Skip to main content
x
ሕይወት በደሳሳ መንደሮች

ሕይወት በደሳሳ መንደሮች

የመፀዳጃ ቤቶችን ፍሳሽና የተለያዩ ቆሻሻዎችን እያንከባለለ ከጀርባቸው የሚያልፈው የግንፍሌ ወንዝ ጠረኑ የረበሻቸው አይመስሉም፡፡ ከቀትር በኋላ የወጣው ፀሐይ ወንዙ እንዲሰነፍጥገን ቢያደርገውም፣ ፀሀዩ ቀዝቀዝ እስኪል እንኳን የያዙትን ሥራ ገትተው ቤት ገብቶ አረፍለማለት ፍላጎቱ ያላቸው አይመስሉም፡፡

በየማዳበሪያ ተሞልቶ የተቀመጠውን ደቃቅ ከሰል መሬት ላይ ይዘረግፉትና  እንደ ገንፎ መሀሉን ይከፍቱታል፡፡ ከዚያም በሰባራ ጀሪካን ሞልተው ከጎናቸው ያስቀመጡትን አተላ መሳይ የተበጠበጠ አፈር ጥቂት ቀንሰው ያፈሱበታል፡፡  

 ወይዘሮ ዙሪያሽ አዋሽ የተበጠበጠውን አፈርና ደቃቅ ከሰል በእጃቸው እያሹ ሲያደባልቁ ለእጃቸው ጓንትም ሆነ ሌላ መከላከያ አላደርጉም፡፡ በኑሮ ተፈትኖ የጠነከረ መዳፋቸውም በቀላሉ የሚበገር አይደለም፡፡ አፈሩንና ከሰሉን ለማዋሃድ ዉሃ በብዛት ይጠቀማሉ፡፡ ታድያ በአቅራቢያቸው የቧንቧ ዉሃ ባለመኖሩ ከሌላ መንደር ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን የልብስ እጣቢ ይጠቀማሉ፡፡  

በእጃቸው ያቦኩትን ደቃቅ ከሰልና የተበጠበጠ አፈር እንዲደርቅ አለት ላይ ይጠፈጥፉታል፡፡ አለቱም ከንጋት ጀምሮ ባዘጋጁዋቸው የከሰል ጥፍጥፍ ተሞልቷል፡፡ እነዚህን የከሰል መርጎች ለማዘጋጀት የሚያስፈልጋቸውን ደቃቅ ከሰል የሚያቀርቡላቸው ደንበኞች አሏቸው፡፡ አንድ ማዳበሪያ ደቃቅ ከሰል በ60 ብር ይገዛሉ፡፡

አብዛኞቹ ጎረቤቶቻቸው ከሰሉን እንደሚገዟቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ዙሪያሽ  የዕለት ከዕለት ሥራቸው አድካሚና አሰልቺ ቢመስልም ተስፋ መቁረጥ አይታይባቸውም፡፡ ብርታትና ቅልጥፍናቸው የሌለባቸው የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ አስመስሏቸዋል፡፡ ከጊዜ ጋር ፉክክር የያዙ ይመስል ሥራቸውን አቀርቅረው ይሠራሉ፡፡ ሲያወሩም ለአፍታ ከሥራቸው ላይ ቀና ሳይሉ ነው፡፡ ከሥራቸው ላይ ከተነሱ፣ ውኃ አንሷቸው ለመጨመር፣ አልያም ደቃቅ ከሰል የያዘ ማዳበሪያ ለመውሰድ ነው፡፡

 በከሰል ብናኝ የቆሸሸ ሻሻቸውን ያሰሩት ወይዘሮ ዙሪያሽ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ደቃቁን ከሰል ከአፈር እያደባለቁ የከሰል ጥፍጥፍ መሸት ከጀመሩ 17 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ብቸኛ ገቢያቸውም ከሰሉ ተሽጦ የሚያገኙት ገቢ ብቻ ነው፡፡

ከሰሉን ሸጠው ከገቢ ወጪ ምን ያህል እንደሚያተርፋቸው በውል አያውቁትም፡፡ በቀን የሸጡት የከሰል ጥፍጥፍ ለልጆቻቸውን ዳቦ መግዣና ሌሎች የቤት ውስጥ ወጪዎች ከቻለ ሌላ ምንም አይጠብቁም፡፡ ትርፋቸው ልጆቻቸው ጠግበው ማየታቸው ብቻ ነው፡፡ ህልውናቸው የተመሠረተውም በአለቱ ላይ በሚደረድሯቸው የከሰል ምርጎች ነው፡፡

