Skip to main content
x
ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ
በምዕራብ ሶሪያ ላይ በምዕራባውያን ኃይሎች ከተወነጨፉ 105 ሚሳይሎች አንዱ

ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ

አሜሪካ፣ ፈረንሣይና እንግሊዝ በመተባበር ዓርብ ሚያዚያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ሌሊት የሶሪያ መንግሥት የኬሚካል መሣሪያዎችን ለማምረት ይጠቀምባቸዋል የተባሉ ሦስት ሥፍራዎችን ዒላማ ያደረጉ 105 ሚሳይሎችን ወደ ምዕራብ ሶሪያ አስወንጭፈዋል፡፡

በዚህም ጥቃት ሆምስ፣ ሜስያፍና የደማስቆ ከተማ አጋማሽ ተጠቂዎች ሲሆኑ፣ አሜሪካ የሶሪያ መንግሥት የኬሚካል የጦር መሣሪያ ለማምረት ይጠቀምባቸው የነበሩ ሥፍራዎችን አቅም ያዳከመ ጥቃት እንደነበረ አስታውቃለች፡፡ የአሜሪካ አጋሮች እንግሊዝና ፈረንሣይም ጥቃቱ ውጤታማ የነበረና በአሳማኝ ምክንያቶች ተመርኩዞ የተፈጸመ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በበሽር አል አሳድ የሚመራው የሶሪያ መንግሥት በበኩሉ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሚሳይሎችን ማምከኑን አስታውቆ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዞታል፡፡ በነጋታው ጠዋት ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል አሳድ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ የተቀረፁ ቪዲዮዎች ተለቅቀዋል፡፡

ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ
በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የሶሪያ ሳይንስ ምርምር ማዕከል አንዱ ነው ተብሏል

 

የሚሳይል ጥቃቱ ምንም እኳን ሌሊት ላይ የተፈጸመ ቢሆንም ያልተጠበቀ ግን አልነበረም፡፡ አሜሪካና ሩሲያ በጉዳዩ ላይ ሲወዛገቡ መቆየታቸውና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚሳይል ጥቃት እንደሚፈጽሙ በትዊተር ገጻቸው መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በሩሲያ የሚደገፈው የሶሪያ መንግሥት በቂ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የሶሪያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2011 ከተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት አንስቶ ባሉት ሰባት ዓመታት ከስድስት ጊዜ በላይ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ተጠቅሟል ተብሎ ወቀሳዎች የተሰነዘሩበት ሲሆን፣ በኋላ ግን በተደረጉ ማጣሪያዎች ውንጀላዎቹ የውሸት አልያም የኬሚካል ጥቃት ያልሆኑ ድርጊቶችን የኬሚካል ጥቃት እንደሆኑ በማድረግና እውነታዎችን በማዛባት የሚቀርቡ ማሳሳቻዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

አሜሪካና አጋሮቿ ጥቅም ማስከበሪያ ዘመቻዎችን ለመፈጸም ሲያልሙ ተመሳሳይ ማሳሳቻዎችን የተጠቀሙባቸው ጊዜያት የሚረሱ እንዳልሆኑ የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ይስተዋላሉ፡፡

የዚህ ማሳያ ሆኖ የሚነሳው አንዱ እ.ኤ.አ. በ2002 እና በ2003 የሳዳም ሁሴን መንግሥት የጅምላ ጭፍጨፋ መሣሪያዎችን ተጠቅመዋል በማለት የተፈጸመውና ኢራቅን የጦርነት ዓውድማ በማድረግ ያበቃውን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ የተመራው ዘመቻ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ሳዳም ሁሴንን ያስወገደው ከአሜሪካ የዓለም ፖሊስነት ፍላጎት የመነጨው ዘመቻ ያለምንም ይፋዊ ማስረጃ በደኅንነት መረጃ ላይ ብቻ ተመርኩዞ የተፈጸመ ነበር፡፡

