Skip to main content
x
ሀገረሰባዊ የሕክምና ጥበብ

ሀገረሰባዊ የሕክምና ጥበብ

የባህል ሕክምና ከዘመናዊ ሕክምና የተለየ ጥበብን እንደሚፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተፈጥሮና በሳይንስ መካከል ያለውን ሚዛናዊነት የማስጠበቅ ባህሪ እንዳለውም የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ አንድ የባህል ሐኪም ለታማሚው ፈውስ ለመስጠት የታማሚውን አካላዊ፣ አዕምሯዊና መንፈሳዊ ሁኔታ በጥልቀት ማጤን ይጠበቅበታል፡፡ ይህም የተለየ ጥበብንና ተሰጥኦን የሚጠይቅና ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ፀጋ ተደርጎ ይታሰባል፡፡

በባህላዊ ሕክምና መድኃኒቱ ከሚቆረጥበት ዕለትና ጊዜ ጀምሮ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች አሉ፡፡ ዕፀዋት የተፈጠሩት በዕለተ ማክሰኞ ነው ተብሎ ስለሚታመን ባህላዊ ሐኪሙ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፀዋትን የሚቆርጠው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ መድኃኒቱን ለመቁረጥ ከመውጣቱ አስቀድሞ መደረግ ያለባቸው የተለያዩ ጥንቃቄዎችም አሉ፡፡

ለምሳሌ አንድ የአፋር ብሔረሰብ የባህል ሐኪም የሚከተላቸው የመድኃኒት ዕፀዋት አቆራረጥ ሥነ ሥርዓት አሉት፡፡ የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች በሚል ርዕስ በተዘጋጀው መጽሔት መሠረት፣ ሐኪሙ መድኃኒት ለመቁረጥ ከቤቱ መውጣት ያለበት በቀን በተወሰኑና ሰው በማይበዛባቸው ሰዓታት ነው፡፡ መድኃኒት ለመቁረጥ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ንፁህ መሆን ግድ ነው፡፡ በአዕምሮ ተንኮል እያሰላሰሉ መድሐኒት መቁረጥና ለታማሚው መስጠት ዋጋ ዋጋ የለውም ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለዚህም በተቻለው ሁሉ ተንኮል አለማሰብ አለበት፡፡ መድሐኒቱን ከመቁረጡና ከቆረጠ በኋላ ከቅዱስ ቁርዓን ውስጥ የተወሰኑ አንቀጾችን መቅራት አለበት፡፡

አንዳንድ በምሽት ሲቆረጡ ዕርኩስ መንፈስ የማዝያስ ባህሪ ያላቸው ዕፀዋት አሉ ተብሎ ስለሚታሰብ አብዛኞቹ የብሔረሰቡ የባህል ሐኪሞች መድኃኒት መቆረጥ ያለበት በቀን እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ በረመዳን ወር፣ በአረፋና በመውሊድ በዓላት ዕለት የመድኃኒት ዕፅ አይቆረጥም፡፡ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ መድኃኒት መቁረጥም አይመከርም፡፡ የተቆረጠው መድኃኒት ቤት እስኪገባ ድረስ በምንም ዓይነት ውኃ ሊነካው አይገባም፡፡

በዚህ መለኩ መድኃኒቱ ከተቆረጠ በኋላ ሕክምናውን ለመስጠት ከታማሚው ጋር ቤተሰባዊ ግንኙት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ሕክምናው ከተደረገለት በኋላ መድኃኒቱ እስኪያሽረው ከማድረግ መቆጠብ የሚገባው አንዳንድ ነገሮችም አሉ፡፡  በክልሉ የባህል ሕክምና ዕውቀት ያላቸው፣ ሕክምናውን ከአሥር ዓመት ዕድሜአቸው ጀምሮ መስጠት ይችላሉ፡፡

የባህል ሕክምና በአፋዊና አንዳንዴ በጽሑፍ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘት ያለው ክዋኔ ነው፡፡ እንደ ዘመናዊ ሕክምና ማንኛውም ሰው በመማርና በማጥናት ሕክምናውን መስጠት አይችልም፡፡ ለበሽታው የሚዘጋጁ ቅመማዎች ምስጢራዊና ዕውቀቱም ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚተላለፍ ነው፡፡ አንድ ባህላዊ ሐኪም ዕውቀቱ እንዲሰጠው የተለየ ነገር ሊኖረው ይገባል፡፡ አካላዊ፣ አዕምሯዊ መንፈሳዊ ስሜቶችን የሚመረምሩ ዓይኖች ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ባህላዊ ሕክምና ከጥበብ የሚቆጠረው፡፡

የተለያዩ ዕፆች የዕፀዋት ቀንበጥ፣ ቅጠል፣ ቅርፊት፣ ሥር፣ ግንድ የእንስሳት ተዋፆዎችና የተለያዩ ማዕድናት ለባህላዊ ሕክምና ግብዓት ናቸው፡፡ ጤና አዳም፣ ነጭ ሽንኩር፣ ዝንጅብል፣ ዳማከሴ፣ ኮሶ፣ ሬት፣ ሎሚ የመሳሰሉት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በባህላዊ መንገድ ራሱን ለማከም ከሚጠቀምባቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ እርኩስ መንፈስን እንደሚያርቅ ስለሚታመንበት ብዙዎች ጤና አዳምን በየበረንዳቸው ሲተክሉ ይታያል፡፡ ጉንፋን የያዛቸው አንዳንዶችም ወደ ዘመናዊ ሕክምና መስጫ ከመሄድ ይልቅ በዳማከሴ መታጠብን፣ መጠጣትና መተሻሸት ይመርጣሉ፡፡

በኤፍራጥስና በጢግሮስ ወንዞች ዳርቻ ላይ ይኖሩ የነበሩ የሱሜሪያ (በአሁኑ ኢራቅ) ሕዝቦች ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ4,000 ዓመታት በፊት፣ እንዲሁም ግብፆች ከ3,700 ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በፊት ባህላዊ መድኃኒቶችን መጠቀም እንደጀመሩ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

ዘመናዊ ሕክምና አስኪጀመር ድረስ ፈውስ የሚገኘውም በባህላዊ ሕክምና ነበር፡፡ ትልቅ በጀት ተይዞለት በቂ ጥናት በሚደረግበት በዘመናዊ ሕክምና የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንደሚቻል ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ይሁንና በአፍሪካና በእስያ የሚገኙ 80 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የባህላዊ ሕክምና ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ አራት ቢሊዮን የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የባህላዊ ሕክምና ተጠቃሚ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚሰጡ ባህላዊ የሕክምና ዓይነቶች፣ በቻይና ለሚሰጡ የባህል ሕክምናዎች ዕውቅና ከሰጠ ሰነባብቷል፡፡ በባህላዊ ሕክምና ቀዳሚ የሆነችው ይህች አገር እ.ኤ.አ. በ2012 በባህላዊ ሕክምና ብቻ 83 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ችላለች፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. 2011 በዘርፉ ካገኘችው ገቢ የ20 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡

ከሌሎቹ አገሮች አንፃር የባህላዊ ሕክምናዎችን ብዙም እንደማይጠቀሙ በሚነገርላቸው በዩናይትድ ኪንግደም አካባቢዎች ለባህላዊ ሕክምና በየዓመቱ 230 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚወጣ የዓለም የጤና ድርጅት ከዓመታት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የዓለም የባህላዊ መድኃኒቶች ገበያ 115 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል የሚል ትንበያም አለ፡፡

በዚህ መጠን የአገርን ኢኮኖሚ እያንቀሳቀ የሚገኘው ባህላዊ ሕክምናን ምዕራባውያን ሰፊ ጥናት እያደረጉበት ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ግን የበርካታ ባህላዊ መድኃኒቶች መፍለቂያ በሆነችው አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ለባህላዊ መድኃኒቶች ተገቢው ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

‹‹የአገር በቀል መድኃኒቶች ቅመማና አጠቃቀም በምሥራቅ ጎጃም ዞን›› በሚል እሑድ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቀረበው ጥናት ይህንኑ እውነታ የሚያጠናክር ነው፡፡

