Skip to main content
x

ሙስናን በዘመቻ መታገል ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም

በአደሙ ጎበና

አገራችን በፈጣን ዕድገት ሒደት ላይ ያለች አገር መሆኗውን እንኳን ዜጋው ዓለም የመሰከረላት እውነታ ነው፡፡ ዕድገቷን ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እያደረገች ያለች አገርብትሆንም የውስጥና የውጪ እንቅፋቶቿዋ ብዙ ናቸው፡፡ ተደጋጋሚ ድርቅ ያጠቃታል፡፡ ረሃብ አይጠፉም፡፡ የነበረውን በማውረድ በተራ ሥልጣን ለመያዝ በሚፈልጉ ዜጎቿ ያልተቋጨ የእርስ በርስ መናቆሮች አሉ፡፡ በዚህም በመንግሥት ላይ የጥላቻ ጣታቸውን የሚቀስሩ ዜጎች ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ መንግሥት ዳር ድንበር እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ ዜጎች በወሮባላዎች እንዳይጠቁና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ተግቶ ይሠራል፡፡ ገንዘብ ያሳትማል፣ ያሠራጫል፡፡ የውጭ ባለሀብት ወደ አገር ውስጥ መጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ የተመቻቸ ሁኔታዎች እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

በአገር ውስጥ የተፈጠሩት ባለሀብቶችም እንዲሁ ሀብታቸውን እንዲያፈሱና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ይሠራል፡፡ ለዜጎች የመሠረተ ልማትን፣ ጤናና ትምህርትን ለማስፋፋት ይሠራል፡፡ መንግሥት በሚሠራው ዕርካታ የሌላቸው፣ መንግሥት ከሚሠራው እኔ ብሠራ የተሻለ ዜጋን እመራለሁ ይላሉ፡፡ ለዜጋ እሠራለሁ ብለው የሚያስቡት ያለው መንግሥት የፈለገውን ያህል በትክክል ቢመራና በትክክል ቢሠራ ዕርካታ የላቸውም፡፡ ለዚህም እንዲያመቻቸው የመንግሥትን ሁሉንም እንቅስቃሴዎች አቃቂር በማውጣት ይቃወማሉ፡፡  ስህተቶችንና ደካማ ጎኖችን በጣም አካብደው ይታቸሉ፡፡ ቢቻላቸው መንግሥት ላይ ጠመንጃ እስከመያዝ ድረስ አልመው ይሠራሉ፡፡ ከተቻለ በሰላም ካልተቻለ ደግሞ በጠመንጃ ሥልጣን ለመያዝ ራዕይ ሰንቀው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ሥልጣን ባናገኝም ጥላሸት እንቀባውና ሕዝብን በመንግሥት ላይ ማነሳሳት አለብን ብለው አስበው የሚንቀሳቀሱም አይጠፉም፡፡

ያለው መንግሥት ዜጎችን ሲመራና ለዜጎች ሲሠራ በራሱ ምሉዕ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንዳለው ሁሉ ደካማ ጎኖቹም ሚዛን የሚደፉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት አመራር ውስጥ ለራሳቸው ከበቂ በላይ ጥቅም ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ፡፡ ሕዝብን እንደ ሻማ እያቀለጡ የሚመሩና ለራሳቸው ሳይሆኑ ለዜጋው የሚሠሩ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ለራስ ጥቅም የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ኃላፊዎች የመንግሥት አገልግሎት ሲሰጡ የበለጠውን ለራሳቸው ለመውሰድ አልመው ይንቀሳቀሰሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ናቸው ሌሎች ዜጎች እየተራቡ፣ በኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ፣ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ሲመሩ እያዩ በሙስና ራሳቸውን ለማበልፀግ የሚጥሩት፡፡ መረሳት የሌለበት ጉዳይ በመንግሥት ተቀዋሚዎች ጎራ ውስጥም ቢሆን ሙስና ከፍተኛ ጥቃት ሲያደርስ ይታያል፡፡ ይህ ጽሑፍ በመንግሥት ላይ ጥቃት የሚያደርሰውን ሙስናን በተመለከተ ስለሆነ የሌሎችን ወደፊት እመለስበታለሁ፡፡

