Skip to main content
x
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን መፍረስ ምክንያቱ ውጤት? ወይስ የአደረጃጀት ክፍተት?

ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን መፍረስ ምክንያቱ ውጤት? ወይስ የአደረጃጀት ክፍተት?

  • ባንኩ ከአትሌቲክስ ቡድኑ መሠረት ደፋርን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ሯጮችንም ቀንሷል

መሰንበቻውን በስፖርቱ ማኅበረሰብ ዘንድ ከተደመጡ አስደንጋጭም አሳዛኝም ዜናዎች መካከል ከሦስት አሠርታት በላይ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ሲወጣ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች የእግር ኳስ ዋናው ቡድን፣ ተስፋውና ታዳጊዎቹ ጭምር ማፍረሱ ነው፡፡ የድርጅቱ ኃላፊዎች ቡድኑን ያፈረሱት ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ቢገልጹም፣ እንደ አስተያየት ሰጪዎች መጠየቅ ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ ግን የቡድኑም ሆነ የድርጅቱ አመራሮች ውጤት እንዲመጣና ጠንካራ ቡድን ለመመሥረት የሚያስፈልጉ አደረጃጀቶችን ከመገንባትም ሆነ ግልጸኝነትን ከማስፈን አንፃር ያደረጉት አስተዋጽኦ ነው፡፡

አንድ ቡድን ሲቋቋም ውጤት ለማስመዝገብ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ተቋሙ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ያደረገው የአደረጃጀት ጥረትና እንቅስቃሴ እንዲሁም ከልብ የመነጨ ቁርጠኝነትና ተጠያቂነት ባልታወቁበት ሁኔታ ‹‹ውጤት አልመጣም›› ተብሎ ቡድን መበተን መፍትሔ አድርጎ መውሰድ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነውም ይላሉ፡፡

ከውጤት ጋር ተያይዞ ዛሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ከተስፋውና ታዳጊዎቹ ጭምር  ማፍረሱ ክለቡ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ እግር ኳስን አጠቃላይ ገጽታ አመልካች እንደሆነ ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡ ምክንያቱም ‹‹ውጤት›› በሚል ሽፋን ዛሬ በንግድ ባንክ የተጀመረው ቡድን የማፍረስ ዕርምጃ መሠረታዊ አሠራሩና አደረጃጀቱ በቅጡ እስካልተፈተሸና እስካልተቃኘ ድረስ ነገ ወደ ሌሎች ክለቦች አለመዛመቱ ዋስትናው ምንድነው? የሚሉ ወገኖች እንዲበረክቱ አድርጓል፡፡ ስለሆነም መፍትሔው ቡድን ማፍረስ ሳይሆን በአጠቃላይ በስፖርቱ ማኅበረሰብ ዘንድ በተደጋጋሚ ሲነገር የሚደመጠውን የአደረጃጀቶች፣ የግልጸኝነትና የተጠያቂነትን መንፈስ ማስፈን የሚለው ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ጭምር ይናገራሉ፡፡

በ50ዎቹ ዘመን ፋይናንስና መድን ተብሎ የተመሠረተው ባንክ

አትሌቲክሱን ጨምሮ በ1975 ዓ.ም. ‹‹ፋይናንስና መድን›› በሚል መጠሪያ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር፣ በስፖርቱ ታሪክ ውስጥ ከሦስት አሠርታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ከሰሞኑ የህልውናው ጉዳይ ማክተሙ የተነገረለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በተቋቋመ በዓመቱ ከሦስተኛ ዲቪዢዮን ወደ ሁለተኛ ዲቪዢዮን ማደጉን ተከትሎ መጠሪያው ፋይናንስና መድን መባሉ ቀርቶ የባንክ እግር ኳስ ቡድን ተብሎ መዝለቁ የስፖርት ማኅበሩ ቀደምት ሙያተኞች ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክና ቤቶችና ቁጠባ (ቢዝነስ ባንክ) በወቅቱ ቡድኑን በባለቤትነት ሲያስተዳድሩት ቆይተው፣ በ1996 ዓ.ም. የግል ባንኮች ማለትም አዋሽ ባንክ፣ ወጋገን ባንክና ኅብረት ባንክ በባለቤትነት እንዲካተቱ ተደርጎ የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማኅበር በሚል መጠሪያ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የስፖርት ማኅበሩ የበላይ ጠባቂ በነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ መመርያ በ2003 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲተላለፍ ተደርጎ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስና በጠረጴዛ ቴኒስ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡

ከሰሞኑ የመፍረሱ ዜና ይፋ የሆነው ዋናው የእግር ኳስ ቡድኑ፣ በ1996 እና 2000 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ክለቦች የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ሆኖ ለአፍሪካ የክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አገሪቱን በመወከል ተወዳድሯል፡፡ በተለይም የአትሌቲክስ ቡድኑ አገሪቱ ካፈራቻቸው ታላላቅ አትሌቶች ውስጥ ከእግር ኳስ ቡድኑ መፍረስ ቀደም ብሎ ከአትሌቲክሱ ቡድን መሰናበታቸው ከተነገረላቸው መካከል መሠረት ደፋር፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ተሰማ አብሽሮ፣ አየለ አብሽሮ፣ ደጀን ገብረመስቀል፣ ስንታየሁ እጅጉ እንዲሁም በመዶሻ ውርወራ የምትታወቀው መርስኢት ገብረእግዚአብሔርና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አቶ ካሱ ዓለማየሁ የወንዶቹን እግር ኳስ ቡድን ጨምሮ አትሌቶቹ እንዲቀነሱ የተደረገበት መንገድ ሙያዊ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንደማይሆን ይናገራሉ፡፡ ለአትሌቶቹ ስንብት መንስኤው ‹‹ለምን ትናገሩናላችሁ›› በሚል ሊሆን እንደሚችል ከራሳቸው  ተሞክሮ በመነሳት ይናገራሉ፡፡

የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሰይፈ ቦጋለ በበኩላቸው፣ ባንኩ ማኅበራዊ ግዴታውን ከመወጣት አኳያ ከሚያስቀምጠው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ስፖርቱ መሆኑን በመግለጽ፣ በተለይ የወንዶቹ እግር ኳስ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀመጠለትን ግብ ያሟላበት ጊዜ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ውሳኔውም ከዚሁ በመነሳት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ባንኩ ለዚህ ውሳኔ ከመብቃቱ አስቀድሞ ጊዜ ወስዶ አጠቃላይ የሆነ ግምገማ ማድረጉን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ‹‹ተቋሙ ለእግር ኳሱም ሆነ ለሌሎች ስፖርቶች ከፍተኛውን መዋዕለ ንዋይ ሲመድብ ተመጣጣኝ የሆነ ውጤት ማግኘት እንዳለበት ያምናል፡፡ ባለው ሁኔታ ግን በተለይ የወንዶቹ ቡድን ውጤት ለባንኩ የገጽታ ግንባታ ጭምር በማይመጥን መልኩ ወደ ከፍተኛው (ሱፐር ሊግ) ወርዷል፡፡ በዚህ መነሻነትም የስፖርት ማኅበሩ ከሚያስተዳድራቸው የወንዶቹ ዋናውን ቡድን ጨምሮ ተስፋውንና በሥሩ የሚገኘውን የ‹‹ቢ››ው የእግር ኳስ ቡድን ሁሉም እንዲፈርሱ ተደርጓል፤›› በማለት ምክንያቱን ተናግረዋል፡፡ ተጠያቂነቱንም በዋናነት ተጨዋቾች እንደሚወስዱ አቶ ሰይፈ ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡

በውጤት ሽፋን ቡድን በማፍረስ ከተጠያቂነት መሸሽ እስከመቼ?

በአገሪቱ እግር ኳስን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርቶች ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ ቢገኙም፣ ህልውናቸው የሚወሰነው ግን በየተቋማቱ መሪዎች መልካም ፈቃደኝነት በመሆኑ የመፍረስ ዕጣ ፈንታቸው ሰፊ መሆኑን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ላይ የተወሰደውን ውሳኔ በመመልከት መናገር ይቻላል፡፡

ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን መፍረስ ‹‹ውጤት›› በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ በቅድሚያ ግን ለውጤቱ መጥፋት እንደ ምክንያት ቀርቦ መታየት የነበረበት የቡድኑ አደረጃጀት ሆኖ ሳለ፣ ከዚህም  በላይ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሁም ሙያዊ ብቃት ከወረቀት ያለፈ ትርጉም ሳይኖራቸው፣ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወንዶች እግር ኳስ ቡድኑ ላይ የወሰደው የማፍረስ ውሳኔ በሌሎች ክለቦችም ሲፈጸም የቆየ አሠራር እንደሆነም የሚናገሩ አሉ፡፡ የቅርቦቹ ዳሸን ቢራና ሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ቡድኖች ለዚህ ትልቅ ማሳያ ይሆናሉ፡፡

