Skip to main content
x
ሐጅ እና ዓረፋ

ሐጅ እና ዓረፋ

የቱርክ ፊልም ባለሙያዎች በድሮን ላይ ካሜራ ገጥመው ፊልም በመቅረፅ ላይ ነበሩ፡፡ ፊልሙን የሚቀርፁት በጋና በምትገኝ አንድ የገጠር መንደር ነበር፡፡ ያዩት ነገር እንግዳ የሆነባቸው አልሀሰን አብደላ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪም ድሮኗን በእጃቸው እንደያዙ የዘመናት ምኞታቸውን እውን ማድረግ ይቻል እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ‹‹ይህቺን በራሪ ነገር ትንሽ ከፍ አድርጋችሁ ብትሠሩ እኔን መካ ይዛኝ መሄድ አትችልም?›› አሉ፡፡

እነሱም ቅንነት የተሞላበት ጥያቄያቸውን በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው አሰፈሩት፡፡ ጉዳዩም በአንዴ ተሰራጨና የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ቻለ፡፡ ከዚያም የተለያዩ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎች የአልሀሰንን ህልም እውን ለማድረግ ተነሱ፡፡ ምኞታቸውም ተሳክቶ አልሀሰን መካ ሊሄዱ ቻሉ፡፡

ከአምስቱ የእስልምና ምሶሶዎች መካከል መካን መጎብኘት ዋነኛው ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ መካን ማየት ሃይማኖታዊ ግዴታው ነው፡፡ ይህንን ሃይማኖታዊ ግዳጅ ለመፈፀም አቅም ይጠይቃል፡፡ ግዴታው ያለባቸውም አቅሙ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሁንና አቅሙ የሌላቸው እንደ አልሀሰን ያሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካቶች መካን የመጎብኘት ትልቅ ምኞት አላቸው፡፡ እንደ አልሀሰን በሆነ ተአምር ካልሰመረላቸው በስተቀር በአቅም ምክንያት ውጥናቸው ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

 

ይህ የብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ችግር ነው፡፡ የሁል ጊዜ ጸሎታቸው ‹‹መካ ሳልሄድ አትግደለኝ›› የሆነ ብዙ ሙስሊሞች አሉ፡፡ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው ለዓመታት ያጠራቀሙትን ገንዘብ አውጥተው መካ የሚሄዱ ብዙ ናቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ በቂ ገንዘብ ያላቸው ያለምንም ውጣ ውረድ መካን ይጎበኛሉ፡፡ የሚያስቸግራቸው ነገር ቢኖር ከተፈቀደው ኮታ በላይ ሆኖ መቅረት ነው፡፡

የነቢዩ መሐመድ የትውልድ ቦታ የሆነችው መካ ቅዱስ ከተማ በመባል ትታወቃለች፡፡ ከባሕር ጠለል ከ277 ሜትር በላይ የምትገኝ እንደመሆኗ በበጋው ወቅት የከተማዋ የሙቀት መጠን 40 ዲግሪ ሴሊሺየስ ይደርሳል፡፡ በረሃማው የአየር ጠባዩዋ ግን በየዓመቱ የሚጎበኙዋትን ምዕመናን ቁጥር የመቀነስ አቅም የለውም፡፡ ሁለት ሚሊየን ሰዎች የሚኖሩባት ሲሆን፣ በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ምዕመናን ይጎበኙዋታል፡፡

ሁሉም እንዳሻው የሚሄድባት ግን አይደለችም፡፡ አገሮች ለሐጅ ጉዞ የሚልኳቸው ሰዎች ብዛት በተቀመጠላቸው ኮታ የተወሰነ ይሆናል፡፡ ኮታ የሚወጣው በየአገሩ ያለውን የምዕመናን ቁጥር መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ትልልቅ ኮታ ከተሰጣቸው የሙስሊም አገሮች መካከል 168 ሺሕ ለኢንዶኔዥያ፣ 143 ሺሕ ለፓኪስታን፣ 136,026 ለህንድ፣ 101,758 ለባንግላዴሽ የተሰጠ መሆኑን  ‹‹Which Countries Have the Highest Number of Hajj Pilgrims?›› በሚል የወጣው ጽሑፍ ያብራራል፡፡

