Skip to main content
x
ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት አይበርታ!

ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት አይበርታ!

ሐሳብ እንደ ጅረት ሲፈስ፣ ማሰላሰልና መወያየት የአገር ልማድ ሲሆን አርቆ አሳቢዎችና አስተዋዮች ይበዛሉ፡፡ አርቆ አሳቢነት ሲነጥፍ ግን ምክንያታዊነት የሚጎድላቸው ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ በስሜት መነዳት የሚከተለው ምክንያታዊነት ሲጠፋ ነው፡፡ አገር በስሜት አትመራም፡፡ አገርን ለመምራት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለአገር ማሰብም ሆነ መቆርቆር እንዲሁ፡፡ አንድ ዜጋ መብቱን ሲጠይቅም ሆነ ግዴታውን ሲወጣ ከስሜት ይልቅ ምክንያታዊ መሆን አለበት፡፡ ምክንያታዊነት ዝም ብሎ የሚገኝ ክስተት ሳይሆን በትምህርት፣ በልምድ፣ በሐሳብ ልውውጥና በማገናዘብ ነው፡፡ የሐሳብ ፍጭት በሌለበት ዕውቀት አይገኝም፡፡ ለአገር ይጠቅማሉ የሚባሉ ሐሳቦች ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጡ ሊደመጡ ይገባል፡፡ የመቀበልና ያለመቀበል መብቱ የአዳማጩ ብቻ ነው፡፡ ሐሳቦች በተገቢው መንገድ መፍሰስ አለባቸው፡፡ ሐሳቦች ሲገደቡ ዕውቀት ይነጥፋል፡፡ ፈጠራ ይደርቃል፡፡ ድህነት ያናጥራል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ሲታይ ደግሞ ሐሳብ ሲገደብ ከዕውቀት ይልቅ ማይምነት ይሰፍናል፡፡ ምክንያታዊ መሆን ይቀርና ስሜታዊነት ይዳብራል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን የሐሳብ ነፃነት ልዕልና ማግኘት አለበት፡፡ የሐሳብ ነፃነት በሌለበት አነስተኛና ጥቃቅን ቅሬታዎች ወደ የማይታረቁ ቅራኔዎች ይሸጋገራሉ፡፡ ቅራኔዎች ሲጦዙ ደግሞ ጥላቻ ይበረታል፡፡ ወደ ግጭት ይሸጋገራል፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንዳለ ይገመታል፡፡ ከዚህ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች የሆኑ 70 በመቶ ናቸው፡፡ በመላ አገሪቱ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዓመት ከ120 ሺሕ በላይ ዜጎች ይመረቃሉ፡፡ ከዲፕሎማ እስከ ዶክትሬት መርሐ ግብር ማለት ነው፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች የሚመረቁት ደግሞ እጥፍ ያህል ናቸው፡፡ ከዚህ አነስተኛ ስታትስቲካዊ መረጃ መረዳት የሚቻለው፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ትምህርት ቀመስ እየሆነ መምጣቱን ነው፡፡ ትምህርት ደግሞ መጀመሪያ አካባቢን መረዳት፣ ቀጥሎ ደግሞ ማሰብና ማሰላሰል ታክሎበት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ልሂቅ መሆን በመቻል ከዓለም በረከቶች መጠቀም ማለት ነው፡፡ አዕምሮ በነፃነት ሲያስብና ነገሮችን ፈልፍሎ ለመረዳት ሲጣጣር ሞጋች ትውልድ ይፈጠራል፡፡ በስሜት የሚነዳ ሳይሆን በምክንያታዊነት ላይ የሚመሠረት ማለት ነው፡፡ በጥልቅ የሚመረምርና የሚያዋጣውን ጎዳና መምረጥ የሚችል ደግሞ የተሻለች አገር ለመገንባት ብርቱና ምጡቅ አዕምሮ ያለው ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለው ግን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

