Skip to main content
x

በሞረሽነት የመመስከር ሕገ መንግሥታዊነት

በውብሸት ሙላት

በቅርቡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ምስክሮችን የማወቅ መብት ስም ዝርዝርና አድራሻ ማግኘትን እንደማይጨምር የሚገልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ውሳኔ መነሻ የሆነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነአቶ መሐዲ አሊይ የክስ መዝገብ ላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የምስክሮቹን ስም ዝርዝር ባለመግለጹ ምክንያት ተከሳሾች የምስክሮችን ማንነት የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተጥሷል  ሲሉ ያቀረቡት ክርክር መነሻ በማድረግ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በመላኩ ነው፡፡

የምስክሮች ማንነትና አድራሻ ሳይታወቅ ቃላቸውን የሚሰጡ ከሆነ ምስክሮቹ ማንነታቸው ‘’ሞረሽ’’ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምስክሩን የሚያውቀው ጠሪው ብቻ ስለሆነ በሚያውቀው ምን ምን መጠየቅ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ሌላው ወገን ግን ከዚያው ከጥያቄው በመነሳት መስቀለኛ ጥያቄ ከማቅረብ የዘለለ ተዓማኒነቱን ለማስተባበል አይችልም፡፡ ምስክሩ ሞረሽ ስለሆነ፡፡ ‘ሞረሽ’ ማንነቱ እንዳይታወቅና ጠላት አደጋ እንዳያደርስበት ሲባል አንድ ሰው ሌላን የሚጠራበት ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍም ስምና አድራሻቸው ሳይታወቅ የሚመሰክሩ ሰዎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው በላከው ጉዳይ፣ ተከሳሾቹ ላይ ቀረበው ክስ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል፤ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ጥሰዋል ተብለው ነው፡፡ ጉባዔውም ተከሳሾች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት ማለትም የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ፣ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው ማለት  የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስምና አድራሻ የማግኘት መብት እንደማይጨምር የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በግልጽ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል በማለት ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንደማያስፈልገው አሳውቋል፡፡

በእርግጥ ጉባዔው ያሳለፈው ውሳኔ ከእዚህ ባለፈም ሌሎች ጉዳዮችንም ይዟል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው ግን ተከሳሾች በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ምስክር የመጠየቅ እንጂ ስምና አድራሻ የማወቅ መብትን እንደማይጨምር የገለጸውን የሚመለከት ነው፡፡

በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32(ሐ) ድንጋጌ መሠረት ለምስክሮች ጥበቃ ለማድረግ ማንነታቸውና አድራሻቸው ላይገለጽ እንደሚችል መደንገጉን ይታውቃል፡፡ ከዚህ አዋጅ በተጨማሪም በወንጀል ጉዳዮች ላይ ለምስክሮችና ለጠቋሚዎች ጥበቃ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4(ሸ እና በ) ማንነታቸውና አድራሻቸው እንዳይገለጽ፣ ወይም እንዳስፈላጊነቱ በመጋረጃ በስተጀርባ ሆነውና ተሸፍነው ማንነታቸው ሳይገለጽ ምስክርነታቸውን ሊሰጡ እንደሚችሉም ጭምር ሰፍሯል፡፡ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የሚመሰክሩባቸውን ሰዎች እንዲገለጽላቸው ሲጠይቁ እነዚህ አዋጆች ላይ የተቀመጡትን አንቀጾች ሕገ መንግሥታዊነት እየጠየቁ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በተጨማሪም ለምስክሮች ደኅንነት ተብሎ ማንነታቸውና አድራሻቸው ለተከሳሽ እንዳይደርስ የሚደረገው፣ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት አስመልክቶ ፍርድ ቤቱ ሲፈቅድ፣ ምስክሮቹ ለፍርድ ቤት አመልክተው ሲፈቀድላቸውና ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት የምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሽ እንዳይደርስ ሲወስን እንጂ በራሱ ውሳኔ ይህንን ማድረግ አይችልምም እያሉ ነው፡፡ በአዋጆቹ ላይ ግን በሞረሽነታቸው ለመመስክር የሚስማሙት ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም በውሳኔው ላይ ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ደኅንነት በሚመለከት አደጋ መኖር ወይንም አለመኖሩን አረጋግጦ መፍቀድ ወይም መከልከል ሥልጣን እንዳለው ገልጿል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በአንቀጽ 20(4) ምስክሮችን በሚመለከት የተደነገገው የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ እንጂ፣ የምስክሮችን ስም ዝርዝርና አድራሻ እንዲደርሳቸው መብት የሚሰጣቸው አለመሆኑን ወይም ግዴታ የሚጥል አለመሆኑን አሳውቋል፡፡