አነስተኛ ኮታ ከተሰጣቸው መካከል የሆነችው ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተሰጣት ኮታ ስምንት ሺሕ ብቻ እንደነበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ኡመር ኢማም ይናገራሉ፡፡ የተፈቀደው ኮታ አነስተኛ በመሆኑ ብዙዎች መሄድ እየፈለጉ ይቀራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮታው ወደ 14 ሺሕ ከፍ እንደተደረገ የሚናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሐጅ ማድረግ የቻሉት ስምንት ሺሕ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ሳዑዲ የሚኖሩ ልጆቻቸው አልያም ሌሎች ዘመዶቻቸው ጋር ያርፉ ነበር፡፡ አሁን ግን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በሳዑዲ ይኖሩ የነበሩ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል በአሁኑ ሐጅ የተጓዦች ቁጥር ያነሰው፤›› ብለዋል፡፡

መካን የመጎብኘት ዕድሉ ያጋጠማቸው ምዕመናን በመካ እንዲቆዩ በሚፈቀድላቸው አንድ ወር ውስጥ በከተማው የሚገኙ የተለያዩ ቅዱሳን ቦታዎችን እንዲጎበኙ ይደረጋል፡፡ ሪፖርተር ሼህ ኡመርን ባነጋገረበት ወቅት ከቅዱሳን ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው ሚናን በመጎብኘት ላይ ነበሩ፡፡ ‹‹አሁን በመዲና አድርገን መካ ደርሰናል፡፡ አሁን ሚና ላይ ነን፡፡ ሐሙስ በዋዜማው አረፋ ተራራ ላይ እንወጣለን፡፡ ከዚያ ወደ መካ ተመልሰን በበዓሉ ዕለት ሚና ላይ እናድራለን፤›› በማለት በቆይታቸው የሚያደርጉትን ገልጸዋል፡፡

 ከሚጎበኙ ቦታዎች መካከል አንዱ የዓረፋ ተራራ ቦታው ለኢድ አልአድሀ በዓል መሠረት የሆነ በእስልምና እምነት ውስጥ ትልቅ ገድል የተሠራበት ነው፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከነቢዩ መሐመድ ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነቢዩ ኢብራሂም ከፈጣሪ የቀረበላቸውን ትልቅ ፈተና በድል የተወጡበት ዘመን ነበር፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም  ለልጅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖራቸውም ልጅ ሳያገኙ ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ከጾም ጸሎት በኋላ ግን በዕድሜያቸው ማምሻ ላይ አንድ ልጅ አገኙ፡፡ ስሙንም ኢስማኤል አሉት፡፡

በስተርጅናቸው ባገኙት ልጅ በጣም ደስተኛ የነበሩ ቢሆንም ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ አንድ ቀን ፈጣሪ ልጃቸው ዒስማኢልን እንዲሰዉለት ሲጠይቃቸው በህልማቸው ታያቸው፡፡ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ለሚወዱት ነቢዩ ኢብራሂም ጉዳዩ ከህልም በዘለለ ትርጉም ነበረው፡፡ ልባቸው ክፉኛ ቢያዝንም ዒስማኢልን ለመሰዋት ወሰኑ፡፡ ውሳኔያቸውንም ለልጃቸው ነገሩት፡፡ የፈጣሪ ፍላጎት ከሆነ ቢሞት ምንም እንዳልሆነ በመግለጽ በሐሳባቸው መስማማቱን ነገራቸው፡፡

 አባትና ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘው ራዕዩን ለማስፈጸም ከመካ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ዓረፋ ተራራ ገሰገሱ፡፡ ከተራራው አናት ላይ እንደደረሱም ዒስማኢልን ለማረድ ተዘጋጁ፡፡ ነገር ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ሰይጣን በሰው ተመስሎ እየሄደ ሊያሳስታቸው ሞክሮ ነበር፡፡ ሐሳባቸውን ቀይረው ሁለት ሦስት ጊዜያት ያህል ከተራራው ወርደው ነበር፡፡ ይሁንና የፈጣሪ ትዕዛዝ ከልጃቸው እንደማይበልጥ በማሰብ ቢላውን ከልጃቸው አንገት ላይ አሳረፉት፡፡ በቀላሉ ሊታረድላቸው ግን አልቻለም፡፡ ጠበቅ አድርገው ቢገዘግዙም ሊሆን አልቻለም፡፡ በዚህም ጊዜ አንድ ተአምር ተፈጠረ፡፡

