Skip to main content
x

መንግሥት ለአክሰስ ሪል ስቴት ጊዜያዊ የሞግዚት አስተዳደር ያቋቁምለት

የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ያለበትን የዲሬክተሮች ቦርድ አወቃቀርና የፋይናንስ ማኔጅመንት ችግር አስቀድመው በመገንዘብ ኩባንያውን በማፍረስ ወይም በመውረስ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከውስጥና ከውጪ በተሰባሰቡ የጥበቃ ድርጅትና ባለቤት፣ የግለሰብ ቤት ገዥ ወኪሎች፣ የምስለ ዳይሬክተሮች ቦርድ (በምርጫ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተሰየሙ ቤት ገዥነትና አክሲዮን ባለድርሻነትን አጣምረው የያዙ)፣ እንዲሁም ከበስተጀርባ የቤት ገዥውን ስሜት በማስመሰል ፕሮፖዛል በሚያዘጋጁ ሁለት የሕግ ባለሙያዎች የተጠለፈ ኩባንያ ነው፡፡

ቤት ገዥው ለቤት መግዣ የከፈለውን ገንዘብ ወደ አክሲዮን መግዣ በማዛወር ድርጅቱ በበላይነት ለመጠቅለል፣ የቤት ገዥ ፍላጎት በማስመሰል ለመንግሥት የሚቀርብ ፕሮፖዛል በማዘጋጀት፣ አንድ ማኅበር አቋቁመን መሬት መረከብና በቤት ገዥው ተጨማሪ ክፍያ በባንክ ብድር እንሠራዋለን በማለት፣ ማኔጅመንቱ፣ የቤት ገዥ ወኪል ዓብይ ኮሚቴና ምስለ ቦርዱ በየፊናቸው በጋራና በተናጠል በአልሚ ባለሀብቶች ጋር ለመገናኘትና ለመደራደር ያደርጉት የነበረው እሽቅድምድም የቤት ገዥ ያዋጣውን የብር 5,000 (አምስት ሺሕ ብር) በድምሩ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ መዋጮ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለአክሰስ ሪል ስቴት በብድር ተሰጠ በማለት በእጅ አዙር በደመወዝ፣ በአበል፣ ለነዳጅ፣ ለሞባይል ስልክና ለጥበቃ ድርጅት እየተከፈለ ለጠለፋው ተግባር እንደዋለ፣ ከዚህ ቀደም ከኩባንያው ጋር ኮንትራት ገብተው ያላግባብ ገንዘብ የወሰዱ አንዳንድ ግለሰቦችና ኮንትራክተሮች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ድርጅቱን በማፍረስ ማዳፈን በመፈለጋቸው የተነሳ ይኼንን የመሳሰሉ በግርግር ያላግባብ በመበልጸግ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ቡድን የተጠለፈ ድርጅት ነው፡፡

ንጹሐኑ ቤት ገዥ የሚፈልገው ላቡን ብቻ ስለሆነ ቅድሚያ ተሰጥቶት ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በውላችን መሠረት ነገ ሳይሆን ዛሬ ቤቱ ተሠርቶለት ቁልፍ መረከብ ብቻ ስለሆነ ለዜጎቹ የቆመው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥትን የምንለምነው፡-

  1.  ለአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ የጊዜያዊ የሞግዚት አስተዳደር የዲሬክተሮች   ቦርድ እንዲሰየምለት ነው፡፡
  2. ይህ የሞግዚት አስተዳደር ቦርድ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ገለልተኛ ማኔጅመንት እንዲያዋቅር ወይም እንዲቀጥር ይደረግ፡፡
  3. የኩባንያው ሕጋዊ ባለቤቶች ባላቸው ከፍተኛ የአክዮን ድርሻ መጠን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ፕሮፖዛላቸውን ለሞግዚት ቦርዱ በማቅረብና በማስፈጸም የሞግዚት ቦርዱ አማካሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡
  4. የኩባንያው ባለቤቶች በፍጥነት ሊያለሙ የሚችሉ የውጭ ባለሀብቶችን ከጊዜያዊ አስተዳደር ቦርዱ ጋር በማገናኘት፣ ቤት ገዥው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁልፉን እንዲረከብ ያመቻቻሉ፡፡
  5. የቤት ገዥ ኮሚቴ በአዲስ መልክ በየሳይቱ በቤት ገዥዎች አባላት ብቻ በማቋቋም፣ እንደየሳይታቸው ባህርይ ከሞግዚት አስተዳደር ቦርዱ እንዲሁም ከአማካሪ ባለድርሻ አካላት ጋር እስከ ፕላን ማሻሻል ድረስ መደራደር የሚችል ኮሚቴ ማቋቋም ይገባል፡፡
  6. የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ውስጥ በመጣስ ያልተገባ ውል በመፈራረም የቤት ገዥውን መዋጮና የድርጅቱን ተመላሽ ገንዘብ በማባከን፣ የድርጅቱን ንብረት በመሸጥ እጃቸውን ያስገቡ በዚሁ የሞግዚት አስተደደር ቦርድ አቅራቢነት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
  7. መንግሥት የወሰደውን ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት የክረምቱን ወራት ለዝግጅት በመመደብ በመጪው አዲስ ዓመት ግንባታ ተጀምሮ የምናይበትና ሁላችንም የበኩላችንን የሥራ ድርሻ የምንወጣበት ዓመት እንዲመቻችልን ከወዲሁ ጥልቅ ምኞታችንን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

