Skip to main content
x
በምግብ ኦሊምፒክ መድረክ በባህላዊ ምግቦች ተጠቃሚ ለመሆን ያለመው ማኅበር

በምግብ ኦሊምፒክ መድረክ በባህላዊ ምግቦች ተጠቃሚ ለመሆን ያለመው ማኅበር

የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን ለዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ማስተዋወቅ ለቱሪዝም ዕድገትም ሆነ ለሆቴሉ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ ምግቦችን ለማስተዋወቅም በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የምግብ ፌስቲቫሎችና ውድድሮች ዓይነተኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች (ሼፎች) ማኅበር አገራዊ ፌስቲቫል ለማከናወን አቅዶ ተነስቷል፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከማኅበሩ ፕሬዚዳንትና የግልግል ካተሪንግ (ምግብ አቅራቢ ድርጅት) ባለቤት ዋና ሼፍ ሔኖክ ዘሪሁን ጋር ታደሰ ገብረማርያም ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር- ስለማኅበሩ አመሠራረትና እንቅስቃሴ ቢያብራሩልን፡፡

አቶ ሔኖክ- ማኅበሩ የተመሠረተው በዚህ ዓመት መጀመርያ ሲሆን፣ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሕጋዊ ዕውቅና አለው፡፡ በውስጡም 280 ዋና (ኤክስኪዩቲቭ) ሼፎችን ጨምሮ ጀማሪ ኩክ (የምግብ ዝግጅት) ባለሙያዎችን ያካተተ ነው፡፡ በተለይ ሼፎቹ በተለያዩ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች በሥራ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከመካከላቸውም ከአገር ውጭ በርካታ ልምዶችን ያካበቱ ይገኙባቸዋል፡፡ ማኅበሩ በአገራችን የቱሪዝም ዕድገት በተለይ በሆቴል ዘርፍ ላይ አዎንታዊ ለውጥን ለማምጣት ድርሻውን ከመያዙም በላይ ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓታችን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ አካል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማኅበሩ ተቀማጭነቱ ፓሪስ ፈረንሣይ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የሼፎች ማኅበር (ወርልድ ሼፍ አሶሴሽን) አካል ለመሆን ቅጽ በመሙላት የአባልነት እንቅስቃሴውን በማድረግ ላይ ያለ ሲሆን በቅርብ ጊዜያትም ሒደቱ ተጠናቅቆ ክፍያውን ፈጽሞ በአባልነት ይታቀፋል፡፡

ሪፖርተር- የዓለም አቀፉ ማኅበር አባል መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?

አቶ ሔኖክ- በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከጥቅሞቹም መካከል አንዱና ዋነኛው በመካከላችን ነፃ የሆነ የልምድ ልውውጥ እንደሚኖር ነው፡፡ በርካታ የውጭ ሼፎች ወደ አገራችን መጥተው ሥልጠና እንዲሰጡ ቢደረግ የሚጠይቁት ክፍያ በጣም ውድ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪያቸውን የመሸፈን ግዴታም ይኖራል፡፡ አባል ከሆንን ግን ብዙ ልምድና ዕውቀት ያካበቱ፣ በሙያቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ የውጭ ሼፎች በየወቅቱ ወደ አገራችን ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በዚህም ለአገራችን ሼፎች የአሠልጣኝነት ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር ምናልባት የሆቴላቸውንና የትራንስፖርታቸውን ወጪ መሸፈን ብቻ ነው፡፡ ሥልጠናውን የሚቀስሙትም የአገራችን ሼፎች ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች እንዲያካፍሉ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ሌላ የአገራችን ባህላዊ ምግቦች ለዓለም ኅብረተሰብ ለማስተዋወቅ የሚያስችል መንገድ ይከፍታል፡፡ ሙያተኞቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ምን ያህል ዕውቀት እንዳላቸው የምንመዝንበት ወይም የምንመዘንበት መድረክ ይሆናል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉት ሼፎች በውጭ አገር ነፃ የትምህርት ወይም የሥልጠና ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ መፈጠሩ ከጥቅሞቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር- ባህላዊ ምግቦችን በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ በምን መልኩ ነው ማስተዋወቅ የሚቻለው?

አቶ ሔኖክ- በዓለም አቀፉ ማኅበር አማካይነት በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ የምግብ ኦሊምፒክ ውድድር አለ፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበር አባል ከሆንን በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ የመሳተፍ መብት ይኖረናል፡፡ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ማስተዋወቅ የምንችለውም በእንደዚህ ዓይነት ዕድሎችን መጠቀም ስንችል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ህንድ ከዚህ በፊት በምግብ ዝግጅት በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ፈፅሞ አትታወቅም ነበር፡፡ አሁን ግን በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ምክንያት ምግቦቻቸውን በማስተዋወቃቸው የተነሳ ተፈላጊነታቸው በጣም ጨምሯል፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የህንድን ምግብ ለመመገብ ወደ አገሪቱ መጉረፍ ጀምረዋል፡፡ እኛም የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ብናደርግ ተጠቃሚ ለመሆን እንችላለን ብለን እናስባለን፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ ወር ውስጥ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምግቦችን ያካተተ ፌስቲቫል ለማከናወን አቅደን ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነን፡፡ ፌስቲቫሉ ያስፈለገው ኅብረተሰቡ ባህላዊ ምግቦችን እንዲያውቃቸውና ባለሙያዎችም በዓለም አቀፍ ምግብ አዘገጃጀት ላይ ምን ያህል ብቃትና ችሎታ እንዳላቸው ባለሀብቱ እንዲገነዘበው ለማድረግ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ባለሀብቱ ባለሙያዎች የዕውቀት እጥረት አለባቸው በሚል ጥርጣሬ የተነሳ ብዙ ዶላር የሚከፍላቸውን የውጭ ባለሙያዎችን የማስመጣቱን እንቅስቃሴ ገታ አድርጎ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ትኩረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር- በእንቅስቃሴያችሁ ዙሪያ ከየትኛው መንግሥታዊ አካል ጋር ነው የምትገናኙት?

