Skip to main content
x

ብሔራዊ ባንክ ካቀደው በላይ የገንዘብ አቅርቦት ፍላጎት እያስተናገደ እንደሚገኝ ገለጸ

በሁለተኛው የአግሮ ኢንዲስትሪ ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ ከተስተናገዱና እየተስተናገዱ ከሚገኙ በርካታ የፓናል መድረኮች አንዱ የንግዱ ዘርፍ ፋይናንስ ማግኘት የሚችልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮረው የውይይት መድረክ ነው፡፡

የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚ ባለሙያ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ለሚካሄደው ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መንግሥት በዕቅድ የያዘው የገንዘብ አቅርቦት መጠን ከኢኮኖሚው አኳያ የ28 በመቶ ድርሻ ነበር፡፡ ይሁንና የኢንቨስትመንት ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ ከታቀደው የገንዘብ አቅርቦት በላይ ከፍተኛ የገንዘብ ፍላጎት ተፈጥሯል ያሉት ምክትል ገዥው፣ በመሆኑም ከኢኮኖሚው የ40 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው የገንዘብ አቅርቦት እንዲሆን ለማድረግ ባንኩ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አኳያ ለኢንቨስትመንት የዋለው ገንዘብ መጠን የኢኮኖሚውን 40 በመቶ እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አብራርተዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በገንዘብ ሲተመን ከ750 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ20 ትሪሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ 

ሆኖም ለኢቨስትመንት የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ሙሉ ለሙሉ ከቁጠባ መሟላት ባለመቻሉ መንግሥት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ምንጮች ለመበደር መገደዱ ግልጽ ነው፡፡ በአገሪቱ የማይክሮ ኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ ምክትል ገዥው ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል ያለው ከፍተኛ ክፍተት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአገሪቱ ሀብትና ዕዳ መካከል የሚታየው ክፍተት ነው፡፡

በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የቁጠባ ዘዴዎችን በመጠቀም ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማሟላት የመንግሥት ዕቅድ ቢሆንም፣ ኢኮኖሚው ከሚፈልገው የገንዘብ አቅርቦት አኳያ በባንኮች በኩል የሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዝብ የሚጠበቀውን ያህል ሊሆን አልቻለም ብለዋል፡፡ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከጠቅላላ ኢኮኖሚው ውስጥ እስከ 25 በመቶ የሚደርሰውን መጠን በቁጠባ መልክ ማሰባሰብ ከተቻለ ትልቅ ዕርምጃ እንደሚሆን ምክትል ገዥው ገልጸዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ይፋ ከተደረገው የብሔራዊ ባንክ መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በአገሪቱ የተሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 500 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ የኢንቨስትመንት መጠኑ ወይም የተፈጠረው ካፒታል መጠን 590 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ በመሆኑም አገራዊ የቁጠባ መጠን ከኢኮኖሚው ውስጥ የ32 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ኢንቨስትመንት ወይም ካፒታሉ ወደ 40 በመቶ ገደማ ይይዛል፡፡ በዚህ የተነሳም በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል እስከ ሰባት በመቶ የሚጠጋ ክፍተት ይታያል ወይም የቁጠባው መጠን ከኢንቨስትመንቱ በሰባት በመቶ ያነሰ ሆኖ ይታያል፡፡