ሙስና የሚፈጽሙ ሰዎች ለመንግሥት ታማኝም ጠላትም ናቸው፡፡ ጥቅም ሲያገኙና ሲመቻቸው የመንግሥት ታማኝ ይሆናሉ፡፡ ካልታመቻቸው ደግሞ መንግሥትን በኃይል እንዲወገድ ያስባሉ፡፡ ለዚህም ሕዝብና መንግሥትን የሚያጣሉ የተለያዩ ተግባራትን አቅደው ይሠራሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲንሰራፋ አልመው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ ቅድሚያ ለራሳችን የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በጣም ራስ ወዳዶች፡፡ እነዚህ ሰዎች ሙስና እንዴት ይፈጽማሉ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡  በገንዘብ ላይ ለመወሰን ወይም በገንዘብ በቅርቦት ላይ ለመሥራት የሚያስችለውን ትምህርት መስክ/ዘርፍ አስበውና መርጠው ይማራሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ትምህርቱን አስበው ባይማሩም፣ በአጋጣሚ ለገንዘብ ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ለመሥራት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታም አለ፡፡ ሙስና የሚፈጽሙት ገንዘብ ወጪ የሚደረግባቸው ሰነዶች ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የግዥ በጀት ዕቅድ ሲያዝ ጀምሮ ሙስና ለመፈጸም ነቅተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ለሙስና ቀድመው የበጀት ዕቅድ ይይዛሉ፣ ወይም ያስይዛሉ፡፡ እንዲሁ ለሙስና የሚጠቅም ሥራ ያቅዳሉ፡፡ በመቀጠልም በጀት ተፈቅዶ ሥራ ሲጀመር ከማን፣ እንዴት፣ ምን ያህል ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ አስበው በጥንቃቄ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዕቅድ ስለሚንቀሳቀሱ ይሳካላቸዋል፡፡

በሌላኛው ወገን ደግሞ ዕላፊ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ኃላፊዎችን ጠንቅቀው የሚያወቁ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ይህም በጥናትና በምርምር የሚከናወን ነው፡፡ የሰው ኃይል መድበው ያሠራሉ፡፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሾፌር የነበረ ሰው ቀደም ሲል ለሌሎች ሰዎች በደላላነት ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ፣ በአጭር ዓመታት ውስጥ ባለአምስት ኮካብ ሆቴሎችን መገንባት መቻሉን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች በማንኪያ ሰጥተው በአካፋ መውሰድ አቅም ያላቸው ስለሆኑ፣ ለማን በምን ጉዳይ ጉቦ ከፍለው ሥራ ማግኘት እንደሚችሉ ከመጀመርያው አቅደው ይንቀሳቀሰሉ፡፡ ሚና ሊረሳ አይገባም፡፡ ደላሎችም ጉቦ ሰጪውንና ተቀባዩን በጥናትና ምርምር ለይተው ያግባባሉ፡፡ የሚግባቡት ደግሞ በባለሥልጣናት ቢሮ አይደለም፡፡ ዱባይ በመውሰድ ወይም ከተማ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ ባለኮከብ ሆቴል ውስጥ ውስኪ እየጠጡ፣ በጣም በጥንቃቄና በንፅህና የተዘጋጀ ምግብ እየጋበዙ ነው፡፡ ደላላው ከሁለቱም ወገን የሚፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ስለሚንቀሳቀስ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በተለይ ትንንሽ  ሙስናዎች ሲሆኑ የደላላ ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ደላላ ሲባል በየሠፈሩ የቤት ተከራዮችን እያፈናቀለ ለሌላ ቤት ተከራይ የሚያከራይ ዓይነት አይደለም፡፡ ባለሀብትና ባለሥልጣን የሚያገናኝ ደላላ እንግሊዝኛ ቋንቋ ጠንቅቆ መናገር ይችላል፡፡ የመጀመሪያዲግሪና ከዚያም በላይ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ከፍተኛ የመንግሥት ከፍተኛ ሹም ነው፡፡ በእርግጥ ተከራዮችን ከቤት እያፈናቀለ ከፍተኛ ኮሚሽን የሚያገኘውም በአቅሙ ሙስና ሥራ ፈጽማ፡፡ እንዲያውም በአገሪቱ የሙስና ደም ሥር ወይም አንቀሳቀሽ ሞተር ደላላ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሙስና ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን የሚያገናኝ ደላላ ከማንም በላይ የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራል፡፡ ምንም እሴት ሳይፈጥር ሀብታም የሚሆነው ‹ኪራይ ሰብሳቢ› የሚለው ቃል በትክክል የሚገልጸው ደላላን ነው፡፡

