Skip to main content
x
መድን ድርጅቶች በሕይወት መድን ሽፋን ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል

መድን ድርጅቶች በሕይወት መድን ሽፋን ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል

የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ የአገልግሎት ሽፋኑም ከሚጠበቀው ይልቅ አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 17 ኩባንያዎች ዓመታዊ የትርፍ መጠንም አነስተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ዓመታዊ ትርፍ ከባንኮች ዓመታዊ ትርፍ ጋር ማነፃፀር ካስፈለገም፣ የመድን ኩባንያዎች አፈጻጸም አዝጋሚ ጉዞ እንደሚታይበት ያመላክታል፡፡ ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት፣ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ጉዞ በዋናነትም በኢንሹራንስ አገልግሎት ደላሎች ዙሪያ በቡና ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር አስተባባሪነት በተሳናደው መድረክ አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡   

መድን ኢንዱስትሪው ከሌሎች አገሮች አኳያ

ቡና ኢንሹራንስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የሚገኝበትን ደረጃ ለማመላከት፣ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ፋይዳ ምን ያህል እንደሆነ የሚጠቁሙ አኃዛዊ መረጃዎችና አስተያየቶች ተስተናግደዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳኛቸው መሓሪ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ዘርፍ ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማመላከት መንደርደሪያ ያደረጉት፣ ከወራት በፊት የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በተዘጋጀ ፕሮግራም ወቅት ተከስቶ እንደነበር የጠቀሱትን አጋጣሚ በማስታወስ ነው፡፡  

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዕድገት ሲጠቀስ በአብዛኛው ባንኮች ለኢኮኖሚው ዕድገት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ባወሳው መድረክ ላይ የመድን ድርጅቶች ድርሻ ሳይጠቀስ መታለፉን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፣ የፋይናንስ ተቋማት ሲጠቀሱ ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ተካተው ቢሆንም፣ የኩባንያዎቹ አስትዋጽኦ ኢምነት መሆኑ በየመድረኩ ሳይጠቀሱ እንዲታለፉ እያደረጋቸው መሆኑ የመድን ዘርፉን ተዋናዮች ከንክኗቸዋል፡፡ በመድን ኢንዱስትሪው ‹‹ምን የሚነገር ነገር ሠራችሁና ነው፤›› እንደሚባሉም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አባባል ኢንዱስትሪው ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ዝቅተኛ ግምት እንደሚሰጠው ያሳያል ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ የ0.5 በመቶ ድርሻ ብቻ መሆኑ ለዚህ አባባል ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሁን ባለበት ደረጃ ሲገመገም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ጠቅላላ ምርት አኳያ ያለው አስተዋጽኦ 0.5 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ይህ ምጣኔ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡ በምሳሌ ሲሳዩም፣ የሞሮኮ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ የሦስት በመቶ፣ የናይጄሪያ 0.6 በመቶ፣ የደቡብ አፍሪካ 15.4 በመቶ እንዲሁም የኬንያ 3.5 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ከዓረቦን ገቢ አንፃር የ2007 ዓ.ም. አኃዞችን መሠረት ያደረገው የሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በሞሮኮ የተመዘገው የኢንዱስትሪው ገቢ 3.18 ቢሊዮን ዶላር፣ በናይጄሪያ 1.8 ቢሊዮን፣ በደቡብ አፍሪካ 5.4 ቢሊዮን፣ በኬንያ 1.52 ቢሊዮን ዶላር ሲያስመዘግብ፣ በኢትዮጵያ ግን 219 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተመዝግቦበታል፡፡

‹‹ከዚህ መረጃ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የእኛ ኢንዱስትሪ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገንዘብ ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ እያንዳንዱ ባለድርሻ ማድረግ ስለሚጠበቅበት አስተዋጽኦ ማሰብ እንደሚጠቅበት አሳስበዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ የገበያ የንግድ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ባቀረቡት ጽሑፍ ኢንዱስትሪው የሚገኝበትን ደረጃ አመላክተዋል፡፡

