Skip to main content
x

መንግሥት ሕግ እየጣሰ ሕግ የማስከበር ወኔ ይኖረዋልን?

በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት እየተደረጉ ካሉ የሚያሳዝኑ፣ የሚያሳፍሩና የሚያስገርሙ በርካታ ነገሮች ውስጥ ሰሞነኛ የሆኑ ሁለት ጉዳዮች ላይ ያለኝን ቅሬታና ጥያቄ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ አንደኛው የ40/60 የኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ሥርዓት መቀየሩን ይመለከታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቅርቡ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስላደረገው ምሕረት ይሆናል፡፡

ከኮንዶሚኒየም ዕጣ አወጣጥ ስንጀምር፣ ለመሆኑ ኅብረተሰቡ 40 በመቶ  ሲቆጥብ 60 በመቶው በመንግሥት በሚሸፈን ወጪ የቤት ዕጣ ውስጥ ግቡ በማለት ውል ከተዋዋለ፣ ከታሰረ፣ ፊርማ ከተፈራረመ፣ ከሕዝቡም ገንዘብ ከሰበሰበና በገንዘቡም ቤቱን ሠርቶ ከሠራበት በኋላ፣ ለውል ተቀባይ የሠራውን ቤት ሳያስረክብና የውል ለውጥ ማድረጉን ሳያሳውቅ ማሻሻል ወይም በሌላ መተካት ይችላል ወይ? ውል ማፋረስ አይሆንም ወይ? አካሔዱስ ሕጋዊ ነው ወይ? በማለት ጥያቄ ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሰማነው የመንግሥት ኃላፊዎች ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ የተለያየ ምላሽ ሰጥጠዋል፡፡ ገሚሱ መሉ ለሙሉ የከፈሉ ሰዎች ገንዘባቸውን ሌላ ነገር ላይ በማዋል ትርፍ ማግኘት ሲችሉ፣ ለ40/60 ቤት ፕሮግራም በማዋላቸው ምክንያት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው አድርገናል ሲሉ ሌሎቹ ኃላፊዎች ደግሞ ኅብረተሰቡ ቅድሚያ ለማግኘት የበለጠ የመክፈል ፉክክር ውስጥ ስለሚገባ ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያስችላል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ ቤቶችን እንድንገነባ አቅም ይሰጠናል፡፡ ለዚህ ነው አሠራሩን ያሻሻልነው፤›› በማለት ሲናገሩ አድምጠናል፡፡

ምክንያታቸው አጥጋቢ ሆነም አልሆነ፣ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ግን አንድ አካል ከሌላው ተዋዋይ ዕውቅና ውጪ፣ ከተዋዋሉበት አግባብ በማፈንገጥ ያሻውን ምክንያት ቢደረድር እንኳ ያለምንም ቅጣት ውል ማፍረስ ይችለዋልን?

ለመሆኑ አንድ የግል ሪል ስቴት ከደንበኞቹ ጋር ከተፈራረመና በገንዘባቸው ቤት ከሠራ በኋላ የውል አቅጣጫውን መቀየር ይችላልን? ለመንግሥትና ለግል ተቋማት ሕጉ ይለያያልን? መንግሥት እንደ መንግሥት ከሕዝብ ጋር የገባውን ውል ላለመተግብሩ ምክንያት እየደረደረ የሚያፈርስ ከሆነ፣ ሕዝቡስ ወደፊት ምን ይሁነኝ ብሎ መንግሥትን ያምናል?

መንግሥት ለግለሰቦች አስባለሁ ባለበት አንደበቱ ውልና ሕግን በአደባባይ በመጣስ ይኼን ካደረገ፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮችና ኃላፊዎች፣ ለምሳሌ አንዱ የነሸጣቸው የመሬት አስተዳደር ኃላፊ ‹‹ጎዳና ላይ ሦስት ልጆቿን ይዛ ስትሰቃይ በማየቴ ስላሳዘነችኝ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነቷም መሬት ማግኘት እንዳለባት ስላመንኩኝ፣›› የሚል ምክንያት አቅርቦ ከሕግ ውጪ መሬት መስጠት ይቻላል ማለት አይደለም ወይ?

 ከመንግሥት አድራጎት ተነስተን፣ የባንክ አመራሮች ተሰብስበው ለመሰላቸው ዜጋ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸውና እንደ ኢትዮጵያዊነታችን በማሰብ ገንዘብ እንዲሰጠው ወስነናል ቢሉ ማን አለብኝነት ሊባል ነው? ‹‹ገንዘባቸውን ሌላ ቦታ ማዋል ሲችሉ ሙሉ በመሉ በመክፈላቸው  ቤቶቹን በቅድሚያ እንሰጣቸዋለን›› እንዲሉ የሚፈቅድላቸው የትኛው ሕግ ነው?

