Skip to main content
x

ለሙሰኞች ሀብት ምቹ ምሽግ የሆነው የእሽሙር ማኅበር ነገር

በውብሸት ሙላት

ከሰሞነኛዎቹ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የፀረ ሙስናው ዘመቻ ነው፡፡ በዘመቻውም ከሃምሳ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሥልጣናት፣ ባለሀብትና ደላላዎች ታስረዋል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሀብታቸው በፍርድ ቤት ታግዷል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት የሚሠራጩት መረጃዎች ግን መታሰር ያለባቸው ዋናዎቹ ገና አልተነኩም የሚል ይዘት አለው፡፡

በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሠራጨው የሰዎችን ስም እንዲሁም ንብረታቸው የሚሉትን ጭምር አልፎ አልፎ በሐሜት መልኩም ቢሆን ሲገልጹ ይታያል፡፡ በርካታ ሕንፃዎችንም ሆነ የንግድ ተቋማትንም ሳይቀር በስም እየጠቀሱ የእንቶኔ ባለሥልጣናት እንደሆኑ በሕዝብ ዘንድ የሚታወቅ፣ ነገር ግን በሐሜት መልክ የሚወራ ነው፡፡

ሐሜቱን ለማረጋገጥም ይሁን ለማስተባበል የሚያስችል መረጃ ማግኘት አዳጋች ስለሆነ ሕዝብ በእንደዚህ ዓይነት አሉባልታ እንዲጠመድም፣ እንዲታመስም የመንግሥት አሠራር በራሱ ምቹ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ሐሜት የተመቹና የተጋለጡ በሕጋዊ መንገድ የሚሠራባቸው የንግድ ድርጅት አለ፡፡ ይኸውም፣ የእሽሙር ማኅበር (Joint Venture) ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍም ዋና ዓላማ የእሽሙር ማኅበር ምንነትና ባህርያት በማሳየት በሙስናና በሌሎች ሕገወጥ አሊያም ተገቢ ባልሆኑ አሠራሮች የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማድረጊያ ዘዴ መሆኑን በማሳየት መፍትሔ መጠቆም ነው፡፡

ገበያ መር ኢኮኖሚን በሚከተል አገር መንግሥት በገበያ ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት አጋጣሚዎች ውስን ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ የገበያ ጉድለት ሲያጋጥም፣ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል የአገሮች ተሞክሮዎች ምስክር ናቸው፡፡ በአገራችን ደግሞ በስፋት ሊያጋጥም እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም፣ ገበያው ላይ ጉድለት ሳይኖርም መንግሥት በራሱ ነጋዴ የሆነባቸው ዘርፎች በርካታ ናቸው፡፡

ከዚህ የበለጠ ጣልቃ የሚያስገባው ምክንያት ግን መንግሥት የሚከተለው የልማት መንግሥት ፖሊሲ ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥትነቱን የሚፈታተኑ ተግባራት እየተፈጸመ ነው ብሎ ሲያምን ጣልቃ ይገባል፡፡ ቁም ነገሩ ያለው ጣልቃ ከመግባቱ ላይ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱን መርህ የሚያዛባ ተግባር በመንግሥት ባለሥልጣናትና በንግድ ድርጅቶች እንዲሁም በግለሰቦች ጭምር ሊፈጸም መቻሉ ነው፡፡ በመንግሥት ስም ጣልቃ እየገቡ የሚወስኑት ያው ባለሥልጣን የሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ጣልቃ መግባት ማለት ደግሞ ባለሥልጣኖቹ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ማሳለፍ ማለት ነው፡፡

ውሳኔዎቹ ከቅን ልቦና የመነጩና የሕዝብን ጥቅም ያስቀደሙ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ግምቱን ውኃ እየበላው፣ አንዳንዶቹ ባለሥልጣናት ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግለሰቦችንና ወይም የራሳቸውን ጥቅም ማስቀደማቸው አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ቢሆንም፡፡ የዚህ ዓይነትን ሁኔታ ከሚፈጥሩት አጋጣሚዎችና እንደመገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱት ሁኔታዎች መካከል አንዱ በግልጽ የሚታወቀው የሙስና ተግባር ነው፡፡

 