ጥናቱ የአገር በቀል ዕውቀት (ባህላዊ መድኃኒቶችን አካቶ) አብዛኛውን ጊዜ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበት መንገድ በቃል ወይም አንዱ ከአንዱ በመኮረጅ በመሆኑ ባለበት ይዘትና ቅርፅ ለማቆየት አስቸጋሪ እንደሆነና ለመጥፋት የመጋለጥ ዕድሉም በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡

የጥናቱ መነሻም፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ያልታወቁ ትኩረት የተነፈጋቸው በርካታ አገረሰባዊና አገር በቀል መድኃኒቶች መኖር እንደሆነ ጥናቱን ያደረጉት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲት በሀዲስ ዓለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የባህል ጉዳዮች ጥናትና ምርምር አስተባባሪ ወ/ሮ ደጅይጥኑ አለነ ይገልጻሉ፡፡

በጥናቱ የተካተቱ የባህላዊ መድኃኒት አዋቂዎች በአካባቢያቸው በሰዎች፣ በእንስሳትና በሰብል ላይ የሚከሰቱ 12 ዓይነት በሽታዎችን ለይተው በማውጣት ለእያንዳንዳቸው መድኃኒት አዘጋጅተዋል፡፡  ለቁንጫ፣ ትኋንና አይጥም እንዲሁ፡፡ መድኃኒቶቹን ለማዘጋጀት ቅንጭብ፣ ምሬዝ፣ እሬት፣ ጭረት፣ የአዞ ሐረግ፣ ሰንሰል፣ የገበር እንቦይ፣ ቅንቦ፣ የጅብ ሽንኩርትና ቁልቋል የተባሉ የዕፀዋት ዓይነቶችን ተጠቅመዋል፡፡ መድኃኒቶቹ ተሞክረው ውጤታማ መሆናቸውንም ወ/ሮ ደጅይጥኑ ተናግረዋል፡፡

 ‹‹ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረው የባህላዊ መድኃኒት ቅመማ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ በግልና በቡድን ነበር፡፡ የመድኃኒቱ የመቀመሚያ ሒደትም ምስጢራዊና ተምሳሌታዊ ነበር፤›› ሲሉ መድኃኒቱ የሚቆረጥበት፣ የሚቀመምበት ቀን ሳይቀር ተምሳሌታዊነት ያለው እንደሆነ፣ ይህኛው ግን ከዚህ በተለየ መንገድ የተዘጋጀ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ልክ እንደ ምርምር ሙከራዎችን በማድረግ የግኝቶቹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ መቻላቸውንም ያክላሉ፡፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን እየተጠቀሙበት እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ባህላዊ ሕክምናዎች በልምድ ብቻ የሚሠራባቸው መሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብቻ እንዲወሰን አድርጓል፡፡ ይህም ሐገረሰባዊ ዕውቀት ብዙ ርቀት እንዳይሄድ አድርጎታል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ባህላዊ መድኃኒት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ መድኃኒቱ ለማንም ከተነገረ ይረክሳል በሚል ዕምነት ምስጢራዊ ሆኖ በቃል እንዲተላለፍ መደረጉ ግን የሚገባውን ያህል እንዳይበለፅግ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም፣ አገላብጦ የሚያያቸው ስለጠፋ እንጂ የተለያዩ በመድኃኒት ቅመማ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍት እንዳሉ በመጥቀስ የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ዕፀ ደብዳቤ፣ መጽሐፈ መድኃኒት የባህላዊ መድኃኒቶች ከተከተቡባቸው መጻሕፍት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አቶ ፋንታሁን አየለ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ባህላዊ ፈውስ፣ ባህላዊ መድኃኒትና ቅመማ ላይ በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍት አሉ፡፡ የመድኃኒት ቅመማን በተመለከተ ምን ተቀላቅሎ ለምን ዓይነት በሽታ ፈውስ እንደሚሆን የሚያስረዱ የተለያዩ የብራና መጻሕፍትም አሉ፡፡ ይሁንና የግዕዝ ቋንቋ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እየተዳከመ መምጣቱና በቤተ ክህነት ብቻ መወሰኑ እነዚህ ጽሑፎች እንዳይነበቡ፣ የያዙት ዕውቀት ጥቅም እንዳይሰጥ አድርጓል፡፡