የአሜሪካ የኢራቅ ዘመቻ ካሁኑ የሶሪያ ዘመቻ ጋር የሚያመሳስሉት ሁለት ነገሮች ተከስተዋል፡፡ አንደኛው የሳዳም ሁሴን ሐውልት ከባግዳድ የተፈነቀለበትና ዓርብ በሶሪያ መንግሥት ላይ የተፈጸመው የሚሳይል ጥቃት በተመሳሳይ ሳምንት ውስጥ የተፈጸሙ መሆናቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ዘመቻው በኋላ ጆርጅ ቡሽ የተጠቀሙበትን ቃል ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ መጠቀማቸው ነው፡፡

ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ
ሶሪያውያን የምዕራባውያንን የሚሳይል ጥቃት በመቃወም የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ ሲያቃጥሉ

 

ከሚሳይል ጥቃቱ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ‹‹ሚሽን አኮምፕሊሽድ›› (ዘመቻው በድል ተጠናቅቋል) በማለት ማስፈራቸው፣ ድርጊቱ የቡሽን ጊዜ ያስታውሳል፡፡

የሶሪያ መንግሥት በተቀናቃኞቹ ላይ የሳሪን ጋዝ ጥቃትን ፈጽሟል በሚል ውንጀላ አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ ሶሪያን በሚሳይል ማጥቃቷ ሩሲያን ጨምሮ ኢራንንና ቱርክን ያስቆጣ ሲሆን፣ ገለልተኛ ታዛቢዎችን ደግሞ ያስገረመ ድርጊት ነበር፡፡

የሚሳይል ጥቃቱ የተፈጸመው የተከለከሉ የኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ድርጅት አባላት የኬሚካል ጥቃቱ ተፈጸመ ወደ ተባለበት ሥፍራ ተጉዘው የማጣራት ሥራ ለማከናወን አንድ ቀን ሲቀራቸው መሆኑ ደግሞ፣ ጉዳዩ ይበልጡኑ በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመ በነጋታው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የአሜሪካ የመከላከያ ተቋም ፔንታጎን ቃል አቀባይ የሆኑት ዳና ኋይት፣ የተገኘው መረጃ አሳማኝና ጥቃቱን ለመፈጸም ብቁ እንደሆነ ገልጸው መረጃው የደኅንነት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና ተገኘ የሚባለው መረጃ አጠራጣሪ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የመጀመርያው አጠራጣሪ ጉዳይ መረጃው የተገኘበት ምንጭ ነው፡፡ መረጃዎቹ ከየት እንደተገኙ ከአሜሪካም ሆነ ጥቃቱን ከፈጸሙት አጋሮቿ ባይገለጽም፣ ከሁለት ምንጮች እንደሆነ የተለያዩ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

የመጀመርያው የመረጃ ምንጭ ከሶሪያ መንግሥት ጋር እየተዋጋ የሚገኘው ጃኤሽ አል ኢስላም ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ቡድን በሥፍራው የራሱ ፍላጎት ስላለውና የሶሪያ መንግሥት የበላይነትን እየተቀዳጀ ስለመጣ፣ የአሳድን መንግሥት ለማዳከም በሚል የተጠቀመበት ሥልት ነው የሚሉ አሉ፡፡

ሁለተኛው ምንጭ ደግሞ ‹‹ባለ ነጭ ቆብ›› እየተባሉ የሚጠሩት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪዎች ናቸው፡፡ በሥፍራው የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃት ተፈጽሟል በማለት ይኼንን ያሳያሉ የተባሉ ምሥሎችን በተለይ በፌስቡክና በትዊተር የለቀቁትም እነዚህ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና በካናዳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚደገፉ በመሆናቸው፣ መረጃዎቹ ከእነርሱ መገኘታቸው  አጠራጣሪነታቸውን አጠናክሮታል፡፡

ለእንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች የሚውሉ አለባበሶችንና ጥንቃቄዎችን ያሟሉ ቢሆኑም፣ የዚህ ባለ ነጭ ቆብ አባላት ግን በጂንስና በቲሸርት ሆነው የኬሚካል ጥቃት ተፈጸመበት የተባለን ሕፃን በውኃ ሲያጥቡት ታይቷል፡፡ ይህም የውሸት ማስረጃ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አስነስቷል፡፡

ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ
በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የሩሲያው መልዕክተኛ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ የምዕራባውያንን ጥቃት ለመቃወም ላቀረቡት ሰነድ ድምፅ ሲሰጡ

 

ከዚህ በተጨማሪም ሶሪያ እ.ኤ.አ. በ2013 ያላትን የኬሚካል የጦር መሣሪያ ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ የኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ድርጅት ለሚባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ማስረከቧን በመጥቀስም፣ የጥቃቱን አሳማኝነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ ብዙ ናቸው፡፡

ትክክለኛ ማስረጃዎች ቢኖሩ አሜሪካ ከሩሲያና ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት ጋር በመጋራት የተቀናጀ የወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማስተባበር እየቻለች፣ ለምንስ በችኮላ ጥቃቱን ለመፈጸም ወደደች? ብለው የጠየቁም ነበሩ፡፡

ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ አለኝ ያሉትን መረጃ ይዘው ኮንግረስ ቀርበው ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ፈቃድ ማግኘት ስለማይችሉ፣ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው አስወሰኑ፡፡ እንግሊዝና ፈረንሣይም በፓርላማቸው አለን ያሉትን መረጃ ይዘው ተከራክረው ማለፍ እንደማይችሉ ሲያውቁ፣ ቀላሉንና ፈጣኑን አቋራጭ መንገድ መረጡ፡፡

የእንግሊዝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በምን ሕጋዊ መርህ ይኼንን ድርጊት ሊፈጽሙ እንደቻሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ ድርጊቱም ጠቅላይ ሚኒስትሯን ከሥልጣን እስከማውረድ የሚደርስ ውጤት ሊኖረው ይችላል የሚሉም አሉ፡፡

አሜሪካ ልክ ኢራቅ ላይ እንደፈጸመችው ዓይነት የተሟላ ጦርነት ያላደረገችበት ሌላኛው ምክንያት የሰሜን አትላንቲክ የቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው ቱርክ፣ በአሜሪካ ከሚደገፉት የኩርድ አማፅያን ጋር ጦርነት ላይ በመሆኗ፣ አጋርህ ከጠላትህ ጋር እየተኛ ወደ ጦርነት አትገባም የሚለውን የጦርነት ሀ ሁ በመከተል ከሙሉ ጦርነት እንደሸሸችም እንደማሳያ የሚገልጹ አሉ፡፡

ይኼም በኔቶ አባላት መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ሩሲያ የሶሪያን ጥቃት በጥብቅ ያወገዘች ሲሆን፣ በሶሪያ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ጥቃት የከፋ ውጤትን ሊያስከትል ይችላልም ብላለች፡፡ በዚህም የሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊጀመር ይችላል የሚሉ መላ ምቶች እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና የአሜሪካና የአጋሮቿ ሚሳይሎች የሩሲያንም ሆነ የሒዝቦላን ንብረቶች ዒላማ አላደረገም፡፡

በጥቃቱ ማግሥት በተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሩሲያ የቀረበው ጥቃቱን የማውገዣ ሰነድ ሦስት ድጋፎችን ብቻ በማግኘቱ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆነችው ኢትዮጵያም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ እንቅስቃሴ እንዲደረግ፣ ብልኃት የተሞላበት ድርጊት እንዲኖርና ኃያላን አገሮች በፍጥነት ወደ ውይይት እንዲመለሱ በመልዕክተኛዋ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ አማካይነት አሳውቃለች፡፡

ከሶሪያ የሚሳይል ጥቃት በስተጀርባ
በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የአሜሪካ መልዕክተኛ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ አገራቸው ሠራዊቷን ከሶሪያ እንደማታስወጣ ሲናገሩ