የአገሪቱ ቡድኖች በአንድም ሆነ በሌላ በጀታቸው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ከመንግሥት ቋት መሆኑ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኖቹ ለምንና እንዴት እንደሚቋቋሙ እንዲሁም ያላቸው ሕጋዊ ሰውነት በውል ስለማይታወቅ ህልውናቸው የሚወሰነው በሚሰጡት የማኅበረሰብ አገልግሎት ሳይሆን፣ በሚያስተዳድሯቸው የተቋማት መሪዎች መልካም ፈቃደኝነት ብቻ ለመሆኑ ከባንክ ስፖርት ማኅበር ውሳኔ በመነሳት መናገር እንደሚቻል ይታመናል፡፡

ለዚህ በመነሻነት ባለፈው ዓመት ከፕሪሚየር ሊግ ወደ ከፍተኛው ሊግ መውረዳቸው በተረጋገጠ ማግሥት እንዲፈርሱ የተደረጉት ዳሸን ቢራና ሙገር ሲሚንቶ የእግር ኳስ ቡድኖችን ተሞክሮን በመውሰድ የኢትዮጵያ ንግር ባንክ ውሳኔ በተለይም በአሁኑ ወቅት በመቶ ሚሊዮኖች በጀት በመንቀሳቀስ ላይ ለሚገኙት ሌሎች ክለቦች የሚመለከተው አካል ከፋይናንስ ሥርዓታቸው ጀምሮ እስከ መዋቅራዊ አደረጃጀታቸው እንዲሁም ከሚወጣባቸው በጀት አኳያ እየሰጡ ያለውን ማኅበራዊ ግልጋሎት ጭምር እንዲጠይቅ፣ እንዲፈትሽና እንዲመረምር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንለት ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በባለቤትነት ሲያስተዳድረው የቆየውና መፍረሱን ይፋ ያደረገው የእግር ኳስ ቡድን፣ ለ2010 የውድድር ዓመት 85 ሚሊዮን ብር በጀት ይዞ እንደነበር ከስፖርት ማኅበሩ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የስፖርት ማኅበሩ ማኔጅመንትም ቡድኑን እንዳፈረሰ ያረጋገጠበትን መግለጫ እስከሰጠበት ድረስ የእግር ኳስ ቡድኑን ወቅታዊ ብቃትና ውጤቱን ጭምር የሚያመላክት ቁጥጥርና ግምገማን መነሻ ያደረገ መግለጫ ሰጥቶ አያውቅም፡፡

እግር ኳስ ክለቡ ከዋናው ቡድን ሥር ተስፋውን ቡድን ጨምሮ የ‹‹ቢ›› ቡድን እንደነበረው ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ ከተስፋውም ይሁን ከ‹‹ቢ››ው ቡድን ምን ያህል ተተኪዎች ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ እንደቻለ እንኳ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ሳይሰጥ፣ ቡድኑን ያፈረሰበትን ምክንያት ይፋ ባደረገበት መድረክ የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሰይፉ ቦጋለ ቡድኑ ታዳጊ ወጣቶችን እንደማያሳድግ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ይህንኑ ክፍተት ተከታትሎና ተቆጣጥሮ ተፈጻሚ የማድረግ ኃላፊነት የማን እንደሆነ ግን በኃላፊው የተብራራ ነገር አልነበረም፡፡ ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው፣ ‹‹በዋናነት ተጨዋቾቹ ናቸው›› በማለት ነበር መልስ የሰጡት፡፡

የስፖርት ማኅበሩን አሠራር አስመልክቶ የሚናገሩ ነገር ግን ለደኅንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ የባንኩ ሙያተኞች በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ለገጽታውና ለውጤቱ የሚመጥን ቡድን ለመገንባት የስፖርት ማኅበሩን መዋቅራዊ ይዘት ፈትሾ ማስተካከያ ማበጀት ሲገባው፣ በደፈናው ቡድን ማፍረስን በመፍትሔነት መውሰዱ የሚያሳምን እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ውሳኔው ተጠያቂነትን ለመሸፋፈን ሆን ተብሎ የታቀደ ስለመሆኑም ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ለቡድኑ ውጤት ማጣት ድርጅቱ ያስቀመጣቸው አመራሮችና ሙያተኞች እያሉ ተጨዋቾችን ተጠያቂ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነ በተለይ ‹‹ይመለከተኛል›› ለሚለው አካል ሊጠፋው እንደማይችል ነው ያስረዱት፡፡  

