Skip to main content
x
ሐዲዱን የጣሰው ተሽከርካሪ

ሐዲዱን የጣሰው ተሽከርካሪ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ፣ አልፎ አልፎ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ሲያደርሱ ይታያሉ፡፡ ነሐሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአያት ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ፣ ሰአሊተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ቶዮታ ፒካፕ ተሽከርካሪ መስመሩን ጥሶ ባቡሩን ገጭቷል፡፡

አገር በቀል ችግኝ ተከላ በእንጦጦ  

ክረምት በመጣ ቁጥር በየአካባቢው ችግኝ ተከላ ይከናወናል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን ከአናት ሆኖ የሚያያት የእንጦጦ ተራራማ ሥፍራ ሥነ ምህዳሩን ለመጠበቅ በተለይ በሐምሌና ነሐሴ በየዓመቱ ችግኝ ተከላ ይካሄድበታል፡፡ በእንጦጦ ተራራማ ሥፍራ ላይ የራሱ የችግኝ ጣቢያ ያቋቋመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር በተከታታይ ዓመታት ባደረገው ጥረት አካባቢው በአገር በቀል ዛፎች በመሸፈኑ አጥቢ የዱር እንስሳት እንደ አነር፣ የምኒልክ ድኩላ፣ ሚዳቋና የመሳሰሉት ወደ ቀደመ አካባቢያቸው መመለሳቸው ታውቋል፡፡ ፎቶዎቹ የሚያሳዩት መሰንበቻውን የቅርስ ባላደራ ማኅበሩ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር በእንጦጦ ችግኝ ተከላ ሲያካሂድ ነው፡፡

ምንም አልል

እሺ እንግዲህ በዝምታ

የልቤን ደም ሥር ትርታ

የደቂቅ ዕድሜን ትዝታ

ትር ስትል አፍታ ለአፍታ

እያዳመጥኩ እያስታመምኩ፥ ጊዜዬን እያሰላሰልኩ

ሳልናገር ሳልጋገር፥ እየደገምኩ እያሰለስኩ

ሳልሰለች እየመላለስኩ……

እሺ እንግዲህ በጸጥታ

የልቤን ደም ሥር ትርታ

የእስትንፋሴን ቃል ጉምጉምታ

ትር ስልት አፍታ ለአፍታ

ሳልሰለች እየደጋገምኩ

በእግረ ሕሊና እያደነቅኩ….

እሺ እንግዲህ አልናገርም

በአንደበቴ አልተነፍስም

በልሳኔ አልመሰክርም

አልልም፡፡ ምንም አልልም

እንዲያው ዝም እንጂ ዝም ዝም…

የልቤ ደም ሥር ሲያቃጭል

ልሳኔን ሲያነሳ ሲያስጥል

ቃላቴን ሲቃኝ ሲያጋግል

ትንፋሼን ሲያንር ሲያዳውል

ክል ሲል ትር ድም ሲል

ማዳመጥ ማስታመም እንጂ ፥ ሌላ ምንም አልል፡፡

ጸጋዬ ገብረ መድኅን “እሳት ወይ አበባ” (1966)


*********

‹‹ይህ ግን ለመንግሥት ክፉ ምልክት ነው››

ያማረ የግንብ ቤትና ትንንሽ ጐዦ አጠገብ ላጠገብ ተሠርተው እናያለን፡፡ ባንዱ ቤት ውስጥ ትልቁ ጌታ ሕዝቡ ደክሞ ያፈራውን ገንዘብ በከንቱ ሲያባክን በጐዦው ውስጥ የሚኖረው ድኻ የሚበላውና የሚለብሰው የሚያበራውም አጥቶ በረኃብና በብርድ ተጨብጦ በኲበት ጢስና በእድፍ ውስጥ ይጨማለቃል፡፡ ባንዱ ቤት ጌትነቱ እየበዛ ሲሄድ ባንዱ ቤት ድኸነቱ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ የጐዦውንና ያዲሱን ግንብ ቁመት ብናስተያይ ባገራችን ድኻ ጌታ እንዴት እንደተራራቁ እንደሄዱ ይገልጹልናል፡፡ ይህ ግን ለመንግሥት ክፉ ምልክት ነው፡፡ ይህም ክፉ ነገር እየሰፋ እንዳይሄድ መንግሥት ሕዝቡን በሥራ እንዲያሰለጥን ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝቡ በሥራ ከሠለጠነ ዘንድ ጌታና ድኻ እንደገና ይቃረባሉ፡፡ በምክርና በኃይልም ተደጋግፈው የመንግሥታቸውን መሠረት ያጠነክራሉ፡፡ ብርና ወርቅም ረዳቶች የለውጥ መሣሪያዎች የሚሆኑት በዚያ ጊዜ ነው፡፡

ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› (1916)

