Skip to main content
x
ሩሲያና አሜሪካ ቀንዳቸውን ያቆላለፉበት ያልተረጋገጠው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት
ሰባ ያህል ሰዎች ተገድለውበታል በተባለው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግለት

ሩሲያና አሜሪካ ቀንዳቸውን ያቆላለፉበት ያልተረጋገጠው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት

ሶሪያ ከሰባት ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በሕዝብ እምቢተኝነት አምሳል በተነሳው ቀውስና ተከትሎ በመጣው፣ በበሽር አል አሳድ በሚመራው በሶሪያ መንግሥትና በአማፅያን መካከል የሚደረገው የእርስ በርስ ጦርነት ማብቂያ ‹ላም አለኝ በሰማይ› እየሆነ ነው፡፡

ጦርነቱም በሶሪያ መንግሥትና በአማፅያን መካከል ከመሆን አልፎ፣ በሽር አል አሳድን በሥልጣን ላይ ለማቆየት በሚፈልጉና ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ለመጣል በሚታገሉ ኃያላን አገሮች መካከል የሚደረግ የእጅ አዙር ጦርነት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከአሜሪካ ጎን የተሠለፉት እንግሊዝና ሌሎች የምዕራቡ አገሮች ፕሬዚዳንት አሳድ ከሥልጣን ካልወረዱ በስተቀር እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይመስልም፡፡ በዚህም ምክንያት አማፅያንን በማስታጠቅና የአየር ላይ ድብደባዎችን በማድረግ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሩሲያ ደግሞ ፕሬዚዳንት አሳድ ከሥልጣናቸው የሚወርዱት በመቃብሬ ላይ ነው ያለች ይመስላል፡፡ የፕሬዚዳንቱን የጦር ኃይል በቁሳቁስና በሥልጠናም ስትደግፍ ይታወቃል፡፡

ሩሲያና አሜሪካ ቀንዳቸውን ያቆላለፉበት ያልተረጋገጠው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሶሪያ ተፈጽሟል በተባለው የኬሚካል ጥቃት ምክንያት ስለሚወሰድ የአፀፋ ምላሽ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል

 

ይሁንና ይህ የእጅ አዙር ጦርነት እ.ኤ.አ. ከ2014 እና 2015 ጀምሮ በሶሪያ ምድር ተፈጽሟል በተባለ የኬሜካል ጥቃት ምክንያት ገጽታው እየተቀየረ መጥቶ፣ ሩሲያና አሜሪካን ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚችሉ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡

ካሁን ቀደም በነበሩ የኬሚካል ጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል ውንጀላዎች አሜሪካ የበሽር አል አሳድ መንግሥት ላይ ጣቷን ስትቀስር፣ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳትይዝ እንደነበር የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይባስ ብሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሶሪያ ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን መረጃዎች በአሜሪካ የሚደገፈው የአመትያን ቡድን፣ የኬሚካል መሣሪያዎችን ተጠቅሟል የሚል ጠንካራ መረጃ እንዳለ አስታውቆ ነበር፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ሲለቀቁ የነበሩ ቪዲዮዎችና ምሥሎች ሕፃናት በመተንፈሻ መሥሪያዎች ታግዘው ሲተነፍሱና መተንፈስ አቅቷቸው ሲቃትቱ ያሳዩ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ምሥሎች በተመልካች ስሜት ለመጠቀምና በሶሪያ ለሚደረገው ድብደባ ማሳመኛ ምክንያቶችን ለማቅረብ የሚለቀቁ እንጂ፣ ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ የሆኑ መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የግሎባል ሪሰርች ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

ብዙኃኑ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት የሚሰነዘሩ ውንጀላዎችን ከማስተጋባት በዘለለ፣ ከሌላኛው ወገን የሚነሱ ሐሳቦችን ለማስተናገድ ጆሮ ገብ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት፣ ‹‹በደቡባዊ ሶሪያ የኬሚካል ጥቃቶች ትንኮሳ መፈጸም እንዲችሉ በአሜሪካ እየሠለጠኑ ያሉ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እንዳሉ የማያወላዳ መረጃ አለን፡፡ የተለያዩ የኬሚካል መሣሪያዎች ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ ይህም የመንግሥት ኃይል የሆነውን አካል ለመወንጀል ሊጠቀሙበት ያለሙት ነው፡፡ እነዚህን ትንኮሳዎች አሜሪካና አጋሮቿ በሶሪያ በወታደራዊና በመንግሥታዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም ይጠቀሙባቸዋል፤›› ሲል አሳስቦ ነበር፡፡

እነሆ ከሦስት ቀናት በፊት በድጋሚ ሩሲያንና የአሳድን መንግሥት በተለይ በአሜሪካ ለመወቀስ ያበቃ አዲስ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ውሏል የሚል ውንጀላ፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሰነዘራል፡፡

