Skip to main content
x
አራት የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ከዩኒዶ ዳይሬክተር ጄነራል ሊ ዮንግ ጋር ሁለተኛውን የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም ሲከፍቱ፣ በአገሪቱ እንዲገነቡ ስለተመረጡት አራት ፓርኮች በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴአታው መለሰ መብራህቱ (ዶ/ር) ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል

አራት የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ ነው

  • የአግሮ ኢንቨስትመንት ፎረም ለሁለተኛ ጊዜ መካሄድ ጀምሯል

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በነደፈው ዕቅድ መሠረት የመጀመርያዎቹ አራት የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮችን ለመገንባት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ ባለፈው ዓመት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይኼንን ተከትሎም ሲከናወኑ ከነበሩ ሥራዎች ውስጥ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮቹን ዕውን ለማድረግ የሚረዱ የአዋጭነት ጥናቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንቨስትመንት ዓለም አቀፍ ፎረም (አግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም)፣ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከየካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮቹን ግንባታ ለማካሄድ ከሚያስችሉ የአዋጭነት ጥናቶች ጎን ለጎን በተመረጡት አራቱ ዋና ዋና ክልሎች ውስጥም የአግሪ ፕሮሰሲንግ ፓርኮችን ግንባታ ለማካሄድ ኮርፖሬሽኖች ተቋቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው መብራህቱ መለስ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ባለቤቶች ክልሎች በመሆናቸው የሚያስዳድሯቸውም ራሳቸው ክልሎቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አማካይነት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታን ማከናወን የሚያስችሉ ኮርፖሬሽኖች ተመሥርተዋል፡፡

መንግሥት ለፓርኮቹ ግንባታ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ከራሱ ባሻገር ከውጭ ምንጮች ማግኘት የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ሲገለጽ የቆየው ካለፈው ዓመት ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ሥር የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በፋይናንስም በቴክኒክም ፕሮጀክቱን መደገፍ ይፈልጋል፡፡ የዩኒዶ ዳይሬክተር ጄነራል ሊ ዮንግ እንዳስታወቁት፣ ዩኒዶ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮቹን ግንባታ ለመደገፍ የአዋጭነት ጥናት ውጤትን እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም የከፈቱት ፕሬዚዳንት ተሾመ ሙላቱ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው ለውጭ ኢንቨስተሮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ጀልባዋ ሳታመልጣችሁ ኢንቨስት አድርጉ›› በማለት በንግግራቸው መካከል የተጠቀሙበት ዓረፍተ ነገር በዩኒዶና በሌሎችም የማኅበራዊ ድረ ገጾች ትኩረት የሳበ ሆኖ ሲጠቀስ ታይቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ዩኒዶ ‹‹ፕሮግራም ፎር ካንትሪ ፓርትነርሺፕ-ፒሲፒ›› በማለት ተቋሙ ድጋፍ በሚሰጣቸው አገሮች ውስጥ እንዲተገበር በነደፈው የአጋርነት ፕሮግራም አማካይነት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመረች አስታውሶ፣ በተለይም ወደ አሜሪካ የጫማ ምርቶችን ለመላክ የሚያችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ስለሚሰጠው የፋይናንስ ድጋፍም ዩኒዶ ጠቅሷል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አሜሪካ ተልከው 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስገኙ ለሚታሰቡ የጫማ አማራቾች ድጋፍ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ይህ የኢዱስትሪ ሚኒስቴር ዕቅድ በመንግሥት አነጋገር ‹‹የተለጠጠ›› የሚባል ቢሆንም፣ ከ330 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ስለሚታሰብ ትኩረት የሚሻ ግብ እንደሆነ ዩኒዶ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በሞጆ እየተገነባ ለሚገኘውና የቆዳ ፋብሪካዎች የጋራ የዝቃጭ ማስወገጃና ማከሚያ ፕሮጀክትም ዩኒዶ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ሊ ዮንግ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ምንም እንኳ በመንግሥት ከታያዘለት ዕቅድ አኳያ ከሚጠበቀው በላይ የዘገየ ቢሆንም፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ዩኒዶም ይህንኑ ጠቅሷል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ቢያንስ ከሰባት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ዓላማውም በአገሪቱ የሚገኙትን የቆዳ ፋብሪካዎች በሞጆ ከተማ በማሰባሰብ በአንድ የፍሳሽ ማጣሪያ እንዲጠቀሙ፣ የሚለቁትም ፍሳሽ ተጣርቶ እንዲወጣና አካባቢ ላይም ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል የሚደረግበትን አሠራር የሚያካትት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይሁንና በፋይናንስ ዕጦት ሳቢያ ለረጅም ጊዜ ሲጓተት እንደቆየ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለአራቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ የሚያስፈልገውን የ30 ቢሊዮን ብር ወይም የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክ፣ ዩኒዶ እንዲሁም የጣልያን መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ፋይናንስ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለፓርኮቹ ግንባታ የሚያስፈልገው የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ፣ በክልሎቹ የሚያስፈልገው ቦታ ተለይቶ፣ ለሥራው ተጠሪ የሆኑ ኮርፖሬሽኖችም መቋቋማቸው ተጠቅሷል፡፡

 ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚጠናቀቀው በዚህ ዓለም አቀፍ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከ3,000 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ሲገለጽ፣ የፎረሙ ትኩረትም ከምግብ ማቀነባበሪያ ጀምሮ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ እንደሚያጠነጥን ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ አጋዥ በሚባሉት የማሸጊያና የታዳሽ ኃይሎች ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችም የፎረሙ አጀንዳ ካካተታቸው መካከል ይገኙበታል፡፡