ከወደ ሰማይ ያልተጠበቀ ጥሪ ተሰማ፡፡ ‹‹ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው›› በማለት አወጀ፡፡ ድምፁ የመላእክተኛው ጅብሪል ነበር፡፡ በምትኩም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርዱና ልጁን ወደቤቱ እንዲመልሱ ነገራቸው፡፡ በዚህ መሠረትም በጉ ታረደ፡፡ ኢብራሂምና ዒስማኢልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል አድሐ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡

የዓረፋ በዓል ከመከበሩ 10 ቀናት አስቀድሞ ለ9 ቀናት  ይጾማል፡፡ በዚህ ወቅት የሚደረገው ጾም ከሌላው ጊዜ በተለየ ዋጋ እንዳለው ሼህ ዑመር ‹‹ዘጠኙን ቀናት ለጾመ የሁለት ዓመት ኃጢአቱ ይሰረዝለታል፤›› በማለት ቀናቱ በጾም ሲያልፉ ከበድ ያለ ምንዳ እንደሚያስገኙ ይናገራሉ፡፡ በጾሙ መገባደጃ ማለትም በዘጠነኛው ቀን ምዕመናን ዓረፋ ተራራ ላይ በመውጣት ለፈጣሪ ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ ‹‹እኛ በተለምዶ በዓሉን ዓረፋ እንለዋለን እንጂ ዓረፋ የሚባለው ተራራው ላይ የሚወጣበት ዘጠነኛው የጾም ቀን ወይም የበዓሉ ዋዜማ ነው፡፡ በዓሉ ደግሞ ኢድ አል አደሃ ነው የሚባለው፤›› ይላሉ፡፡

ዒስማኢል ለመስዋዕትነት የቀረበበት ድርጊት በዚሁ ዕለት ለሚከናወነው  ‹‹ኡድሒያ›› መነሻ በመሆኑ በዓሉ የእርድ በዓል እንዲሆን ሆኗል፡፡ ዒድ አል አድሓ የመስዋዕትነትና የመዳን በዓል ነው፡፡ የሐጅ ጸሎት የሚፈጽሙ  በዚህ ዕለት ኡድሒያ የማረድ ግዴታ አለባቸው፡፡  ወደ ሐጅ ያልሄዱ ደግሞ ከተቻለ በዚሁ ዕለት በየቤታቸው እንስሳት በማረድ ኡድሒያ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ታዲያ ኡድሒያ ተብሎ የሚመዘገበው ለኡድሒያ ከታረደው ሥጋ አንድ ሦስተኛው በቀጥታ ለድሆች ሲከፋፈል፣ አንድ ሦስተኛው ለዘመድና ለወዳጅ ሲሰጥ፣ የተቀረው አንድ ሦስተኛው ብቻ ለቤተሰቡ አገልግሎት ሲውል ብቻ ነው፡፡

የመስዋትነት በዓል በመባል የሚታወቀው ኢድ አል አድሐ ወይም የዓረፋ በዓል የሚከበረው በሒጅራ ዘመን አቆጣጠር ዓረፋ የሚውልበት ወር በገባ በአሥረኛው ቀን ነው፡፡ በአሥራ ሁለት ወራት የሚከፋፈለው የሒጅራ አቆጣጠር 354 ወይም 355 ቀናት አሉት፡፡ በየዓመቱ የአሥር ቀናት ለውጥም አለው፡፡ ከጨረቃ መውጣት ጋር ተያያዥነት ስላለውም እንደ ዒድ አል አድሐ ያሉትን የሙስሊም በዓላት ለማክበር ትክክለኛውን ቀን አስቀድሞ ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ቀናቱ የሚወሰኑት ከጨረቃ መውጣት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ዘንድሮ ለ1438ኛ ጊዜ የሚከበረው የዒድ አል አድሐ በዓል በሒጅራ አቆጣጠር ዙልሂጃ 10 ነው፡፡ የዘንድሮው በዓል በፀሐይ አቆጣጠር ነሐሴ 26 ቀን 2009 ሆኗል፡፡