በዋናው እግር ኳስ ቡድን ሥር ተሰፋውና የ‹‹ቢ››ው ቡድኖች ቢኖሩም፣ ነገር ግን ከእነዚህ ቡድኖች ለዋናው ቡድን የሚመጥኑ ተጨዋቾችን በመመልመል ማሳደግ የሚችሉ ሙያተኞች ተገቢው መስፈርት ወጥቶ የተቀመጡ ባለመሆኑ፣ ብዙዎቹ የተስፋውም ሆነ የ‹‹ቢ››ው ቡድን  ተጨዋቾች ተገቢውን ግልጋሎት ሳይሰጡ ዕድሜያቸው የሚያልፍ ስፍር ቁጥር እንደሌለቸው እነዚሁ የስፖርት ማኅበሩ ተቆርቋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቅሱት ሙያተኞቹ፣ ከንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ አማካይነት ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት የመታየት ዕድል ያገኘው ቢኒያም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮፌሽናል ዕድል አግኝቶ ወደ አውሮፓ አምርቶ በአልባኒያ እየተጫወተ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡

ተጨዋቹ ለብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድል ከገጠመው በኋላ ክለቡ ወደ ዋናው ቡድን አሳድጎት እንደነበርና ለክለቡ በቋሚ ተጨዋችነት በማገልገል ላይ በነበረበት ወቅትም ወርኃዊ ክፍያው ዘጠኝ ሺሕ ብር እንደነበር የሚናገሩት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ክለቡ በወር እስከ ዘጠና ሺሕ ብር የሚከፍላቸው የአፍሪካ አገሮች ተጨዋቾች ግን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበረበትን አጋጣሚም ይጠቅሳሉ፡፡ ማኔጅመንቱ ለእግር ኳስ ቡድኑ መፍረስ ውጤትን ምክንያት ሲያደርግ እንዲሁም ባንኩ ለተጨዋቾች ከሚያወጣው በጀት አኳያ ‹‹ውጤቱ ተመጣጣኝ አይደለም›› ሲል ሜዳ ላይ በተለይም ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ በአደባባይ ሲከወኑ የቆዩ አሠራሮችን እንዴት መመልከት ተሳነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ከዚህም በላይ የስፖርት ማኅበሩን የሚያስተዳድሩት አመራሮችስ ሙያዊ ዕውቀታቸው ባንኩ በአሁኑ ወቅት ምክንያት ለሚያደርገው ‹‹ውጤት›› የሚመጥኑ መሆን አለመሆናቸውን የተመለከተበት ሙያዊ ዕይታስ እንዴት ነበር? ለውጤቱ መበላሸት እንዴትስ ተደርጎ ነው ተጨዋቾች ተጠያቂ የሚሆኑት? ሲሉ የባንኩን ማኔጅመንትና የስፖርቱን አመራር የሚጠይቁት እነዚሁ የቡድኑ ተቆርቋሪዎች፣ አሁንም ድርጅቱ ወደ ራሱ ተመልክቶ አደረጃጀቱን መፈተሽ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት በተለይ በስፖርቱ የሚስተዋለው ተጠያቂነት የሌለው የደመ ነፍስ አሠራር በባንክ ብቻ እንዳልሆነ፣ በሌሎችም ክለቦችና በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጭምር ተመሳሳይ አሠራሮችና አደረጃጀቶች  መኖራቸውን ነው ሙያተኞቹ የሚያስረዱት፡፡ እነዚህና ሌሎችም በስፖርቱ ተንሰራፍተው የሚገኙ ዘልማዳዊ አሠራሮች በሰፈነበት ሁኔታ ስለ እግር ኳስ ውጤትና ዕድገት ማውራት ቀርቶ ማሰብ እንማይቻልም ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ንግድ ባንክ ሙሉ የኦሊምፒክ ስታንዳርዱን የጠበቀ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 52 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት በሲኤምሲ አካባቢ ተረክቦ ግንባታ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ አገልግሎት ላይ ለማዋልም 770 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ድርጅቱ ያስታወቀው ቀደም ብሎ ነበር፡፡

የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ይህንኑ ከእግር ኳስ ቡድን መፍረስ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ የመሠረተ ልማት ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው ያስረዱት፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስታዲየም ማስገንቢያ ከተረከበው 52 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ አምስት ሺሕ ካሬ ሜትሩን የባንኩን ዋና መሥሪያ ቤት ለሚገነባው የቻይናው ኩባንያ ለግምጃ ቤትነት እንዲጠቀምበት በነፃ የሰጠ ስለመሆኑም የስፖርት ማኅበሩ ሙያተኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