Skip to main content
x
ማሰብ ደጉ ባይኖር ምን እንሆን ነበር?

ማሰብ ደጉ ባይኖር ምን እንሆን ነበር?

ሰላም! ሰላም! ‹‹እኔን ያሰኘኝ ፍቺው ፍቺው...›› አለች አሉ ዘፋኟ፡፡ ገር ልብ ያለው ሰው ድሮም መጨረሻው ፍቺ እንጂ አብሮነት አይሆን። ዋናው አያችሁ ማጠንጠኛው ነው። ገር አገር ሲያጣም ዕጣው ተመሳሳይ ነው። ‹‹ዕድል የቢራ ቆርኪ ያህል አታዝንልህም፤›› አለኝ አንድ ወዳጄ። አዲሱን ዓመት በቆርኪ መልካም ፈቃድ የቤት ባለቤት እንዲሆን ቋምጦ እኮ ነው። ወይ ገርና አገሩ። እና ይኼ ወዳጄ ለበዓል መዋያ የያዘውን በጀት በቢራ ጨርሶት እኔን ካላበደርከኝ ‘ሞቼ እገኛለሁ’ ይለኛል። የባሻዬ ልጅ ይኼን ሰምቶ፣ ‹‹ለምን ጥቃቅንና አነስተኛ ሄደህ አትበደርም?›› አለው። ‹‹ቆርኪ አስይዤ?›› ብሎ አይመልስለት መሰላችሁ? ሆዴን ይዤ ክትክት አልኩ። ልሳቅ እንጂ ተውኝ። እንዴ አሮጌ ዓመት ሳያስተክዝ አያልፍም። የትካዜ ብዛት ደግሞ ሲያድግና ሲመነደግ ሆድ አስይዞ ያስቃል። ለዚያ አይመስላችሁም ከልማታዊ ፎቆቻችን ትይዩ አገራችን ኮሜዲያን በማፍራት ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ የወጣችው። አልሰማችሁም እንዴ?

ለነገሩ መብራት ሲኖር እኮ የምትሰሙት። አሁን አሁንማ ሳስበው ይኼ የመብራት መቆራረጥ ከምንም ነገር በላይ የኢንፎርሜሽን ክፍተት ሳይፈጥር አልቀረም። ‘ሥራ ለሠሪው’ በሚለው ማለቴ ነው። ለምን መሰላችሁ ከሰው ጋር መግባባት እያቃተኝ ተቸግሬ እኮ ነው። እንደ ልማዴ (አዝ ኤ ፕሮፌሽናል ደላላ) ቀድሞ ለመገኘት፣ ‹‹ሰማችሁ የእከሌን ማስታወቂያ? በ2010 ዓ.ም. ዓለም ታስንቃለች አለ እኮ?›› ምናም ብዬ ሻጭና ገዢ ላነቃቃ ጮማ ወሬ ሳወራ፣ ‹‹በየት በኩል እንሰማለን? ከተማው በሙሉ በጄኔሬተር ጩኸት ተበክሎ፤›› ይሉኛል። ይኼ ነገር ሐበሻ አሁን ገና በዓይኑ ነገር መጣ ያስብላላ። ያለወሬ ማለቴ ኢንፎርሜሽን እንዴት ተብሎ? ትራንስፎርሜሽን ምናምን ብላችሁ እናንተም አግዙኛ። ነው ጄኔሬተር አለኮሳችሁም? ወይ ገርና አገሩ!