ታዲያ ደርቆ እስኪሰበስቧቸው ድረስ በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ካፊያ ነገር ከጀማመረም በላስቲክ መሸፈን፣ ጠንከር ካለ ደግሞ ሰብስቦ ማስገባት ግድ ይላቸዋል፡፡ የግንፍሌ ወንዝ ሞልቶ በአለቱ ላይ የደረደሯቸውን የከሰል ጥፍጥፎች ጠራርጎ ወስዶባቸው ያውቃል፡፡ ገጠመኙም፣ አይከሱት ነገር ግዑዝ፣  አያማርሩት ነገር ችግር ገፍቷቸው የሄዱበት እሳቸው ያስብላል፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ራሳቸውን አፅናንተው በማግስቱ ለሚጠብቃቸው ስራ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡

ከቤተ መንግሥት 100 ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው አዋሬ ሌላኛው የኑሮ ገፅታ ምን እንደሚመስል፣ የተደላደለ ኑሮ በሚኖሩና የድሀ ድሀ በሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ያለውን የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህም ያለ ኑሮ አለ ያሰኛል፡፡

ለመተላለፍ አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ መንደሩ የተጨናነቀ ነው፡፡ የሚተላለፉበት ጠባብ መንገድ ወጣ ገባ በመሆኑ እንዳይደናቀፉ የሚራመዱበትን መሬት በደንብ ማየት ግድ ይላል፡፡ ቤቶቹ በቆርቆሮና በማዳበሪያ የተሠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ቤቶች ጠባብ ከመሆናቸው የተነሳ የጥበቃ ቤት ይመስላሉ፡፡ ምግብ ለማብሰል ደጃፍ መውጣት ግድ ነው፡፡ ንጹህ ውኃ የሚያገኙትም ከሌላ ቦታ በመግዛት ነው፡፡ መኖሪያ ቤቶቹ የተሠሩት ረባዳ በሆነ ቦታ ላይ ከመሆኑ አንፃር በግንፍሌ ወንዝና በመንደሩ መካከል  የከፍታ ልዩነት የለም ማለት ያስችላል፡፡ ወዲያና ወዲህ የሚተላለፉትም በወንዙ ውስጥ ባሉ አለቶች ለይ በመረማመድ ነው፡፡

ተፈጥሯዊ ቀለሙን ወደ ጥቁር የቀየረው ወንዝ፣ ጠረኑም በፅዳት እንዳልተያዘ መፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ዝናብ ሲጥል ወንዙ ወደየቤቶቹ ደጃፍ የሚደርስ ሲሆን፣ እንደ ክፉ ባለጋራ መስመሩን አስፍቶ የሚተኛበት ስፍራም እርጥበ ይዟል ጠቁሯልም፡፡ ጫን ሲል ደግሞ በራቸውን አልፎ ቤታቸው ሰተት ብሎ ይገባል፡፡ በራሱ ጊዜ እስኪሄድላቸው ቤታቸውን ለቀው ከመሄድ ባለፈ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡

‹‹በክረምት ተኝተን አናውቅም፡፡ ከአሁን አሁን ጎርፍ ሊወስደን እንደሚችል ስለምናስብና አጋጥሞም ስለሚያውቅ ነቅተን እንጠባበቃለን›› ትላለች አንዲት የመንደሩ ነዋሪ፡፡

መንደሩ ከተመሠረተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ መንደር በራሳቸው ቤት የሚኖሩና ተከራይተው የሚኖሩ አሉ፡፡ እንደ ወ/ሮ ዙሪያሽ ያሉ የአቧሬ ነዋሪዎች ለቤት ኪራይ በወር 1,500 ብር ከፍለው ይኖራሉ፡፡ ቤታቸው መኖሪያቸው ብቻ ሳይሆን መሥሪያ ቦታቸውም ነው፡፡

አቶ ዳዊት ጌታሁን በዚህ መንደር ከ40 ዓመታት በላይ እንደኖሩ ያናገራሉ፡፡ ተወልደው ያደጉትም በዚሁ መንደር ነው፡፡ ውጪው በቆርቆሮ ውስጡ ደግሞ በቡራቡሬ ማዳበሪያ የተሠራውን ጠባብ ክፍል ለሁለት ከፍለውታል፡፡ በአንደኛው ከፍል የልብስ ስፌት ማሽናቸውን አስቀምጠው ይሰራሉ፡፡ በአንዴ ከሁለት ሰው በላይ መያዝ የማትችለው ጠባብ ክፍል ውስጥ ለመሰፋት ተራቸውን በሚጠብቁ ያረጁ ልብሶች ተሞልታለች፡፡ ልብሳቸውን ለማሰፋት የመጡ ደንበኛቸው ከጎናቸው በተከመረው ልብስ ላይ ቁች ብለው ይጠባበቃሉ፡፡

