Skip to main content
x
ለሠርግ የሚከፈል ዋጋ

ለሠርግ የሚከፈል ዋጋ

በአንዴ ከስድስት ሰው በላይ መያዝ በማይችለው የእንፋሎት (ስቲም) መታጠቢያ ክፍል ውስጥ በከፊል የተሸፈኑ ሴቶች ተደርድረዋል፡፡ ከሁለቱ በስተቀር የተቀሩት እርስ በርስ አይተዋወቁም፡፡ ሲያወሩም ድምፃቸው ሌላውን እንዳይረብሽ ተጠንቅቀው ነው፡፡ እንፋሎቱን መቋቋም ያቃታቸው በየደቂቃው እየወጡ ይናፈሳሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል ሲቆዩ ማንም በማንም ጉዳይ ገብቶ ሐሳብ አልሰጠም፡፡

ሁለቱ ጓደኛሞች ያነሱት ነጥብ ግን ፀጥ ብሎ የቆየውን ክፍል በወግ እንዲሞላ አደረገ፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ፀበኛ ይመስል ተኮራርፈው የቆዩት ሴቶች ስለግል ጉዳያቸው እየተወራ ያለ ይመስል ጉዳዩን እየተቀባበሉ ያወሩበት ጀመረ፡፡ ወሬውን የጀመረችው ልጅ ከቀናት በኋላ ለአንድ ሠርገኛ ጓደኛዋ ሚዜ ለመሆን እየተዘገጃጀች ነበር፡፡ ስቲም መግባትም የዝግጅቱ አካል ነበር፡፡ በሚዜነት በመመረጧ ደስተኛ ብትሆንም ወጪው ከባድ መሆኑ አበሳጭቷታል፡፡

የሚዜ ልብስ እንዲሆን የተመረጠው ኪራዩ 2,000 ብር ነበር፡፡ ዋጋው መጋነኑን በብስጭት ስታወራ ሁሉም የገጠማቸውን ያወሯት ጀመሩ፡፡ ከዚያ በበለጠ ገንዘብ የሚከራዩ የሚዜ ልብሶች እንዳሉ፣ የሚያውቋቸው በተሻለ ዋጋ የሚያከራዩ መኖራቸውን ነገሯት፡፡ ዋጋው ግን አልሸሹም ዞር አሉ ዓይነት ነገር ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በተለያዩ ሰዓታት የሚለብሷቸው ሌሎች የእራትና የሐበሻ ልብሶች ወጪም ነበረባት፡፡ ለፀጉርና ለአጠቃላይ ሜካፕ ሥራ ሌላ ከ7,000 ብር በላይ ወጪ ይጠብቃታል፡፡ ‹‹ሐበሻ ልብሱን ሌላ ጊዜ እንዳልጠቀምበት እንኳን የተመረጠው ስፌት ድጋሚ የሚለበስ ዓይነት አይደለም፤›› አለች፡፡