ሙስና የሚፈጽሙ ሰዎች ባህሪያቸው ከሌሎች ሰዎች ላይ የተለዩ ናቸው፡፡ ሲሠሩ እሳት ሲባሉ እሳት የሚባሉ ዓይነት ናቸው፡፡ ሙስና በሚሠሩት ሥራ ላይ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ናቸው፡፡ ምስኪን የሚባሉ አይደሉም፡፡ ሥራን በዕውቀትና በክህሎት ያከናውናሉ፡፡ የሚሠሩትን በምንም ዓይነት ያለጥቅም አይሠሩም፡፡ በጣም ካጡ ነፃ ምሳ ይበላሉ፡፡  በግሉ ዘርፍ ፈጣሪ ኢንተርፕሩነር እንደሚባለው ዓይነት በመንግሥት ሥራ ላይ ፈጣሪ ኢንተፕሩነር የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ብዙ ወዳጅ ያላቸው ስለሆኑ ሰጥቶ የመቀበል መርህን በትክክል የሚከተሉ ናቸው፡፡ የአገሪቱ ሀብት እያደገ ሲመጣ የሙስና መጠንም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሙስና ምሳ በመጋበዝ ይጀመራል፡፡ አሥር ሺሕ ብር ጉቦ ይወሰዳል፣ ባለሀብቱ የሚፈልገው ይደረግለታል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ወደ መቶ ሺሕ ብር ጉቦ ይጠየቃል፣ ወይም ባለሀብት በሚገያገኘው ገንዘብ ላይ ድርሻን በፐርሰንት ይተሳሰባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ባለሀብቱን በመጥቀምና በመንግሥት ላይ ወጪ በመጨመር የሚፈጸም ነው፡፡ አሁን ደግሞ ሙስና መጠየቅ ከአምስት መቶ ሺሕ እስከ ሚሊዮን ብሮች ደርሷል፡፡ የሙስና ዋጋ በመናሩ አሁን አሁን ወደ ቢሊዮን በማደግ ላይ ነው፡፡ በአሁን ወቅት የታሰሩት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች በድምሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መመዝበራቸውን (ጉዳት ማድረሳቸውን) ሚዲያዎች ሲዘግቡ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ የሙስና ዋጋንም በጣም እንዲንር አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለይም ከገንዘብ ወጪ ሰነድ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች  መጠኑ ይለያይ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙስና ይፈጽማሉ፡፡ እዚህ ላይ በራሳቸው ላብ ብቻ ለመኖር ጥረት የሚያደርጉና ፈሪኃ እግዚአብሔር ያላቸው ምስኪን ሰዎች እንዳሉም አንርሳ፡፡ ሙስና የማይፈጽሙ ሰዎች በተለምዶ የሚለጠፍባቸው ስምም ‹በልቶ የማያስበላ፣ ገገማ ወይም ገጠሬ› ይባላል፡፡ ሙስና አይፈጽሙም፣ ሌሎች እንዲፈጽሙም አይፈቅዱም፡፡ ንፁህ ዜጋ ስለሆኑ አሁንም ፈጣሪ ይባርካቸው፡፡ ሙስና የሚፈጽሙ ሰዎች ቤታቸው ሙሉ ነው፡፡ በባንክ ሒሳብ ውስጥ ብዙ ገንዘብ አላቸው፡፡ ሳይሸማቀቁ እንደ ልባቸው ይዝናናሉ፡፡ በትንሹ ሙስና የሚፈጽሙ ሰዎች በደረጃቸው የሚመጥን ቦታ መርጠው እንደ ልባቸው ሲዝናኑ (ይጣጠሉ፣ ይባላሉ፣ ከመረጡት ጋር ይተኛሉ፣ ይለብሳሉ)፣ ሚሊዮን ብር በሙስና የሚያገኙ ሰዎች ደግሞ ዱባይ ከመመላለስ በተጨማሪ ከተማ ውስጥ ባሉ ትልልቅ ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ይዝናናሉ፡፡ በሙስና ሀብት ያካበቱና ምርጥ ቦታ መዝናናትን የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ስላሉ በቀን ሦስት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ የአውሮፕላን በረራዎች አሉ፡፡

