Skip to main content
x

መኖሪያ ቤት የማግኘት መብቴ ይከበርልኝ!

መንግሥት በ2005 ዓ.ም. ባወጣውና ልዩ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም በማለት፣ ሙሉ ክፍያ  ለከፈሉ ቅድሚያ በማግኘት ተጠቃሚ ስለሚሆኑበትና ስለሌሎችም ዓላማዎቹ በወቅቱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ይባል ለነበረው  መሥሪያ ቤት ሚኒስትር የነበሩትና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት  ስለፕሮግራሙ በሰጡት መግለጫና በተደረገው ቅስቀሳ ተነሳስቼ፣ እምነትም አድሮብኝ ተመዝግቤ ነበር፡፡ 

 ካለብኝ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር የተነሳ ከነሐሴ 6 ቀን እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የ40/60 መኖሪያ ቤቶች የምዝገባ ፕሮግራም መሠረት በነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ያውም፣ ከምሳ ሰዓት በፊት ለሁለት መኝታ ክፍል ቤት 250,000 ብር (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ) ወዲያውኑ ከፍዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውል አስሬ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ለመንግሥት ያስገባሁት ገንዘብ በባንኩ የ46 ወራት ጊዜ አስቆጥሯል፡፡

በወቅቱ በሠንጋ ተራና በክራውን አካባቢ ግንባታቸው የተጀመረው የ40/60 መኖሪያ ቤቶች የተባለላቸውን እንተወውና በእነዚህ ሳይቶች ለመኖሪያ የተዘጋጁት ቤቶች ብዛት 972 ሆኗል፡፡ እነዚህም ምዝገባው በተካሄደበት ወቅት ማለትም ከነሐሴ 6 እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስ መቶ በመቶ ከፍለው ለተመዘገቡ 2,200 ተመዝጋቢዎች በዕጣ ይተላለፋሉ ሲባል ነበር፡፡ በጣም በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለ11,000 ተመዝጋቢዎች ዕጣ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

በመሠረቱ ሙሉ በሙሉ የከፈሉ ቅድሚያ ያገኛሉ ተብሎ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት ቅስቀሳ ተነሳስተን ከችግር በቶሎ እንላቀቃለን በማለት እኔና መሰሎቼን ጨምሮ በመጀመርያው የምዝገባ ቀን እንዲሁም እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ መቶ በመቶ ከፍለን የተመዘገብነውን ቤት ፈላጊ ዜጎች ለመጥቀም ሳይሆን፣ ከነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ ቀስ እያሉ ሙሉ ክፍያ እንዲከፍሉ ጊዜው ተመቻችቶላቸው፣ የቤት ዕድሉ እንዳያመልጣቸው የተፈለጉ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ካልሆነ በቀር፣ በጉጉት ተሽቀዳድመን ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ በንግድ ባንክ ደጃፎች ተሰልፈን በብድር እየተንዘረዘርን የተመዘገብነው ገንዘብ ስለተረፈን አልነበረም፡፡ ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው ዜና እስከማምሻው ድረስ 400 ተመዝጋቢዎች ሙሉ ክፍያ ከፍለው እንደተመዘገቡ አሰምቶናል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በገባሁት ውል አንቀጽ 2 ሥር የደንበኛው መብትና ግዴታን በሚመለከተው የውሉ ተራ ቁጥር 6 ላይ፣ የቤት ድልድል ቅደም ተከተል በደንበኞች የቁጠባ መጠን ልክ፣ በምዝገባ ጊዜና በዕጣ ይሆናል ይላል፡፡ በዚህም መሠረት ለብድር ብቁ የሆኑና ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ቅድሚያ ዕድል ይኖራቸዋል ይላል፡፡

በዚህም መሠረት ተሠርቶ ያለቀው ቤት 972 መሆኑ እየታወቀ፣ የምዝገባ ጊዜውም እንደሚጤን በውል ውስጥ እያለ፣ እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. 2200 ተመዝጋቢዎች መቶ በመቶ ከፍለዋል እየተባለና የከፈሉት ገንዘብ ከ18 ወራት እስከ 46 ወራት በባንኩ ውስጥ እያለ ይኼን አነስተኛ ቤቶች ለ11,000 ተመዝጋቢ ዕጣ ማውጣት ለምን አስፈለገ ፍትሐዊነትስ ነው ወይ?

በመሆኑም የምጠይቀው ነገር ቢኖር፡

የዕጣ አወጣጡ ስለ 40/60 ቤቶች ፕሮግራም የተደረገው ቅስቀሳና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምዝገባ ወቅት በተበተነው ብሮሸርና ከንግድ ባንክ ጋር በተገባው ውል አንቀጽ 2 ተራ ቁጥር 6 መሠረት፣ የቤት ማስተላለፉ ሥርዓት ስላልተካሄደ ድረስ ቤት የማግኘት መብቴን ተነፍጌያለሁ በማለት ፍትሕ እንዲታይልኝ እጠይቃለሁ፡፡
በ2005 ዓ.ም. ባለ40/60 የቤት ፕሮግራም በተደረገው ቅስቀሳ መቶ በመቶ ሙሉ ክፍያ የከፈሉ ቅድሚያ ያገኛሉ በተባለው መሠረት ነሐሴ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ባለው የምዝገባ ፕሮግራም መቶ በመቶ የከፈሉት 2,200 ተመዝጋቢዎች ብቻ ለምን በዕጣው እንዲሳተፉ ያልተደረገበት ምክንያት ቢጣራልን፡፡
ለ972 ቤቶች በዕጣ እንዲወዳደሩ የተደረጉት 11,000 ተመዝጋቢዎች የምዝገባ ጊዜያቸው ቢመረመርና በእውነት ከቤቶቹ አነስተኛ ቁጥር የተነሳ ለዕጣ መቅረባቸው አግባብነት አለው ወይ?
ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ፕሮግራም ዕጣው ደረሳቸው የተባሉት ዕድለኞች በእውነት ከነሐሴ 6 ቀን እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ውስጥ መቶ በመቶ ከከፈሉት ጋር ሲነፃፀሩ አወጣጡ ፍትሐዊ ነው ሊያስብል ይችላል?
ስለዚህ ከላይ ባነሳሁት የመብት ጥያቄ ላይ ባንኩ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ እኔንም ሆነ ሌሎች እኔን መሰል በሕግ አግባብ ተመዝገበው ተጠቃሚ ያልሆኑ ሰዎች፣ የቤት ማግኘት መብታችንን እንዲያስከብርልን እማፀናለሁ፡፡