ይህ አካሄድ ለእኔ እንደሚመስለኝ ሙሉ በመሉ በከፈሉ ሰዎች ስም ቤቶቹን ለሚፈልጓቸውና አስቀድመው ላዘጋጇቸው ሰዎች ለመስጠት ተፈልጎ የተዘጋጀ ዘዴ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ለከፈሉት ሰዎች ሌላ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ማስተናገድ ይቻል ነበር፡፡ ደግሞስ የቤት ግንባው አቅሙ ለማይችለውና ለመካከለኛው ሰው ነው ተብሎ ሳለ ምነው ታዲያ ቤቶቹ ተገንብተው ሲያልቁ ይህ ቃል ኪዳን ተዘነጋሳ?

ከደመወዙ፣ ከሚበላውና ከኑሮው ተፍጨርጭሮ በመቆጠብ ቆጥቦ መከራውን አይቶ 40 በመቶ ላወጣው ሰው ሊታሰብለትና ሊታዘንለት በተገባ ነበር፡፡ መንግሥት ሁሉን በእኩል የሚያይበት ዓይኑ እዚህ ላይ የተንሿረረ ይመስለኛል፡፡

ሌላኛው የሚገርመውና የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በመጠቀም ፈቃድ አውጥተው በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ላላቸው 136 ተቋራጮች ምሕረት ማድረጉ ነው፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በመጠቀም መንግሥትን ማታለልና ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል አይደለም ወይ? ታዲያ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ወንጀል ለሠሩ ምሕረት የማድረግ ሥልጣን ማን ይሆን ያጎናጸፈው? ሲደረግ የምናውቀው በሕግ ተጠይቀው ከተፈረደባቸው በኋላ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ይቅርታ ሲያደርግ እንጂ አንድ ሚኒስቴር ለወንጀለኛ ይቅርታ ማድረጉ አዲስ አሠራር ይመስለኛል፡፡

ይኼን ስሰማ አንድ ጓደኛዬ ትዝ አለኝ፡፡ ካርታ የሌለው መሬት ለገጣፎ አካባቢ ሲገዛ፣ ካርታ ካልፀደቀለት እንደሚከስር ልመክረው ስሞክር እንዲህ ነበር ያለኝ፤ ‹‹እኔ መሬቱን የገዛሁበት አካባቢ ሌሎች ሰዎች በብዛት ስለገዙ፣ እነሱ የወጣውን ሕግ ይቅርና አዲስ ሕግ አስወጥተው የሚያፀድቁና ካርታ የሚያሰጡ ናቸው፡፡ እነ እንቶኔ ናቸው፡፡ ለዚያ ነው ከእነሱ ጎን የገዛሁት፡፡ ይልቁንስ አትሞኝ አንተም ብትገዛ ይሻልሃል፡፡ መጽደቁ እንደሆነ አይቀርም፡፡››

እንግዲህ ሕግ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በባለሥልጣኖችና የሕግ ወሰናቸውን እንኳ በማያውቁ ኃላፊዎች እንደፈለገ እየተጣሰ፣ እየተጣጠመ፣ እየተሻሻለ፣ ችላ እየተባለ አገርን እንዴት ነው በቅጡ ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ የሚቻለው? መንግሥትና ባለሥልጣናት የገዛ ሕጋቸውን ካላከበሩትና እንደሚገባው ካልተገበሩት ማን ነው የሚያከብረው?

(ጌድዮን ኤልያስ፣ ከቦሌ)

***

ለጋራ ብልጽግና የፀረ ሙስና ትግሉ ይፋፋም!

ሰሞኑን መንግሥት በሙስና በጠረጠራቸው ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ላይ እየወሰደ ያለው የእሥራት ዘመቻ፣ የኅብረተሰቡ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ እርምጃው በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ መደናገጥና ሥጋትን ፈጥሯል፡፡ በሙስኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች የተጎዱ ዜጎች፣ የፍትሕ ተስፋ ጭሮባቸዋል፡፡ ነገር ግን ዘመቻው ሙስናን በዘላቂነት የመቀነስ ብቃቱ እስከ የት ድረስ ይዘልቃል? የሚለውን ጥያቄ ጎልቶ ያሰማል፡፡

እንደሚታወቀው ሙስና ያለ ድካምና ጥረት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የማግኘት ሒደት ነው፡፡ የሌሎች የሥራ ፍሬና ውጤትን በአቋራጭ መቀማትና መዝረፍ ነው፡፡ በአካልና በአዕምሮ ታግለው፣ ሠርተውና ደክመው ያፈሩትን ሀብት በቀጥታና በተዘዋዋሪ፣ በግልጽና በስውር የሠራተኛውን ሀብት መዝረፍ ነው፡፡ ይኼ ድርጊት በተግባርና በአመለካከት ውስጥ ሲነግስ የሥራ ባህል፣ ሠርቶ የመኖር ዕምነትና አመለካከትን ቀስ በቀስ ይሸረሸራል፡፡ ዋልኔነት፣ ግድየለሽነት፣ ስንፍና እና ሥራ መጥላትን ያመጣል፡፡ ሥራ የመሠረታዊ ፍላጎቶችና የሌሎችም ፍላጎቶች ማሟያ ወሳኝ መሠረት መሆኑ እየተረሳ ይሄዳል፡፡ በዚህም የተነሳ በሥራ የሚፈጠሩ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ማለትም ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስና የቅንጦት ቁሳቁሶች አቅርቦት ያጥራል፡፡ ይኼ ሲዛመት የኅብረተሰብ ቀውስ ያስከትላል፡፡

