Skip to main content
x
ሙስና የዝቅጠት መገለጫ ነው!

ሙስና የዝቅጠት መገለጫ ነው!

ሙስና ሌብነት ነው፡፡ ሌብነት ደግሞ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የዘቀጡ ሰዎች ድርጊት ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ በቡድን የሚካሄድ ሙስና ታማኝነት በሌላቸውና ሥነ ምግባር አልባ በሆኑ ሰዎች የሚፈጸም በመሆኑ፣ በጤናማ ማኅበረሰብ ዘንድ የተናቀ ነው፡፡ እንደ ዛሬው በአቋራጭ መበልፀግ እንደ ጀብድ በማይታይበት ዘመን እንደ ተራ ኪስ አውላቂነት የሚታየው ሙስና፣ አሁን እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፍቶ አገር እየለበለበ ነው፡፡ ከትንሹ ቀበሌ እስከ ትልቁ ፌዴራል መንግሥት መዋቅር ድረስ ተንሰራፍቷል፡፡ በእጅ ከሚቀባበሉት አነስተኛ ጉቦ እስከ ትልልቅ በጀት ዘረፋ ድረስ አድማሱን አስፍቷል፡፡ ከቀበሌ ደንብ አስከባሪ እስከ ቱባ ባለሥልጣናት፣ ከመንደር ደላላ እስከ ኢንቨስተር ተብዬዎች ድረስ ዘልቋል፡፡ ‹ጉዳይ ገዳይ› በሚባሉ አቀባባዮች አስተናባሪነት የአገር ሀብት ይዘረፋል፡፡ የመንግሥት የግዥና የፋይናንስ አስተዳደር ሕጎች በጠራራ ፀሐይ እየተጣሱ የደሃ አገር አንጡራ ሀብት ይመዘበራል፡፡ ጠያቂና ተጠያቂ የሌለ እስኪመስል ድረስ ሌቦች በአገር ላይ ይቀልዳሉ፡፡ ከዚህ በላይ መዝቀጥ ከየት ይመጣል?

ሥርዓተ መንግሥቱ ጤናማ ሆኖ አገር የምታድገውና የሕዝቡ ኑሮ የሚሻሻለው፣ ሙስናን የማይታገስና ምሕረት የለሽ ዕርምጃ መውሰድ የሚችል መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ለዓመታት ሲቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶች በግልጽ የሚሳዩት፣ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ እየተጣሰ በበርካታ መሥሪያ ቤቶች በአግባቡ ሒሳብ አይወራረድም፡፡ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ይታያል፡፡ የገቢና ወጪ ሒሳብ የተዝረከረከ ነው፡፡ የመንግሥት የግዥ ሕግ እየተጣሰ ያለ ጨረታ ኮንትራት ይሰጣል፡፡ በአግባቡ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት የተጋነነ ክፍያ ይፈጸማል፡፡ ብቃት የሌላቸው ኮንትራክተሮችና ተቆጣጣሪዎች እየተመረጡ ጥራት ለሌለው ሥራ ሚሊዮኖች ይባክናሉ፡፡ በተጋነነ ዋጋ የዕቃዎች ግዥ ይፈጸማል፡፡ ደረሰኝ የማይቀርብባቸው በርካታ ግዥዎች ይፈጸማሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ ድርጊት ከመሥሪያ ቤቶች አልፎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደ ወረርሽኝ ገብቶባቸዋል፡፡ ሙስና ተቋማዊ እስኪመስል ድረስ በሁሉም ሥፍራ ተስፋፍቷል፡፡ ጥቂቶችን እያሳበጠ ብዙኃኑን ኮስማና አድርጓል፡፡  