እንደ ተከሳሾች ሁሉ ለምስክሮችም ጥበቃ የሚሰጡ ሕጎች በየአገሮቹ አሉ፡፡ ጉዳዩም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ካገኘ ሰነባቷል፡፡ በተለይም በሩዋንዳና በዩጎዝላቪያ የዘር ማጣፋት ድርጊቶችን ተከትሎ በተቋቋሙ ችሎቶች እንዲሁም የሽብር ወንጀሎችን ተከትሎ በሚኖረው የፍርድ ሒደት ላይ ለምስክሮች ዋስትናና ጥበቃ ማድረግ በሰፊው እየተለመደ መጥቷል፡፡ ዋስትና የሚሰጠው ደግሞ በምስክሮቹ ብቻ ላይ ሳይገደብ ቤተሰብንም ያካትታል፡፡ ምስክሮቹን የሚያሠጋቸው ድርጊት ሊከሰት የሚችለው በሕይወታቸው፣ በአካላቸው ወይም በንብረታቸው ላይ ሊሆን ይችላል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም በሽብር፣ በዘር ማጥፋት፣ የተደራጁ ወንጀሎችን (ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ)፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለምስክሮች ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በብዙ ውሳኔዎች ላይ ተካትቷል፡፡  እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች በባሕርያቸው እጅግ አደገኛ ስለሆኑ እንዲሁም በርካታ ሰዎችን የሚያገናኙ በመሆናቸው ከሌሎች ሰዎች ጥቃት እንዳይኖር ለመከላከል ይረዳል፡፡ ጥቃቱ በቀጥታ በተከሳሹ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሰውም ሊፈጸም ይችላል፡፡ በመሆኑም ፍትሕ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የተከሳሹ መብት ብቻ ሳይሆን መጠበቅ ያለበት የምስክሮችም ጭምር ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የሁለቱን ወገኖች መብት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የአንደኛው ሊጎዳ ይችላል፡፡ የተከሳሹ መብት ሲጠበቅ የምስክሮች ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ የምስክሮቹ ሲጠበቅ የተከሳሹ መብት ይጣሳል፡፡ በእኛም አገር በፀረ ሽብርና በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጆች እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ፍትሕ ለማስገኘት ወጥተዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የተከሳሾችን መብት በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ የበለጠ ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ለምስክሮቹን ደግሞ አዋጆቹ ናቸው፡፡

በወንጀል የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ብቻ የሚመለከቱ የሰብዓዊ መብቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በምርመራ አለበለዚያም ደግሞ በክስ ሒደት ወቅት ሊከበሩና ሊጠበቁ የሚገባቸው መብቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ  የሚቀርቡባቸውን ማስረጃዎች መመልከትና መመርመርና ዓቃቤ ሕግ የሚያቀርባቸውን ምስክሮች መጠየቅን ያካትታል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲመሠርት በክሱ ላይ የሚገልጸውን የወንጀል ድርጊት ለማረጋገጥ የሚረዳውን ማስረጃ መግለጽ ይጠበቅበታል፡፡ የማስረጃ ዓይነቶቹ የሰነድ፣ የሰው፣ ገላጭና ተጨባጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ተከሳሽ የሆነ ሰው የቀረበበትን ማስረጃ ሳይመረምር፣ ምስክሮቹን በአግባቡ ሳይጋፈጥ የሚሰጥ ፍርድ የተከሳሹን መብት የሚያጣብብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተለይም ፍትሐዊ በሆነ የፍርድ ሒደት የመዳኘት መብት ይኖር ዘንድ የምስክሮች ማንነት ለከሳሽም ለተከሳሽም ሊገለጽ ይገባል፡፡ ማወቅም አለባቸው፡፡