በዚህ ዘመን አገርን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋለው ዋናው ችግር፣ ራስን ለነፃ ውይይትና ክርክር አለማዘጋጀት ነው፡፡ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ጥላቻ ውስጥ ሆኖ የአንድ ጎራ አጀንዳ ማቀንቀን ብቻ  ማገዶ ከመፍጀት ውጪ በሳል አያደርግም፡፡ አበው እንደሚሉት ‹አድሮ ቃሪያ› መሆን ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ እየሰበኩ የማይፈልጉትን ሐሳብ መላወሻ ማሳጣት መርህ አልበኝነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች እንደ ልባቸው የሚንሸራሸሩበት ማዕቀፍ እንጂ፣ ሐሳቦች የሚዳፈኑበት የአምባገነንነት ምድጃ አይደለም፡፡ ምክንያታዊነት የአገር ቤዛ እንዲሆን፣ ትውልድ የሚጠለልበት ታዛ መሆን እንዲችልና ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ እንዲንጎማለል በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ዓውድ መኖር አለበት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለ ፍላጎት ግን ዜጎችን በስሜት እየተነዱ ለአደጋ የሚንደረደሩ ሮቦት ያደርጋቸዋል፡፡ የራሳቸውን ሳይሆን የሌሎችን እንደ ወረደ አስተሳሰብ ማራገፊያ በማድረግ ወደ ጥፋት መሣሪያነት ይቀይራቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር ጠንቅ ከመሆኑም በላይ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ያመክናል፡፡ ተረኛ አምባገነኖችን ይፈለፍላል፡፡

ዜጎች በሕግ የተረጋገጡላቸው መብቶች ሲጣሱ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለጥያቄያቸውም በአግባቡ የመደመጥና ምላሽ የማግኘት መብት ስላላቸው፣ የሚመለከተው አካል ኃላፊነትም ግዴታም አለበት፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደታየው ዜጎች ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች  ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ለማዳመጥም ፈቃደኝነት እየጠፋ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ይጠፋል፡፡ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ መብትን መጠየቅም ሆነ መብትን አክብሮ ምላሽ መስጠት የአገር ወግና ልማድ መሆን ሲገባው፣ ብዙ ጊዜ ለግጭት የሚዳርጉ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ ሕግ ማክበር የምክንያታዊነት ማሳያ ነው፡፡ ሕግን ማስከበርም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን ዓይነቱን ሥልጡን መንገድ በመተላለፍ ሕገወጥነት ስለሚቀድም፣ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት የበላይነቱን ይይዛል፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንድ ሦስተኛው ክፍል መሠረታዊ መብቶችን በማካተት ዋስትና ሰጥቷል፡፡ እነዚህን መብቶች ማስከበር ባለመቻሉ ግን የሐሳብ ነፃነት ክልከላ ያለበት ይመስል ድረስ በርካታ ስህተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የመደራጀት መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ባገኘበት አገር የፖለቲካ ምኅዳሩ ተበለሻሽቶ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመናምነዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ አሉ የሚባሉት እንኳን አቅመ ቢስ ሆነው ያሳዝናሉ፡፡ በዚያ ላይ ዜጎች በነፃነት የሚፈልጉትን ለመደገፍ ወይም ሐሳባቸውን ለመግለጽ አይደፍሩም፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕጉ ሳይሆን የሚከበረው አስከባሪው ነው፡፡ ይህ ለአገር አደጋ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር አለመቻል ክፉ አደጋ ነው፡፡ በምክንያታዊነት ሳይሆን በስሜት የመመራት አደጋ፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት የሚቀፈቀፈው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ሌላው ችግር በአገሪቱ ደካማ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የሚታየው አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም በሚባል ደረጃ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ጭፍንነት ተፀናውቷቸዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ጎራ ያሉት የተቃዋሚዎችን ማደግ፣ መመንደግና ማበብ አይፈልጉም፡፡ በዚያኛው ጎራ ያሉትም እንደ ጭስ ብን ብሎ ቢጠፋላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሁሉም ግን ዴሞክራሲ የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ ልክ እንደ ማስቲካ ሲያላምጡ ነው የሚውሉት፡፡ በተግባር ግን አያውቁትም፡፡ አንዳቸው የሌላቸውን ሐሳብ ከማዳመጥ ይልቅ፣ በራሳቸው ትርክት ውስጥ ሆነው ከነባራዊው ዓለም መንነዋል፡፡ በገዥው ፓርቲና ተከታዮቹ እምነት ተቃዋሚዎች ለአገር የማይበጁ ፍጡራን ሲሆኑ፣ ለተቃዋሚዎቹ ደግሞ ገዥው ፓርቲ አገር አፍራሽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከቶች ባሉበት ከስሜት በላይ መሆን አልተቻለም፡፡ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርሆች እየተጣሱ ተፎካካሪነትን በጠላትነት መፈረጅ ጌጥና ባህል ሆኗል፡፡ አሁንማ ለይቶለት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በመሳሰሉት ልዩነቶች እየታከኩ ችግሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማግዘፍ ተለምዷል፡፡ ዘረኝነት የተጠናወታቸው ከንቱዎች ነገን አስፈሪ በሚያደርጉ ዛቻ ውስጥ ሆነው እየፎከሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በስፋት እየተከናወነ ያለው ዕውቀት ቀስመናል በሚሉ ወገኖች ነው፡፡ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት ሲጎመራ ተምረናል የሚሉትን ዕውቀታቸውን መጠራጠር ይገባል፡፡ ምክንያቱም አውጥቶና አውርዶ ከሚያሰላስል አዕምሮ እንዲህ ዓይነቱ ተራና አስፀያፊ ድርጊት አይጠበቅምና፡፡

