Skip to main content
x
ሲወጡም ሲወርዱም ግብግብ?

ሲወጡም ሲወርዱም ግብግብ?

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከቦሌ ወደ ካዛንቺስ ነው። ሁሉም ሠፈር አቋራጭ እንጂ አገር አቋራጭ ባለመሆኑ፣ ከአንድ ራሱ በቀር ተጎታች ሳይኖረው ይሳፈራል። ወያላው ራቅ ብሎ ቆሟል። “የት ነው?” እያለ እርስ በርሱ ተጠያይቆ የሚሳፈረው መንገደኛ ብዙ ነው። የጎዳናው አቀማመጥ የሕይወት ገጾችን የሚወክል  ይመስላል። ለአንደኛው ቀላል ለአንደኛው ደግሞ ከባዱን ጎዳና እንደሚሰብኩ የወንጌል መጻሕፍት ተከፍቶ ሲታይ፡፡ አስተዋይ ብቻ ይኼንን ይለኛል። ሁሉም በመሰለው እንደመሰለው ይሮጣል፣ መንገድ ነውና። የተሸወደው ወደ ኋላው ለመራመድ ዋጋ እየከፈለ፣ መስመሩን ያገኘው ደግሞ ወደፊት እየገሰገሰ። የማይጨበጠውን ለመጨበጥ፣ የሌለው እንዲኖረው፣ ያለው ለማካበት ሩጫ በሩጫ። ጎዳናው በገስጋሾች ታጭቋል። አልፎ አልፎ የቆመ አይጠፋም። አንዳንዱ ነዳጅ እንደ ጨረሰ መኪና አቅሙን አሟጦ ከመንገድ ወድቋል። በሞትና በሕይወት መሀል ውስጡን ማንም ሳያውቅለት።

ሌላው በቸልታ ‘ለማን ብዬ?’ ብሎ የሰው አጥር ተደግፎ አልያም የካፌ ወንበር አጣቦ ጥርሱን እየፋቀ አቃቂር ያወጣል። ሳይታገል እየደከመውና እየሰለቸው። ሞክሮ በከሰረው፣ በወደቀውና በተኮላሸው ይስቃል። የፍርኃት ሳቅ። ላለመንቀሳቀስ በሚያስር ስሜት ተገፋፍቶ። ‘ጎመን በጤና!’ እያለ ውስጡ ይሰቃያል። ምክንያታቸው ከበዛ ለማኞች ገሚሱ ተንጋሎ፣ ገሚሱ በጥሞና ተቀምጦ፣ ገሚሱ ከመንገደኛው እኩል እየተሽከረከረ ይለምናል። በእምነት፣ በአስተሳሰብና በአቋም ስም ርህራሔን ለመፍጠር ቃላት ይቀምራል። እንደ ታላቅ ባለቅኔ። ግን ይህ ሁሉ ጋጋታና ውዥንብር ምንም የማይመስለው ሲደጋገም ብቻ ነው። የየዕለት ሥራ ሲሆን፣ ሁሉም የተለምዶ ይሆናል። መንገድም ቢሆን!

“የመረጃ እጥረት ብሎ ብሎ ታክሲ ተራ ገባ?” ቢል አንድ ወጣት መንገደኛ፣ “ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች  መውረዱ መቼ ሊከብድ?” ሲል አዋዝቶ መሀል መቀመጫ ላይ ጎልማሳው መለሰ። “ሰው ምን አንደሚታየው እንጃለቱ ታክሲ ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ፤” ይለዋል አንድ ጎልማሳ አብሮት ለሚጓዘው ጓደኛው። “የዘንድሮዋን አሜሪካ እንዲህ እንደ ዋዛ መርገጥ አለ ብለህ ነው? ዕድሜ ለትራምፕ. . .” ሲለው፣ ‹‹ትራምፕን ለትራምፕ ተወውና ሰውን አትታዘብም? ታክሲ ውስጥ በነፃነት እንዴት እንደሚጨዋወት?” በአግራሞት እያየ ጠየቀው። “መብቱ ወረቀት ላይ ብቻ ነው ቢባልም የትም ይሠራል። ይልቅ የሚገርመኝ ሰው ታክሲ ሲሳፈር የሚያመጣው የማውራት ድፍረት ነው. . .” እየተባባሉ ቀጠሉ። አዳማጩ ጆሮውን አንቅቷል። የሚጥለውን እየጣለ የመረጠውን የሚለቅመውን ልቦውና ይቁጠረው። አላምጦ መዋጥና አጥርቶ ማዳመጥ ሕመሙ ሲከብደን አላውቀው ብለናል። አዳሜ ሳያላምጥ ሲውጥ ከነገር እስከ እንጀራ እያነቀው አለሳዝን ማለት ጀምሮላችኋል። አለመተዛዘን ‹ለካ እንዲህ ቅርብ ነው?› እንበል ይሆን?