በሙስና ውስጥ የሚሳተፉ ኃይሎች በኔትወርክ የተሳሰሩና የተጠናከሩ በመሆናቸው ወንጀላቸውን በቀላሉ ማግኘት ሊከብድ ይችላል፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው ሲቀየርና ለማመን የሚከብዱ ንብረቶች ባለቤት ሲሆኑ ደግሞ ይታያሉ፡፡ ትናንት ላቡን ጠብ አድርጎ የትም መድረስ ያልቻለ ባተሌ በድንገት እንደ ሮኬት ተተኩሶ የሀብት ማማ ላይ ሲቀመጥ እንደ ተዓምር መታየት የለበትም፡፡ የራሱ እንኳ ባይሆን የሙሰኛ ሹም ንብረት እያስተዳደረ ሊሆን ይችላል ተብሎ መጠርጠር አለበት፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ወሩን መግፋት ያቅተው የነበረ ግለሰብ፣ የግሉ ዘርፍ ውስጥ ገብቶ በተራዘመ ጊዜ አሳማኝ በሆነ ጥረት ሀብት ቢያፈራ ሊገርም አይገባም፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ መና ከሰማይ የወረደላቸው የሚመስሉ ሲያጋጥሙ ደግሞ እንዴት ሊሆን ቻለ መባል አለበት፡፡ ሌላው ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈጸሙ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶችን እንዳላዩ ማለፍ ስለበዛ ነው እንጂ፣ የሌብነት መቀፍቀፊያ ዋሻ መሆናቸው በእጅጉ የታወቀ ነው፡፡ ከአንድ የከተማ ነዋሪ ባለጉዳይ እስከ ኢንቨስተር ድረስ የሚስተናገዱባቸው እነዚህ የሌብነት ዋሻዎች ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ ዓይንን መጨፈንና ጀሮ ዳባ ልበስ ማለት ግን ሊያጋልጣቸው አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ዝቅጠት የበላይነት ይይዛል፡፡

‹‹ሙስናን መፀየፍ››፣ ‹‹ሙስናን መዋጋት ወይም መታገል››፣ ‹‹ሙስናን ማስወገድ››፣ ወዘተ. በሚባሉ ጭምብሎች ውስጥ የተደበቁ ዓይነ ደረቆች መልሰው ሕዝቡን ለማታለል ሲሞክሩ በስፋት ይታያሉ፡፡ ሙስና ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን አገሪቱን እየገዘገዘ መሆኑ ታውቆ ዘመቻ ሲጀመር መደናገሮች ይፈጥራሉ፡፡ የሙስና ዋርካ መመታት ያለበት ግንዱ ላይ ነው ሲባል እነሱ ቅርንጫፉ ላይ ይረባረባሉ፡፡ ሕዝብ ደግሞ የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ለይስሙላ ነው ብሎ ይደመድማል፡፡ ሌላው ቀርቶ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት ብቻ መጠየቅ ያለባቸው ሹማምንት ከላይ እስከ ታች መሆናቸው ግልጽ ሆኖ እያለ ማመንታት ይታያል፡፡ እዚህ ላይ ሙስናን ማጣራትና ማስረጃ መሰብሰብ ከባድ ነው የሚል ክርክር ቢነሳም፣ ጥርትና ግልጽ ብሎ የቀረበን ማስረጃ ወደ ጎን መግፋት ለምን ያስፈልጋል? እርግጥ ነው አንድ ቦታ ላይ ምርመራ ሲጀመር የሚነካካው ሊበዛ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጫማ ጠበበ ተብሎ እግር እንደማይቆረጥ ሁሉ፣ ገና ለገና የማይደፈሩና የማይጠየቁ ከሕግ በላይ የሆኑ ያሉ ይመስል አገርን ለአደጋ ማጋለጥ ተገቢ አይደለም፡፡ የሙስና አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀ በወንረጦ ተለቅሞ በሕግ መጠየቅ አለበት፡፡ ከሕግ በላይ ማንም የለምና፡፡