‹‹በጣም ብዙ ቁም ነገርና ዕውቀት ያላቸውን ማጻሕፍት እንዳናውቅ ሆነናል፡፡ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችም በጣም ውስን ናቸው፡፡ ባህላዊ መድኃኒቶችን በተመለከተ ብዙ መሄድ አልተቻለም፤›› ይላሉ፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላትም ቋንቋውን ማስተማር ግድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና እንዲህ ያሉት መጻሕፍት በተለያየ ጊዜ ከአገር ውስጥ ተሰርቀው መውጣታቸውን አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹አፄ ታዎድሮስ ራሳቸውን ባጠፉበት ወቅት እንግሊዛውያኑ ከቤተ መጻሕፍታቸው ብዙ መጻሕፍት ወስደዋል፡፡ ከወሰዱት መካከል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለማንቀሳቀስ የሦስት ሰዎች ትብብር የሚጠይቁ ሁለት ትልልቅ ዕፀ ደብዳቤ የተባሉ ስለ ባህላዊ መጽኃኒቶች የሚዘረዝሩ ይገኙባቸዋል›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥንታውያት መዛግብት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉ በርካታ መጻሕፍት በተለያዩ ጊዜያት ከአገር ተሰርቀው መውጣታቸውና በሌላ አገሮች ምርምር እየተደረገባቸው እንደሚገኝ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ ሕክምና ከተጀመረ 100 ዓመት አልሞላውም፡፡ ከዛ በፊት ሰዎች ሲታመሙ የሚታከሙት በባህላዊ ሕክምና ነበር፡፡ ይሁንና ተገቢው ትኩረት ስላልተሰጠውና ጥናት ስላልተደረገበት የሚጠበቅበትን ያህል ማደግ አልቻለም፡፡ ‹‹መጽሐፍ መድኃኒት ላይ ይህንን ቅጠል ከዚህ ነገር ጋር ቀምመህ ለዚህ በሽታ ተጠቀም ይላል፡፡ ይህንን በደንብ ጥናት አድርገንበት መድኃኒቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በፋብሪካ ደረጃ ማምረት የሚቻልበት አቅም መፈጠር ነበረበት፡፡ አሁን እኮ በተገኘው ነገር ደቁሰው ነው የሚያቀርቡት፤›› በማለት ቸል መባሉንም ይኮንናሉ፡፡

ምሁራን የሀገረሰባዊ መድኃኒትን ምንነት የአጠቃላይ ዕውቀትና ተግባር ድምር ውጤት የሆነ፣ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ማኅበራዊ ጠንቆችንና ተውሳኮችን ለመከላከልና ለማስወገድ እንዲሁም ለመመርመር የሚተገበር ሙያ በማለት ይገልጹታል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከመስፋፋቱ አስቀድሞ ለዘመናት ሲተገበር የቆየ፣ ከሰው ልጅ ንቃተ ህሊና፣ አስተሳሰብና ፍልስፍና ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የዘመናት ጥበብ፣ ልምድ፣ ተሞክሮና ዕውቀት ውጤት በማለት ወ/ሮ ደጅይጥኑም በጥናታቸው ገልጸውታል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ደግሞ በዕውቀትና በእምነት ላይ ተመስርቶ የተለያዩ ዕፀዋት፣ እንስሳት፣ ማዕድናትና፣ የመሳሰሉትን በተወሰነ የቅመማ ሒደት አዘጋጅቶ በሽታን ለማከም፣ ለመከላከልና ጤናን ለመጠበቅ የሚደረግ ክንውን በማለት ይገልጸዋል፡፡ መንፈሳዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ሕክምናንም ከባህላዊ ይመድበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ መንፈሳዊ ተአምራት የሚሠራበት አገር እንደመሆኗ ሰዎች ጤናቸውን ለመመለስ በየሃይማኖታቸው የሚያደርጉት ድርጊት ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ዶ/ር መርሻ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሌላው ዓለም እንዲህ ያሉ ነገሮች በደንብ ጥናት ይደረግባቸዋል፡፡ እኛ ጋ ያሉትን ዝም ብሎ ከመግፋት የራሳቸው የተለየ ቀመር ያላቸው እንደሆነ ማጥናትና በስፋት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል፤›› በማለት መንፈሳዊ ሕክምናዎችም ካላቸው ጠቀሜታ አኳያ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