እንደሚታወቀው፣ በወንጀል ጉዳይ ላይ ምስክርነት ግዴታ እንጂ መብት አይደለም፡፡ አንድ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን የሚያውቅ ሰው የሚያውቀውን ለፍርድ ቤት የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ የመመስከር ግዴታ ካለበት በመመስከሩ ሕይወቱም ሆነ ንብረቱ አደጋ ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡ ጥበቃ ሊደረግለት ግድ ነው፡፡ ቁምነገሩ ያለው የትኛውም ምስክር ለሕይወቴ እሠጋለሁ ስላለ ብቻ በሞረሽነት እንዲመሰክር ማድረግ ተከሳሹን ስለሚጎዳ እጅግ ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ማበጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሞረሽነት መመስከር እንዴት መፈቀድ አለበት? የሚፈቅደውስ ማን ሊሆን ይገባል? ለሚለው ግልጽ ሕግ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ጹሑፍ መነሻ የሆነው ጉዳይም አንዱ ክርክር ዓቃቤ ሕግ ስለፈለገ ብቻ ምስክሮችን በሞረሽነት ማቅረብ አይችልም የሚል ይዘት አለው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ሲያዘጋጅ ከወትሮው በተለየ አኳኋን የሰው ምስክሮችን አለመግለጹ ነው፡፡ ያልገለጸው ደግሞ የምስክሮች ሕይወት ለአደጋ ያጋልጣል ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከሰጠው ውሳኔ መረዳት የሚቻለው የምስክሮች ሕይወት ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በሚያቀርበው ማስረጃ መሠረት ይወሰናል፡፡ ስለሆነም በሞረሽነት የቀረቡ ምስክሮች ስምና አድራሻቸው እንዲታወቅ በችሎትም ቀርበው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ሊወስን ይችላል ማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ የተከራካሪዎችን ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት ተገድቦ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በዝግ ሊያስችል ይችላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተከስተዋል የሚለው ወገን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ከግልጽ ወደ ዝግ ችሎት ሊያስቀይር ይችላል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ችሎቱ በዝግ እንዲሆን መነሻ የሚሆነው የተከራካሪዎቹን (የተከሳሽና የተጎጂ ምናልባትም ዓቃቤ ሕግ) ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ አንደኛው ነው፡፡ ቀሪዎቹ የሕዝብና የአገር ጉዳዮች ናቸው፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ ነጥብ አለ፡፡ ተከራካሪዎች የሚለው ቃል ምስክሮችን የማያካትት ከሆነ ለምስክሮች ሲባል ችሎትን ዝግ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህ አንቀጽ በግልጽ ያስቀመጠው ተከራካሪ ወገኖችን እንጂ ምስክሮችን የሚያካትት አይደለም፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ምስክርን በሞረሽነት መስማት በግልጽ ችሎት ከመዳኘት እንደሚቃረን እንመለከት፡፡ ምስክሮችን በመጋረጃ ወይንም በሌላ መንገድ ደብቆ የክስ ሒደትን ማከናወን የችሎትን በር ከመዝጋት በእጅጉ የባሰ ነው፡፡ በተለምዶ ችሎት ዝግ ሲሆን ከዳኞች፣ ከተከራካሪ ወገኖችን፣ ችሎት እስከባሪና ጸሐፊዎች እንዲሁም ምስክሮችን ሳይጨምር ሌላ ሰው እንዳይሳተፍ ማድረግ ነው፡፡ ውሳኔ በሚሰጥበትም ጊዜ እንደ ሁኔታው የባለጉዳዮች እውነተኛ ስም ላይጠቀስ ይችላል፡፡ ፍርዱም ላይታተም ይችላል፡፡ 