እናማ ዓይኔ ብዙ አየ። ዘመን መጣ ዘመን ሄደ። ሳወጣው ሳወርደው በዚህ አያያዜ ማንም ሰው ሳያውቀኝ ራሴን በራሴ እንዳንቆለጳጰስኩ ባሻዬ ላይ ልደርስ ነው። ይህ ሲሆን ቆሜ አላይም ብዬ ለ2010 ዓ.ም. ቃል ገባሁ። በመጪው ዓመት ከእኔ በላይ የዝና ማማ ላይ የሚሰቀል መኖር የለበትም ብዬ ዕቅዴን ወደ ተግባር ለመለወጥ ስትራቴጂ መቀመር ጀመርኩ። ከልማታዊው መንግሥታችን በተማርኩት መሠረት ስትራቴጂ ሲቀመር ወደ ምሥራቅ መዞር ሊኖርብኝ ሆነ። ቻይናና ኮሪያ ደግሞ የቀን ሠራተኛ እንጂ ስመጥር አያውቁም። ማለቴ ከአውራው ፓርቲያቸው በቀር ማለቴ ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚያችን ከሚጓዝበት መስመር መማር አለብኝ ማለት ነው። ወደ ምዕራብ ዞርኩ። የምዕራባውያን ስመጥሮች እንኳን በአገራቸው፣ አገራችን መጥተው ብዙ እንደ ጎበኙን ትዝ አለኝ። ሐሳባችን ቢበላሽም ‘ሚሞሪ’ ካርዳችን ‘ሴፍ’ ነዋ ምን ነካችሁ?

ስለዚህ ስመ ጥርነቴን የምቋቋምበት አቅም ሳላዳብር ደግሞ በኋላ ምን ልሆን ነው ብዬ ራሴን ስጠይቅ ደግሞ ‘አፍርሰህ ትሠራዋለሃ። በአገርህ እየሠሩ ሲያፈርሱ አይተህ አታውቅም?’ አለኝ ልቤ። ብቻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሶፍት ዌር መልክ ተዘጋጅቶ በቺፕስ ልባችን ውስጥ የሚቀበርበት ቀን አይምጣ እንጂ፣ የአሁኑን ማንም አልሰማኝ ብዬ ስትራቴጂዬን ነድፌ አጠናቀቅኩ። አሁን በምን ልታወቅ? ወደሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ስዞር ‘አፏጭ አፏጭ’ የሚል ድምፅ ሰማሁ። ብቻዬን ሆኜ ‘ማነው የት ነህ’ ስል ባሻዬ ቢያዩኝ ሦስት ሰባት ያዙልኝ ነበር። ደግነቱ ብቻዬን ነኝ። ብቻ ሆኖ ማበድን የመሰለ ነገር የለም አንዳንዴ። ብቻ እብደታችሁ በባልቦላ እንዳይሠራ አስቀድሞ መጠንቀቅ ነው። መብራት ጠፍቶ ‘ስታክ’ ካደረጋችሁ መመለሻ የለማ። አስቡት እስኪ ‘የፍትሕ ያለህ’ እያላችሁ በእብደታችሁ መድረክ ‘አርት’ ስትሠሩ ድርግም ሲል። እናንተን አያድርገኝ ያኔ!

እና ወደ ፉጨቴ ስመለስላችሁ ቀትር ሳልል ምሽት ‘ሰው መሆን አልቻልኩም ብርቄን ሰው ወድጄ’ እያልኩ ተያያዝኩት። ምነው በሰው ዘፈን እንዳትሉኝ ብቻ። ዋ ብያለሁ። ሰው በሰው ላብ ሰው በሚመስልበት በዚህ ጊዜ፣ ሰው በሰው ዜማ አቧራ በሚያስነሳበት በዚህ ጊዜ፣ ታምኖ የተሾመ የሕዝብ ገንዘብ እየዘረፈ ለራሱም ለሚወዱትም ሳይሆን እንዳሴረ በሚቀርበት በዚህ ጊዜ እኔን እንዳታሙና ክፉ እንዳልናገር። ይልቅ የሚረባውን ሥራዬን ውስጠ ወይራ በሆነች ፉጨት እያጀብኩ (ጉንፋን እኮ አይደለም የያዘኝ ፍቅር ነው፣ ተው ሰው አድርገኝ አንተ ሰው) ደፋ ቀና ስል ባሻዬ ሰምተው ያልጠበኩት ዕዳ ውስጥ ከተቱኝ። እኔ ሳልሰማ ለሠፈርተኛው ሁሉ፣ ‹‹ሲያፏጭ ከሰማችሁት እጅና እግሩን ይዛችሁ እኔ ዘንድ አምጡት፤›› ብለው አስከለከሉኝ። ‹‹በገዛ ፉጨቴ ባሻዬ? በአዲስ ዓመት ዋዜማ ያውም ያለ መንግሥት በጀት በራሴ ወጪ ባፏጭ ምነው? ምነው?›› ብዬ እግራቸው ሥር ወደቅኩ።