‹‹ሌላው ቢቀር የሜካፑን ወጪ ለምን አትቀንሱም፡፡ ፀጉራችሁን በተለመደው ዋጋ ከ50 እስከ 70 ብር ከፍላችሁ ተሠሩ፡፡ ሜካፕም ቢሆን ለምን ቀላል አታደርጉትም፡፡  አለች በሚጠሩት ዋጋ የተደመመችው ወጣት፡፡ ፈገግ ብለው አዩዋትና ለምን እንደዛ እንደማይሆን ያብራሩላት ያዙ፡፡ ሜካፑን በራሳቸው መሥራት እንደማይከብድ ‹‹ዋናው ነገር እኮ የእንትና ሠርግ ይህንን ያህል አወጣ፣ ፀጉራቸውን የሠራው ደግሞ በከተማው አለ የሚባል ባለሙያ ነው ብሎ ማስወራቱ ስለሚፈለግ ነው፤›› በማለት አንደኛዋ ስትናገር ሁሉም በመስማማት አንገታቸውን ነቀነቁ፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ማኅበራዊ ክንውኖች መካከል ሠርግ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የሰው ልጆች ትልቁ የሕይወት አጋጣሚ እንደሆነም ይታሰባል፡፡ ሠርግና ሞት አንድ ነው የሚለው አባባልም ማኅበረሰቡ ለሠርግ የሚሰጠውን ቦታ ያሳያል፡፡ አንድ ሰው ለወግ ማዕረግ በቃ የሚባለውም ሠርጎ ሲያገባና ሲመረቅ ነው፡፡ በተለይ ለሴት ልጆች ሠርግ የተለየ ክብደት እንዳለው ይታሰባል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ትልቅ ዝግጅት የማይሰናዳ የለም፡፡ ልጆቼ ሲያገቡ እያሉ የደስታቸውን ቀን የሚያልሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ አስቀድመው የድግስ ዕቃ የሚገዙም ብዙ አሉ፡፡ ሳልሞት አግባ ብለው ልጆቻውን የሚወተውቱ ወላጆችም ያጋጥማሉ፡፡ ምርቃቱም ቢሆን ለሠርግህ/ሽ ያብቃን ነው፡፡ ለዚህ ቀን ገንዘብ የማያጠራቅም የለም፡፡ አቅማቸውን አገናዝበው ከመደገስ ይልቅ ድል ባለ ሠርግ ልጃቸውን ዳሩ መባልን የሚመርጡና የሚፈጠርባቸውን የኢኮኖሚ ቀውስ በፀጋ መቀበል የሚሻላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ለሠርግ የሚያወጡት ወጪ በሕይወታቸው ከሚያወጡት ሁሉ ከፍተኛው ነው፡፡ ሠርጉ ከተወደደ ታዲያ ይህንን ያህል አወጣሁ ብሎ ማስወራቱ ኩራታቸው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ለአልባሳት፣ ለሜካፕና ለሌሎች ጉዳዮች የሚወጣው ከምግብና መጠጡ ጋር ሲተያይ ብዙም የሚባል አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለሠርግ የሚወጣው ወጪ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሆኗል፡፡ ለሙሽሮችና ሚዜዎች አልባሳት የሚወጣው ወጪም ጣራ ነክቷል፡፡

ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ ከምግብና መጠጡ ውጪ ያሉ የአልባሳት፣ የሜካፕ፣ የፎቶና የመኪና ኪራይ መሆኑ እንዴት ነው ነገሩ ያሰኛል፡፡ ለአንድ ሠርግ የፎቶ ሥነ ሥርዓት እስከ 70 ሺሕ ብር ድረስ የሚያስከፍሉም አሉ፡፡ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ግን ከፍተኛ የሠርግ ወጪዎችን ማውጣት ተለምዷል፡፡

ይህንንም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቶ በነበረው ‹‹አዲስ ብራይዳል ሾው›› አውደ ርዕይ ላይ ማየት ችለናል፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጅ የሮምሀይ ትራቭል ኤንድ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሳምራዊት ታከለ እንደምትለው፣ አንድን ሠርግ ለመደገስ ስድስት ወራት ያህል ጊዜ ወስዶ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ ሠርጉን ከሚያቅዱ ድርጅቶች ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች በአንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በአንዳንድ የሠርግ ድግስ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ይወጣል፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው አውደ ርዕይ ላይም በሠርግ ዙሪያ የሚሠሩ ከ70 የሚበልጡ የስፓ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የሜካፕ ሥራ የሚሠሩ፣ አልባሳት የሚያከራዩና የሚሸጡ፣ መኪና የሚያከራዩ፣ የሠርግ ዕቅድ የሚያወጡ (ዌዲንግ ፕላነሮች)፣ ምግብ የሚያዘጋጁ ድርጅቶችና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

