Skip to main content
x
ሦስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ምን ይሠራሉ?

ሦስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ ምን ይሠራሉ?

ባልተለመደ ሁኔታ የሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተመሳሳይ ሳምንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክሰ ቲለርሰን፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላብሮቭና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሒ ቢን ዘይድ አል ናህያን ናቸው፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሰኞ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ እንደገቡ የታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ደግሞ ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ላብሮቭ ደግሞ ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡

የእነዚህ ሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትኩረትን የበመሳብ የተለያየ ትርጉም ሲሰጠው ተስተውሏል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በአንድ በኩል ትልቅ ተስፋ እንዳለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከወትሮው የተለየ ትርጉም እንደሌለው ሲነገር እየተደመጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከመንግሥት ጋር ለመመካከርና ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ነው ሲሉ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፣ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ታደርገው ከነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችልና በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ቀውስ ኢትዮጵያውያንን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ነው ብለው ሲከራከሩ ተደምጧል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተቀስቅሰው በበርካታ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር ደርሷል፡፡  እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ከላይ ታች ቢባልም፣ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም፡፡ በዚህም ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከመንግሥትና ከኢሕአዴግ ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አገሪቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስተዳደር ባለመቻሉም፣ መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይና በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ክርክርና ውይይት ከተደረገበት በኋላ በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ከታወጀ በኋላ፣ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተው ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ በአራተኛው ቀን በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው አካባቢዎች የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት የሦስቱ  አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከማክሰኞ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ አዲስ አበባ እየገቡ ነው፡፡ የእነዚህ ሦስት አገሮች ኢትዮጵያ መጥተው ምን እንደሚሠሩና የመምጣታቸው ፋይዳ ምን እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በተለይ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ትኩረት የሚስብና የሚያነጋግር ሆኗል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ የእነዚህ ሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ፋይዳ እንደሌለው፣ መጥተውም ምን እንደሚሠሩ ግልጽ የሆነ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ከዚህ በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ  ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት አገሪቱ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደነበረች፣ በወቅቱ  ችግሩ እንዲፈታ ምክረ ሐሳብ አቅርበው አልሄዱም ይላሉ፡፡  

‹‹ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በምን ጉዳዮች እንደተወያዩና ምን ዓይነት ምክረ ሐሳብ እንዳቀረቡ ግልጽ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የየራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት አኳያ እንጂ፣ በአፍሪካ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ችግሮች ባሉባቸው አገሮች የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትና ሌሎች ችግሮችን ከመፍታት ጋር የተያያዘ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡

የውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ የሦስቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ካለው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መወሰን የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡  ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከሩሲያና ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ሹማምንት መምጣታቸው ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ሦቱም አገሮች በየአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ አስታውሰው፣ ‹‹አሁን ያሉብን ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው ግንኙነት የሚሰጡትን ትኩረት ነው የሚያሳየው፤›› ብለዋል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተመሳሳይ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የመገጣጠም ጉዳይ እንጂ፣ አንዱ ከሌላው ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፕሮግራሙ ከወራት በፊት የተያዘ እንጂ አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹የእነዚህ ኃላፊዎች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ  ጋር የተያያዘ ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ የተሳሳቱ ናቸው፤›› ያሉት አቶ መለስ፣ ‹‹በአገር ቤት የምናደርገውን ጉዳይ በተመለከተ ሞግዚት አያስፈልገንም፤›› ብለዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በአቶ መለስ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የራሷ ችግሮች አሉባት፡፡ አሁን ከባድ በሆነ ችግር ውስጥ ነው ያለችው፤›› ብለው፣ የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚያመለክተው የኢትዮጵያን አስፈላጊነት ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የሚያገባቸው ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ያስታወሱት አቶ ልዑልሰገድ፣ የየአገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በዋናነት የሚያያዘው፣ አገሮች በተናጠል የራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ ደግሞ ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉት ከዚህ በፊቱ የተለየ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ምናልባት አሁን ወደ መጨረሻው አካባቢ የኢትዮጵያ ችግር ተሰምቷቸው የተወሰነ ምክር ወይም ድጋፍ ሊያደርጉ ከመጡ ጥሩ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ በሚመጡበት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሊነጋገሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በበኩላቸው የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ በሚቆዩበት ወቅት ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል በምሥራቅ አፍሪካ የሰላምና ደኅንነት፣ በሽብርተኝነትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሊመክሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ደግሞ የሦስቱ አገሮች የኢትዮጵያ ጉብኝት በተናጠል መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ግንኙነት ለረዥም ዓመታት የቆየ እንደሆነ አስታውሰው፣ ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች በጋራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም ይህንን ለማጠናከር ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በሚቆዩበት ወቅት ምን ይሠራሉ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ፣ ሁለቱ አገሮች ተባብረው የሚሠሩባቸውን ጉዳዮች በመገምገም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደረስ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ ከዓረብ አገሮች በተለይም ከሳዑዲ ዓረቢያና ከመሰሎቿ ተወዳዳሪ የሆነ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት የዓረብ አገር ነች፡፡ አሸባሪ ኃይሎችን ትረዳለች በማለት ኳታርን ካገለሉና ማዕቀብ ከጣሉ የዓረብ አገሮች መካከል አንዷ የተባበሩት ዓረብ  ኤምሬትስ ነች፡፡

ከኤርትራ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ቁርኝነት ካላቸውና በቀይ ባህርና በአሰብ ወደብ አካባቢ ከፍተኛ ፍላጎት ካላቸው አገሮች መካከልም አንዷ ነች፡፡ በኳታር ላይ ማዕቀብ እንዲጣልና ከሌሎች የዓረብ አገሮች መገለል እንዲደርስባት ሚና ከነበራቸው አገሮች መካከልም አንዷ ነች፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ የየመን ጦርነትም ጉልህ ሚና አላት፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት እያሻሻለችና እያጠናከረች መጥታለች፡፡ ኢትዮጵያ አልጄዚራ የተሰኘው የኳታር ሚዲያ ቢሮ እንዲከፍት ከመፍቀድ ጀምሮ በተለያዩ መስኮች ተባብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ኳታር አቅንተው ከአገሪቱ መሪ ጋር ውይይት እንዳደረጉና ኳታር ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገች ይታወቃል፡፡ በዚህም ሳቢያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትኩረት እየሳባ ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ አቶ መለስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴዎች ከሚያግዙ አገሮች ጋር ግንኙነት ታደርጋለች፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ነፃ የሆነ የውጭ ፖሊሲ ትከተላለች የምንለው፡፡ ከየትኛውም አገር ጋር የምታደርገው ግንኙነት አንዱን አገር ለመጉዳት አይደለም፡፡ መነሻና መድረሻው የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅምና ከየአገሮች ጋር ያለንን የጋራ ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር የምታደርገው ግንኙነት የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲኖረው፣ የአገራችን ምርቶች በውጭ ገበያ እንዲኖራቸው፣ በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎቻችን ክብራቸው ተጠብቆ መሥራት እንዲችሉ ለማድረግና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን በተመለከተም አቶ መለስ አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ቀደም ብሎ የተያዘ ዕቅድ መሆኑን ጠቁመው፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት 120 ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰዋል፡፡