ኢንቨስትመንት በአገሪቱ በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ላይ ማለትም ከግብርና ተኮር ወደ ኢንዱስትሪ እንዲለወጥ ብሎም እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልጉ፣ እንደ ቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎችም የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማሟላትን የሚፈልጉ አገልግሎቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ጭምር በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሚደረገው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ኢንቨስትመንቱ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ አስፈላጊ በመሆኑ እንዳይቋረጥና እንዳይቀንስ ማድረግ ግድ ሆኗል ያሉት ምክትል ገዥው፣ አገሪቱ ያላት የፋይናንስ ሀብትና ዕዳ ላይ የሚታየው ክፍተት ግን ሌላኛው ወሳኝ ፈተና እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከፋይናንስ ሀብት አኳያ በተለይ የቁጠባ መጠን በአብዛኛው የሚሰበሰበው በባንኮች ቢሆንም፣ መንግሥት ለሚፈልጋቸውና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች የሚውል የገንዘብ መጠን ባለመሆኑ ሌሎች የቁጠባ መጠንኑን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ገዥው ባንክ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡ ባንኮች የቅርንጫፍ ብዛታቸውን እንዲያስፋፉ ማድረግ አንደኛው ዕርምጃ ነው፡፡ በዚህም በሰባት ዓመት ውስጥ ከ2,000 በታች የነበሩት የባንኮች ቅርንጫፎች ብዛት፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 4,000 መድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ፈንድ መቋቋሙም ለቁጠባ መስፋፋት አንደኛው ተጠቃሽ ዕርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ትልቁን ድርሻ የያዘው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያም ዋነኛው የቁጠባ ምንጭ ነው ተብሏል፡፡ በየወሩ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚያደርጉት የገንዘብ መጠን እስካለፈው ሁለት ዓመት 69 ቢሊዮን ብር እንዳስመዘገበ ምክትል ገዥው አስታውሰዋል፡፡ ይህም ከመካከለኛ እስከ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ እንዳገዘ፣ በአሁኑ ወቅትም ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚለው ገንዘብ ከ11 በመቶ ወደ 21 በመቶ እንዳደገ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፍላጎት በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ማስከተሉ አልቀረም፡፡ የገቢ ንግዱ የካፒታል ዕቃዎችን ጨምሮ እስከ ጥቃቅኑ ሸቀጣ ሸቀጥ ድረስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚፈስበት ሲሆን፣ በአንፃሩ የወጪ ንግዱ ‹‹በውጫዊ ምክንያቶች›› ማለትም በዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መዳከም፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎች የሚታየው ደካማ ተወዳዳሪነት ለወጪ ንግዱ ዝቅተኛ መሆን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት በአገር ውስጥ የቁጠባ መጠንን ለማሳደግ ማበረታቻዎችን እንዲመለከት ሐሳብ ቀርቦለታል፡፡ በፓናል መድረኩ ከተገኙ እንግዶች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ አድማሱ ታደሰ ናቸው፡፡ አቶ አድማሱ የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ባንክ በመባል የሚታወቀው የንግድና የልማት ባንክ (ቲዲቢ) ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ መንግሥት የሚፈልገውን የቁጠባ መጠን ለማሰባሰብ ወይም የገንዘብ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚችልባቸው ልዩ ልዩ የማበረታቻ ዘዴዎችን እንዲያጤናቸው ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ከሚጠቅሳቸው ችግሮች አንዱ በገቢና ወጪ ንግዱ ላይ የሚታየው ከፍተኛ ክፍተት አንዱ ነው፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ይህን ችግር ሲያስተጋባ ኖሯል፡፡ ምክትል ገዥው ባቀረቡት ማብራሪያ ወቅት ያልጠቀሱት ነገር ቢኖር በአገሪቱ ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው ወለድ ነው፡፡ ምንም እንኳ በቅርቡ ማሻሻያ ተደርጎበት ከአምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ከፍ የተደረገው የወለድ ምጣኔ በአገሪቱ ከሚታየው የዋጋ ንረት አኳያ ዝቅተኛ ነው፡፡

‹‹ሪል ኢንተረስት ሬት›› የሚባለው ወይም ከዋጋ ንረት አኳያ አስቀማጮች የሚያገኙት ወለድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይኸውም በአሁኑ ወቅት የዋጋ ግሽበቱ ወደ 13 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ባንኮች የሚከፍሉት የተቀማጭ ገንዘብ ዓመታዊ ወለድ ሰባት በመቶ በመሆኑ ከወለዱ ላይ የዋጋ ግሽበቱ ሲቀነስለት ኔጌቲቭ ስድስት በመቶ ስለሚያሳይ አስቀማጮችን ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ቢሆንም፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ አስቀማጮች ከወለድ ይልቅ እንደ የፋይናንስ ደኅንነት ያሉ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ገንዘባቸውን በባንክ ማስቀመጡን ይመርጣሉ የሚል ምክንያት ሲሰጡ ይደመጣሉ፡፡

ይሁንና የዓለም ባንክና መሰሎቹ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ያለውን ሁኔታ መንግሥት መለወጥ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ሌሎች የማበረታቻ ዓይነቶችን እንዲከተል አቶ አድማሱም ጠቅሰዋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ገንዘብ በቁጠባ ሒሳባቸው ውስጥ ለሚያስቀምጡ ደንበኞች የንግድ ባንኮች የሽልማት ማበረታቻዎችን መስጠት መጀመራቸውም አንደኛው የተቀማጭ ገንዘብን ለማሳደግ ከሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የሚካተት ቢሆንም፣ ኢኮኖሚው የሚጠይቀውን የገንዘብ ፍላጎት ግን የሚያረካ አልሆነም፡፡