ፕሮግራሙ የተዘጋጀበት ሚሊኒየም አዳራሽ በሠርግ ግርግር ደምቆ ነበር የሰነበተው፡፡ ጥንድ ጥንድ ሆነው ወደ አዳራሹ የሚገቡ የሚወጡ ብዙ ናቸው፡፡ አዳራሹ መግቢያ ላይ በአበቦች ያጌጡ ረዣዥም ሽንጥ ያላቸው መልከኛ መኪኖች ቆመዋል፡፡ ከበር የሚቀበልዎት የሠርግ ዘፈኖች ጨፍሩ ጨፍሩ ያሰኛል፡፡ በአገር ባህል ልብስ የደመቁ እንስቶችን ሲያዩ ደግሞ ትክክለኛ የሠርግ ፕሮግራም ላይ የተገኙ ያህል ይሰማዎታል፡፡

በሦስት መደዳ የተደረደሩት የቬሎና የተለያዩ የሠርግ አልባሳት መሸጫዎች፣ የዲኮር ድርጅቶች፣ የስፓ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ የሜካፕ ባለሙያዎች፣ የጫጉላ ፕሮግራም አዘጋጆችና ሌሎችም እዩኝ እዩኝ ይላሉ፡፡ ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁትን ዋጋ እስኪሰሙ ድረስ ባለው ደስ የሚል ድባብ ይደሰታሉ፣ የሠርግን ግርግር የሚጠሉን እንኳን ሐሳባቸውን መልሰው እንዲያጤኑ የሚያደርግ ነው፡፡

‹‹የአዳራሽ ኪራይ በራሱ ትልቅ ወጪ ነው፡፡ እስከ መልስ ድረስ በሚኖረው ዝግጅት ብዙ ወጪዎች ይወጣሉ፡፡ አጠቃላይ ፕሮግራሙ አንድ ሚሊዮን ብር ቢፈጅ የበጀቱን 20 በመቶ እናስከፍላለን፤›› በማለት ወይዘሮ ሳምራዊት ወጪው የሚጀምረው ሠርጉ መታቀድ ሲጀምር እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ከዌዲንግ ፕላነሮች ውጪ ያሉ አካላትም የሚጠይቁት ዋጋም ቀላል አይደለም፡፡ ሆኖም ገበያቸው የደራ ነው፡፡ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ሁሉም ደንበኛን በማስተናገድ ሥራ ተወጥረዋል፡፡ የሜካፕ ባለሙያዋ አትክልት ለማ ከእነዚህ መካከል ነች፡፡ በዙሪያዋ የተለያየ ብራንድ ያላቸው የሜካፕ ዓይነቶች ተደርድረዋል፡፡

በሙያው በቂ ልምድ እንዳላት ፊቷን ዓይቶ መገመት አይከብድም፡፡ ደብዘዝ ያለ ሮዝ ቀለም ያለው ደረቅ ያለ ሊፒስቲክ ተቀብታለች፡፡ ዓይኗም በኩልና በሻዶ አሳምራዋለች፡፡ ፊቷን የተቀባችው ፋውንዴሽንና ፓውደርም በስሱና በሚያምር መልኩ ነው፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ በሚካሄደው የፋሽን ሾው ትርኢት የምትሳተፍን አንድ ሞዴል በመኳኳል ላይ ነበረች፡፡ የአልባሶ ሹሩባ የተሠራችውን ሞዴል ከፀጉሯና ከፊቷ ጋር የሚሄድ ሜካፕ እየሠራችላት ነበር፡፡ ከጎኗም  ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሌሎች ሞዴሎች ነበሩ፡፡

‹‹የሜካፕ ሥራ ደስ ይለኛል፤›› የምትለው አትክልት፣ ተወልዳ ያደገችው አቡዳቢ ነው፡፡ የመጀመርያ የሜካፕ ትምህርትም የተማረችው በአቡዳቢ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮችም ተጨማሪ የሜካፕ ትምህርት መከታተሏን ትናገራለች፡፡ እዚህ ከመጣች አምስት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ከሜካፕ ሥራ ጎን ለጎን የስፓ አገልግሎትም ትሰጣለች፡፡ በተለያዩ በሠርግ፣ የፋሽን ሾው ፕሮግራሞች፣ በፊልም ሥራዎች በሙያዋ ትሳተፋለች፡፡ ትልቁ ገቢዋ ግን በሠርግ የምታገኘው እንደሆነ ትናገራለች፡፡