ለምስክሮች ጥበቃ ከሚሰጥበት መንገድ አንድኛው ስማቸውና አድራሻቸው ሳይገለጽ፣ በአካል ችሎት ላይ ሳይገኙ፣ በመጋረጃ ተሸፍነውና ድምፃቸውን የሚቀይር መሣሪያ በመጠቀም ወዘተ. ሊመሰክሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ የአመሰካከር ሁኔታ የተከሳሹን መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ ወይም የመጋፈጥ መብትን በእጅጉ እንደሚያጣብብ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ለምስክሮች ጥበቃ የሚሰጥበት ሁኔታ የተከሳሽን የመጠየቅ መብት እንደሚያጣብብ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ለምስክሮች ጥበቃ የመስጠት ጉዳይ በአገሮች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት መወያያ ጭብጥ ሆኖ የተነሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን አጀንዳነቱ ያለቀለት ጉዳይ አይደለም፡፡ ቢያንስ በየአገሩ አጀንዳ ከመሆን አልቆመም፡፡ የምስክር ማንነት ከተደበቀ በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን ያጣብባል፡፡ ምስክሩን የመጠየቅ ወይንም የመጋፈጥ መብትን ያሳጣል፡፡ በመሆኑም በግልጽ ችሎት የመዳኘት ቀጥሎም ምስክርን የመጋፈጥን መብት በመቃኘት የምስክር ማንነት አለመገለጽ በምን ሁኔታ የተከሳሽን መብት አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚያስገባ እንመለከታለን፡፡

በግልጽ ችሎት በመዳኘት መብት መሠረት ማስረጃ የሚሰማው ተከሳሹ ባለበት በግልጽ ችሎት መሆን አለበት፡፡ ይህ መብት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም ላይ ይኼንኑ በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን አካትተውት እናገኛለን፡፡ 

በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን ማስከበር በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ሸፍጠኝነትን በማስቀረት የምስክርነት ቃሉ ትክክለኛ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ይህ መርህ ምስክሮች ሀቀኛና እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ለማጣራት የሚረዳና ተከሳሹ ምስክሮችን ለመመርመር ያለውን መብት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባሻገር ለውሳኔው ትክክለኛነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት መንግሥት ሕግን በመጣስ ከሕግ ውጭ ማስረጃን እንዳያቀርብ ይከለክለዋል፡፡ 

የምስክሮች ማንነት ሳይገለጽ የሚሰጥ ሲሆን፣ ግን ችሎቱ ለማንም ክፍት ቢሆንም እንኳን መስካሪውን ተከሳሽም ይሁን ዳኞቹ ስለማያዩትም ስለማያውቁትም የተዘጋ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ አንድ ምስክር በችሎት ቀርቦ ቃሉን ካልሰጠ ምስክርነቱ የስሚ ስሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምስክርነት ሲሰጥ ዋናው ተናጋሪ ለጥያቄ ስለማይቀርብ በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን ይነካል፡፡

በመሆኑም በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብትን ያሳጣል፡፡ ከዳኛም ጭምር የተዘጋ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የማስረጃ አመዛዘን ሕግ በሌለበት አገር ሲሆን፣ የተከሳሽን መብት የበለጠ ማጣበቡን ያባብሰዋል፡፡  

ምስክርን የመጠየቅ መብት ማስረጃን የመጋፈጥ መብት አካል ነው፡፡ ተከሳሹ የከሰሱትንና የሚመሰክሩበትን ሰዎች ፊት ለፊት የማየት መብት አለው፡፡ በፊት ለፊት የመጋፈጥ መብት መሠረት የግል ተበዳዩ ወይም አቤቱታ አቅራቢው ከመጋረጃ በስተጀርባ ሳይሆን በተከሳሹ ፊት ክሱን ማቅረብ አለበት ከሚል ነው፡፡ በተጨማሪም ምስክሮች መሃላ ፈጽመው በችሎት ፊት እየታዩ መመስከር አለባቸው፡፡ በመሆኑም ክስ የሚያቀርብ ሰው ከሚከሰው ሰው ፊት ቀርቦ የማሰማት ግዴታ አለበት፡፡

ከሳሽም ሆነ መስካሪ ሰዎች ፊት ቀርቦ እንጂ በድብቅ መክሰስም መመስከርም አግባብነት የለውም፤ ሆኖም ግን ተከሳሹ አግባብነት የሌላችው ባህርያት የሚንፀባረቅ ከሆነ ፊት ለፊት መቅረብ አያስፈልግም፤ የስሚ ስሚ ምስክሮችን ፊት ለፊት አግኝቶ መጠየቅ ስለማይቻል የስሚ ስሚ ማስረጃ ከዚህ መርህ ያፈነግጣል፡፡