የሩሲያ መንግሥት ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መለስ፣ ‹‹ሩሲያ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በተመለከተ ፅኑ አቋም ነው ያላት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሁለቱ አገሮች በጤና፣ በትምህርት፣ በኃይልና በሌሎች መስኮች ተባብረው ይሠራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ይህን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ነው፡፡ ወዳጅነታችንን የበለጠ በማጠናከር የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነቱን የሚረከብበትና ከዚህ በፊት ስለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና የሚያገኝበት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በቆይታቸውም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር እንደሚገናኙ ጠቁመዋል፡፡ የሰርጌ ላብሮቭ ወደ አዲስ አበባ መምጣት አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ትኩሳት ጋር ይገናኝ እንደሆነም አቶ መለስ ተጠይቀው፣ ግንኙነት እንደሌለውና ፕሮግራሙ ቀደም ብሎ የተያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አዲስ አበባ በሚቆዩበት ወቅትም ሁለቱ አገሮች ባለፉት 120 ዓመታት የነበራቸው ግንኙነት እንደሚገመገምና ይህን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ በሁለቱም አገሮች መካከል ስምምነቶች ይደረጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

አቶ መለስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን በተመለከተም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አፍሪካ መምጣት፣ አሜሪካ ከአኅጉሪቱ ጋር ባላት የንግድና የኢንቨስትመንት፣ የሰላምና ደኅንነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ወዘተ. ላይ ለመምከር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ ኢትዮጵያና አሜሪካ በመደበኛነት የሚተባበሩባቸውና የሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በዋነኛነት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ ሁለቱ አገሮች አብረው ይሠራሉ፡፡ ከዚያ ውጪ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ሁለቱ አገሮች ከዚህ በፊትም በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ጉብኝት ያደርጋሉ፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝትም ከዚህ በፊት በነበሩ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ማቀድ በዋናነት በአገሪቱ የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በዋናነት አገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ካላት ተፈላጊነትና ስትራቴጂካዊነት አኳያ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ በተለይም በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ያለው ሽብርተኝነትና የኤርትራ አሸባሪነት በቀጣናው ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ልዑልሰገድ፣ ይህን ችግር በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አገሮች ትኩረት በመስጠት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በገልፍ አገሮች በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ኢትዮጵያ የእኩልነት አቋም ነው ያላት፤›› ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ ከዚህም አኳያ አገሪቱ ኳታርን ካገለለችና ከኤርትራ ጋር ውግንና ካላት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር እንኳ ሳይቀር ግንኙነት እንዳላት አስታውሰዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ማዞር የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት አቶ ልዑልሰገድ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በመጀመርያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊና ለም መሬት አለ፡፡ የኢንዱስትሪ ግንባታም እየተፋጠነ ነው፡፡ የዓረብ አገሮች ኢኮኖሚ ነዳጅ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሥጋት ስላላቸው ያንን መለወጥ ይፈልጋሉ፡፡ ከዕቅዳቸው መካከል ደግሞ አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህ የእነሱን መምጣት ከኳታር ወይም ከኤርትራ ጋር ሳናያይዘው በንግድና በኢንቨስትመንት የሚያተኩር ነው የሚመስለኝ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛ ምክንያት ብለው የሚጠቅሱት ጉዳይ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ካላት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውድድር የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ፊቱን ወደ ግብፅ ማዞር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በጂቡቲ ወደቦች ላይ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ሊሆን እንደሚችልም ያሳስባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርበራ ወደብ ድርሻ መያዟን ተከትሎ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር መገደዷን ያወሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ አገር ከመሆኑ አኳያ፣ የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መምጣት በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሩሲያና አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸው ሰምተናል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከላዊነቷን ያሳያል፡፡ የኳታርና የቱርክ ወደዚህ አካባቢ መሳብም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ አሁንም ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ጥረት እያደረገች ቢሆንም እስካሁን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ ይህን ቀውስ ለማስወገድ ሲባልም ለስድት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ በአዋጁ ውስጥ ብትሆንም የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትኩረት ስቧል፡፡ በብዙ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡

ቲለርሰን በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ከኢትዮጵያ እንደሚጀምሩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶናልድ ያማማቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ጀምረው በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በጂቡቲና በቻድ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ቲለርሰን ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት ማድረጋቸው አሜሪካ ለአፍሪካ ያላትን ግልጽ ፖሊሲ ያመለክታል፤›› ሲሉ ያማማቶ አስረድተዋል፡፡