አቶ ሔኖክ- ማኅበራችን እንደተቋቋመ የፌዴራል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ተጋግዘን እንድንሠራ በደብዳቤ አሳውቆልናል፡፡ የአገሪቱን ባህላዊ ምግቦች የምናስተዋውቀው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ተረዳድተን ለመሥራት የሚያስችለንን አካሄድ ፈጥረናል፡፡

ሪፖርተር- የዓለም አቀፍ የሼፎች ማኅበር በአሁኑ ጊዜ ስንት አባላት አሉት?

አቶ ሔኖክ- 78 አባላት አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አምስቱ የአፍሪካ አገሮች ማኅበራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ ደግሞ ስድስተኛዋ የአፍሪካ አገር ሆና ነው የምትመዘገበው፡፡

ሪፖርተር- የሼፎች የደረጃ ዕድገት ምን ዓይነት ነው?

አቶ ሔኖክ- በዓለም ደረጃ ያሉት ወደ 14 የሚጠጉ ማስተርስ ሼፎች ናቸው ፡፡ እነዚህን ሼፎች የራሳቸው ሆቴሎች ያሏቸውና ታዋቂዎች ናቸው፡፡ በአገራችንና በአፍሪካ ደረጃ ማስተርስ ደረጃ ያላቸው ሼፎች የሉም፡፡ በአገራችን የኮከብ ደረጃ ባላቸው ሆቴሎች ውስጥ በዋና ሼፍነት የሚሠሩት ‹‹ኤክስኪዩቲቭ ሼፎች›› ተብለው የሚጠሩ ሲሆን በሬስቶራንት ውስጥ ያሉት ደግሞ ‹‹ዋና (ሄድ) ሼፍ›› ተብለው ይጠራሉ፡፡

ሪፖርተር- የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች ሥልጠና ላይ ክፍተት አለ ይባላል፡፡

አቶ ሔኖክ- እዚህ ላይ በጣም ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ሙያው በመንግሥት ዕውቅና አግኝቶና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት እንደ አንድ ትምህርት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም ውስጥ እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን መንግሥታዊ በሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛና በአንዳንድ የግል ማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ ሲሰጡ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህም መካከል የግል ማሠልጠኛ ተቋማት ጠንከር ያለ ትምህርት ወይም ሥልጠና ሲሰጥ ቆይተው ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ነገሮች መወደድና ብዙ ከማትረፍ ፍላጎት አንጻር ጥራት የጎደለው አሠለጣጠን እየተሰጠ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ሪፖርተር- ሙያ ማኅበሩ ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ሔኖክ- ሙያው ወይም ሆቴሉ፣ እንዲሁም የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሚፈልገው መልኩ ላይ ያተኮረ የትምህርት አሰጣጥ መኖር አለበት በሚለው ላይ በደንብ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር- በሼፍነት ሙያ የሴቶች ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሔኖክ- እየተሳተፉ ነው፡፡ ሙያው በአገራችን የሚታወቀው በሴቶች ነው፡፡ ነገር ግን ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ሆቴሎች ላይ ብንመለከት በብዛት ያሉት ወንድ ሼፎች ናቸው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ሙያው ከጥበብ ውጪ የጉልበት ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ከማሠልጠኛ ተቋማት የሚወጡ ሴቶች ቁጥር ብዙ ቢሆንም ወደ ሥራ ሲገባ ግን ሴቶች ይቀሩና ወንዶቹ ናቸው የሚቀጠሩት፡፡ ሴቶቹ በሥራው ላይ የሚቆዩበትን መንገድ ማኅበሩ እያየና ክትትል እያደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር- የማኅበሩ የወደፊት ዕቅዱ ምንድነው?

አቶ ሔኖክ- የራሳችንን የሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል ለማቋቋም አቅደናል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበር አባል ከሆን በገንዘብና በዕቃ ይረዱናል፡፡ ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል ቦታ መንግሥት ቢያመቻችልን ጥሩ ነው፡፡ በየወሩ ቢያንስ አንድ ሆቴል ሲከፈት ይታያል፡፡ በዓመት ደግሞ 12 ይሆናል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የሠለጠነ ባለሙያ ለማግኘት በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችን የማግኘቱ ሁኔታ ያለው ከሆቴል ሆቴል በመነጣጠቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን የመነጣጠቅ ተግባር ለማስቀረትና በቂ ሙያተኛ ለማትረፍ የማዕከሉ መገንባት ወሳኝ ነው፡፡