የሙስና ተግባር ገበያን በማዛባትና የተወሰኑ ሰዎችን ጥቅም በማረጋገጥ ሊፈጸም የሚችል ሲሆን በሌላ በኩል የጎደለን ገበያ ለማስተካከል መንግሥት በሚወስደው የጣልቃ ገብነት ዕርምጃ ብርቱ ጥንቃቄ ካላደረገ በስተቀር የመፈጸም ዕድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡ ይህንን ተገቢ ያልሆነ አሠራር ለመዋጋት የሚያስችል የመንግሥትን አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ማድረግን የሚጠይቅ ሕገ መንግሥታዊ መርህ አለ፡፡ የወንጀል ኃላፊነትን የሚጥሉ በርካታ ሕግጋት አሉ፡፡ እንዲሁም ባደረሱት ጉዳት መጠን በፍትሐ ብሔርም ካሳ የመክፈል ግዴታም ይኖርባቸዋል፡፡

ሕጎቹ ይደርደሩ እንጂ፣ የሕግ የበላይነትን የማስፈን የዘወትር ግዴታቸው የሆኑት ተቋማት ያለባቸውን ግዴታ ወቅት እየጠበቁ ዘመቻ ከማከናወን ባለፈ በአዘቦት ቀናት ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ነገሩን የሚያወሳስበው፣ ባለሥልጣናቱ ራሳቸው (በዘመድ አዝማዳቸው ስም) ንግድ ውስጥ በመግባት በኢኮኖሚው ላይ ጣልቃ የሚገቡት የራሳቸውንም ጥቅም ከግምት በማስገባት ሊሆን መቻሉ ላይ ነው፡፡

በተለይ ራሳቸው ነጋዴ እንዲሆኑ የእሽሙር ማኅበር እጅግ የተመቸ መሆኑ ነው፡፡ የእሽሙር ማኅበር ምቹነቱን ለማስረዳት ይመች ዘንድ ምንነቱንና ባህርያቱን አስቀድመን እንመልከት፡፡

የእሽሙር ማኅበር ምንነት

በ1952 ዓ.ም. የወጣውና አሁንም በሥራ ላይ ያለውን የንግድ ሕግ በሁለት ምድብ ውስጥ የሚካተቱ የንግድ ድርጅቶችን ዕውቅና ይሰጣል፡፡ እነሱም የሽርክና ማኅበርና ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ስለኩባንያዎች ገለጻ ማድረግ ለዚህ ጽሑፍ ብዙም እርባና ስለማይኖረው እዚሁ ላይ ቆሟል፡፡

 

የሽርክና ማኅበር በተራው በአራት ዓይነት  በአንዱ ሊቋቋም ይችላል፡፡ እነዚህም፣ ተራ የሽርክና ማኅበር፣ የኅብረት የሽርክና ማኅበር፣ የእሽሙር ማኅበር፣ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር ይባላሉ፡፡ የመጀመርያው ዓላማቸው ትርፍ ላልሆኑ የሙያ ማኅበራትና መሰል ድርጅቶችን ለማቋቋም ይጠቅማል፡፡ ትርፍ በሚያስገኝ መስክ መሰማራት የሚፈልጉ ሰዎች በዚህ መልክ ማኅበር ማቋቋም አይችሉም፡፡

በሽርክና የንግድ ድርጅትን በማቋቋም ትርፉንም ዕዳውንም ለመጋራት ሲባል የሚቋቋመውና በብዛት በኅብረተሰቡ ዘንድ የተለመደው የኅብረት ሽርክና ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ ላይ ዕዳ ያላቸው ሰዎችም ሲፈልጉ ከሸሪኮቹ አንደኛውን ወይም ሁለቱን ወይም ሁሉንም መርጦ የመክሰስ መብትን ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ሦስተኛ ወገኖች ከእንዲህ ዓይነቱ ማኅበር ጋር ውል ሲፈጽሙ አመኔታቸው ከፍ ይላል፡፡ ገንዘባቸውን ለማስመለስ አማራጮች ስላላቸው፡፡

ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር ሲባል ደግሞ፣ በአንድ በኩል ከኅብረት የሽርክና ማኅበር ሸሪኮች ጋር ተመሳሳይ ግዴታ ያላቸው አባላት ሲኖሩበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማኅበሩ ላይ ባላቸው መዋጮ ልክ ብቻ ኃላፊነት ያለባቸውን ሸሪኮች ያላቸውን አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በመዋጯቸው ልክ ኃላፊነት ያለባቸው አባላት፣ መብትና ግዴታዎቻቸው ከአክሲዮን ማኅበር ባለአክሲዮኖች ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ሌሎቹ ግን እንደ ኅብረት የሽርክና ማኅበር አባላት ድርጅቱ ላይ “ገንዘብ አለን” የሚሉ ሰዎች ከግል ንብረታቸው ሳይቀር ሊጠይቋቸው ይችላሉ፡፡

እነዚህ ሦስቱ ማኅበራት የሚመሠረቱት በጽሑፍ ነው፡፡ ለሁሉም ማኅበራት ቢያንስ ሁለት አባላት ያስፈልጉታል፡፡ በጽሑፍ ያደረጉትን የመመሥረቻ ጽሑፍም የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው፡፡

 

የእሽሙር ማኀበር ግን ሸሪኮቹ በጽሑፍ ቢሆንም ባይሆንም በፈለጉት መንገድ መመሥረት ይችላሉ፡፡ በጽሑፍ ቢመሠርቱት እንኳን አይመዘገብም፡፡ ከተመዘገበ የእሽሙር ማኅበርነቱ ይቀርና የኅብረት ሽርክና ይሆናል፡፡

የእሽሙር ማኅበር (Joint Venture) የሚባለው አደረጃጀት ዓይነት ከአማርኛው ይልቅ የእንግሊዝኛው ስያሜ በተወሰነ መልኩ የተሻለ ይገልጸዋል፡፡ ቢያንስ በጋራ የሚሠራ፣ የሚተገበር ሥራ መኖሩን፣ በጋራ የሚፈጠር ድርጅት እንዳለ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ድርጅት አንድን ነገር በጋራ ለመፈጸም ሲባል የሚቋቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡

በጋራ የሚሠሩት ግለሰብ ከግለሰብ፣ ግለሰብ ከድርጅት፣ ግለሰብ ከመንግሥት፣ ድርጅት ከድርጅት፣ ድርጅት ከመንግሥት ያለበለዚያም መንግሥት ከመንግሥት ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ለሕግ ሰዎች ስለሆኑ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በጋራ የሚፈልጉትን ግብ ለማሳካት ሲሉ ሊያቋቁሙት ከሚችሉት የድርጅት ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሰው ግን ግለሰብ ከግለሰብ ጋር የሚመሠርቱትን ነው፡፡

በመሠረቱ የእሽሙር ማኀበር ማንኛውም የሽርክና ማኅበር የሚመራበትን ሁኔታ ይከተላል፡፡ ነገር ግን መመሥረቻ ጽሑፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ወዘተ የሚባሉትን ሰነዶች ላይጠቀም ይችላል፡፡ አባላቶቹ በፈለጉት መንገድ በውል የሚያቋቁሙት ነው፡፡ ስለሆነም መነሻውም ሆነ መፈጠሪያው ውል ነው፡፡ ውሉ ደግሞ በጽሑፍም ያለበለዚያም በቃል ሊሆን ይችላል፡፡ የማኅበሩ ዓላማንም በተመለከተ ትርፍ ለማስገኘት ሲባል የተቋቋመ የንግድ ድርጅት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ምልከታችን ግን ለንግድ ሲባል የሚቋቋመውን ነው፡፡

 

በዚህ መንገድ የሚደራጅና ንግድ ውስጥ የሚገባ ድርጅት ብዙ ጊዜ የሚታወቀው በአንድ ነጋዴ እንደሚተዳደር ነው፡፡ የንግድ ፈቃድ የሚወጣውም እንዲሁ በሚያስተዳድረው ወይም ባለቤት እንደሆነ በሚታወቀው ሰው ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አቶ “ሀ” የተባለ ግለሰብና ወ/ሮ “ለ” የምትሰኝ ሴት አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ከፈቱ እንበል፡፡ ወ/ሮ “ለ” በተለያዩ ምክንያቶች በሆቴል ሥራው ውስጥ ዕለት ከዕለት መሳተፍም ሆነ ማስተዳደር ስላልፈለገች ገንዘብ ብቻ አዋጣች፡፡ መዋጮውንም የሚያውቁት ሁለቱ እንጂ መንግሥትና ሦስተኛ ወገኖች አይደሉም እንበል፡፡

እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ የሆቴል ሥራ ለማከናውን ፈቃድ የሚያወጣውም ሆነ ሌሎች ነገሮች የሚያከናውኑት በባለቤትነትም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ሰዎች ዘንድ የሚታወቀው አቶ “ሀ” ነው፡፡ ወ/ሮ “ለ” ንግዱን ከጀርባ ሆና ታስኬድ እንደሆነ እንጂ በአደባባይና ሕጋዊ ውጤት የሚኖራቸውን ተግባራት በሆቴሉ ስም ልታከናውን አትችልም፡፡ በሁለታቸው የተቋቋመ መሆኑ መንግሥትና ሌሎች አካላት ካወቁት የእሽሙር ማኅበርነቱ ይቀርና የኅብረት የሽርክና ማኅበር ይሆናል፡፡ በዚህን ጊዜ ደግሞ ተፈጻሚ የሚሆነው የኋለኛውን ማኅበር የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

እንደ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ የንግድ ሕግ ላይ የእሽሙር ማኅበር የየመመሥረቻ ጽሑፍ እንዲኖረው ያስገድዳል፡፡ በተጨማሪም ሰነድ ለማረጋገጥ ሥልጣን ባለው  አካል መረጋገጥ አለበት፡፡ ሆኖም በንግድ መዝገብ የማስመዝገብ ሥርዓት ተፈጻሚ አይሆንበትም፡፡  የእሽሙር ማኅበር መኖሩ ለሦስተኛ ወገኖች የታወቀ አይደለም፡፡ የማኀበሩ መኖር በሦስተኛ ወገኖች ከታወቀ ማኀበሩ ከእነዚህ ወገኖች ጋር በሚኖረው ግንኙነት እንደ አንድ የሽርክና ማኀበር ይቆጠራል የሚለው ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

በረቂቅ ሕጉ ሁለት ነገሮች ተጨምረዋል ማለት ነው፡፡ የመጀመርያው የእሽሙር ማኅበር ምሥረታ የግድ በጽሑፍ ሆኖ መመሥረቻ ጽሑፍ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የንግድ ሕግ አንቀጽ 271 ላይ ካለው የተለየ ነው፡፡ አንቀጽ 271  ማኅበርተኞቹ በውል ወስነው የሚያቋቁሙት እንጂ እንደ ሌሎቹ ማኅበራት በመመሥረቻ ጽሑፍ መቋቋም አለበት አይልም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ይህ የመመሥረቻ ጽሑፍ በሰነዶች ማረጋገጫ መፅደቅ እንደሚገባው ረቂቁ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ተቋም ካልፀደቀ የእሽሙር ማኅበር እንደተቋቋመ አይቆጠርም፡፡ ረቂቁ ሚስጥራዊነቱን ለማስጠበቅ የመረጠው በማኅበርነቱ የንግድ ምዝገባ አያስፈልገውም በማለት ነው፡፡ 

በእሽሙር ማኅበር ድርጅት ለማቋቋም የወሰኑ ሰዎች መዋጮን በተመለከተ  ግዴታዎች ከሌሎቹ ማኅበራት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ወደውና ፈቅደው በውል እስካልወሰኑ ድረስ እያንዳንዱ አባል ለከፈለው መዋጮ ባለቤትነቱን እንደያዘ ይቆያል፡፡ ያዋጡት ገንዘብም ሆነ ንብረት የድርጅቱም ሆነ የጋራ ሀብት አይሆንም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ የማኅበሩ እንዳይሆን ማኅበሩ ሕጋዊ ሰውነት ስለሌለው ሀብት አያፈራም፡፡ የአባላቱ የጋራ ሀብት ይሆናል እንዳይባል፣ አመሠራረቱም ሆነ አስተዳደሩ አባላቱ በነፃነትና ባሻቸው መንገድ እንዲያደርጉት ሕጉ አስቀድሞ ፈቅዷል፡፡ ወደውና ፈቅደው የጋራ እንዲሆን ከወሰኑም ሕጉ አይከለክልም፡፡ 

