Skip to main content
x

ለዋልያዎቹ ውጤት ተጠያቂ ማን ነው?

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደመነፍሳዊ ጉዞው ነቅቶ በስልት መጓዝ ወደሚችልበት መንገድ በመግባትና ዓለም አቀፉን የእግር ኳስ ቅኝት መሠረት በማድረግ  መሥራትና መትጋት ካልጀመረ፣ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ትንሳዔ መቼም ቢሆን ሊቃረብ እንደማይችል ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ስላስመዘገበው ውጤት ሳይሆን፣ ስላሳየው ትጋትና ብቃት ሳስብ ለአቋሙ መውረድ እልፍ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም፣ ለእኔ ግን እንደ ዋና ምክንያት የሚታየኝ የክለቦቻችን የብቃት ደረጃ ዝቅተኛና የሊግ ውድድራችን በብዛትም በጥራትም አንሶ መገኘት ነው፡፡

በተለይ በክለቦቻችን ላይ ስናተኩር፣ የአሠልጣኞቻችን የብቃት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ በክለቦች ውስጥ የሚታየው ዕውቀትና ክህሎት የጎደለው አሠራር፣ የአገሪቱን የሊግ የውድድር ደረጃ ከመቀነሱም በላይ በብሔራዊ ደረጃ የሚገነባውን ቡድናችንን ሰንካላ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በመላው አፍሪካ ደረጃ ቀርቶ በምሥራቅ አፍሪካ እንኳ ያለንን የችሎታና የተፎካካሪነት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡

አሠልጣኞቻችንን ስናስብም እነሱን ያፈሩት ኢንስትራክተሮችን ማንነት መመርመር ይገባናል፡፡ የኢንስትራክተሮቹን ማንነት ስንመለከትም ታዋቂም አዋቂም ያልሆኑ፣ ለአሠልጣኞቻቸው የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት የሌላቸው፣ አንዳንዶቹ ‹‹Position›› እና ‹‹Possession›› የማይለዩ፣ አንዳንዶቹ የፆታ ትንኰሳ የሚያደርጉ፣ ተመሳሳይ ኮርስና ይዘት ለሁሉም የሲ፣ የቢ እና የኤ ደረጃዎችን ፈቃድ የሚሰጡ፣ ቁንጽል ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን ውድቀት በተዘዋዋሪም ቢሆን ተጠያቂ በመሆናቸው ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡

(እውነቱ ይታየው፣ ከካምቦሎጆ)

***

ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎችም ሆስፒታሎች ቅርንጫፎችን እንዲከፍቱ ይደረግ

ነሐሴ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ የማስፋፊያ ቦታ አጣን ብለው በጻፉት ላይ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሆስፒታል ከአንገት በላይ፣ የስኳር በሽታ፣ የደም ብዛት፣ የአጥንት ስብራትና የዓይን ሕክምናን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሕክምና ለማግኘትም ከየክፍላተ አገሩ በርካታ ታካሚዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡

በሚመጡበት ጊዜ፣ ለሆቴል፣ ለመኪና ኪራይና ለመሳሰለው ብዙ ወጪ ሲያወጡ ይታያሉ፡፡ ስለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከመስፋፋት ይልቃ ሆስፒታሉ በየክልሉ ቅርንጫፍ ቢከፍት፣ ለዜጎች በጣም አመቺ አገልግሎት መስጠት በተቻለው ነበር፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በየገጠሩ ኮሌጅ እየከፈተ ዕፎይታን አስገኝቷል፡፡ እንደሱም ባይሆን እንኳ፣ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በምሥራቅ ከፋፍሎ ቅርንጫፎቹን ቢያስፋፋ፣ ታማሚዎችና አቅመ ደካሚዎች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ሲሉ ከሚደርስባቸው መንገላታት በዳኑ ነበር፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተመሠረተው በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ቢሆንም፣ ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ በነበረበት እንዲቀጥል አደረጉት እንጂ በየክልሉ ቅርንጫፍ እንዲኖረውና እንዲስፋፋ አላደረጉም፡፡ በየክፍላተ አገሩ የሚመጣው ሕዝብ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለአጥንት ስብራት የሚመጡ ታማሚዎች ሕክምና ክትትል ሲባል ዘጠና ሚሊዮን ብር ለቤት ኪራይ ማውጣት አግባብ አይደለም፡፡

እውነት ለወላጆች የሚታሰብ ከሆነ፣ ጳውሎስ ሆስፒታልን ብቻም ሳይሆን ሌሎችንም በመላ አገሪቱ  እንዲስፋፉ ማድረግ፣ ቅርንጫፍ እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባል፡፡

(ከታዛቢ)

***

ስለ ቤልካሽ የተጻፈው ዜና ቢስተካከል

በነሐሴ 24 ቀን 2009 ዕትም ገጽ ስምንት ላይ ስለ ቤልካሽና ሃሎ ካሽ የተጻፈውን ተመልክተናል። ድርጅታችን ቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶልዩሽንስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን አቅራቢ ሲሆን፣ የሃሎ ካሽ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቶችን የሚሰጡት ደግሞ እንደ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክና ሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ (ኤስኤምኤፍአይ) ያሉ የገንዘብ ተቋማት ናቸው። የገንዘብ ተቋማቱ ደንበኞች ሃሎካሽን በመጠቀም ገንዘብ መላክ ወይም መቀበል፣ የሞባይል ካርድ መግዛት፣ የተለያዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን መግዛትም ሆነ ልዩ ልዩ ክፍያዎችን መፈጸም ይችላሉ።

በኦሮሚያ ክልል የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ ሃሎ ካሽን በመጠቀም ለተረጂዎች የዕርዳታ ገንዝብ ማከፋፈል መቻላቸውን ጠቅሰን መግለጫ ልከናል፡፡ በመሆኑም ጋዜጣው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ማስተካከያ እንዲያደረግ እንጠይቃለን፡፡

  • ሃሎ ካሽን በመጠቀም ለተረጂዎች የዕርዳታ ገንዝብ የማከፋፈል ሥራ ያከናወኑት በኦሮሚያ ክልል የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ መሆናቸውን፤
  • የዕርዳታው ለጋሽ ድርጅት ስም ‹‹ሜርሲ ኮርስ›› ሳይሆን፣ ‹‹ሜርሲ ኮርፕስ›› መሆኑን፤
  • የገንዘብ ማስተላልፊያው ዘዴ ‹‹ኤሌክትሮኒክ›› መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

(አቶ ነገደ አበበ፤ የቤልካሽ ኩባንያ የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ)