አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መንግሥት በጀት እንዲጨምር ሚኒስትሩ ጠየቁ

  • የሐሰት ሪፖርቶችን ከተቋማቸው እንደሚያጠፉ አስታውቀዋል

መንግሥት ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዘርፍ እየመደበ ያለው በጀት እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ፣ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ በጀት እንዲመደብ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ጠየቁ፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፓርላማ ያቀረቡት ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ተገቢውን በጀት እንዲመድብ ፓርላማውም ጫና ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ሕዝብ በገጠር በጨለማ ውስጥ እየኖረ መንግሥት በሚመድበው አንድ ቢሊዮን ብር የትም ርቀት መሄድ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽንን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ እንደሚንቀሳቀሱም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ በጀት ዓመት እንዲከናወኑ ዕቅድ የተያዘላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶች በዕቅዱ መሠረት ማከናወን እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ተግባር ለዚህ ዓመት የተበጀተው አንድ ቢሊዮን ብር የተለቀቀው ባለፈው ሳምንት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚቻል ለመንግሥት ማሳወቃቸውንና ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ እስከ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡ ሚኒስትሩ የበጀት እጥረት ችግርን ያነሱት በኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በውኃ ኢንቨስትመንት ላይ ነው፡፡ መንግሥት እየመደበ ያለው በጀት በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

በአፈጻጸም ወቅት ከገጠሙዋቸው ችግሮች መካከል በሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች የሚዘጋጁ ሪፖርቶች የሐሰት መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ትክክለኛ የክትትልና ግምገማ፣ እንዲሁም የመረጃ አደረጃጀት ለተቋማዊ ውጤታማነት ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ዘመናዊ የመረጃና ትንተና ሥርዓት በወሳኝ ሥራዎቻችን ላይ በመዘርጋት የሐሰት ሪፖርቶችን በማስቀረት ጥራት ባላቸው የፕላን ፕሮግራሞች ክትትል እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