የአባላት በማኅበሩ ላይ የሚኖራቸውን የሀብት ሁኔታ በተመለከተ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር  33470 ኅዳር 2 ቀን 2001 ዓ.ም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ለውሳኔው መነሻ የሆነው ክርክር የተነሳው የእሽሙር ማኅበር ሸሪኮች ከነበሩት ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛው በመሞቱ የሟቹ ሚስት የማኅበሩን ሀብት የጋራ እንደሆነ በመቁጠር ክፍፍል በመጠየቋ ነው፡፡

 

ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ እንዳመለከተው ተዋዋዮቹ ውል ሲያደርጉ በየግላቸው የነበሩዋቸውን መሣሪያዎች ይዘው መግባታቸውን ከውሉ ላይ በማስታወስ በዚህ ሁኔታ የጋራዥ ንግድ ሥራ በጋራ ቢያቋቁሙም መሣሪያዎቹ የግላቸው ትርፉ የጋራ ሆኖ ከመቀጠል ባለፈ ጋራዡ የሁለቱም እንደ ነበር ተቆጥሮ ሊፈርስ አይገባም፡፡ የተመዘገበውም በሕይወት ባለው ሸሪክ ስም በመሆኑ ባለቤትነቱ የእሱው ሆኖ እንደሚቀጥል የንግድ ሕጉን አንቀጽ 273 ዋቢ በማድረግ ወስኗል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ አስገዳጅነቱ አባላት በውላቸው ላይ የድርጅቱ ሀብት የጋራ እንደሚሆን ካልገለጹ ብቻ ነው፡፡

ማኀበሩ ሲፈልግ በአባላቱ ወይም አባል ባልሆኑ በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ሥራ አስኪያጆች ሊተዳደር ይችላል፡፡ ለማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ የሚሆን ሰው በአባላቱ ሙሉ ስምምነት ካልተሾመ ሁሉም አባላት ሥራ አስኪያጆች እንደሆኑ ይቆጠራል፡፡ የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ ተግባርና ኃላፊነት በመመሥረቻ ጽሑፍ/በውል ይወሰናል፡፡ ሆኖም ይህ ውሳኔ በጽሑፍ መቀመጡ ለሦስተኛ ወገኖች መቃዎሚያ ሊሆን አይችልም፡፡ ማለትም ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት መኖሩን አያመለክትም፡፡

የእሽሙር ማኅበር ሥራ አስኪያጅ መሆን በርካታ ኃላፊነቶችን ያስከትላል፡፡ ስለማኅበሩ ለሌሎች ድብቅ በመሆኑ ለሦስተኛ ወገኖች የሚታወቀው የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ነው፡፡ ማኅበሩን መሠረት ያደረጉ የወንጀል ኃላፊነትም ይሁን የፍትሐ ብሔር ዕዳዎች ቢመጡ እስከመጨረሻው ድረስ ኃላፊ መሆንና ተጠያቂነት የሚወድቀው በሥራ አስኪያጁ ላይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሥራ አስኪያጁ ወካዮቹ እንደማይታወቁ እንደራሴ (Undisclosed Agent) ይቆጠራል፡፡ ከራሱ አንፃር ወኪል ነው፡፡ ነገር ግን ወካዮቹንም ሆነ ወኪልነቱን በሚመለከት ሦስተኛ ወገኖች አያውቁም፡፡

 

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ያልሆኑ አባላት ለማኅበሩ ዕዳዎች ተጠያቂ የሚሆኑት በማኅበሩ መመሥረቻ ስምምነት/በውሉ ላይ በተወሰነው መጠን ብቻ ነው፡፡ ሥራ አስኪያጆች ያልሆኑ አባላት በማኀበሩ ሥራ አመራር ተካፋይ ከሆኑ እርስ በርሳቸውና ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በአንድነትና በነጠላ ኃላፊዎች ይሆናሉ፡፡

እንግዲህ ይኼ በንግድ ሕጉ ላይ የተገለጸው ስለእሽሙር ማኅበር የተደነገገውን ከሞላ ጎደልና ለዚህ ጽሑፍ የሚያስፈልገውን ያህል ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ በመቀጠል የእሽሙር ማኅበርን ገጽታዎች በአጭሩ እንቃኝ፡፡