“በዚህ ኑሮ እንጀራ እያነቀን ሲባክን፣ ነገር እያነቀን ስንባክን ጉድ አይደል? ብክነትና ብክለት ምነው መንገዱን ሞላው?” ሲል እንሰማለን ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ፡፡ “መባከን የመንገድ አንዱ ምልክት ነው ሲባል ስትሰሙ፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ደግሞ የብዙ ሰው አቅምና ዕድሜ ሲባክን አይታያችሁም?” ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ባለ ጉዳይ ወይዘሮ። “ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነን። መስሚያ የለንም. . .” ይላል ወያላው እያሾፈ። ‹‹አንተን ማን ጠየቀህ?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ወዲያው ደግሞ መንገዱ ዳር ካለው ቋሚ ግንብ ሥር ማንም አያየኝም ባይ ሰካራም ሽንቱን በሰመመን ይሸናል። “እግዚኦ!” ይላል በኃፍረት ተሸማቆ መንገደኛው። ሰካራሙን ላለማየት የታክሲዋ ጣራና መሬት ላይ ያፈጣል።

“እኔ እኮ የሚገርመኝ ክልክል ነው ሲባልም ይቻላል ሲባልም ተቃራኒ መሆን የምንወደው ነገር ነው። ማጨስ ክልክል ነው፣ ማለፍ ክልክል ነው፣ ወዘተ. ሲባል ቡራ ከረዩ። እልህ ያንቀናል። መለወጥ ይቻላል፣ ድህነትን ማሸነፍ ይቻላል ሲባል ቁዘማና መታከት። ምንድን የሚሻለን? ጋሽ ትራምፕ በዚህ ከቀጠሉ ደግሞ ይኼ የተከለከለ ነገር የሚወድ ወገኔ ጉዱን ማየት ነው፤” ሲል፣ “ፉከራና ቀረርቶ እንጂ እሺ ባይነትና ሥራ ስላለመደብን አይመስልህም?” አለው ጎልማሳው። ‹ስንቱን አሳለፍኩት ስንቱን አየሁት› ይላል የትዝታው ንጉሥ ከወደ ስፒከሩ!

አንድ አዛውንት ከሾፌሩ ጎን ተቀምጠው እስከ ኋላኛው መቀመጫ ድረስ በሚሰማ ሳቃቸውና ድምፃቸው ጋቢና ከተቀመጡት ተሳፈሪዎች ጋር ጨዋታ ጀምረዋል። “አቤት ብርዱ አኮማተረን፡፡ ስማ እ? እኔ ድሮ የቦቴ ሾፌር ነበርኩ። በረሃን አውቀዋለሁ እል ነበር። ግን ውሸት ሆኖ አገኘሁት። ይኼ ዘመንማ ለእንደኛ ዓይነቶቹ ሽማግሌዎች ስንቱን መሰላችሁ ውሸት ያደረገብን? እ? ሃሃሃ. . .” ይስቃሉ ለራሳቸው። ድንገት ደግሞ ኮስተር ብለው መሀል ላይ ያለውን ቀጠን ያለ ጎልማሳ አስተዋሉት። ፊታቸውን እንዴት እንዴት እንደሚያደርጉት እያየን በቀልዳቸው መገረም ከመጀመራችን፣ “አንተ እንዴት እስካሁን ሳታገባ ቀረህ?” አሉት ልክ እንደሚያውቁት ሁሉ። አልፎ አልፎ መንገዱ ሲለቀቅ አንደኛ ማርሽ በጭንቅ ለማስገባት ካልሆነ በቀር ፊታቸውን ከሁለቱ ተሳፋሪዎች  አይመልሱትም።

“አለማግባቴን እንዴት አወቁ?” ሲላቸው፣ “ወይ ጉድ ይህቺ ይህቺ መቼ ትጠፋናለች? አንዲት ቀዘባ ብትይዝ ኖሮ እንዲህ በአጥንትህ ባልሄድክ ነበር። እውነቴን ነው። እኔን አታየኝም። ሕይወቴ በረሃ ላይ ነው ያለቀው። አሁንም እንደምታየው እ? ግን ቦርጬ ይታይሃል? ከአገሬ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ያፈራሁት ይመስልሃል? አይደለም። ከባለቤቴ ጋር የምቋደሰው ሰላምና ፍቅር ነው። ለነገሩ የዘንድሮ ልጆች በቤት ምዝገባ፣ በአባልነት ምዝገባና በግብር ከፋይነት ምዝገባ ተወጥራችሁ ሸጋ ሚስት ማግኛ ምን ፋታ አላችሁ?” ብለው አሁንም ለብቻቸው ሳቁ። ቆዩና ድምፃቸውን ቀነስ አርገው በሹክሹክታ አንድ ወሬ አውርተው ሳቅ በሳቅ አደረጓቸው። እኛም ሳቅ አምሮን ባልሰማነው ጉዳይ ፈገግ። ወይ የስበት ሕግ!