ከሞተር የተዋደደው ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ

ዓምና 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሰበሰቡት ዓረቦን (ፕሪሚየም) 6.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በዚሁ ዓመት የኬንያ 49 ኩባንያዎች ግን ሁለት ቢሊዮን ዶላር የዓረቦን ገቢ ሰብስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ኩባንያዎች በበጀት ዓመቱ ከሰበሰቡት 6.4 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘው ስድስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ቀሪው ከሕይወት ነክ ዘርፍ የተሰበሰበ ነው፡፡ ይህም የኢንሹራንስ ዘርፉ የተመሠረተው ሕይወት ነክ ባልሆኑ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተሰበሰበው ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 3.2 ቢሊዮን ብር ከሞተር ኢንሹራንስ የተገኘ ነው፡፡ ያለፉት አሥር ዓመታት የነበረው የሁሉም ኩባንያዎች መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በአማካይ ከ60 በመቶ በላይ የኢንዱስትሪው የመድን ሽፋን በሞተር ወይም በተሽከርካሪ የመድን ዋስትና የተመሠረተ እንደሆነ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪው ማደግም ሆነ ማሽቆልቆል ለሞተር መድን የሚሰጠው ሽፋን ትልቁን ሚና እንደሚጫወት አንዱ ማሳያም ይኸው አፈጻጸም ነው፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኢንዱስትሪው በአማካይ የአሥር በመቶ ዕድገት እያሳየ ቢመጣም፣ በመካከሉ እስከ ሦስት በመቶ የወረደ ዕድገት የተመዘገበበት ጊዜም ይጠቀሳል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ግን ኢንዱስትሪው ሳይታሰብ የ55 በመቶ ዕድገት አሳይቶ ነበር፡፡ ይህም ከአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ጉዞ ከፍተኛው የዕድገት መጠን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህን ያህል ዕድገት በአንድ ዓመት ብቻ ሊመዘገብ የቻለው ግን አስገዳጁ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ተግባራዊ የተደረገበት ወቅት በመሆኑ እንደነበር አቶ እንዳልካቸው አስታውሰዋል፡፡ በሌላ ጎኑ ኩባንያዎቹ በሌሎች የመድን ዋስትናዎች ላይ ደካማ መሆናቸውን ያሳየ ክስተትም ተደርጓል፡፡  

እንደ አቶ እንዳልካቸው ገለጻ፣ በአገሪቱ ከተከፈቱ 420 የመድን ኩባንያዎች ቅርንጫፎች ውስጥ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ቅርንጫፍ ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በአብዛኛው በከተማና ከተማ ነክ በሆኑ ቦታዎች የተወሰኑ ናቸው፡፡ ከተደራሽነት አኳያ መድን ድርጅቶች ደካማ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

ከዓለም የተለየው ኢንዱስትሪ

የኢትዮጵያን የመድን ኢንዱስትሪ ከሌሎች አገሮች የሚለየው ዓቢይ ጉዳይ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋኑ ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ ከፍተኛው የዓረቦን ገቢ የሚሰበሰበው ከሕይወት ኢንሹራንስ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ተቃራኒው ነው የሚታየው፡፡  

አቶ እንዳልካቸው እንደጠቀሱት፣ የኢትጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ከስድስት በመቶ በታች ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ ያደረጉት ዓምና የነበረውን አፈጻጸም ነው፡፡ ከጠቀላላው የመድን ዓረቦን ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ 5.2 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከዓለም አቀፉ አሠራር ጋር በተፃራሪው የሚቀመጥ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ ሕይወት ነክ ካልሆነው አብላጫ አለው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከ95 በመቶ በላይ የኢንሹራንስ ሽፋን ሕይወት ነክ ላልሆነው ቁሳዊ ንብረት የሚውል ነው፡፡

ከጠቅላላው የዓረቦን ገቢም ከ54 በመቶ በላይ ከሞተር ኢንሹራንስ የተሰበሰበ በመሆኑ፣ የኩባንያዎቹ አገልግሎት በአብዛኛው በሞተር ኢንሹራንስ ሥራ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥ የሞተር ኢንሹራንስ ይህንን ያህል ድርሻ እንደማይዝ የሚጠቀሱት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ በዚህ ረገድ ከዓለም የተለየ የገበያ አካሄድ እንደሚታይበት ይስማሙበታል፡፡

በአመዛኙ በሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን ላይ የተጠለለው ይህ ኢንዱስትሪ፣ ከፍተኛ ውድድር ይስተናገድበታል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች በሞተር መድን ሽፋን ረገድ የየራሳው የገበያ ድርሻ አላቸው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የቆየው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ከ22 ዓመታት ወዲህ ከተቋቋሙት ከ16ቱ የግል ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገው ውድድር እያየለ መምጣቱም እየተስተዋለ ነው፡፡ በብዙ ጊዜ በበላይት የቆየበትን የገበያ ድርሻ ለግሎቹ ማካፈል ግድ ሆኖበታል፡፡ ከአሥር ዓመት ወዲህ ካለው የየኩባንያዎቹ የገበያ ድርሻ መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ በ2008 ዓ.ም. እንኳ ወደ 35 በመቶ ወርዷል፡፡

በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ማለትም በ2000 ዓ.ም. 42.7 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የገበያ ድርሻ እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 42 በመቶ ላይ ቢቆይም በ2006 ዓ.ም. ማገባደጃ ወደ 40 በመቶ ዝቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ካቻምና ወደ 37.2 በመቶ ሲቀንስ፣ ዓምና ወደ 35.6 በመቶ ዝቅ በማለት በየጊዜው የገበያ ድርሻው ከበፊቶቹ ዓመታት ይልቅ እያነሰ እንደመጣ አኃዞቹ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ እንዳልካቸው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ጨምሮ ሰባት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከአጠቃላይ ገበያ ውስጥ የ74 በመቶውን ከፍተኛ ድርሻ ተቀራምተዋል፡፡ የተቀሩት አሥር ኩባንያዎች 26 በመቶውን ይጋራሉ፡፡