‹‹ባይሆን በዓሉን ውለን ታፏጫለህ። እስከዚያ ግን አይሆንም። እባብ ትጠራለህ፤›› ሲሉኝ ክው አልኩ። ባሻዬ እኔ የማላውቀው ሕይወት አላቸው? ከመቼ ወዲህ ነው ባዕድ እምነት የጀመሩት? ብዬ ትዝታዬን ስጠራጠር ነገሩ ገብቷቸው፣ ‹‹እባብ ስልህ ነገር ለማለት ነው። እስከ ዛሬ ነገር የጣለውን እንቁላል ሰብረን ሳንጨርስ ደግሞ አንተ አዲስ ልታስፈለፍልብን ነው?›› ብለው እንዳኮረፉኝ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ገቡ። እኔም ምንም ቢሆን ከባሻዬ ቃል አልወጣምና ፉጨቴን ትቼ ድለላዬ ላይ አተኮርኩ። ስመ ጥር የመሆን ህልሜም በምሥራቅ ቢባል በምዕራብ ከሰመ። አዲሱ ዓመት ሳይገባ ጭንገፋ ልቤን በደለው። ደግነቱ ሦስት ቤት በመደዳ ስላሻሻጥኩ ደህና ‘ቻፓ’ ኪሴ ገብቷል። ገንዘብ ዞሮ ዞሮ ኪስ ከገባ የልብን ነገር ማን ልብ ብሎት አትሉም?!

እናውራው ብንል የእኛ ነገር አያልቅም። ‘አመለኛ ፈረስ ልጓም ያላምጣል’ ብለን እንለፈው እንጂ ብዙ ብዙ መከርከም ያለበት ነገር አለ። ከባሻዬ ልጅ ጋር ትናንት አመሻሽ ላይ አንድ አንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን እያመራን ሳለን፣ አንድ ከሰውነት ደረጃ የወረደ ወጣት መጥቶ ፊታችን ወደቀ። ‹‹እናንሳው?›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ኧረ ተወው የት ታውቀዋለህ?›› አለኝ። ትተነው ወደ ግሮሰሪያችን ገባን። የግሮሰሪያችን ታዳሚ የዚያን ምስኪን መጨረሻ እርስ በርሱ ትከሻ ለትከሻ እየተንጠራራ ይከታተላል። አንዱ፣ ‹‹ይኼ ጫት ምናምኑ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገው...›› ይላል። ‹‹የለም ይኼማ የአዕምሮ በሽታ ነው። ቢታከም እኮ ይድናል። አካሚው ሳይጠፋ አሳካሚው ነው የጠፋው...›› ይላል።