በጥረት ባገኙት ገንዘባቸው የሚዝናኑ ንፁኃን ዜጎች እንዳሉ ይታወቅ፡፡ በተለይ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ የሆነ ሰው ያላቅሙ ከገቢው በላይ በሆነ በጣም ውድ በሆነ በተደጋገሚ የሚዝናና ከሆነ፣ ይህ ሰው በሙስና የሚያገኘው ገቢ ምንጭ አለው ማለት ነው፡፡ ተለፍቶ የተገኘ ገንዘብ ስላልሆነ አጠቃቀሙም ልቅ ነው፡፡ መንግሥት ከገቢ በላይ የሚኖሩ ሰዎችን የመረጃ መረብ በመዘርጋት ለማረጋገጥ ዕድሉ ስላለው፣ በተለይም ሥውር ኢንተለጀንሲና ፍሪላንስ በመሰየም ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ትናንትና ሽሮ ጠግቦ የማይበላና ሳልባጅ ገዝቶ የሚለብስ ሰው ከደመወዝ ውጪ ምንም ገቢ ሳይኖረው በጣም ውድ የሆነ ኑሮ ሲመራ ከየት አምጥቶ ነው? የሚለውን መጠየቅ የሚችል አካል ሊዋቀር ይገባል፡፡

እዚህ ላይ አንዳንድ ሚዲያዎች የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የመዘገበውን ሀብት ለምን አያሳይም? እያሉ ሲወሸክቱ አያለሁ፡፡ ምንም እንኳን ዘጋቢ ሚዲያውን የሚመራው አካል ውስጥ የጥቃት በትሩን በሚቀጥለው የመንግሥት አመራር ላይ ለማሳረፍ የሚፈልግ የአመራር ፍላጎት እንዳለበት በግልጽ መረዳት ቢቻልም፣ ሙስና የሚፈጽሙ ሰው ያገኘውን ሀብትና ንብረት ዱባይ መደበቅ እየቻለ፣ ኮሚሽኑ ዘንድ ያስመዘግባል ብሎ ውጤት መጠበቅ ራስን ማታለል ነው፡፡ ስለሀብት ምዝገባ ተደጋጋሚ ዘገባ የሚያወጣው ሚዲያ በቅድሚያ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ አዋጁ አጠገቡ ስላለ ገዝቶ በትክክል ማንበብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የተመዘገበው ሀብት ለሕዝብ ይፋ ሲሆን፣ መረጃውን ማየት የሚፈልግ ሰው በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረብ አለበት ይላል አዋጁ፡፡ ሚዲያው እንደሚለው የተመዘገበውን ሀብት መረጃ ለሕዝብ ለመዘርገፍ ከተፈለገ አዋጁ መቀየር ይኖርበታል፡፡ የተመዘገበው ሀብት መረጃ ለግል ዓላማ ማሟያ ሊሆን አይችልም፡፡ የሙስና ትግልን ለግል ፍላጎት ማሟያ ከማድረግ ይልቅ የሕዝብ ቢሆን ይመረጣል፡፡

በሙስና ገቢ የሚያገኙት ሰዎች ገበያ ላይ የሚፈጥሩት ትርምስ መኖሩን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወር አንድ መቶ ሺሕ ብር ገቢ ያለውና በወር አንድ ሺሕ ብር ገቢ ያለው ሰው በገበያ ውስጥ ዕቃ የመግዛት አቅማቸው በጣም የተለያየ ነው፡፡ የሙስና ገቢ ያለው ሰው የተጠየቀውን መግዛት ስለሚችል ነጋዴውም ይኬንን በጣም ስለሚረዳ የገበያ ዋጋን በዚያው ልክ ያስተካክላል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው የሚፈልገውን መግዛት ስለማይችል በኑሮ ውድነት በየዕለቱ በመንግሥት ላይ ያማርራል፡፡ ዕቃውን እየፈለገውና እያማረው ሳያገኝ ኑሮውን ይገፋል፣ ይሞታል፡፡ አቅም ካለው ገዥ ጋር ተወዳድሮ መግዛት አይችልም፡፡ የቤት ኪራይም እንዲሁ የሙስና ገቢ ያለው ሰው ክፈል የተባለውን ቤት አማርጦ ስለሚከራይ፣ ደላላ ደግሞ ለሚያገኘው ኮሚሽን ሲል የቤት ኪራይ ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው የሰው ኩሽና ወይም ከከተማ በመውጣት ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ቤት ኪራይ ፍለጋ ሲሄድ፣ በሙስና ገቢ ያለው ከተማ ውስጥ ለዚያውም ለኑሮ አመቺ በሆነ አካባቢ ተንዳለቆ ይኖራል፡፡ የቀብር ቦታም ቢሆን የሙስና ገቢ ላለውና አነስተኛ ገቢ ላለው እኩል አይሆንም፡፡ ደሃው ከ100 በላይ ተማሪዎች አንድ ክፍል የሚማሩበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ልጁን ሲያስተምር፣ የሙስና ገቢ ያለው 25 ተማሪዎች የሚማሩበት ክፍለ ያለው ትምህርት ቤት ልጁን ያስተምራል፡፡ ደሃው በኮንትሮባንድ የመጣውን ሳልባጅ ልብስ ገዝቶ ሲለብስ፣ በሙስና ገቢ ያለው በቦሌ ኤርፖርት የመጣውን ልብስ ከቡቲክ ገዝቶ ይለብሳል፡፡ የሙስና ገቢ ያለው ጮማ አማርጦ ሲበላ ደሃው ደግሞ ሽሮ ቆጥቦ ይበላል፡፡

