ውጤት ካስመዘገቡ አትሌቶች መዝገብ ተካታለች፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በበላይነት ባጠናቀቁባቸው ውድድሮች አስተናጋጁ ተቋም ለሻምፒዮናው ካዘጋጀው የገንዘብ ሽልማት 1.8 ሚሊዮን ዶላሩን አግኝተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የድርብ ድል ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ 80 ሺሕ ዶላር፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3,000 ሜትርና ሳሙኤል ተፈራ በ1,500 ሜትር እያንዳንዳቸው 40 ሺሕ ዶላር እንዲሁም በ3,000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበው ሰለሞን ባረጋ ደግሞ የ20 ሺሕ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ማክሰኞ ማለዳ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አገሩ ሲገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያምና ሌሎችም የሥራ አመራር ኮሚቴ አባላት አቀባበል አድርገውለታል፡፡ኢትዮጵያውያን ከፍ ያሉበት የበርሚንግሃም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና