Skip to main content
x

ለከተማ ፅዳት ከሕግ በላይ ሕግ አክባሪነት!


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ የሚጥሱ አካላትን ለመቆጣጠርና ጥሰው ሲገኙም ዕርምጃ ለመውሰድ በማለት ደንብ ቁጥር 54/2005 የሚባል ሕግ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ደንቡ በድንጋጌው ካካተታቸው ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳትና ውበትን ለማስጠበቅ የሰፈሩት አንቀጾች ይገኝበታል፡፡

ደንቡ በ2005 ዓ.ም. ይውጣ እንጂ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ አለመዋሉን  ለማረጋገጥ ብዙ መድከም አያሻም፡፡ ምክንያቱም ደንቡ በትክክል ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ የአዲስ አበባችን የፅዳት ደረጃ በተሻሻለ ነበር፡፡ የከተማው ቆሻሻ አላፊ አግዳሚውን መላወሻ በማሳጣት በየአደባባዩ አፍጥጦ የሚታየው ይኸው ደንብ የሚተገብረው በማጣቱ ነው፡፡

ደረቅ ቆሻሻ በየቦታው በዘፈቀደ ይወረወራል፡፡ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውጪ በየቦታው ይጣላል፡፡ የሞቱ እንስሳት መንገድ ላይ ተጥለው አካባቢውን በመጥፎ ሽታ እስኪበክሉ ድረስ የሚያነሳቸው አካል አለሁ አይልም፡፡ ባለቤቶች ያላቸውም ሆኑ የመንገድ ውሾችና ድመቶች፣ አልፎ አልፎም አህና ሌሎችም እንስሳት በየመንገዱ  በመኪና ሲፈጠጡም ሆነ በመንገድ ዳር ተጥለው አገር ሲያውኩ ዞር ብሎ የሚያይ የለም፡፡ የወጣው ሕግ ግን እንዲህ የሚያደርጉ ይቀጣሉ ይላል፡፡ የቅጣቱን መጠንም አስቀምጧል፡፡ የምንኖርበትን ከተማ ከቆሻሻ የፀዳ ለማድረግ የሕግ ማስከበር ብቻውን ሚና ይኖረዋል ባይባልም፣ ፈር የለቀቁ ጉዳዮችን፣ እምቢተኛ ነዋሪዎችን ለመቆጣጠር ግን ሕግ መኖሩ ተገቢ ነው፡፡ በአግባቡ ቆሻሻን ያላስወገደ ግለሰብም ሆነ ተቋም ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕግ የተቀረፀውም ለዚህ ነው፡፡

የደንብ ጥሰትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ዕርምጃ ለመውሰድ የወጣው ደንብ ቁጥር 54/2005 ላይ ደረቅ ቆሻሻ ነው አወጋገድን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ ደረቅ ቆሻሻን ከመኖሪያ ቤት አውጥቶ ባለሌነት የጣለ 500 ብር ይቀጣል ይላል፡፡ ከኢንዱስትሪ የሚመነጭ ቆሻሻ ከሆነ ደግሞ የሰባት ሺሕ ብር ቅጣት ያስከትላል፡፡ ከጤና ተቋማት  የተጣለ ከሆነም የጤና ተቋሙ የ5,000 ብር ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡

ሰሞኑን የተወሰኑ ክፍለ ከተሞች በ2005 ዓ.ም. የወጣውን ደንብ በማሳተም ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው ሲያሰራጩ መታየታቸው መልካም ተግባር ቢሆንም፣ እስከዛሬ የት ነበሩ? ማሰኘቱ ግን አይቀርም፡፡ ሕጉ መኖሩ ታውቆ ከዘገየም ቢሆን ለማስከበር የታየው መነሳሳት መልካም ቢሆንም፣ ሕጉን ለማስፈጸም የሚረዱ ግብዓቶች ካልተሟሉ ግን ሕጉን ሥራ ላይ በማዋሉ ሒደት ላይ ሥጋት ያጭራል፡፡ ለምሳሌ ከገንዳ ውጭ በየጥጋጥጉ ቆሻሻ መጣል የሚያስቀጣ ከሆነ፣ የቆሻሻ ገንዳውን በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የቆሻሻው ገንዳው ሲሞላም ተከታትሎ ማንሳት ይገባል፡፡ አለያ ሞልቶ በሚፈሰው ገንዳ መጣያ ያጣ ሰው ቆሻሻውን ገንዳ ላይ አልጣለም ተብሎ ቢቀጣ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ደንቡን ለማስፈጸም ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይገባል፡፡ የቆሻሻ ገንዳ በሌለበት፣ የሞላውም ባልተነሳበት አግባብ ደንብ ማስከበር ስለማይቻል እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ተግባራት ሳይኖሩ በስመ ደንብ ማስከበር ዕርምጃ ለመውሰድ መነሳት በራሱ ደንብ መጣስ ይሆናል፡፡  

ዋናው ቁም ነገር ቅጣት አይደለም፡፡ ደንብ የተላለፈ መቀጣቱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ደንብ የሚተገበረው በሞላ ጎደለ አካሄድ ከሆነ ከእነ አካቴው ባይጀመር ይሻላል፡፡ ‹‹ትሻል ትቼ ትብስን አገባሁ፤›› እንዳሉት ሰውዬ፣ ዳር የማይደርስ ሕግ እያወጡ ሳይፈጽሙ መቅረት ይባሱን የሕዝብን አመኔታ ያሳጣልና ነው፡፡

የመንገድ ደኅንነትን ወይም የመንገድ ፅዳትን በተለከተ ከግንባታ ወይም ከፍርስራሽ የሚመነጭ አፈር ወይም ቆሻሻ ባልተፈቀደ ቦታ መድፋትም 500 ብር እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ የግንባታ ግብዓት የሆኑ ሲሚንቶ፣ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ አፈርና የመሳሰሉትን መንገድ ዳር ማራገፍም 1,000 ብር ያስቀጣል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንፃር አካባቢያችንን ስንቃኝ የምንታዘበው ደንቡ ሥራ ላይ እንዳልዋለ ነው፡፡

ባሻቸው ሰዓት አፈርና ፍርስራሽ ጭነው የሚከንፉ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሚያንጠባጥቡት አፈርና ጭቃ የተነሳ የከተማው አስፓልት መንገዶችን እየተጉረበጠበጡ፣ እየተቦረበሩ የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማወክ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሕግ ባለበት አገር ከልካይ አጥተዋል፡፡

የመንገድ ነገር ከተነሳ አይቀር በዚሁ ደንብ የተቀመጠን ሌላ ቅጣት የሚስከትል እንመልከት፡፡ ‹‹የዋና መንገዶች በማንኛውም ምክንያቶች አለመዝጋት እንደተጠበቀ ሆኖ በሐዘን ምክንያት ሳይሆን፣ የእግረኛንም ሆነ የተሽከርካሪን መንገድ ድንኳን በመጣል በከፊልም ሆነ በሙሉ መዘጋት 140 ብር ያስቀጣል፤›› ይላል፡፡ በዚህ አንቀጽ የተገለጸው ድንጋጌ እያለና እየተተገበረ መንገድ የሚዘጉ ድንኳኖች ከዓይናችን ጠፍተው አያውቁም፡፡

 የከተማው ጐዳናዎች ላይ ድንኳን ጥለው የንግድ ቤቶቻቸውን ለማስመረቅ፣ ጆሮ የሚበጥስ የሙዚቃ ጨኸት እያናጉ በድግስ የሚያተራምሱ በርካታ መደብሮች ይታያሉ፡፡ ተግባራቸው ሕገወጥ ስለመሆኑ የተገለጸላቸው አይደሉም፤ የገለጸላቸውም የለም፡፡  ድንኳናቸው እንዳይነካባቸው ጥበቃ መድበው አይደለም እንዴ ጐዳናውን የሚዘጉት?

በየትኛውም መንገድ የደንብ ጥሰቶችን የሚመለከቱ ሕግጋት ቢኖሩንም ከልብ ተከታትሎ ማስፈጸም ካልተቻለ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የማይሰጡ ትርፍ የወረቀት ሲሳይ ከመሆን አይልም፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ አንዱ መገለጫም ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለከተማ ፅዳትና ውበት ማስጠበቂያነት እንዲያገለግሉ የወጡ ሕጎችን በአግባቡ ማስፈጸም ነው፡፡ ይህ ሲደረግ የደንብ አስከባሪዎች ሥነ ምግባርና ጨዋነትም ቦታ ይሰጠዋል፡፡