መንግሥት ይህን ችግር በመረዳት ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ካልቻለ ጦሱ ለራሱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝብ መንግሥትን በጣም ይጠላል፡፡ ሕዝብን በጉልበት መግዛት ወይም ማስተዳደር በአሁኑ ዘመን በዓለም ላይ አይደለም፣ በአፍሪካም እየቀረ የመጣ ነው፡፡ በጉልበት ልግዛ ካለ ከአገሩ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከዓለምም ይገለላል፡፡ ይወገዛል፡፡ በአገሪቱ ሰላም አይኖርም፡፡ መንግሥት ሙስናን በዘመቻ ሳይሆን በጣም ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ከምንጩ የማድረቅ አቅሙም ዕድሉም አለው፡፡ በዘመቻ ሙስናን መዋጋት የአንድ ወቅት ወሬ ካልሆነ በስተቀር ውጤታማ አያደርግም፡፡ የባሰውን ደግሞ አሁን በየሠፈሩ እንደሚወራው የቀን ገቢ ግብር ግምት ላይ ያለውን የሕዝብ አመለካከትና እሮሮ አቅጣጫ ለማስለወጥ የተፈጸመ ድርጊት ነው የሚባለውን ዓይነት ስም ያሳጣል፡፡ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በየዓመቱ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዘጠኙም ክልሎች፣ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ዕርምጃ አልወሰዱም ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ሚዲያዎች ካልታዘዙ በስተቀር የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለመዘገብ ባላቸው ዳተኝነት ሥራው ስለመከናወኑ ሕዝቡ እንዲያውቅ አይደረግም ይሆናል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ፣ በአቶ ስዬ አብርሃና በአቶ መላኩ ፈንታ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ  የተወሰደው ዕርምጃ በዘመቻ ነው፡፡ ሚዲያዎች በጉዳዮች ላይ ወቅታዊ ማራገቡን ጠንክረው ሠርተዋል፡፡ ከዚያም ለብዙ ጊዜ ጠፍተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በርካታ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ ተባለ፡፡ ሚዲያዎች የሰዎዡ ማንነት ሳይታወቅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ ብለው አራገቡ፡፡ ስማቸው ወደፊት ይገለጻል ተባለ፡፡ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ስማቸው ሲታወቅ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይሆኑ ሥልጣናቸው ከለቀቁ ዓመታት የተቆጠረባቸውና በመንግሥት ተቋማት የሥራ ክፍል ኃላፊዎች መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በማለት መግለጫ የሰጠው አካልም ስለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ሳይጠይቅ ታለፈ፡፡

 ይቀጥልና ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ወንጀል የመሳተፍ ዕድል አነስተኛ ነው፣ እነሱ የፖለቲካ አመራር ነው ብቻ የሚሰጡት ብሎ አረፈ፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ የአንድ ተቋም የመንግሥት ተሻሚ የሆነ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሳያውቅ የሚፈጸም ክፍያ እንደማይኖር ለማደነጋገር ካልሆነ በስተቀር ረስተውት አይመስለኝም፡፡ ሕዝብን ማታለል ግን አይቻልም፡፡ ብቻ አንድ ሚኒስትር ዴኤታ ለምርቃት ያህል በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ የመንግሥት ተቋማት ጓዳዎች በትክክል መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ሚዲያዎችም አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታሰሩ ብለው ከሚጠበቀው በላይ አራገቡ፡፡ የታዘዙትን ስለሚያደርጉ አይፈረድባቸውም፡፡