የሙስና አደገኛነት የመኖር መሠረት የሆነውን የሥራና ሠርቶ የማደርን ዕምነት፣ አመለካከትና አስተሳሰብ የሚቃረን መሆኑ ነው፡፡ ሰው ራሱን በሕይወት ለማቆየት የግድ መሥራት አለበት፡፡ ሥራ ልማትን፣ ዕድገትንና ብልጽግናን ያስገኛል፡፡ በዚህም የተረጋጋ ሰላምና ደስታ የሞላበት ኑሮን ይፈጥራል፡፡ ሥራን የሚያዳክም ሙስናን የሚያስፋፋ ሁኔታ ሲጠናከር ግን አገርና ሕዝብ ለመከራና ለስቃይ ይጋለጣሉ፡፡ በመጨረሻም አገራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡

አገሮች እንደ ዕድገታቸው ደረጃ ሙስናን ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የመቆጣጠሪያና የመከላከያ ሕጎች በማውጣትና በተግባር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተቋማት መሥርተዋል፡፡ ሆኖም ሙስና ግን በመቀነስ ፈንታ እየተባባሰ መሄዱን ቀጥሏል፡፡ ይኼንን አደገኛ የሕዝብ ጠላት በዘላቂነት ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

የፀረ ሙስና የመፍትሔ ሐሳቦች

ሙስና በአንድ ወቅት የእሥር ዘመቻ አይደርቅም፡፡ ሙስና የጥቅም ጉዳይ በመሆኑ፣ ከራስ ወዳድነት ጋር በቅርበት የተያያዘ ነው፡፡ ሒደቱም ውስብስብ ነው፡፡ ስለሆነም ሙስናን ለመከላከል፣ ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት በዕውቀት የተመሠረተ የተጠናከረና በጠራ ዕምነት ላይ የተመሠረተ የትግል አቅጣጫን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

በዚሁ መሠረት ሙስናን በኃላፊነት ለመከላከል፡-

  1.  የኅብረተሰቡን የፀረ ሙስና ግንዛቤ ማሳደግ፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ዕድሜና ባህልን ያገናዘበ ትምህርት በመስጠት የፀረ ሙስና መርህን በየክፍል ደረጃው ማስረጽ ይገባል፡፡ በዕለት ተዕለት ተግባራቸው በማዋል በዕምነትና በአመለካከታቸው ውስጥ እንዲዳብር የማድረግ ጥረት በመጀመርያ መምህራንን በፀረ ሙስና ዕምነት ማጥመቅ ይገባል፡፡ ተግባራቸውን መከታተልና መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡
  2.  የመንግሥትን ሥርዓት ከሙስና በፍጹም ነፃ ማድረግ፡፡ ሰዎች በችሎታቸው፣ በብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው ብቻ ተወዳድረው የሥራ መደብ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም እንዳያገኙ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት መዘርጋትና መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ማንም ሠራተኛ እንደብቃቱ፣ እንደ ችሎታውና እንዳስገኘው ውጤት እየተለካ ጥቅሙን ማሳደግ በሙስና ተግባር ሲያዝም ተገቢ ቅጣት መስጠቱም ለሙስና መፍትሔ ይሆናል፡፡ የሙሰኞችን የተሰወረ ሀብት በመውረስ ለሕዝብ ጥቅም ማዋልም ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
  3.  የመንግሥት ሀብት አስተዳዳርና ቁጥጥር በማጠናከር የማይንቀሳቀሱና የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ሀብቶችን በግልጽና በታወቀ መንገድ ብቻ ወጪ እንዲሆኑ በማድረግ ከግለሰብ ስሜትና ፈቃድ ማላቀቅ፣ በሥርዓት ብቻ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሕዝብ ሀብት አክብሮት መጠበቅ ይገባል፡፡

በመጨረሻም የፀረ ሙስና ትግል ለጋራ ብልጽግና ተገቢ አካሄድ በመሆኑ የሙሉ ኅብረተሰቡ ዕምነት ታክሎበት ተፈላጊው ውጤት እንዲያመጣ ለማድረግ ከፍተኛ ትግልና መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ከሚያመጣው ውጤት አኳያ ሲመዘን ትግሉና መስዋዕትነቱ ከባድ አይሆንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የጀመረውን የፀረ ሙስና ዘመቻ አጠናክሮ ሊገፋበት ይገባል፡፡ እርምጃው የአገር ዕድገትና ብልጽግና ብሎም የአገር ጉልበት የሚፈታተነውን ሙስና ከመስፋፋት ሊያስቆመው ይችላል፡፡ ይኼ ሲሆን ብቻ ነው ፀረ ሙስና ለጋራ ብልጽግና ፋይዳ የሚኖረው፡፡ አገርና ሕዝብም በተረጋጋና በሰላም የሚቀጥሉት በጋራ ጥቅም ነው፡፡

(ዳዳ ወልደመስቀል፣ ከአዲስ አበባ)