‹‹ለሙሽሮች የተዘጋጁ የተለያዩ ፓኬጆች አሉ፡፡ ፀጉርና ሜካፕ ሲሠሩ፣ ስፓ ሲጨምሩና ጥንድ ሆነው ለሚጠቀሙ ክፍያው የተለያየ ነው፤›› ትላለች፡፡ አገልግሎቱን ከ6,000 ብር ጀምሮ የምታቀርብ ሲሆን፣ የሚጠቀሙት ፓኬጅ በጨመረ ቁጥር ክፍያውም በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ ለአንድ ሙሽራ ፀጉርና ሜካፕ 6000 ብር፣ ስፓ ከጨመሩ 8,000 ብር ታስከፍላለች፡፡ ‹‹ዋጋው የሚጀምረው ከ6,000 ብር ነው፡፡ ነገር ግን ትልቅ የሚባል ዋጋ የለም፡፡ ተጨማሪ አገልግሎቶችን በተጠቀሙ ቁጥር ክፍያውም በዚያው መጠን ይጨምራል›› ብላለች፡፡

ለአንድ ሰው ብቻ እስከ 12000 ብር የሚያስከፍሉ ያጋጥማሉ፡፡ አልተወደደም ለሚለው ጥያቄ ‹‹ለሙያው ክብር ስለምንሰጥ፤›› ነው ይላሉ፡፡ ለሠርግ ከሆነ ደግሞ የተለየ ታክስ የሚያስከፍላቸው አካል ያለ ይመስል ይህም ሲያንስ ነው የሚል መልዕክት አዘል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡

ለሠርግ የሚሠሩ ሜካፖች ከወትሮው በተለየ እንከን የለሽ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና የዚህን ያህል የተጋነነ ወጪ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑ ያጠያይቃል፡፡ ከተጠየቁት ክፍያ ምክንያታዊነት ይልቅ የመክፈል አቅማቸውን ብቻ ከግምት በማስገባት የተጠየቁትን የሚከፍሉ፣ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው የማያሳስባቸው ብዙ መኖራቸውን ከንግግሯ መረዳት ይቻላል፡፡

እንኳንስ ያለን ነገር ተጠቅሞ ማቆነጃጀት የጤና ችግር ያጋጠመውን ፊት አልያም አካል መድኃኒት ቀምመው የሚያክሙ ይህንን ያህል የተጋነነ ዋጋ የመጠየቅ ድፍረቱ አላቸው? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡

በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ሌላውና ዋነኛው የሙሽሮች ጭንቀት የቬሎ ጉዳይ ነው፡፡ በከተማው ጥቂት የማይባሉ ቬሎ የሚያከራዩ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ የሚያከራዩበት ዋጋም እንደ ቬሎዎቹ ደረጃ ይለያያል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ቬሎ ከ5,000 እስከ 10,000 ብር ድረስ ይከራያል፡፡

ዋጋው እጅግ የተጋነነ ስለመሆኑ የተለያዩ ቬሎዎች ኦን ላይን የሚሸጡበትን ዋጋ በማየት ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህን ማገናዘብ መቻል ከዘረፋ ላልተናነሰው ብዝበዛ እንዳይጋለጡ ያደርጋል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ ሁለት ዶላር የማይሞላ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባላት አገር ለአንድ ቀሚስ ኪራይ ይህንን ያህል ገንዘብ መክፈሉ እንዴት? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

የሀገር ልብስ በተለያዩ ዝግጅቶች በተለይ በሠርግ ፕሮግራም በሙሽሮችና በሚዜዎች እየተለመደ መምጣቱ ይህንን የተጋነነ የቬሎ ኪራይ ሊያስቀር እንደሚችል የሚገምቱ ይኖራሉ፡፡ ዲዛይነር መሠረት ተፈራ የአሌፍ ዲዛይን ባለቤት ነች፡፡ ለሠርግና በተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ አልባሳትን ትሠራለች፡፡