ሌላው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በአንዳንድ ግለሰቦች የሚሰጠው አስተያየት ገንቢ አይደለም፡፡ እገሌና እገሊት ካልታሰረችና ካልታሰረ ብለው የሚያራግቡ ሰዎች ሊታረሙ ይገባል፡፡ እንዲህ የሚሉት ሰዎች ምንም መረጃ ሳይዙ በጥላቻ መንፈስ ስለሚነዱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ መረጃውን ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ወይም ሚዲያ ላይ ቢያወጡ ኖሮ እውነትም እነዚህ ሰዎች ሙስና ፈጽመዋል ማለት ይቻል ነበር፡፡ ግን መረጃ ሳይዙ በግብታዊነት እየተነዱ እገሌና እገሊት ካልታሰረና ካልታሰረች ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ እኮ ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከምንም ተነስቶ እንዲታሰሩ ማድረግ ተገቢም አይሆንም፡፡ እባካችሁ በስሜት ከመነዳት ይልቅ አስባችሁና በመረጃ አስደግፋችሁ አስተያየት ስጡ እላለሁ፡፡ ይህ የዜግነት ግዴታም ይሆናል፡፡

ፍርድ ቤቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የሚሰጡት ውሳኔና  በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በዘመቻ የሚታሰሩት ሰዎች ላይ ያለመጣጣም ችግር ያለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በመጀመርያ በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ በቂ መረጃ ሳይያዝ እንዲታሰሩ ማድረግ ተገቢ አይሆንም፡፡ ብዙዎች ይታሰራሉ፡፡ ነገር ግን ነፃ ናችሁ እየተባሉ ከፍርድ ቤት ወዲያው ይወጣሉ፡፡ አንዱ ለሌላው ምስክር እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ያለበቂ መረጃ የታሰሩት ሰዎች ከእስር ቤት ሲወጡ በብዙ መልኩ ተጎድተው ነው፡፡ ዳኞች ያላቸው ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ ስህተቱ ያለው ከአሳሪ (ፖሊስና ፀረ ሙስና) ወይም ከፍርድ ቤት የሚለውም በጣም ሊፈተሽ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ሰዎች በሙስና ሲታሰሩ ለጠበቆች ገበያው ስለሚደራ፣ ጠበቆች ደግሞ ከፍርድ ቤት ዳኞች ጋር በጣም ቅርበት ያለቸው ወይም ጓዳኞቻቸው ስለሆኑ፣ መንግሥት ይህንን በጥንቃቄ ማየትና መፈተሽ እንዳለበት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በጣም ያምናል፡፡ ሌላው መፈተሽ ያለበት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ጓዳ ውስጥ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ያለባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበሩበት ክልልና የከተማ አስተዳደር ሹም ሆነው ሲሠሩ ሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን በግልጽ የሚያሳዩ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለፈጸሙት የሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ አልተደረጉም፡፡ ነገር ግን የሌላውን የሙስና ወንጀል ሲያብጠለጥሉ  እነሱ ሙስና ስለመፈጸማቸው ሕዝብ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ በጣም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖችና በፌዴራል ፖሊስ በሙስና ወንጀል ጥቆማዎች መሠረት መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘመቻ የሚከናወነው ሙስናን የመዋጋት ዘመቻ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ ተጠቃሚና ተጎጂ ያለ ከመሆኑም በላይ፣ የአንድ ወቅት ወሬ ከመሆን ባለፈ ፋይዳው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ መንግሥት ይህን መንገድ ከመከተል ይልቅ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባሉባቸው ተቋማት ውስጥ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ወቅታዊ የሆነ አስተማሪ ዕርምጃ የመውሰድ፣ በሙስና ወንጀል ላይ ክትትል የሚያደርግ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ የተጠናከረ የኢንተለጀንስና የፍሪላንስ አደረጃጀት የመፍጠርና የማጠናከር፣ የአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ከፖለቲካ ቁርጠኝነት በሻገር  የኋላ ታሪካቸውን ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች መረጃዎችን የመውሰድ የማስተካከያ ሥራዎች የማከናወን፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን መዋጋትና መከላከል የሚሠሩ አካላት? አቅም ተገቢ ነው፡፡ ሚዲያዎች የምርምራ ጋዜጠኝነትን በሠለጠነ መንገድ እንዲመሩ ማድረግና ዕድሉን ማመቻቸት ይገባል፡፡ አሁን በሙስና ወንጀል ላይ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ብዥታን ለመቀነስ ይቻላል፡፡ ሙስና በአገሪቱ እያስከተለ ያለውን ችግር በዘላቂነት በመቅረፍ መንግሥት ከሕዝብ አመኔታን ያገኛል፡፡ የተጀመረውን የህዳሴ መስመር ዕውን ለማድረግ የሙስና የጥቃት ደረጃው መቀነስ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዘመቻ ሥራ መውጣት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው[email protected]ማግኘት ይቻላል፡፡