‹‹የምን የአዕምሮ በሽታ ነው ደግሞ እሱ። ገና ለገና ዘመናዊ ነን ለማለት ሲሉ የሰሙትን መደጋገም አይደብራችሁም እንዴ? ይኼ አንድ ሁለት የሌለው የሰይጣን ሥራ ነው። ፀበል ቢሄድ በቃው። ተገላገለ...›› ይላል ወዲያ ማዶ ከባሻዬ ልጅ ጀርባ። ሌላው፣ ‹‹ተውት 2009 ነው። 2010 ሲገባ ይመለሳል...›› ይላል። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን ተሳሳቅን። አንዱ የአዕምሮ በሽታ ነው ሲል፣ አንዱ ሱሴ ነው ሲል፣ አንዱ ዘመን ነው ሲል የጋለ ንትርክ ተነስቶ አረፈው። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ተመልከት የአስተሳሰብ ልዩነትና የግንዛቤ እጥረት። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሰው በየፊናው ትክክል ነኝ ካለ አይመለስም። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አገር የሚለወጠው? በተጨባጭ ማስረጃ መተማመን ዘበት በሆነበት ጎዳና ድክ ድክ ብለው የሚያድጉትስ እንዴት ብለህ ተስፋ ትጥልባቸዋለህ?›› ሲለኝ ቆም ብዬ አሰብኩ። ማሰብ ደጉ ሕይወትን ቢገራው እንዴት ሸጋ ነበር!

በሉ እንሰነባበት። ማንጠግቦሽ በዓሉን በዓል አስመስላለሁ ብላ በጀት እያጎደለች ስታስቸግረኝ ሰነበተች። ከሚበላውና ከሚጠጣው አልፋ ለአመሻሽ ጨዋታ አዝማሪ ሁሉ ቀብድ ከፈለች። ሳትነግረኝ። አስቡት እስኪ። አንድ ምስኪን ደላላ ዓመት አልፎ ዓመት ገባ ብሎ ሲያሸልል ሲሸልል። ጓዳውን ሳያደራጅ ጎረቤት ሲያጫጭስ። ‹‹ምን ይሉታል ይኼን?›› ስላት፣ ‹‹ስትፈልግ ሄደህ ሴቶች ጉዳይ ክሰሰኝ፤›› አለችኝ። ‹‹ምን?›› ስላት፣ ‹‹አዲስ ዓመት ነው። ባይመስልህም ያረጀው እነሆ አዲስ ሊሆን ነው። አይ ካልክ ደግሞ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ብዬ እጠቁምብሃለሁ...›› ስትለኝ ማንጠግቦሽ አልመስለኝ ብላ በማታ ወጥቼ ኮከብ ስቆጥር አመሸሁ። ድሮ ድሮ የዘመን መለወጫ ጨፋሪዎች ኮከብ ቆጥረው ሲገቡ ነበር ቁጣው። አሁን ከኮከቡ በፊትም ተጀመረ ማለት ነው።

ይኼ ምን ይባላል? ካላችሁኝ ‹‹አዝ ኤ ፕሮፌሽናል›› ደላላ ስመልስላችሁ ‹‹ዕድገት›› ይባላል። ያለ የሌለንን ምግብ፣ መጠጥ፣ ሳር፣ ቅጠል ስትገዛበት እያየሁ እውልና ማታ ማታ በትካዜ ኮከብ እቆጥራለሁ። የዘንድሮ ክረምት ደግሞ ክፋቱ ዝናቡ አላቋረጥ ብሏል፡፡ እሱም አንድ ነገር ነው። ባሻዬ ኩርፊያዬን ሰምተው፣ ‹‹ምነው አንተ በአዲስ ዓመት ሟርት አበዛህ?›› ሲሉኝ፣ ‹‹ሟርት አይደርስም ብሎ የነገረሽ ማን ነው፣ እግር የሚሰበር ልብ አቂሞበት ነው፤›› ብዬ መለስኩላቸው። በተራቸው እሳቸው ኮከብ ሲቆጥሩ አመሹ። ዘመን ይመጣል ዘመን ይሄዳል። ልብ ብቻ አልቀየር እያለ በደስታ ዋዜማ ሲያስተክዘን ያመሻል። ቢሆንም ነገም አዲስ ይሆናል ብለን ብናስብስ? ማሰብ ደጉ ባይኖር ምን እንሆን ነበር? መልካም አዲስ ዓመት። መልካም ሰንበት!