Skip to main content
x
በኢትዮጵያ የመኖር ዕድሜ ቢጨምርም ተላላፊ በሽታዎች ሕይወት እየነጠቁ መሆኑ ተመለከተ

በኢትዮጵያ የመኖር ዕድሜ ቢጨምርም ተላላፊ በሽታዎች ሕይወት እየነጠቁ መሆኑ ተመለከተ

ኢትዮጵያውያን በሕይወት የመኖር ዕድሜያቸው ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢጨምርም፣ ተላላፊ በሽታዎች ሕይወት እየነጠቁ ነው ሲል እ.ኤ.አ. በ2016 የተከናወነውና ሰሞኑን ይፋ የሆነው ‹‹ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚዝ›› አመለከተ፡፡

ከ1990 እስከ 2016 በሽታዎች በሰው ልጆች የመኖር ዕድሜ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ጫናን አስመልክቶ በ195 አገሮች ጥናቱ የተከናወነ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን የተመለከተው ዳሰሳ፣ በአገሪቱ የመኖር ዕድሜ በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን አስፍሯል፡፡ ሆኖም የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች፣ ቲዩበርክሎሲስ (ቲቢ) እንዲሁም ተቅማጥ የአገሪቱ የጤና ዘርፍ ችግር ሆነው እንደቀጠሉ አክሏል፡፡

የጨቅላ ሕፃናት ሕመሞች፣ ከመውለጃ ጊዜ ቀድሞ መወለድና ሌሎች ሕፃናትን  በተለይ የሚያሰጉ ሕመሞችን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጥናትና የመከላከል ሥራ እንደሚያስፈልግም በጥናቱ ሰፍሯል፡፡

የኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመቆየት ዕድሜ አስመልክቶም፣ እ.ኤ.አ. በ2016 የተወለዱ ወንዶች 64.7 ዓመት ይኖራሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው አሥር ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ7.9 ዓመት ብልጫ አሳይቷል፡፡ በዚሁ ዓመት የተወለዱ ሴቶች 66.5 ዓመት ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ ይህም እ.ኤ.አ. በ2006 ከነበረው የ9.2 ዓመት ጭማሪ እንዳሳየም ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመኖር ዕድሜያቸው እየጨመረ በሄድም ጤናማ አኗኗራቸው ግን በሕመምና በጉዳት እየተፈተነ መሆኑም በጥናቱ ታይቷል፡፡

እንደ ጥናቱ፣ በ2016 የተወለዱ ወንዶች ጤናማ ሆነው የሚኖሩት በግምት 57.2 ዓመት ሲሆን፣ የሴቶች ደግሞ 58.7 ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ጤናማ ሆነው የመኖር ዕድላቸው እየጨመረ መሆኑን ያሳያል፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ወንዶች ጤናማ ሆነው የሚኖሩት ዕድሜ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሲታይ ልቆ ተገኝቷል፡፡ በ1900 ከነበራቸው 39.3 ጤናማ ሆኖ የመኖር ዓመት ወደ 57.2 በማሻቀብ ከዓለም ቀዳሚ እመርታ የታየባቸው ሆነዋል፡፡

ጥናቱ ኢትዮጵያውያን የመኖር ዘመናቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልጾ፣ በአገሪቱ የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ ተቅማጥ፣ ቲቢ፣ የጨቅላ ሕፃናት ያልተስተካከለ የነርቭ ሥርዓትና የልብ ሕመም በሽታዎችን ቀዳሚዎቹ አምስት የሞት ምክንያቶች መሆናቸውን አስፍሯል፡፡ የጀርባ ሕመም፣ ከአይረን እጥረት የሚከሰት ደም ማነስ እንዲሁም ድባቴ በጥናቱ ወቅት የታዩ ሕመሞች ናቸው፡፡

ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናት ሞት እየቀነሰ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ፈተና ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ አንድ ሺሕ ሕፃናትም 43.4 በመቶው ይሞታሉ፡፡ ይህ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በተለይ ከታንዛኒያና ከኡጋንዳ የተሻለ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው 38.4 በመቶ ሞት ልቆ ተገኝቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ 2016 በዓለም ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ከእጥፍ በላይ የቀነሰበት ነው፡፡ በ2016 ከአምስት ዓመት በታች ካሉ ሕፃናት ከአምስት ሚሊዮን ያነሱ ሲሞቱ፣ እ.ኤ.አ. በ1990 የሞቱት ሕፃናት 11 ሚሊዮን ነበሩ፡፡

ጥናቱ እንዳመለከተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞትን መቀነስ ተችሏል፡፡ ሆኖም ከመጠን በላይ ውፍረት፣ ግጭት (ጦርነት)፣ የአዕምሮ ሕመምና ሱስ አምጭ ዕፆችን መጠቀም ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዳይመጣ አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በዓለም ከአምስት ለአንድ ሰው ሞት ምክንያት ነው፡፡ በ2016 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሁሉም በሽታዎች ከተከሰተው ሞት 72 በመቶውን ይዘዋል፡፡ ይህ በ1990፣ 58 በመቶ ነበር፡፡

ካለፈው አሥር ዓመት በፊት መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የስኳር ሕመም በገዳይነቱ 17ኛ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ዘጠነኛ ሆኗል፡፡

ገዳይ ባይሆኑም የጀርባ ሕመም፣ ማይግሬን የራስ ሕመም፣ የመስማት ችግር፣ ደም ማነስ እንዲሁም ድባቴ የዓለም ሕዝቦችን በ2016 የፈተኑ በሽታዎች መሆናቸው በጥናቱ ታይቷል፡፡