Skip to main content
x
በስህተት መንገድ ላይ መመላለስ በዛ!

በስህተት መንገድ ላይ መመላለስ በዛ!

‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም›› እንዲሉ፣ በስህተት ላይ ስህተት እየተደራረበ ከችግር ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡ መቼም ቢሆን ችግር ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ ነገር ግን አብሮ መዝለቅ አይቻልም፡፡ የማያዳግም መፍትሔ አፈላልጎ ራስን ከችግር ማላቀቅ ብልህነት ነው፡፡ ችግርን እያዳፈኑ ለበለጠ ችግር ራስን መዳረግ ግን ይቅርታ የማይደረግለት ጥፋት ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለውም ስህተትን በስህተት ለማረም የተደረጉ ጥረቶችን ውጤት ነው፡፡ የዛሬ ዓመት አገሪቱን ለቀውስ የዳረጉ ክስተቶችን የፈጠሩት ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ጥፋቶች ናቸው፡፡ ሕዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት አስተዳደራዊ ጉድለቶች፣ የፍትሕ መዛባቶች፣ የመብት ጥሰቶች፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል፣ መረን የለቀቀ ሙስና፣ የመሳሰሉት ሕገወጥ ድርጊቶችን የማስቆምና ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ነበረበት፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ሕገወጥነት ሲሰፍን ከማንም በላይ ተጠያቂነቱ የመንግሥት ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች ግድባቸውን ጥሰው በተፈጠረው ሁከት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካቶች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ አገሪቱ ለአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከርማለች፡፡ ብዙ ጉዳትም ደርሶባታል፡፡

በዚህ ሁሉ አስደንጋጭና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መንግሥት ራሱን አርሞና አስተካክሎ ለመቅረብ ጥረት መጀመሩ፣ ሹምሽር ማካሄዱ፣ በትንሹም በሙስና የተጠረጠሩትን መያዙ፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ቃል መግባቱ፣ ወዘተ. ይታወቃል፡፡ ይህ ሆኖ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ጉምጉምታዎች ይሰማሉ፡፡ የሥራ ማቆም አድማዎች ታይተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡ ከዚህ በፊት ለአመፅ መነሳት ምክንያት የነበሩ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ ሰላምና መረጋጋት እንዴት ይገኛል? በየደረጃው ችግሮች ይፈታሉ ከተባለ እንደ አንገብጋቢነታቸው በቅደም ተከተል ለመፍታት ለምን አዳገተ? ከዚህ ቀደም አገርን ቀውስ ውስጥ ለከተቱ ችግሮች ከሕዝብ ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ ማምጣት ለምን አቃተ? ለመሆኑ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አዳማጭ አላገኙም? ወይስ የማይታወቅ ሌላ ችግር አለ? ከዚህ ቀደም ከክልል እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ሹምሽር ተካሂዶ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ተጀምሯል እየተባለ ችግሩ እንደገና ለምን ያገረሻል? ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ከሕዝብ ጋር በቀጥታ ተነጋግሮ ችግርን ማወቅ ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማመንጨት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ መንግሥትና ሕዝብን ሆድና ጀርባ ያደረጉ በርካታ ጉዳዮች እንደ መኖራቸው መጠን፣ ሕዝብ ውስጥ ገብቶ የሚፈለገው ምን እንደሆነ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ በተዛቡ ሪፖርቶችና በተድበሰበሱ መረጃዎች ብቻ በመተማመን የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ሌላ፣ የመንግሥት ምላሽ ሌላ ሲሆን ሌላ ዙር ጠብ ይቀሰቀሳል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በአግባቡ እየታዩ በቅደም ተከተል ምላሽ መስጠት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡና የተወሳሰቡ ጉዳዮች እንዳሉም እርግጥ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር በግልጽ ተነጋግሮ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ደግሞ ውጥረቶችን ከማርገብ በላይ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ይረዳል፡፡ ነገር ግን እንደተለመደው ማድበስበስና ማውገርገር ሲጀመር ግን የጠብ ግድግዳዎች ይበረገዳሉ፡፡ በዚህ መሀል የራሳቸውን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ደግሞ ጠቡን ያባብሳሉ፣ የአገር ህልውና ለሥጋት ይዳረጋል፡፡ ይህ ከዚህ በፊት አጋጥሞ ትልቅ አገራዊ ቀውስ መፍጠሩ መዘንጋት አልነበረበትም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ያ ችግር ተዘንግቶ እንደ አዲስ እየዳኸ እየመጣ ነው፡፡

ስህተቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሊደጋገሙ ግን አይገባም፡፡ በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ ተመሳሳይ ነገሮችን በመፈጸም ውጤት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ አልያም ሆን ብሎ ችግር መፍጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የታየው መሠረታዊ ችግር በአንድ መንገድ ብቻ መመላለስ ነው፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚታየው ምስቅልቅል መሠረታዊ ምክንያቱ፣ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ የሚታየው የተለመደ ግትርነት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ችግሩ ከመካረሩ የተነሳ እንኳን ተቀምጦ ለመነጋገር ለመተያየት እንኳን አልተቻለም፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚታየው መሠረታዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው፣ ገዥው ፓርቲ አሁን እደራደራቸዋለሁ ከሚላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ላቅ ያለ ደረጃ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ ማግለላቸው እየታወቀ፣ የአሁኑ ድርድር ምን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል ማለት ተገቢ ነው፡፡ አንደራደርም ብለው ያፈነገጡ ኃይሎችም ይህንን ጉዳይ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ የእስካሁኑ ግትርነትና ድርቅና ማንንም መጥቀም ካልቻለ ሌላ ብልኃት ይዞ መቅረብ ተገቢ ነው፡፡ በስህተት ላይ ስህተት መሥራት ትርፉ መረሳት ነው፡፡ ለማንም አይበጅም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የአንድ ፓርቲ የበላይነት በነገሠበት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ በተፈጥሮው የተለየዩ አማራጮችን ይፈልጋል፡፡ በእኩል ሜዳ ላይ መወዳደር የማይችሉ ተፎካካሪዎችን ይዞ ዴሞክራሲ አለ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ቢያንስ ሁሉም እኩል አቅም ባይኖራቸው እንኳ ለሕዝብ ዳኝነት ሲቀርቡ ግን እኩልነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሕዝብ ከቀረቡለት አማራጮች ውስጥ የመምረጥ መብቱ ሲከበርለት ስለዴሞክራሲ መነጋገር ይቻላል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ በሕግ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና እውነተኛ ሲሆን ሕዝብ ይወክሉኛል የሚላቸው ይመረጣሉ፡፡ በመሠረቱ ዴሞክራሲና ሕገወጥነት ስለማይጣጣሙ አመፅና ሁከት ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ የሕዝብን ድምፅ የሚሹ ሕዝብን የሚያሳምኑ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን አንድ ጊዜ ማታለል ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ደጋግሞ ማታለል ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ እየደጋገሙ የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ሲባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሌም ንቁ ሆነው የሚጠበቅባቸውን ይፈጽማሉ፡፡ እየደጋገሙ መሳሳት አደጋ ስላለው ጥንቁቅ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ እሳቤ ውስጥ መሆን ሲቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዓመታት ሲዳክሩበት ከነበረው ማጥ ውስጥ ይወጣሉ፡፡ አገር ሰላም ይሆናል፡፡

ሁሌም እንደምንለው ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ማናለብኝነት ይነግሣል፣ ሥርዓተ አልበኝነት ይንሰራፋል፣ ሌብነት እንደ ሰደድ እሳት ይስፋፋል፣ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፣ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ቀውሶች ይፈጠራሉ፣ የሕዝብን ሕይወት የሚያመሰቃቅሉ ክስተቶች ያጋጥማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ካሁን በኋላ ትርምስ የሚፈጥሩ ድርጊቶችን መፈጸም የማይወጡት አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ወዘተ. የገቡበት ቀውስ አገርን ያመሰቃቀለና መንግሥት አልባ እስከመሆን የዳረገ ነው፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውድቀት ተምሮ በጣም የተሻለች አገር መገንባት ሲገባ፣ ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› በሚባል የደካሞች ፈሊጥ አገር ለማፍረስ የሚሯሯጡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ቀውስ እንዳይከሰት የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ችግሮችን የመፍታት ዳተኝነት ይታይበታል፡፡ በዚህ መሀል ጽንፍ የረገጡና ለአገር የማይጠቅሙ በዘረኝነት የታጀቡ ቅስቀሳዎች ይሰማሉ፡፡ በሕዝብ ላይ ውዥንብሮች እየፈጠሩ ሰላምና መረጋጋት ያደፈርሳሉ፡፡ መርህ አልባ ድርጊቶች በበዙ ቁጥር ስህተቶች ይደራረባሉ፡፡ ዋናው መፍትሔ ግን ከሕዝብ ጋር በግልጽ መነጋገር ነው፡፡ ሐሰተኛ ሪፖርቶችን ትቶ የሕዝብን የልብ ትርታ ማወቅ ለአገር ህልውና ይበጃል፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ በስህተት መንገድ ላይ መመላለስ እየበዛ ስለሆነ ጠንቀቅ ማለት ተገቢ ነው!