Skip to main content
x

መንግሥት ለአንድ መቶ ሺሕ ስደተኞች የሥራ ዕድል ሊሰጥ ነው

  • አሥር ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት ይከፋፈላል  
  • የዓለም ባንክ ለመተባበር ያለውን ፍላጎትና ሥጋቶቹን ገልጿል

መንግሥት 100 ሺሕ ለሚሆኑ በኢትዮጵያ ለተጠለሉ ስደተኞች በአገር ውስጥ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ዕድል ለመስጠት ማቀዱን፣ ከዓለም ባንክ የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡

የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከሳምንት በፊት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያፀደቀው የባንኩና የኢትዮጵያ የቀጣይ አምስት ዓመታት የግንኙነት ማዕቀፍ ነው ይህንን የመንግሥት ዕቅድ የገለጸው፡፡

በኢትዮጵያ 800 ሺሕ የሚሆኑ የጎረቤት አገሮች ስደተኞች በተለያዩ የአገሪቱ የድንበር አካባቢዎች በተከለሉ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ፣ በሰነዱ ያካተተው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

እነዚህ ስደተኞች የተወሰነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እንዲያገኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞውንም ቢሆን የፈቀደ እንደነበር በማስታወስ፣ በቀጣይ ግን እነዚህ ስደተኞች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማግኘት እንዲችሉ ዕቅድ መነደፉን ይገልጻል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘጠኝ ነጥቦችን የያዘ ዕቅዳቸውን እንዳቀረቡ የዓለም ባንክ ሰነድ የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አሥር በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ቀስ በቀስ ከካምፕ ወጥተው እንዲኖሩ ማድረግ፣ እስከ 100 ሺሕ ስደተኞችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቀጠሩ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሥር ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት በማቅረብ በእርሻ እንዲተዳደሩ ማድረግ፣ እስከ 213 ሺሕ ለሚደርሱ ስደተኛ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል መስጠት፣ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩት ሕጋዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የባንክና የመንጃ ፈቃድ እንዲሁም የልደት ሠርተፊኬት እንዲኖራቸው ማድረግም የዕቅዱ አካል ነው፡፡ የዓለም ባንክ ሰነድ ይህንን የኢትዮጵያ ዕቅድ አዲስ ምዕራፍ ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ቢሆን ለስደተኞች እጇን በመዘርጋትና በማስጠለል ታምታ አታውቅም ሲል ያወድሳታል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 800 ሺሕ የሚሆኑ ስደተኞች መካከል 350 ሺሕ ያህሉ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ሸሽተው የፈለሱና በጋምቤላ የስደተኛ ማቆያ ጣቢያዎች የተጠለሉ ናቸው፡፡

በጋምቤላ የሚገኙት የእነዚህ ስደተኞች ብዛት ከአጠቃላዩ የጋምቤላ ሕዝብ እንደሚበልጥ የዓለም ባንክ ሰነድ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል 250 ሺሕ የሚሆኑት ስደተኞች በተለያዩ ጊዜያት ከሶማሊያ ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው፡፡ ከኤርትራ ደግሞ 150 ሺሕ ስደተኞች በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ስደተኞች ግፋ ቢል ለአንድ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ ቆይተው ወደ አውሮፓ አገሮች እንደሚሰደዱ ይገልጻል፡፡

ቢሆንም የሚተኩ ስደተኞች በመኖራቸው ሳቢያ 150 ሺሕ የሚሆኑ ኤርትራውያን በትግራይ ክልል በተከለሉ ካምፖች፣ የተወሰኑት ደግሞ በመቐለና በአዲስ አበባ ከካምፖች ውጪ እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡

የተቀሩት ከ50 ሺሕ በላይ ከየመንና ከሱዳን የመጡ ስደተኞች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥትን ዕቅድ ያደነቀ ሲሆን፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ሥጋቶቹንም አልሸሸገም፡፡ ከእነዚህም መካከል በአገር ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ፖለቲካዊ ተቀባይነት አንዱ ነው፡፡ በተለይ የደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ ስደተኞች ከሌላው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር ተዋህደው የመኖር ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ይህ ዕቅድ ለኤርትራውያን ስደተኞች የበለጠ ሊሠራ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ ሕዝቦች ታሪካዊ የሆነ መልካም ግንኙነት ያላቸው በመሆኑና አሁንም ከካምፕ ውጪ እንደሚኖሩ በማሳያነት ጠቅሷል፡፡

ሌላው ሥጋት የክልል አስተዳደሮች ምን ያህል ዕቅዱን ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉታል የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ስደተኞችን በኢንዱስትሪ ዞኖች የመቅጠር ዕቅድ ስለመኖሩ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

እሑድ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመረቀው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለዚሁ ተግባር የታጨ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ በተመረቀበት ወቅትም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለትግራይ ነዋሪዎች ብቻ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ማለት እንዳልሆነ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የዓለም ባንክ የገለጸውን ሥጋት አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ የተጠየቀው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዝርዝር መረጃ እንደሌለው ገልጿል፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተንታኝ በበኩላቸው፣ ዕቅዱ በተለይ የኤርትራ መንግሥትን ከኤርትራውያን ለመነጠልና ብቻውን ለማስቀረት የሚሠራ አማራጭ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ እየተሰደዱ ያሉ ኤርትራውያንን በኢትዮጵያ ለማቆየት ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ተግባሯ የምታገኘው ዕርዳታና ብድርም መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