የኢንዱስትሪው የፋይናንስ አፈጻጸም

የአቶ እንዳልካቸው ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ አትራፊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይሁንና የሚገኘው ትርፍ ግን ከኢንዱስትሪው ሊገኝ ከሚችለው አኳያ ዝቅተኛ የሚባለው ነው፡፡

በ2002 ዓ.ም. የሁሉም ኩባንያዎች የተጣራ ትርፍ 235.18 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዕድገቱን ጨምሮ፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 823.5 ሚሊዮን ብር ማሻቀብ ችሏል፡፡ ካቻምናም አሥር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ጭማሪ በማሳየት የ835.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህ መጠን ባንኮች ከሚያገኙት አንፃር ሲታይም የመድን ድርጅቶቹ አፈጻጸም ዝቅተኛ ተብሏል፡፡

17ቱ ኩባንያዎች በአንድ ዓመት ያስመዘገቡት 835.3 ሚሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት አንድ የግል ባንክ ለብቻው ከሚያገኘው ትርፍ ያነሰ ነው፡፡ ‹‹እንደ አዋሽ ባንክ ያሉት አንድ ቢሊዮን ብር ድረስ ማትረፍ ችለዋል፤›› ያሉት አቶ እንዳልካቸው፣ መድን ድርጅቶች ግን በጠቅላላው ተደምረው እንደ ባንክ ከሚያገኘው ትርፍ በታች ማስመዝገባቸው ምን ያህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አመላካች ሆኗል፡፡

በአንፃሩ በ2008 መጨረሻ የነበረው የ17ቱም ኩባንያዎች ሀብት 11.5 ቢሊዮን ነበር፡፡ ይህ መጠን በ2000 ዓ.ም. ከነበረው ጋር ሲነፃፀር፣ ከሁለት እጥፍ በላይ ማደጉ ተጠቅሷል፡፡ በ2002 ዓ.ም. የተመዘገበው የሀብት መጠናቸው 3.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የሚሰበስቡት ዓረቦን እየጨመረ ቢመጣም ለካሳ ክፍያ የሚያወጡት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ ዓምና 6.4 ቢሊዮ ብር ዓረቦን ቢሰበስቡም፣ ለካሳ ክፍያ ግማሹን ማለትም 3.09 ቢሊዮን ብር እንደከፈሉ በዕለቱ ይፋ ከተደረገው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የሁሉም ድርጅቶች ካፒታል መጠን 1.18 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር እንዳደገ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪው ፈተናዎች

ለመድን ኩባንያዎቹ አዝጋሚ ጉዞ ብሎም ዝቅተኛ አፈጻጸም ምክንያቶች የነበሩ ጉዳዮች ቀርበዋል፡፡ የቡና ኢንሹራንስ ሥራ አስፈጻሚ ከሚጠቅሷቸው መካከል፣ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች ደካማ የኩባንያና የንግድ አመራር እንዲሁም የባለሙያ ዕጥረት ሚዛን የሚደፉት ችግሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ኢንዱስትሪው ስላሉበት ችግሮች ባለድርሻዎችን እየጠራ አለማማከሩ አንዱ ክፍተት ሆኗል፡፡

የደላሎቹ ሚና

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በኩባንያዎቹ እንቅስቃሴ ብቻ የሚራመድ ባለመሆኑ፣ ከኩባንያዎቹ ጋር የሚሠሩ የኢንሹራንስ ደላሎች፣ የሽያጭ ሠራተኞችና ሌሎችም ሚና አላቸው፡፡ በተለይም ደላሎች ለመድን ገበያ መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እንደ ባንክና መድን ድርጅቶች፣ የኢንሹራንስ ደላሎችም ሥራቸውን የሚያከናውኑት፣ ብሔራዊ ባንክ በሚሰጣቸው ፈቃድና ዕውቅና መሠረት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደላሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ውበቱ ወርቅነህ እንደገለጹትም፣ በመድን ኢንዱስትሪው ውስጥ ደላሎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የንግድ ሕጉም የኢንሹራንስ ደላሎችን ሚና ይደነግጋል፡፡

በኢንሹራንሶች አሠራር ሕግ መሠረት፣ እያንዳንዱ ደላላ ለሁሉም ኩባንያዎች መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የሚያመጣውንም ሥራዎች ለኩባንያዎች የሚሰጠው፣ በሚያቀርቡለት ዋጋ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ በኩባንያዎቹ አቅም መሠረት እንደሆነም ተብራርቷል፡፡

ሁሉም ደላሎች ለ17ቱም ድርጅቶች በተገቢው መንገድ መሠራት ሲገባቸው በተወሰኑት ላይ ብቻ አተኩረው እንደሚሠሩ የጠቀሱ ባለሙያዎችም ደላሎቹን ተችተዋል፡፡ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች የቡና ኢንሹራንስን ፈለግ በመከተል በቋሚነት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀትና በችግሮቻቸው ዙሪያ እየመከሩ መትሔዎችን ለማፈላለግ ተስማምተዋል፡፡