Skip to main content
x
በመደበኛው ፕሮግራም ተምረው ያልተመረቁ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ  መምህር ሆነው መሥራት እንደማይችሉ ተነገራቸው

በመደበኛው ፕሮግራም ተምረው ያልተመረቁ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መምህር ሆነው መሥራት እንደማይችሉ ተነገራቸው

የመጀመርያም ሆነ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመደበኛው ፕሮግራም ያልተማሩ ግለሰቦች፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመምህርነት ተቀጥረው መሥራት እንደማይችሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በቅርቡ ለ33 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በጻፉት ደብዳቤ እንደተገለጸው፣ የመጀመርያ ዲግሪ በክረምት የተማሩና ሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛ ወይም የመጀመርያ ዲግሪ በመደበኛ ሁለተኛ ዲግሪ በክረምት የተማሩ ግለሰቦች፣ በመምህርነት ተቀጥረው መሥራት አይችሉም፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ የወሰነው በተቋማት መካከል ልዩነት እንዳይፈጠርና የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እንዳይቀርብ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በ2004 ዓ.ም. የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር) ጊዜም ተመሳሳይ ደብዳቤ ተጽፎ እንደነበር ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. በፊት በዩኒቨርሲቲዎች የመምህራን ቅጥርን በተመለከተ በሚኒስቴሩ ብቻ ሲደረግ እንደቆየ የተጠቆመ ሲሆን፣ ነሐሴ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ዶ/ር ካባ በወቅቱ ለነበሩ ለ31 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በጻፉት ደብዳቤ እንደተገለገጸው፣ ከኢንጂነሪንግና ከቴክኖሎጂ፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚ እንዲሁም ከጤና ትምህርት መስኮች በስተቀር ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው ግልጽ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥተውና አወዳድረው መቅጠር ይችላሉ፡፡

የአሁኑ ሚኒስትር ዴኤታ በጻፉት ደብዳቤ እንደተጠቀሰው በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ከተማሩት በስተቀር ለዩኒቨርሲቲ መምህርነት መወዳደርም ሆነ መቀጠር አይችሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት ባሉት 33 ዩኒቨርሲቲዎች በክረምትና በማታው የትምህርት መርሐ ግብር በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ግለሰቦች፣ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲሪያቸውን እንደሚማሩ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ በፊትም በተለይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚህ መርሐ ግብር ያገኙ ባለሙያዎች ቁጥራቸው የበዛ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች እነዚህን ባለሙያዎች ለመምህርነት አወዳድረው እንደነበር ትምህርት ሚኒስቴር ጠቅሷል፡፡ ይህ ደብዳቤ ሊጻፍ ያስገደደበት ምክንያትም ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እነዚህ ባለሙያዎች እንዲወዳደሩ የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን በመቀበሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛው ተምረው በሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ መምህራን በአሁኑ ወቅት ትምህርት ሚኒስቴር በክረምት መርሐ ግብር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያስተማራቸውና እያስተማራቸው እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ትምህርት ሚኒስቴር ዕውቅና በሰጣቸው የዩኒቨርሲቲዎች ጨርሰውና ዲግሪያቸውን ይዘው ለዩኒቨርሲቲ መምህርነት አትቀጠሩም መባሉ፣ የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ወጥነት እንደሌለው ማሳያ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡

አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የትምህርት ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹በዲግሪያችን መካከል ልዩነት ካለ ለምን በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቃችኋል ብለው ማስረጃ ይሰጡናል?›› በማለት ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢው፣ ‹‹መንግሥት የሚያምነው በወረቀት ነው ወይስ በሰዎች ችሎታ?›› ሲሉም ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ መደበኛ ትምህርት ብቻ ብቁ ዜጋ የሚፈራበት ሆኖ ከታሰበ፣ መደበኛ ባልሆነው መርሐ ግብር ላይ ለምን ገንዘብና ጊዜ ማባከን እንዳስፈለገ እንዳልገባቸውም ተናግረዋል፡፡

ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ ‹‹ማንኛውንም ዲግሪ ከእነ ሙሉ ክብሩና ጥቅሙ ተብሎ የሚሰጠው ትምህርት ሚኒስቴር ሳያውቀው ቀርቶ ነው?›› የሚል ሌላ ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