ከዓመታት በፊት አሜሪካ በሶሪያ ላይ የአየር ላይ ድብደባ ለመፈጸም ተመሳሳይ ምክንያት ተጠቅማ ስለነበር፣ የሶሪያን ፖለቲካ የሚከታተሉ የተለያዩ አካላትም ይኼንን ፊልም ካሁን ቀደም ዓይተነው ነበር ማለት ጀመሩ፡፡

‹‹በሶሪያ በተፈጸመ ህሊና ቢስ የኬሚካል ጥቃት ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ በርካቶች ሞተዋል፡፡ የጉዳቱ አካባቢ ዝግ የተደረገና በሶሪያ ጦር የተከበበ ነውና የውጭው ዓለም ሊደርስ አልቻለም፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ሩሲያና ኢራን እንስሳውን አሳድ በመደገፋቸው ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ አካባቢውን በቶሎ ለመድኃኒት አቅርቦትና ለማጣራት ክፍት አድርጉ፡፡ ያለምንም ምክንያት ሰብዓዊ ቀውስ እየተፈጠረ ነው፡፡ ይኼ በሽተኛነት ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

ሩሲያና አሜሪካ ቀንዳቸውን ያቆላለፉበት ያልተረጋገጠው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለኬሚካል ጥቃቱ ምላሽ ይኖራታል እያሉ ነው

 

ምንም እንኳን የማጣራት ሥራ እንዳልተከናወነ የተረጋገጠ ማስረጃ ባይኖርም፣ ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ እየተደረገች ያለችው ሩሲያ ናት፡፡ እነዚህን ውንጀላዎች ሩሲያ በእጅጉ ስትቃወማቸውና ስታጣጥላቸው ቆይታለች፡፡ የኬሚካል መሣሪያ ጥቃት ተፈጽሟል መባሉንም በጣም አጣጥላለች፡፡

‹‹ይኼንን መረጃ በእጅጉ እንቃወማለን፡፡ ዱማ ከታጣቂዎች ነፃ እንደወጣችም የሩሲያን የጨረራ፣ የኬሚካልና የባዮሎጂያዊ ባለሙያዎችን ወደ ሥፍራው ልከን እየተሰነዘሩ ያሉ ውንጀላዎችን እንዲያጣሩ ለማድረግ ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፣›› ሲሉ በሶሪያ የሚገኘው ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ዩሪ ዬቭቱሼንኮ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ሩሲያ በሶሪያ መንግሥት ይፋዊ ጥያቄ ምክንያት መንግሥትን ለማገዝ የገባች አገር በመሆኗ፣ ማንኛውም በሶሪያ ላይ የሚደረግ ጥቃት እጅግ የከፋ ውጤት ያስከትላል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡

ምንም እንኳ አሜሪካ የኬሚካል ጥቃት ተፈጽሟል በማለት የምትወነጅለው እርግጥ ባልሆኑና ከአማፅያኑ ተገኘ በተባለ መረጃ ላይ ተመሥርታ ቢሆንም፣ በሶሪያ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በሩሲያና በአሜሪካ መካከል ቀጥተኛ የሆነ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚሉ ሥጋቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡

የሶሪያ መንግሥት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ካሉት ጊዜያት ሁሉ አሁን ይበልጥ የተጠናከረ መሆኑ፣ የኬሚካል መሣሪያ የመጠቀም ውንጀላው እምብዛም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ የሚከራከሩም አልጠፉም፡፡ የሶሪያ መንግሥት ጠንካራ በሆነበት በዚህ ጊዜ ለምን ብሎ የኬሚካል ጦር መሣሪያን ጥቅም ላይ ሊያውል ይችላል ብለውም ይጠይቃሉ፡፡

ይልቁንም ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ሺሕ በላይ የአሜሪካ ወታደሮችን ከሶሪያ ለማስወጣት በማቀዳቸው ደስተኛ አይደሉም የተባሉት የፔንታጎን ሰዎች፣ የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ለማስለወጥ የፈበረኩት ምክንያት ነው ብለው የሚወነጅሉ በዝተዋል፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች በሶሪያ ምድር መቆየታቸውም የኮንግረሱ የእግር እሳት ሆኖ ሰንብቷል፡፡

የሶሪያ ጦርነት ከእጅ አዙርነት ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ሊሸጋገር እንደሚችልም በርካቶች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ሩሲያና አሜሪካ ቀንዳቸውን ያቆላለፉበት ያልተረጋገጠው የሶሪያ የኬሚካል ጥቃት
በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን የኬሚካል ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራ እንዴት እንደሚደረግ ማብራሪያ ሲሰጡ