የእሽሙር ማኅበር ልዩ ባህርያት

ከላይ እንደተገለጸው የእሽሙር ማኅበር ተብሎ የንግድ ምዝገባ አይደረግም፡፡ ካልተመዘገበና በንግድ ማስታወቂያ መገለጽን የሚጠይቅ ሕግ የለም፡፡ ስለሆነም የሕግ ሰውነት የለውም፡፡

ሁለተኛው ገጽታው ሚስጥራዊነቱ ነው፡፡ በእሽሙር ማኅበር ሁለት ነገሮች ሚስጥራዊ ናቸው፡፡ ሚስጥራዊነታቸው ከሦስተኛ ወገን (መንግሥትንም ጨምሮ) ነው፡፡ ማኅበር መኖሩ አይታወቅም፡፡ እንዲሁም ማኅበርተኞቹ እነማን እንደሆኑም አይታወቁም፡፡ የማኅበርተኞቹ ማንነት የሚታወቀው እርስ በርሳቸው የሚያከራክር ጉዳይ ተነስቶ ፍርድ ቤት ሲሄዱ ነው፡፡

ሌላው የእሽሙር ማኅበር መለያ የተወሰነ ግብን ለማሳካት ሲባል የሚቋቋም መሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዘላቂነትና ለልጅ ልጅ እንዲተላለፍ በማሰብ አይቋቋምም፡፡ በመሆኑም ለአጭር ጊዜ ይመሠረታል፡፡ ከሆነ ጊዜ ወይንም የተወሰነን ግብ ካሳኩ ያለበለዚያም የተወሰኑ ሁኔታዎች ከተፈጸሙ በኋላ ሊቀር ይችላል፡፡

 

አባላት ድርሻቸውን በፈለጉት መንገድ ማስተላለፍ አይችሉም፡፡ በጣም ግላዊ ግንኙነትን ይጠይቃል፡፡ የማኅበሩ አባላት ከመነሻውም ዝምድናን ወይንም ጓደኝነትን መሠረት ስለሚያደርጉ እጅግ በጣም ግላዊ የሆኑ ግንኙነቶች ይበዙበታል፡፡ ይኼ ደግሞ መልሶ ሚስጥራዊነቱን ያጠናክረዋል፡፡

የእሽሙር ማኅበር የሚመራው በዋናነት በአመኔታ (በአማና) ነው፡፡ የአባላቱ ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር በጽሑፍ አይሰፍርም፡፡ አመኔታው ከላይ ከተገለጹት ግንኙነቶች የሚመነጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም እርስ በርሳቸው ሊኖራቸው የሚችለው የጥቅም ግንኙነት ጥብቅ በሆነ አመኔታ እንዲመራ ሊያስገድደው ይችላል፡፡

ሌላው መለያው ከሕግም ይሁን ከሌላ የሚመነጩ ጥብቅ ሥነ ሥርዓት ስለሌሉበት ሁልጊዜ መከበርና መፈጸም ያለባቸው ስብሰባ፣ የውሳኔ ሥርዓት፣ ወዘተ የሉትም፡፡

እነዚህ ከእሽሙር ማኅበር መለያዎች የተወሰኑት ናቸው፡፡ ለመሆኑ በእነዚህ መልኩ የንግድ ድርጅትን ማቋቋም ስለምን አስፈለገ? የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡

የእሽሙር ማኅበር ዓላማው

እንግዲህ አሁን በሥራ ላይ ያለው የንግድ ሕግ በግል ከመነገድ በተጨማሪነት ከስድስት ዓይነት የንግድ ማኀበራት አንደኛውን በመምረጥ ነጋዴዎች በንግድ ለመሰማራት ከፈለጉ የመምረጥ ነፃነትን ይሰጣል፡፡ ስድስቱም የማኅበራት ዓይነቶች የየራሳቸው የተለየ ባሕርያት፣ አሠራር፣ ጥቅምና ጉዳት አላቸው፡፡ የንግድ ሕጉ  ስለምን የእሽሙር ማኅበርን መረጠ ለሚለው መልሱ በቀጥታ ከሕጉ ባይገኝም ከአርቃቂዎቹ ማስታወሻ፣ ከባለሙያዎች ማብራሪያ ጥናትና እንዲሁም በሌሎች አገሮች ስላለው የእሽሙር ማኅበር ከተጻፉ ጽሑፎች በመነሳት ከዚህ በታች በተገለጹት ምክንያቶች ሕጋዊ ዕውቅናና ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡

የእሽሙር ማኅበር ዋናው ጠቀሜታው ግለሰቦች በንግድ ውስጥ መሳተፋቸውን በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ካልፈለጉ ይህን ፍላጎት ለማሳካት አማራጭ ስለሚሰጥ የመነገድ ነፃነትን ይሰጣል፡፡ ለአብነት አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም የሃይማኖት አባት ንግድ ውስጥ መግባት ፈልገው ነገር ግን በሕዝብ ዘንድ እንዳይታወቅ ቢፈልጉና ለንግድ የሚሆን ገንዘብም ፍላጎትም ቢኖራቸው፣ በሌላ ሰው ስም ለመነገድ እንዲችሉ ሕጉ ነፃነትን ይሰጣል፡፡

ሌላው ጠቀሜታው ደግሞ ለመመሥረትም ይሁን ለማፍረስ እንዲሁም ለማስተዳደር በጣም ቀላል መሆኑ ነው፡፡ የተለያዩ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ለምሥረታና ለምዝገባ ብዙ ጊዜ ማጥፋት፣ የተለያዩ የሒሳብ አያያዝ ደንቦችን የመከተል ግዴታ፣ ወዘተ ስለማይጠይቅ በቀላልነቱ ተመራጭ ነው፡፡

የእሽሙር ማኅበር እንደ ድርጅት በንግድ መዝገብ ስለማይገባ አባላቱ ግብር አይከፍሉም፡፡ ፈቃድ የወጣበት ንግድ ግብር ይከፍላል፡፡ ትርፉን አባላቱ ይከፋፈላሉ፡፡ እንደ ሌሎች ባለአክሲዮኖች ከሚደርሳቸው የትርፍ ድርሻ ላይ የገቢ ግብር አይከፍሉም፡፡ ግብር ሰብሳቢውም ሊደርስባቸው አይችልም፡፡

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ ደግሞ ማኅበሩ እንዲሰማራባት በተፈለገው በየንግድ ዘርፍ ሙያውና ልምዱ የሌላቸው ሰዎች ንግዱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ኃላፊነት ካለማወቅም ካለመፈለግም የተነሳ ገንዘባቸውን አዋጥተው ሌላ ሰውን ሸሪክ በማድረግ እንዲያስተዳድረውም በማድረግ ሊመጣ የሚችልን ኃላፊነት ለመገደብ ሲባል ይመረጣል፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ ኃላፊነቶችና ተጠያቂነቶች ያድናል፡፡

እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ ያልሆነው የማኅበሩ አባል የማስተዳደር ጣጣ ውስጥ ስለማይገቡ ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ ከሚመጡ ጫናዎች ይገላግላል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ከእሽሙር ማኅበር የሚገኙ ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡ ሕጉም ይኼን ዓይነት መንገድ ለሚመርጡ ለአሠራሩ ዕውቅና ሰጥቷል ጥበቃም አድርጓል፡፡ ችግሩ ግን ሕጉ ለማሳካት ያሰባቸውን ግቦች ለሌላ ዓላማ መዋላቸው ላይ ነው፡፡

በእሽሙር ማኅበር ለምን ማሸሞር

ሕጉ ሲነሳ ታሳቢ ካደረጋቸው ግቦች ውስጥ አንደኛው የመነገድ ነፃነትን መጠበቅ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ይህን ነፃነት ለማስከበር ደግሞ ሚስጥራዊነቱ እንዲጠበቅ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ሕጉ የሰጠውን ነፃነት ወደ መደበቂያነት ወይም መሸሸጊያነት በማገልገል ላይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ባለሥልጣን የሆኑ ሰዎች ንግድ ውስጥ ለመሳተፍ እጅግ የተመቸ ሆኗል፡፡ ውላቸውን በቤታቸው ወይም በአመኔታ ብቻ በማቋቋም በሌሎች ሰዎች ስም ለመነገድና በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊ የማድረጊያ ዘዴም ነው፡፡ 