ማስረጃን የመጋፈጥ መብት መስቀለኛ ጥያቄ በመጠየቅ የምስክሮችን ቃል ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የመጣል መብትን ያካትታል፡፡ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት ተከሳሹ እውነቱን ለማሳየት ስለሚረዳው መሠረታዊ መብት ነው፡፡ መስቀለኛ ጥያቄ የማስረጃ ተዓማኒነትን ለመፈተሸ የሚያገለግል ነው፣  ዳኞች ለማስረጃው የሚገባውን ክብደት በመስጠት ጉዳዩን ተረድተው ውሳኔ ለመወሰን ያስችላቸዋል፡፡ ይህ መብት ምስክር በመስማት ሒደት ተከሳሹ ተሳትፎ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡

በአንዳንድ አገሮች መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብት በርካታ ገደቦች ያሉበት ሲሆን፣ የወሲብን ጥቃት በሚመለከት አቤቱታ ሲቀርብ እንዲሁም የሕፃናት ምስክሮችን መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ አይቻልም፡፡

በመሠረቱ የምስክሮችን ማንነት ሳያውቁ መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብትን ገቢራዊ ማድረግ ይቻላል ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ቢሆንም የምስክርን ማንነት ማወቅ የመስቀለኛ ጥያቄዎችን አድማስ ያሰፋዋል፡፡ ተከሳሹ የምስክሩን ማንነት ካላወቀ፣ ስለኋላ ታሪኩና ስለዝናው ስለማያውቅ መስቀለኛ ጥያቄ ለመጠየቅ ይቸገራል፡፡ በጥቅሉ፣ ከላይ እንደተመለከትነው በአንድ በኩል ተከሳሽ ሊጠበቅለት የሚገባውን ማስረጃ የመጋፈጥ መብት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ መብቶችንና ጥቅሞችን ለማስከበር የሚኖረውን ፍላጎት በመመዘን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን መለየትና መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡

በሞረሽነት የሚሰጥ ምስክርነት መስቀለኛ ጥያቄ ከማቅረብና ማስረጃን ከመጋፈጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች የየራሳቸው አካሄድ አላቸው፡፡ የተለያየ ማስረጃን የመጋፈጥ መብት በ‘ኮመን ሎው’ እና በ‘ሲቪል ሎው’ የመጋፈጥ መብት የተከሰሰ ሰው የቀረቡበትን ምስከሮች ፊት ለፊት ቆመው  የመመርመር መብት ስለሆነ መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅን ይጨምራል፡፡

መሠረታዊ ጠቀሜታውም አቤቱታ አቅራቢ በተከሳሹ ፊት እንዲቆም ማድረግ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ የምስክር ማስረጃውን ተዓማኒነት ለመመዘን ዕድል ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመጋፈጥ መብት ከሳሹና ምስክሮች ምን እንዳሉ መስማት ብቻ ሳይሆን በፊቱ ቆመው የሚናገሩትን ማዳመጥ ስለሆነ የመጋፈጥ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ተከሳሹ አቤቱታ አቅራቢዎች በፊቱ ቆመው በእሱ ላይ የሚናገሩትን ማዳመጥና የሰውነት ሁኔታቸውን ማየቱ ተገቢ ስለሆነ በተከሳሹ ፊት መመስከር አለባቸው፡፡ ‘ኮመን ሎው’ በተለይ በስሚ ስሚ መርህ ልዩ ድንጋጌዎች ሥር ማስረጃን የመጋፈጥ መብትን ገደቦች የተቀበለ ሲሆን፣ ተናጋሪው በማይገኝበት ጊዜ ወይም ማስረጃው አስተማማኝ በሆነ ጊዜ የሚፎካከሩ ጥቅሞችን ማለትም ማስረጃን ለመጋፈጥ ተከሳሽ ያለውን መብትና  የፍትሕን ጉዳይ አጣጥመው የያዙ ናቸው፡፡