የስፌት መኪናቸው አርጅታለች፡፡ ሪፖርተር ሊያነጋግራቸው ወደ ክፍላቸው ሲገባ በእግራቸውን የስፌት መኪናውን ፔዳል እየመቱ፣ እጃቸውንና ሙሉ ትኩረታቸውን  በሚሰፉት የሕፃን ልብስ ላይ አድርገው ነበር፡፡ የጀመሩትን ሥራ ወደ ጎን ብለው በመንደሩ ሕይወት ምን እንደሚመስል ያወጉ ጀመረ፡፡ የማማረር ነገር አይታይባቸውም፡፡ የሚያወራቸው የሚሰማቸው ይፈልጋሉ፡፡   

 በዚህ መንደር ተወልደው ቢያድጉም፣ ኑሮን አሸንፎ ወደ ተሻለ አካባቢ የመኖር ተስፋ ነበራቸው፡፡ ይህ ተስፋቸው በትምህርታቸው ዕውን እንደሚሆን ይገምቱ ነበር፡፡ ይሁንና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ ያስመዘገቡት ነጥብ በወቅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ አላስገባቸውም፡፡ ከአቧሬ ወጥቶ በተሻለ አካባቢ የመኖር ህልማቸውም በዚያው ህልም ሆኖ ቀረ፡፡

በወቅቱ አስመዝግበው በነበረው ነጥብ በዲፕሎማ ፕሮግራም መማር ቢችሉም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይማሩ ቀሩ፡፡ የቤተሰቦቻቸው ይዞታ በመወረሱ በየወሩ ለ 350 ብር የቤት ኪራይ መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

መንደሩ ለጎርፍ ብቻ ሳይሆን ለእሳት አደጋም የተጋለጠ ነው፡፡ ቤታቸው ሁለት ጊዜ ተቃጥሎባቸው ሙሉ ንብረታቸው ወድሞ እንደሚያውቅ ይናገራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ተከስቶ በነበረ የእሳት አደጋም 135 ቤቶች ተቃጥለው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ቤተሰብ የመመሥረት ፍላጎት ቢኖራቸውም ገቢያቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለበለጠ ለችግር እንዳይዳረጉ ይሠጋሉ፡፡ ‹‹በቀን እስከ 50 ብር ብሠራ ነው፡፡ መንደሩ አያመችም፡፡ በተለይ ፀሐይ ሲወጣ ወንዙ በጣም ይሸታለ፡፡ ለዚህም ሰዎች ወደዚህ መጥተው አያሠሩኝም፡፡ በጣም በቅናሽ ዋጋ የምሠራውም ደንበኛ ለመሳብ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ከንፈሮን በሚመጡለት በዚህ መንደር ጥቂት የማይባሉ አባወራዎች ይኖራሉ፡፡ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ላይ ታች በሚሉ ወዛደሮችም የተሞላ ነው፡፡ ድክድክ የሚሉ የመንደሩ ሕፃናትም በየትኛውም አይነት ሁኔታ መኖር እንደሚቻል ይመሰክራሉ፡፡ አዋሬ ሰዎች እንደ አቅማቸው መኖር የሚችሉበት ቦታ ነው፡፡

አንድ ሻይ በሁለት ብር፣ ቡና በሦስት ብር፣ ምግብ በጣም ከተወደደ በ20 ብር ይበላበታል፡፡ የሦስት ብር ዘይት ተሰፍሮ ይሸጣል፡፡ አንድ ሙሉ ከብሪት መግዛት ባይችሉ የተወሰነ ፍሬ ቆጥረው በሳንቲም ደረጃ መግዛት ይችላሉ፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙ በልቶና ጠጥቶ ያድራል፡፡ ወደ መንደሩ ሲገቡ የሚሰማዎት የምሥጋና መዝሙርም ባላቸው መኖር በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ማሳያ ነው፡፡ አብረው ለዓመታት የኖሩ በመሆናቸው እርስ በርስ ይተዋወቃሉ፡፡ አንዱ የአንዱን ስም እያቆላመጠ ይጠራል፡፡ ባላቸው ይረዳዳሉ፡፡ ብዙ የሚያማርሩት ያለም አይመስልም፡፡ በነገሮች ተማሮ ከማልቀስ ይልቅ ቀልድ ይቀናቸዋል፡፡ ስለ ኑሯቸው አለመመቸት ሲያወሩም በቀልድ እያዋዙ ነው፡፡