በአጠቃላይ አገር የምትከበረውና የምትታፈረው፣ በዕድገት የምትገሰግሰው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሰፍኖ ዜጎች በሙሉ በእኩልነት የሚተዳደሩትና የሁሉም ነገር ማሰሪያ ልጡ የሕግ የበላይነት የሚሆነው ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቀና ጎዳና እክል ሲገጥመው ግን አገሩን የሚሞላው ስሜታዊነት ነው፡፡ የሚጠይቅና የሚሞግት ሳይሆን የተነገረውን ይዞ ደሙ የሚንተከተክ፣ የሚያየውን ሳይሆን የሚሰማውን የሚያምን፣ ማስረጃ የሚጠይቅ ሳይሆን አሉባልታ እንደ ወረደ የሚጋት፣ በስሜት ውስጥ ሆኖ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለስ፣ ወዘተ. ማኅበረሰብ ለአገር አደጋ ነው፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከባድ  አይደለም፡፡ ቀና አስተሳሰብና ተነሳሽነት እስካለ ድረስ በዚህ ዓለም የማይፈታ ችግር የለም፡፡ አሁን ትልቁ ችግር ከጨለምተኝነት ለመውጣት አለመፈለግ ነው፡፡ ከጥላቻና ከመፈራረጅ ዳዋ ውስጥ መውጣት ካልተቻለ፣ ሕዝብን ማዕከል ያላደረገና ከምክንያታዊነት ጋር የሚጋጭ የስሜታዊነት ፈረስ መጋለብ ካልቆመ ችግሩ ገዝፎ ይቀጥላል፡፡ የውስጥ ችግርን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት አለመቻል ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ጠላት አገርን ሲወር የነበረው በውስጥ ድክመት እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ከጭፍን ጥላቻ ውስጥ ወጥቶ ለመነጋገር አሁንም ሰፊ ዕድል አለ፡፡ ይህ እንዲሰምር ደግሞ ልብን ሰፋ አድርጎ መቀራረብ ያስፈልጋል፡፡ ሁሌም በሁሉም ነገር መስማማት አይቻልም፡፡ ነገር ግን አማካይን ለመፈለግ አለመሞከር በስህተት ጎዳና ላይ ያናውዛል፡፡ በዚህ የሠለጠነ ዘመን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወጣቱ ትውልድ በየእርከኑ በትምህርት ገበታ ላይ ሆኖ፣ ምክንያታዊነትን እያስወገዱ ስሜታዊነትን መታቀፍ ያሳፍራል፡፡ ሥልጣን ከአገር በላይ አይደለም፡፡ የአንድ ጎራ ፖለቲካ አጀንዳ ከአገር አጀንዳ አይበልጥም፡፡ ይህችን የተከበረችና የታፈረች ኩሩ አገር አይመጥንም፡፡ ይህንን ታሪካዊና በተምሳሌትነቱ የተከበረ ሕዝብ አይወክልም፡፡ ልዩነቶችን እያራገቡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚበትን ዘመቻ ውስጥ መግባትም መሠልጠን ሳይሆን መሰይጠን ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት አይበርታ! ለእናት አገራችን አይበጃትምና!