በ‘ሲቪል ሎው’ ማስረጃን የመጋፈጥ መርህ የወንጀል አስተዳደር አንዱ ምሰሶና የፍትሐዊነት መመዘኛ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በ‘ሲቪል ሎው’ ማስረጃን የመጋፈጥ መብት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በቅጡ የማይሠራበት የነበረ ሲሆን፣ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በጥያቄ የመመርመር ሥርዓት ገቢራዊ ተደርጓል፡፡ ማኅበራዊ ሥርዓትን ለመጠበቅና የሕዝብ ተቃውሞ እንዳይነሳ ለማድረግ ማስረጃዎች በሚስጥር ይያዙ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር የምስክሮች ማንነት እንዳይታወቅ ይደረግ ነበር፡፡ ይህም በወንጀል ጉዳይ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ለአታላይነት፣ ለሐሰተኛነትና ለወገናዊነት እንዲጋለጡ በር የከፈተ አሠራር ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎች ማስረጃዎችን ለመፈተሽ ዕድል አልነበራቸውም፡፡

በዘመናዊው ‘ሲቪል ሎው’ ግን ዓቃቤ ሕግና ተከሳሽ እኩል ጉልበት ይኑራቸው በሚል አስተሳሰብ ማናቸውም በወንጀል የተከሰሰ ሰው ስለጉዳዩ እንዲነገረው፣ ማስረጃንም እንዲመረምር የሚያስችል መርህ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መብት ተከሳሹ የቀረቡበትን ማስረጃዎችና ክርክሮች በሙሉ እንዲያውቃቸው ለነሱም ምላሽ እንዲሰጥባቸው ዕድል ይሰጠዋል እንጂ በቀጥታ ምስክሮችን የመመርመር መብትን አይጨምርም፡፡ በ‘ሲቪል ሎው’ የማስረጃ ማግለልን የሚመለከቱ የማስረጃ ደንቦች እጅግ ጥቂት በመሆናቸው ማስረጃን የመጋፈጥ መብት ብዙም ትኩረት የተሰጠው አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በአመዛኙ ወደ ‘ሲቪል ሎው’ የሚያዘነብል ሥርዓት ስለምንከተል ወደዚያው ማዘንበል ተገቢነት አይኖረውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ሕገ መንግሥቱ በተለይ በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩ፣ የተያዙና የተከሰሱ ሰዎችን በሚመለከት ከ’ሲቪል ሎው’ ይልቅ ወደ ‘ኮመን ሎው’ ስለሚያዘነብል ነው፡፡

ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት ሊከበር የሚችለው የቀረቡባቸውን ምስክሮች ማንነት ሲያውቁ እንጂ መናፍስት ይመስል አካልና አድራሻ ሳይታወቅ አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው በቀላሉ የመጠየቅን መብት አድራሻና ስም ማወቅን እንደማያካትት መግለጹ ትርጉም ሰጠ የሚያሰኘው አይደለም፡፡ ምስክሮችን የመጠየቅ መብት ምን ማለት እንደሆነና እንደምንስ ሊከበር እንደሚችል ማብራራትም ይገባዋል፡፡ በተከሳሽ ላይ የቀረቡ ምስክሮችን የመጠየቅ መብት ማለት መቼውንም ቢሆን ተከሳሽ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለምስክሩ የሚያቀርብትን ሥርዓት ብቻ ማመቻቸት አይሆንም፡፡ የጥያቄውንም ይዘት ይመለከታል፡፡ በአጠያየቅ አይገደብም፡፡

ማንነታቸው ሳይታወቅ የሚናገሩ መናፍስታዊ ምስክርን (Ghost Witness) ቃላቸው ሊሰጠው የሚገባው ክብደትም በአግባቡ ሊጤን ይገባዋል፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ በግልጽ የስሚ ስሚ ማስረጃ ተቀባይነት እንዳለው ይገልጻል፡፡ በሞረሽነት የሚሰጥ ምስክርነት በመሠረቱ በችሎት ስለማይሰጥ የስሚ ስሚ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በችሎት ቀርቦ ከሚሰጥ የስሚ ስሚ ምስክርነት በከፋ መልኩ የሞረሽነት ምስክርን መጋፈጥ ወይም በመስቀለኛ ጥያቄ የማስተባበል ዕድልን ስለሚያሳንስ፣ ፍርድ ቤቶች አፈቃቀዱ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያርጉ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ጥሩ ጉልበት ሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