ተወልዳ ያደገችው በዚሁ መንደር ነው፡፡ ገባይነሽ ለማ 22 ዓመቷ ሲሆን፣ ትዳር ይዛ አንድ ልጅ ወልዳለች፡፡ ሰው ቤት ተመላልሳ በልብስ አጣቢነት ትሠራለች፡፡ የሥራ ሰዓቷ እስኪደርስ ገና መራመድ ያልጀመረ ህፃን ልጇን ታቅፋ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ታወራለች ትስቃለች፡፡ ልብስ አጥባ በወር እስከ 1000 ብር ታገኛለች፡፡ የምናገኘው ለመኖር በቂ ባይሆንም ነገ የተሻለ ነገር እስኪመጣ ባለን ነገር ጥረት እናደርጋለን ትላለች፡፡ ምሽት ላይ ከየመንደሩ ቆሻሻና የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ እንደሚለቀቅ የምትነገረው ገባይነሽ  አብዛኛው ሰው በአስምና በጉንፋን እንደሚሰቃይ ትናገራለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት የሚመራው የከተማ ጤና ልማት ማዕከል አማካይነት በተዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም ነበር አዋሬን መጎብኘት የተቻለው፡፡ በከተሞች አካባቢ በተፋፈጉና በተጨናነቁ መንደሮች የሚከሰተው የጤና ቀውስ ምን ደረጃ እንደሚደርስ ለመገናኛ ብዙኃን ለማሳየት በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም አፍንጮ ሰፈር ልዩ ስሙ ኮሪያ በመባል የሚታወቀውን መንደርም መጎብኘት ተችሏል፡፡

 ከኮሪያ ዘማቾች ፓርክ ፊት ለፊት መንገዱን ተሻግሮ የሚገኘው መንደሩ፣ የአዋሬን ያህል ባይሆንም የተጨናነቀ ነው፡፡ መንደሩ ዳገታማ በሆነ ቦታ ከመገኘቱ  ባሻገር መውጫና መግቢያው እጅግ ጠባብ ነው፡፡ የእሳት አደጋና ሌላም ችግር ቢያጋጥም በቀላሉ ለመወጣት ከባድና ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የተጨናነቁ መንደሮች በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በትልቅነታቸው በሚታወቁት በመራካቶና በሾላ የገበያ ቦታዎች ከዚህ የባሱ የተጨናነቁ መንደሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡

በእንዚህ ቦታዎች በተለያዩ ጊዜያት የእሳት አደጋ ተነስቶ በሚሊኖች ብር የሚገመቱ የሚቆጠር ንብረቶች ወድመዋል፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች የድንገተኛና የእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን በፍጥነት አለመድረሱን ዜጎች ሲያማርሩ ባለስልጣኑ ደግሞ እንዲህ ባሉ ቦታዎች ፈጥኖ ለመድረስ አስቸጋሪ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ በመግለፅ ራሱን ሲከላከል ይሰማል፡፡

ቤቶቹ የሚሰሩት በቀላሉ በእሳት ሊቀጣጠሉ በሚችሉ ነግሮች መሆኑም ለአደጋው ያላቸው ተጋላጭነት እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ በዚህ አመት ከደረሱት የእሳት አደጋዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆነው የቤት ቃጠሎ ሲሆን፣ አብዛናዎቹ አደጋዎች የደረሱት በእነዚህ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑና በተጨናነቁ መንደሮች ነው፡፡ ከፅዳትና ከቆሻሻ አወጋገድ ችግር ጋር በተያያዘ እንዲህ ያሉት መንደሮች ለተለያዩ ተላላፊና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው፡፡ የመተንፈሻ አካል ችግርና እንደ አተት ያሉ ወረርሽኖች በቀላሉ እንዲዛመቱም መኖሪያዎቹ አመቺ ናቸው፡፡ በከተማዋ የሚገኙት አባዛኛዎቹ ደሳሳ መንደሮች በመልሶ ማልማት ተነስተዋል፡፡ እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈባቸውም አሉ፡፡

20 ሚሊዮን ወይም 19.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከተማ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ለተሻለ ኑሮና የሥራ ዕድል ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ፍልሰትና በከተሞች መስፋፋት ምክንያት በከተማ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. 2050፣ 38 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ነዋሪነቱ በከተማ እንደሚሆን ተተንብዮዋል፡፡