በሙስናና በሌሎች ሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ንግድ ውስጥ በማዋል ከእንደገናም ሥልጣንን በመጠቀም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የራስን ጥቅም ለማካበቻነትም ይጠቅማል፡፡ የንግድ ችሎታ በማጣት ማኅበሩ ከሚያስከትለው ኃላፊነት ለመራቅ በማሰብ ሳይሆን የተለያዩ የሙስናና በሥልጣን ያላግባብ በመገልገል የሚመጡ የወንጀል ድርጊት መፈልፈያነት በመዋልም ላይ ይገኛል፡፡

በመሆኑም መንግሥታዊ ኃላፊነትን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ የግል ጥቅምን ለማካበቻነት ውሏል፡፡ ከላይ በዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ላይ የተገለጸው የልማታዊ መንግሥት አመራር ዘዬ ለባለሥልጣናት የሚሰጠው ሰፊ የመወሰን ሥልጣን ለሌላ ዓላማ እንዲውል ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ እንዲሁም ድርጅት እስከማቋቋም እንዲገፉ የእሽሙር ማኅበር ለሙሰኞች የተመቻቸ የሕግ ማዕቀፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሌላው ሕዝብ ከሚያሸሙርባቸው ጉዳዩች አንዱ ባለሥልጣናት በዚህ መንገድ ያቋቋሟቸውን ድርጅቶች በማሰብ ሕገ መንግሥቱም ይሁን ሌሎች ሕጎች የሚጠይቁትን መንግሥታዊ ግልጽ አሠራር ወደ ጎን በመተው የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ሕገወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ደንበኛ ለኪራይ ሰብሰቢ አሠራር የተጋለጠ የሕግ ማዕቀፍ ሆኗል፡፡

ከዚህ በከፋ ሁኔታም ባለሥልጣናት ከተወሰኑ ባለሀብቶች ጋር በጋራ ንግድ ውስጥ ስለሚገቡ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከመንግሥታዊ የንግድና ገበያ ጣልቃ ገብነት ገበያን ወደማዛቢያነት ሲቀየሩም ይስተዋላል፡፡ የተወሰኑ ድርጀቶችን ለመጥቀም ከላይ ታች የሚሉ እንዲሁም በሕዝብ ጥቅም ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ባለሥልጣናት ውለው ሲያድሩ የራሳቸውን ንግድ ሲያጧጥፉ እንደነበር የሚታወቀው ዘግይቶ ነው፡፡

የእሽሙር ማኅበር ዋሻነትን ለመድፈን መንግሥት የተለያዩ አሠራሮችን መከተል ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም ደግሞ የእሽሙር ማኅበር በመመሥረቻ ጽሑፍ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሚስጥራዊነቱን ማስጠበቅ ካስፈለገም እነዚህ መመሥረቻ ጽሑፎች ለሕዝብ ክፍት ሳይሆኑ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪ ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ ብቻ የሚታዩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በቅርብ ምንም ዓይነት ሀብት ያልነበራቸው ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ባለሥልጣን ሆነው ሲወርዱ ቱጃሮች ሲሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡

አንዳንድ ምንም ወረት የሌላቸው ሰዎችም በድንገት ሰማይ የነኩ ባለሀብት ሲሆኑም ታዝበናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከጀርባ ሰዎች ስላሉ ሊሆንም እንደሚችል ማጣራት ነው፡፡ እነኚህ ሰዎች እንዲህ በድንገት ባለሀብት የሚሆኑት ደግሞ በሞትና በሕይወት መካከል የሚኖሩ ምስኪን ለፍቶ አደሮች በሚከፍሉት ግብርም ነው፡፡

ሕዝቡም የቱ ሀብት የማን እንደሆነ ያው የመጠርጠር መብት ስላለው ጥርጣሬውንና ሐሜቱን ይቀጥላል፡፡ ችግሩ ያለውና ማጣፊያው የሚያጥረው ሐሜቱ እየበዛና እየቀጠለ፣ የሚታሙትም እየበዙና ዕርምጃ መውሰድ ሳይቻል ሲቀር የሚፈጠረው አገራዊ አደጋ ላይ ነው፡፡  “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ አገርም ጭምር ሊፈታ መቻሉም ላይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