(በስማቸው ቤት የገዙ የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ደንበኞች)

***

ልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሊቆምላቸው ይገባል!

የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ ስለሆኑት ልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ ሰሞኑን ዛሚ 90.7 ኤፍኤም በተባለው ሬዲዮ ጣቢያ የተገለጸውን አዳምጫለሁ፡፡ ልዕልት ፀሐይ በወቅቱ ለነበረው ባህልና ወግ ራሳቸውን ሳያስገዙ፣ የንጉሥ ልጅ በመሆናቸው ሊሰጣቸው የሚገባውን ክብር በመተው፣ ለሰው ልጆች ጤና የሚጨነቀውን የነርስነት ሙያ መርጠው በተግባር የተረጎሙ ከመሆኑም ሌላ፣ የሕክምና ተቋማትን በማቋቋምና የሴቶች ማኅበራትን በመመስረት ታላቅነታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ሰው እንደነበሩ ከቀረበው ዘገባ ተገንዝቤያለሁ፡፡

ይህን መሰሉን ለሕዝብ በጎ ለሠሩ ሰው የስማቸው መጠሪያ ይሆን ዘንድ በአድናቂዎቻቸው የገንዘብ መዋጮ የተሠራውን ‹‹ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል›› እየጠባለ ይጠራ የነበረውን ሆስፒታል በደርግ መንግሥት የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተብሎ ስሙ መቀየሩ፣ እንደ ልዕልት ፀሐይ ያሉ የፊውዳል ካባቸውን አውልቀው ጥለው የሕዝባዊ ወገናዊነትን በተግባር የተላበሱ ሰዎችን ሞራል የሚጎዳ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል፡፡

ስለሆነም ልዕልት ፀሐይ ለስማቸው መታሰቢያ የሚሆናቸው የጤና ተቋም ሊቋቋምላቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ሕዝብና መንግሥት በተለይም የሴቶች ማኅበራትና የነርሶች ማኅበር ሊተጉበት ያስፈልጋል፡፡

ዛሚ 90.7 ኤፍኤም ሬዲዮ የሰኔን ወር 2009 ልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ እንዲሆን ማድረጉም የሚያስመሰግነው ነው፡፡

(ይገለጥ እውነቱ፣ ከአዲስ አበባ)

***

የአማራ ክልል የወጪ ቅነሳ ለሌላውም አርዓያ ይሆናል

ከዚህ በታች የቀረበውን አስተያየቴን በሪፖርተር ጋዜጣ የአስተያየት ዓምድ እንዲሰፍርልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

 በቅርቡ በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ፕሮግራም የክልሉ አንድ በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ባለሥልጣን በሰጡት መግለጫ ከዚህ ቀደም በክልሉ ውስጥ ስብሰባዎች ሲከናወኑ ለኮፍያ፣ ለቲሸርትና ለአንገት ሻርፕ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በ2010 በጀት ዓመት ግን ይኼ ወጪ እንደሚቋረጥ መግለጻቸው ክልሉ የወሰደው ዕርምጃ የመንግሥትን ወጪ አግባብ ባለው መንገድና ቁጠባን ባህል በማድረግ ለመጠቀም የተወሰነ ውሳኔ መረዳት ይቻላል፡፡ ይኼ ውሳኔ ቀደም ባሉት ዓመታት ተወስኖ ቢሆን ኖሮ ግን ለዚህ ጉዳይ ያውም ለአንድ ቀን ብቻ ለሚያገለግል ጉዳይ የወጣው ወጪ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተላላፍ ፋይዳ ላለው በርካታ ትምህርት ቤቶችን ወይም የጤና ኬላዎችን መገንባት በተሻለ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን የአማራ ክልል ከሌሎች ክልሎች ቀድሞ የወሰደው ዕርምጃ ሊያስመሰግነው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ውሳኔ ነውና ብራቮ የአማራ ክልል እላለሁ፡፡

(ማቴዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ)

***

በ40/60 ቤቶች በቃሉ ያልተገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም መሠረት ከነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባዘጋጀው ዝርዝር የቁጠባ ውልና የሒሳብ አከፋፈል መመርያ መሠረት መረጃዎችን ሞልተን ባቀረብነው ውል መሠረት ሒሳብ መክፈታችን ይታወቃል፡፡ የንግድ ባንኩም በበተነው በራሪ ወረቀት መሠረት አንብበን ተረድተን

  1. ስለመኖሪያ ቤቶቹ ዓይነት፣
  2. ስለማስተላለፊያ ዋጋና የቁጠባ መጠን ግምት፣
  3. አማካይ የተጣራ ስፋታቸው ስለ ባለአንድ መኝታ ቤት፣ ባለሁለትና ባለሦስት ተብሎ በግልጽ ተዘርዝሮ ተቀምጦ ነበር፡፡

ከእነ ማስተላለፊያ ዋጋቸው ጭምር ስለክልከላ፣ ስለቀጣት ጭምር በተቀመጠው የውል ስምምነት መሠረት  እኛም ንግድ ባንክን በሙሉ ልባችን አምነን፤ በተለይ ለእኔ ለብዙ ዓመታት በግለሰብ ቤት ኪራይ ለተንገፈገፍኩኝ፣ ከቤት ኪራይ በቶሎ ለመላቀቅ በሚል እሳቤ ከባለሁለት መኝታ ቤት ይልቅ ባለአንድ መኝታ ቤት ብዙ ተመዝጋቢ አይኖረውም በሚል ስሌት ዕድሉ ይደርሰኛል ብዬ በመጓጓት ስጠብቅ ቆይቻለሁ፡፡ ንግድ ባንክና ተባባሪዎቹ ግን ያልተሰማና ያልተገመተ፣ በፕሮግራሙ ያልተገለጸ፣ ቁጠባም ያልተከፈተለት  አስገራሚው ነገር የባለ አንዱን መኝታ ቤት ወደ አራት መኝታ ቤት ቀይረውት መገኘታቸው ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ የሚያሳየው ኅብረተሰቡ አመኔታ እንዲያጣባቸው ያደርጋቸዋል ሌላው በ40/60 መርሐ ግብር መሠረት 100 በመቶ ተቀማጭ ያደረጉ ቅድሚያ ያገኛሉ ይላል እንጂ በፆታ፣ በመንግሥት ሠራተኛነት፣ በዲያስፖራ፣ በተሹያሚነት በሎ ያስቀመጠው ነገር የለም አሁን ታዲያ የምን ክህደት ነው እነኚህ መስፈርቶች የመጡት ትልቁ የኔ ጥያቄ ለምንድነው ባለ አራት መኝታ ቤቶችስ ሊገነቡ የቻሉት ፕሮግራሙ የሚለው የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ነው፡፡

ባለ አራት መኝታ ቤቶች ለማን ታስበው ነው የተሠሩት? ቤት ለቸገረው ወይስ ሌላ ምስጢር ነበራቸው? አላውቅም፡፡ ምክንያቱም የሰንጋ ተራና ክራውን የ40/60 ቤቶች ብዙ ጥያቄዎች ሲነሳባቸው ነበር፡፡ ኅብረተሰቡም ብዙ ጥርጣሬ ነበረው፡፡ ይኼው አሁን ባለ አራት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች ሊገዟቸው ይችላሉ ካልሆነም መንግሥት የሚያደርገውን ያደርጋል የሚል ምላሽ ሲሰጥ ሰምተናል፡፡ እኛ በቆጠብነው ያውም መቶ በመቶ በከፈልንበት ቤት የበላይት አቅሙን ተጠቅ ሊወስድብን መነሳቱ ግን ያሳዝናል፡፡

(ከበደ ዓለሙ፣ ከአዲስ አበባ)