***

በስቃይ የታጀበ ውበት

ሰዎች ውበታቸውን ለመጠበቅ የተለያዩ መዋቢያዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ በንቅሳት ሰውነትን ማስዋብ ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም ዓይነት ንቅሳቶች ቀለል ያለ ሕመም ያላቸው ወይም ሕመም አልባ አይደሉም፡፡ በተለይ በእጅ ሲቆነጠጥ እግር ድረስ የሚነዝረው ጆሮ ላይ በቀለም ብቻ ሳይሆን ስለትን ተጠቅሞ መነቀስ ሕመሙን በጣም የበዛ እንደሚያደርገው ሚረር ዩኬ ዘግቧል፡፡ ሆኖም ይኼንን የጆሮ ላይ ንቅሳት የሚፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ሴቶች የጆሯቸውን ቅጠል በውስጥ በኩል ያለውን ክፍል ይነቀሳሉ፡፡ ታዲያ ጆሮዋቸው በመቅላት ብቻ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ቆስሎና እዋባለሁ ያሉትን በሕምም አሰቃይቶ ማለፉ አይቀሬ ነው፡፡ በጆሮዋቸው ላይ አበቦች ከነቅጠላቸው፣ ቅጠል ብቻውን፣ አንዳንዴም መስመርና ሌላም ዓይነት ቅርፆችን በንቅሳት ማስዋብ እየተለመደ መምጣቱን፣ ጆሮ ደግሞ በጥቂቱ ለመታመም ቅርብ መሆኑን ዘገባው ያሳያል፡፡ ሲያጌጡ ይመላለጡ እንዲሉ፡፡

***

ከ13 ዓመታት በኋላ ካሮት ላይ ጠልቆ የተገኘው የዳይመንድ

ቀለበት

የ84 ዓመቷ ካናዳዊት ሜሪ ግራምስ፣ ከ13 ዓመታት በፊት ከዳይመንድ የተሠራው ቀለበታቸው የጠፋው በቤተሰባቸው ማሳ ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ባለቤታቸውን በመፍራትም ምስጢር አድርገውታል፡፡ ለወንድ ልጃቸው ብቻ በመንገር ተመሳሳይ ቀለበት በርካሽ ዋጋ ዝተውም ያደርጋሉ፡፡ ይኼ ጉዳይ ምስጢር ሆኖ ለዓመታት ቢቆይም የልጃቸው ባለቤት ምስጢሩን ትሰማለች፡፡ ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ የልጃቸው ባለቤት ኮለን ዴሌይ የባሏ እናት ቤተሰቦች የሚኖሩበት  ማሳ ስፍራ በመሄድ አትክልትን መንከባከብና ለቤት ፍጆታ የሚውሉትን ማምጣት ትጀምራለች፡፡ በዚህ መሀል የአማቷን ቀለበት ለማግኘትም ትማትር ነበር፡፡ ተሳክቶላትም ቀለበቱን በካሮት ውስጥ ጠልቆ ታገኘዋለች፡፡ ቢቢሲም አስገራሚ አጋጣሚ ሲል ጉዳዩን ዘግቦታል፡፡

***

ፓሽን ፍሩት

ፓሽን ፍሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየተስፋፋ የመጣ ተክል ነው፡፡ ከዚህ ተክል ግንድ ልክ እንደ ሐረግ የሚመዘዝ ነው፡፡ አበባና ፍሬ አለው፡፡ ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉት አበባውና የፍሬው ልጣጭ ናቸው፡፡ የአበባው ቅመማ ውስብስብ በመሆኑ የፍሬውን ልጣጭ ጠቀሜታ መቃኘቱ ይበጃል፡፡ ፍሬውን /ሁለትና ሦስት ፍሬ/ ትኩሱን መመገብ ይቻላል፡፡ የፍሬውን ልጣጭ በመውቀጥ፣ አንድ የሻይ ማንኪያ /ድርበብ/ አንድ ብርጭቆ ውስጥ በጥብጦ ጠዋትና ማታ መጠጣት የፈውስ ረድኤቱን መቀራመትም ይቻላል፡፡

ፓሽን ፍሩት የነርቭ ዕውክታን በማስተካከል፣ የእንቅልፍ ችግርን በመክላት፣ ግልፍተኝነትንና ንክነትን የመሳሰሉ የአእምሮ ችግሮችን በማረም በኩልም ምስጉን ነው፡፡ ፍሬው ለሚያገግሙ በሽተኞችና ላረጡ ሴቶችም ጠቀሜታ አለው፡፡ ፓሽን ፍሩት ለትኩሳትም ይበጃል፡፡ ፍሬው ሱስ ባያስይዝም፣ የዕፅ ሱሰኞችን ባህርይ ለማረም ይረዳል፡፡ ነርቮችን በማለሳለስ በብስጭት ሳቢያ ከፍ የሚል የደም ግፊትን ያወርዳል፡፡ የነርቭ ችግር ላለበት ሁሉ የፈውስ ረድኤትን ይፈነጥቃል፡፡ በአእምሮ ውጥረት ሳቢያ ለሚከተል የራስ ምታትም ፓሽን ፍሩት መድህን ነው፡፡ በስሜት መገንፈል ሳቢያ በሚነሳ አስም /ስፓስሞዲክ አስማ/ ለሚሰቃዩም እፎይታን ይሰጣል፡፡

ዶክተር ቤዲ ‹‹ዳየት-ክዩር›› ጥንቅር በሻለቃ ዓባይነህ አበራ ‹‹ካዘና››