ከፊታችን የተቀመጡ ወይዘሮዎች የሚጫወቱት በአካባቢያቸው ያለነውን ተሳፋሪዎች ቀልብ ስቧል። ሁለቱ ወይዘሮዎች እርስ በርሳቸው አንቱ እየተባባሉ ነው የሚጨዋወቱት። ዘመናቸው ያስጠናቸው እንዲህ ያለውን መቀባበልና መከባበር ብቻ ይመስላል። “ልጅዎ እንዴት ነው? እየተማረ ነው?” ይላሉ በመስኮቱ በኩል ጥግ የተቀመጡት። “ኤድያ ምኑን ይማረዋል? ያንዛርጠዋል እንጂ!” ይላሉ መልስ የሚሰጡት ወይዘሮ። “የለም መምከር መቆጣት ነው። ልጅ አይደል?” ሲሉ በምናብ የሳልነውን ታዳጊ ልጅ ጉዳይ ያነሱት ወይዘሮ “የዘንድሮ፣ ልጅ ነው የሚመከረው? ጫት እና ‘ቻት’ ያለ ዕድሜያቸው ይለምዳሉ አንድ ሲሏቸው አንድ ይላሉ። መቼ ያዳምጣሉ?” አሉ የወዲህኛዋ። “ይኼ ጫት ያላማረረው የለም እ? ታዲያ ምን እንብላ? 1,000 ብር በማትሞላ ደመወዛችን እንኳን ጤፍ ልንሸምት ከሱቅ እንጀራ ገዝቶ መብላት የሚቻል አልሆነም፤” ይላል ሌላው። ነገሩ እየተጋጋለ ሄደ። “መንግሥትስ እሱን ብሎ አይደል ወጣቱ ሲደነዝዝ በርቱ የሚል በሚያስመስል ዝምታ የተጀቦነው፤” ብላ ደግሞ አንዲት ወጣት ዘው አለች።

“ምን ብንለው ምን ስቅ ላይለው በከንቱ እኮ ነው ስሙን የምናነሳው፤” አላት ከጎኗ የተቀመጠ ጎልማሳ። “እሱስ እውነትህን ነው፤” ብላ ዝም ከማለቷ ሁለቱ እናቶች ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። “እሱ ፈጣሪ ይርዳቸው ማለት እንጂ ይኼን ዘመን ምን ዓይነት ምክር ያሳልፋቸዋል ብለው ነው?” ይባባላሉ። “እውነት ነው! እውነት ነው!” ሥጋትና ቅሬታ ልሳናቸው ውስጥ ለውስጥ ይሹለከለካሉ። ‘እህትማ ነበራት ያውም የእናት ልጅ፣ ተሟግቶ የሚረታ ወንድም አጣች እንጂ’ ሆኖባቸው ነገሩ ግራ ተጋብተዋል። ግጥሙን ሳይቀር ‘ኢትዮጵያ አገሬ ታጠቂ በገመድ፣ ልጅሽን ‹ሱስ› ነው እንጂ አይቀብረውም ዘመድ’ ብለው ሳይቀይሩት አልቀሩም። ኅብረት ጉልበት አጥቶ ትውልድ ምግባር ላይ ሲያለምጥ እያዩ የሚያደርጉት ቢያጡም በሐሳብ መብሰልሰላቸው አልቀረም። ምንስ ቢሆን የወለደ መቼ ይችላል?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጨዋታው ረገብ ብሏል። “አንዴ ፈጽመን ያሰብንበት ላንደርስ ዘላለም መጓዝ፤” ይላል አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት። ስልቹነት ከዕድሜው በላይ ተጭኖት አያለሁ። ለነገሩ ማን ያልተጫነበት አለ? “ወራጅ” ይላል አንዳንዱ። ቸኩሏል። “ቆይ ቦታ ይያዝ!” ይላል ወያላው። “እሰይ ደርሳችሁ ሕግ አክባሪ ሆናችሁ ደግሞ?! ምነው ሲያሰኛችሁ መሀል መንገድ ገትራችሁ ትጭኑን የለም እንዴ?” አለው አንድ ግልፍተኛ። “መጫንና ማውረድ ይለያያላ”! አለ ወያላው እያፌዘ። “ለነገሩ እውነትህን ነው። “መጫንና ማውረድ አንድ አልሆን ብሎ አይደል እንዴ ሕገወጡ የበዛው? ሙሰኛው እንደ አሸዋ በዝቶ ፍትሕ የሚሻው እንደ ከዋክብት የበዛው? መጫንና ማውረድ አንድ አልሆን ብለው ነው!” እያለ ብቻውን ማነብነቡን ቀጠለ ሰውዬው። 

ቦታ ከመያዙ ደግሞ ለመውረድ ግብግቡ አየለ። “ኧረ ጎበዝ ቀስ በሉ። ስንሳፈር ግብግብ ስንወርድ ግብግብ?” ብሎ ጎልማሳው ሄደ። ለጎልማሳው ሒስ ጆሮ የሚሰጥ የለም። ግብግቡ ቀጠለ። ቅድሚያ መሰጣጣት፣ መከባበር፣ መደማመጥ ደበዘዘ። አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው ወጣት፣ “ምነው እንዲህ የሚያልቀው መንገድ ሁሉ ጠባሳ በጠባሳ ሆነ?” አለኝ። መልስ አልነበረኝም። በዚህች ምድር የማውቀው ሲወጡም ሲወርዱም ግብግብ መሆኑን ነው። መልካም ጉዞ!