Skip to main content
x

ምርት ገበያና መጋዘን አገልግሎት በሰኔ ወር መጨረሻ ዳግም ይዋሀዳሉ

  • የቡና ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ

ቡና ነጋዴዎች በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ በነበረው ቅሬታ መሠረት እንዲሁም በተለያዩ የአሠራር ችግሮች ሳቢያ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሁለት እንዲከፈል መደረጉ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት የተባለ መንግሥታዊ ተቋም ተመሥርቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆቷል፡፡ ይሁንና ተቋማት ለሁለት የከፈለው አሠራር ለሁለት ዓመታት ያህል ከተጓዘ በኋላ ከምርት ገበያው ጋር መልሶ እንዲዋሀድ፤ የሁለቱ ተቋማት ውህደትም በዚህ ወር መጨረሻ ዕውን እንዲሆን መወሰኑን ምርት ገበያው ይፋ አድርጓል፡፡

በአጭር በተቀጨው አሠራር ማዕቀፍ ውስጥ በአገሪቱ የግብርና ምርቶችን የወጪ ንግድ በማቀላጠፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲገኝ ለማስቻል ተስፋ ተጥሎበት የተመሠረተው የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት፣ በአንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና በሩብ ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረትም አብዛኛውን የምርት ገበያውን የሰው ኃይል በመጠቅለል ጭምር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ምርት ገበያው ከነበሩት 750 ሠራተኞች ውስጥ 600 ለአዲሱ ድርጅት መመደባቸው ይታወሳል፡፡

የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት ምርቶችን በማዕከል የማከማቸት አገልግሎት ለምርት ገበያውና ለላኪዎች ከመስጠት ባሻገር፣ የጥራት ደረጃ የማውጣት አገልግሎትም በዚሁ መጋዘን አገልግሎት ድርጅት እንዲሰጥ ተደርጎ ቆይቷል፡፡

የመጋዘን አገልግሎቱ ከምርት ገበያው መለየት እንዳለበት በጥናት ከጠቆሙት መካከል ለምርት ገበያው የአሥር ዓመት የፍኖተ ካርታ ጥናት በማጥናት አስተዳደራዊም ሆነ የኦፕሬሽን እንቅስቃሴው ምን መምሰል እንዳለበት እንዲሁም ላለፉት ዓመታት የተጓዘባቸውን ሒደቶች የገመገሙ አጥኚዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የመጋዘን አገልግሎቱ የተጠበቀውን ውጤት ሊያስገኝ ባለመቻሉ ግን በሚኒስሮች ምክር ቤት የተቋቋመበት ደንብ ተሽሮ በምትኩ የዳግም ውህደታቸው ሕግ መርቀቁንና ይህም ፀድቆ ወደ ተግባር መገባቱን ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡

ይህ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ የቡና ግብይት አሠራርን ለማሻሻል ሲባል እንደሆነም ታውቋል፡፡ ምርት ገበያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቡና ልማትና ግብይት ላይ የሚታዩን ለዘመናት ሥር የሰደዱ ማነቆዎችን ለማስወገድ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ዘመናዊ የቡና ግብይት ተደራሽነትን ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም የምርት ባለቤትነትንና የቡና መገኛ ሥፍራን ገላጭ የሆነ የመኪና ላይ የቡና ግብይት ማካሔድ፣ አቅራቢዎች፣ ሻጮችና ገዥዎች ያለአገናኝ መገበያየት የሚችሉት መንገድን ለመፍጠር እንዲረዳም ምርት ገበያው ገልጿል፡፡

እነዚህን ለውጦች በተግባር ለማዋል ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸው ምርት ገበያ፣ አዳዲስ የግብይት ሞዴሎች መዘጋጀታቸውንና እነዚህን ሞዴሎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስደግፎ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የአጠቃቀም ማሻሻያዎች መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

በቡና ጀምሮ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ማሾና ሌሎችም የቅባትና የሰብል ምርቶችን የሚገበያየው ምርት ገበያ ድርጅት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲመሠረት የግብይቱ ዘይቤ በጩኸት የሚከናወን ነበር፡፡ ገዥና ሻጭ ፊት ለፊት ቀርበው፣ ሻጭ የሚሸጥበትን ዋጋ ገዢም የሚገዛበትን መጠን ከፍ ባለ ድምጽ በማስተጋባት፣ በዋጋ ከተስማሙ በመጨባበጥ ግብይቱን ያፀኑ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን የሚቀይር፣ በኮምፒዩተር የታገዘ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ዘዴ መተግበር ጀምሯል፡፡፡ በዚህም ከአዲስ አበባ ባሻገር በክልል ከተሞች የተስፋፋው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓቱ በጩኸት ሲደረግ የነበረውን ግብይት ሙሉ ለሙሉ ሊተካው ጫፍ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