Skip to main content
x
በሞጀ ደረቅ ወደብ የተከማቹ ከሰባት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮችን እንዲያነሱ ለአስመጪዎች ጥሪ ቀረበ

በሞጀ ደረቅ ወደብ የተከማቹ ከሰባት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮችን እንዲያነሱ ለአስመጪዎች ጥሪ ቀረበ

በሞጆ ደረቅ ወደብ ዕቃ የጫኑ ከሰባት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮች ለዓመታት ተከማችተው በመቆየታቸው፣ አስመጪዎች በአስቸኳይ እንዲያነሱ የወደቡ ኃላፊዎች አሳሰቡ፡፡

 የሞጆ ደረቅ ወደብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ አየለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዩኒ ሞዳል ወደ መልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ዘዴ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት፣ በአስመጪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የተንዛዛ አሠራር ለመቀነስ ቢሞከርም አስመጪዎች ያስገቡትን ዕቃ ከደረቅ ወደቦች እያነሱ አይደሉም፡፡

በተለይ ውጭ አገር የሚኖረውን የወደብና የመጋዘን አገልግሎት ወጪን ለመቀነስና አስመጪዎች በተቀላጠፈ መንገድ እንዲገለገሉ በአገር ውስጥ ደረቅ ወደቦችን ማቋቋም ቢቻልም፣ አስመጪዎች የሚጠበቅባቸው አሟልተው ንብረት ባለማንሳታቸው በአሁኑ ጊዜ ከሰባት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮች መከማቻታቸውን ጠቁመዋል፡፡

አስመጪዎች በበኩላቸው የሚያቀርቧቸው የራሳቸው ምክንያት ቢኖሯቸውም፣ አብዛኞቹ ‹‹ፈቃድ ስላላቸው ብቻ›› ዕቃ አስገብተው የባንክ ሰነዳቸውን በማቅረብ አስፈላጊውን ቀረጥና ታክስ ላለመክፈል በመወሰናቸው፣ ኮንቴይነሮቹ ተከማችተው መቆየታቸውን አቶ አዲስ አስረድተዋል፡፡ የዕቃዎቹ ክምችት በደረቅ ወደቡ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ፣ አስመጪዎች በፍጥነት አስፈላጊ ክፍያ በመፈጸም እንዲያነሱ አሳስበዋል፡፡

የደረቅ ወደቡ ኃላፊዎች በቅርቡ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ሁለቱም አካላት ዕቃቸውን በማያነሱ አስመጪዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስዱ መወሰናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በበኩሉ በአገሪቱ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ዕድገት ለገቢ ዕቃዎች መበራከት ምክንያት መሆኑን ይገልጻል፡፡

ባለሥልጣኑ ችግሩ የተፈጠረው በአስመጪዎችና በባለሀብቶች ‹‹የኃላፊነት መጓደል ጭምር›› መሆኑን ገልጾ፣ ኮንቴይነሮቻቸውን ለማንሳት ዝግጁ ባልሆኑት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል፡፡

ባለሀብቶቹ በበኩላቸው ከባንክ የሚፈለገውን ሰነድ በፍጥነት አለማግኘታቸውን፣ በባሕርና ትራንዚት በኩል ስለገቢ ዕቃዎች መረጃ በሚፈለግበት ጊዜ እያገኙ አለመሆኑንና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶችን ለደረቅ ወደቡ እየገለጹ መሆኑን አቶ አዲስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ ለአገሪቱ የመጀመርያው ሲሆን፣ በ2001 ዓ.ም. ነበር የተቋቋመው፡፡ ወደቡ ሲቋቋም ታሳቢ የተደረገው የአገር ውስጥ ኮንቴይነር ማከማቻ አገልግሎት በመስጠት፣ በጂቡቲ ወደብ ዕቃዎች ሲቆዩ ወጪና ጊዜ ለመቀነስ ታስቦ ነው፡፡

ደረቅ ወደቦች ከመገንባታቸው በፊት መንግሥት ለጂቡቲ ወደብ በዓመት እስከ 70 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያወጣ እንደነበር መረጃዎች ያመለከታሉ፡፡