ጥበቡ፣ የሚሠራበት ግብዓት፣ የሚፈጀው ጊዜ፣ ድካሙ ዋጋውን እንደሚወስነው ትናገራለች፡፡ ጥበቡ ብቻ ከ600 እስከ 8,000 ብር ድረስ እንደሚሸጥም ታክላለች፡፡ እነዚህ ነገሮች የአልባሳቱን ዋጋ የሚወስኑት ሲሆን አንድ የሠርግ ልብስ እስከ 12,000 ብር እንደምትሸጥ ትናገራለች፡፡ ይህ የተሻለ የሚባለው ዋጋ እንደሆነ ‹‹ገበያ ላይ ከ30,000 እስከ 40,000 ብር ድረስ እንደሚሸጥ እናውቃለን፤›› በማለት የገበያውን ሁኔታ ትናገራለች፡፡ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ይህ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ድል ያለ ሠርግ የሚደገስበት ገንዘብ መሆኑ ነው፡፡

ለአዳራሽና ለዲኮር የሚጠየቀው ዋጋም የተጋነነ ነው፡፡ ለዲኮር እስከ 200,000 ብር ድረስ የሚያስከፍሉ ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው የመኪና ኪራይ ነው፡፡ ቄንጠኛ መኪኖችን አሠልፎ ሙሽሪትን ከቤተሰቦቿ ቤት መውሰድ የድግሱ ዋናው አካል ነው፡፡ ለዚህ ፕሮግራም የሚሆኑት አብዛኛዎቹ መኪኖች ከተለያዩ ድርጅቶች በኪራይ የሚገኙ ናቸው፡፡

በከተማ ውስጥ የሚገኝ የሠርግ መኪኖችን በማከራየት የሚታወቅ አንድ ድርጅት ነው፡፡ ቮልቮ፣ መርሰዲስና ቢኤምደብሊው የተባሉ መኪኖች አሉት፡፡ አራት ሰው የመያዝ አቅም ያለውን ቮልቮ መኪና ለአንድ ቀን በ27,000 ብር የሚያከራይ ሲሆን በአንዴ ከአምስት እስከ ሰባት መኪኖችን የሚከራዩ ደንበኞች አሉት፡፡ የድርጅቱ የሴልስ ኃላፊ እንደሚሉት፣ መኪኖቹ ሥራ ፈተው አይውሉም፡፡

ቅጥ ያጣው የሠርግ ወጪ ብዙዎች ያስጨንቃል፡፡ ለፍተው ለዓመታት ያጠራቀሙትን ሜዳ ላይ የመበተን ያህል የሚሰማቸውም አሉ፡፡ ያላቸው ባይበቃቸው ለብድር የሚዳረጉ አሉ፡፡ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ግን ጥንዶቹ አብረው መኖር ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ ትዳርን ሀ… ብለው ከመጀመራቸው ዕዳቸውን በመክፈል ይጠመዳሉ፡፡ ለሠርግ ያወጡትን ወጪ ለሌላ ቁም ነገር ብናውለው ብለው የሚመኙም አይጠፉም፡፡ ትዳር ከተጀመረ በኋለ ለሠርግ ወጪ የተበደሩትን በመክፈል ኑሮአቸውን ከጅምሩ የማያመሳቅሉ ለፍች የተዳረጉም አሉ፡፡ ለፎቶና ቪዲዮ ቀብድ ከፍለው፣ ያለቀለትን ሥራ ከፍሎ ለመውሰድ በመቸገራቸውም ለወራት ፎቶና ቪዲዮዋቸውን ከሠራላቸው ድርጅቶች የማይወስዱም ቀላል አይደሉም፡፡ ሠርግ ከዕቅዱ አስከ ፍፃሜው ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፣ ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ለማስደሰት የሚከፍሉት ዋጋም ነው፡፡