(ነገደ ወ/ሰማያት፣ ከአዲስ አበባ)

***

ግብር ከፋዩ ማን ነው?

ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ዓመታዊ የኪራይ ገቢ ግብር ለመክፈል በጠዋት ነበር በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በሚገኘው የገቢዎችና ቁምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ቢሮ የደረስኩት፡፡ ረዥሙን ሠልፍ ለማምለጥ ብዬ ነበር በጠዋት መውጣቴ፡፡ እንደፈራሁት ሳይሆን ቀርቶ፣ በጣት የምንቆጠር ግብር ከፋዬች ብቻ ነበርን የተገኘነው፡፡ እናም ሠራተኞች ገብተው ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ አብረን በነበርነው መካከል ጨዋታ ቢጤ ተጀመረ፡፡ አብረውኝ የነበሩት ሰው ከቀናት በፊት ያጋጠማቸውን ሲያወጉን ጊዜ በርዕሱ ያነሳሁትን ጥያቄ ራሴን ጠየቅሁት፡፡

ያጫወቱኝ ሰው ለሥራ ጉዳይ ወደ ዓለም ገና ከተማ ሄደው ነበር፡፡ ጊዜው ክረምት ስለነበር ድንገት ከጀመረው ዝናብ ለመጠለል በቅርብ ወዳገኙት ቤት ይገባሉ፡፡ ባህላዊ መጠጥ መሸጫ ቤት ነበር፡፡ የገቡት ለመጠጣት ባይሆንም ቀድመው ቦታ ከያዙት ጋር መቀላቀል ግድ ስለነበር የሚቀማምሱት አዘው ይቀመጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግድግዳው ላይ የተጻፈው ማስታወቂያ ቀልባቸውን የሳበው ‹‹ግብር ስለጨመረብን አንድ መለኪያ አረቄ አምስት ብር መሆኑን እናስታውቃለን፤›› ይላል ማስታወቂያው፡፡

እርግጥ ነው በቀን ገቢ ግመታው የተነሳ ነጋዴዎች ቀድሞ ሲከፍሉት በነበረው የግብር ተመን ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ለዚህም ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ከግብር ከፋዩ የሚቀርብለትን ቅሬታ ተቀብሎ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን መግለጹ እውነትም ጭማሪው መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ ግብር ለመንግሥት የሚከፈል ዕዳ ሳይሆን፣ ለአገር ልማትና ዕድገት የሚከፍል የዜግነት ግዴታ ነው፡፡ ለልማት የተያዙ ዕቅዶች የሚከናወኑት፣ መሠረት ልማቶች የሚስፋፉት እንዲሁም ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚውለው ወጪ በአብዛኛው የሚሸፈነው ከግብር በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ግብርን ወደን የምንከፍለው ነው፡፡

ታዲያ ጨመረም ቀነሰም ግብር በነጋዴው የገቢ መጠን ላይ ተመስርቶ የሚሰላ በመሆኑ፣ ለዋጋ ጭማሪ እንደምክንያትነት ሊያገለግል ይችላል ወይ? ከዚህ ጨዋታ በኋላ በገበያ ላይ ያሉትን ሸቀጦች ዋጋ ለመመልከት ስሞክር፣ ጭማሪው በመለኪያ አረቄ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሁሉም ሸቀጦች ላይ ተጭኖ አገኘሁት፡፡ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሐምሌ ወር የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት፣ በተለይም ከመሠረታዊ ፍጆታዎች አንፃር ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ይነግረናል ብዬ በማሰብ የዋጋውን ጉዳይ ልተወው፡፡ ኤጀንሲው ቢናገርም ባይናገር፣ ጭማሪው ግን በሸማቹ ጫንቃ ላይ ተጥሎ እኛም ተሸክመነው እንገኛለን፡፡

ግብር ከፋዩ ታዲ ማን ነው? ነዳጅ፣ ትራንስፖርት፣ ደመወዝ፣ የዶላር ምንዛሪ አሁንም ደግሞ ግብር ሲጨምር ደመወዝተኛው፣ በኪራይ የሚተዳደረውና ጡረተኛው ላይ ዋጋ ይጨመራል፡፡ ይኼንን ሸክም ለማቃለል መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሸማቾች መብትን አስጠብቃለሁ የሚለው መሥሪያ ቤትስ የሚለን ይተገብረው ይሆን?

ለማንኛውም መሸመታችን ይቀጥላል፡፡ ግብር መክፈላችንንም እንቀጥላለን፡፡ የሚታደገን እስከምንናገኝ ድረስ ግን በየሰበቡ እንቆስላለን፡፡

(ሽመልስ፤ ከአዲስ አበባ)