አንድ ሥርዓት ጠናማ ሲሆን ዜጎች በሙሉ መተማመን የሚኖርባቸው በሕግ የበላይነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የአንድ ጤናማ አገር መመኪያ ነው፡፡ ሥርዓቱ ጤና የሚያጣው ሕገወጦች እንደፈለጉ ሲፈነጩ ነው፡፡ ሕገወጥነት መረን ሲለቅ ሕዝብ አዳማጭ ያጣል፡፡ አዳማጭ ያጣ ሕዝብ ብሶቱ ገንፍሎ አደባባይ ሲወጣ ደግሞ ለማቆም ያዳግታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ ለእነዚህ ወገኖች መሠረታዊ የሚባሉት ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና የመሳሰሉት የሰማይ ያህል የራቁ ናቸው፡፡ እነዚህን ወገኖች ከእዚህ ዓይነቱ የድህነት አረንቋ ውስጥ አለማውጣት ማለት፣ ነገ አገሪቱን ታይተውና ተሰምተው ለማያውቁ የወንጀል ዓይነቶች ማዘጋጀት ነው፡፡ በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነገር ግን በኑሮ ውድነትና በመጠለያ ችግር የሚሰቃዩ ወገኖችን ኑሮ መለወጥ አለመቻል ራሱን የቻለ ችግር አለው፡፡ በዚህ ላይ የሌብነት ቃፊሮች ሕዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ ድርጊቶችን ከልካይ በሌለበት ሲፈጽሙ ነገን ማሰብ ይከብዳል፡፡ መንግሥት ሙስናን እታገላለሁ ሲል ቁርጠኝነት ይጎድለዋል የሚባለው ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ አስቸጋሪ ጉዳዮች እንዳሉ በመገመት ጭምር ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ሥርዓቱንም ሆነ አገሪቱን እንደ ነቀዝ እየበላ ያለው ሙስና ለማንም የማይመለስ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዘቀጡ ሙሰኞች አገር ቢወድም፣ ሕዝብ ቢተራመስ ደንታ የላቸውም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚታወቅባቸው የጋራ እሴቶቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ አገርን መውደድ፣ ከማናቸውም ወራሪ ጠላቶች በጀግንነት መከላከል፣ እርስ በርስ መፋቀርና መከባበር፣ ልጆችን በሥነ ሥርዓት ኮትኩቶ ማሳደግ፣ እንደ እምነቶች ሥነ ምግባር ማስተማር፣ ሌብነትንና ክፉ ድርጊቶችን ማውገዝና ማጋለጥ፣ አጉራ ዘለልነትን መናቅና ሥፍራ ማሳጣት፣ ወዘተ. ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን ግን ሙስና የአገር መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ አገርን እየለበለበና ዝቅጠቱ ትውልድን እየበከለ ነው፡፡ ይህንን ፀያፍ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይቻል እንኳን፣ በተቻለ መጠን ያለበትን ደረጃ በጣም ዝቅ ለማድረግ በትንሹም ቢሆን መስዕዋትነት መክፈል ተገቢ ነው፡፡ በአቋራጭ ጉዳይን ለመተኮስ መራኮት ቆሞ ለመጪው ትውልድ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ፍትሕ በገንዘብ ለማግኘት የሚሯሯጥ ቆም ብሎ ማሰብ ካልቻለ፣ ነገ ባለጉልበት መጥቶ የሚሳሳለትን ነገር እንደሚነጥቀው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በወገኖቹ ጀርባ ላይ ተሸጋግሮ ዛሬ ጉዳዩን ያሳካ ነገ በእሱ ጀርባ ላይ ቆሞ ንብረቱን የሚቀማው ወንበዴ እንደሚኖር ማሰብ አለበት፡፡ ሕግ እየተጣሰና የሕግ የበላይነት እየተሸረሸረ ሲቀጥል አገር በማፊያዎች ትወረራለች፡፡ ማፊያዎች ሲበዙ ደግሞ በፊልም ላይ እንደሚታየው እንኳን ንብረት የሰው ልጅ ሕይወት የረከሰ ይሆናል፡፡ አገርንና ሕዝብን ከእንዲህ ዓይነቱ ዝቅጠት ለመታደግና የነገውን ትውልድ ጤናማነት ለማረጋገጥ ብርቱ አለመሆን አደጋ አለው፡፡ ሙስናን የሚገታው ጠንካራ ኅብረት ከሌለ ነገን ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ ለዚህም ነው ሙስና የዝቅጠት መገለጫ ነው የሚባለው!