Skip to main content
x
በከባድ የጀርባ ሕመም የታወከው አትሌቲክሱ

በከባድ የጀርባ ሕመም የታወከው አትሌቲክሱ

በደረጀ ጠገናው፣ ከለንደን

አትሌቲክስ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ውጤት ብቻ ሳይሆን የማንነታቸው መገለጫ ከሆነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ከስድስት አሠርታት በፊት በሻምበል አበበ ቢቂላ ስኬት ከኢትዮጵያውያን ጋር ትውውቁን አንድ ብሎ የጀመረው አትሌቲክስ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ይህን አጠናክሮና ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማቆየት ደግሞ ለነገ ሊባል የማይገባ የውዴታ ግዴታ መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባ የብዙዎች እምነት ስለመሆኑ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የብስና ውቅያኖስ አቋርጠው በእንግሊዝ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ ያለውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲከታተሉት የነበረበት መንገድ ለዚህ ትልቁ ማሳያ ይሆናል፡፡

ይህ ዘገባ እስተጠናቀረበት ድረስ በሩጫው የውድድር ዘርፍ ብቻ እየተካፈለች ያለችው ኢትዮጵያ በእንስቶቿ ወትሮም በምትታወቅበት ረዥም ርቀት በተለይም በ10,000 ሜትር በአልማዝ አያናና ጥሩነሽ ዲባባ፣ እንዲሁም በወንዶች ማራቶን በታምራት ቶላ አማካይነት በተገኘው በአንድ የወርቅና በሁለት የብር ሜዳሊያ በደረጃ ሰንጠረዡ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተካታለች፡፡ በወንዶች 10,000 ሜትርና  በሴቶች ማራቶን ውጤት ማግኘት ያልተቻለው በጥቃቅን ስህተቶች ስለመሆኑም በስፍራው የነበሩ አሠልጣኞችና ሌሎች ሙያተኞች ሲያብራሩ ተደምጧል፡፡

ማንነታቸውን ከመግለፅ የተቆጠቡና ለአትሌቲክሱ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት ስፖርቱ ከዓለም አቀፍ መርህ ውጪ በሆኑ በተለይም የግል ፍላጎትን መነሻ ባደረጉ ነገሮች እግር ተወርች ተሳስሯል፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ. . .›› የሚለውን የአበው አነጋገር የሚጠቅሱ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች አትሌቲክሱ በእነዚህና ተዛማጅ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

የውጤቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ለስፖርቱ  በተለይም ይመለከተናል የሚሉ አካላት  ለቀጣይ ዕጣ ፈንታ እንቆረቆራለን የሚሉ ከሆነ ከጊዜያዊ ውጤቱ ጀርባ እየተቀጣጠለ ያለ፣ ቀላል የሚመስለው አደገኛ አዝማሚያ የማያዳግም የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያበጁለት እንደሚገባ ይጠይቃሉ፡፡ በአትሌቲክሱ ትርጉም የሌለው የወንዜነት አተያይ እየተስፋፋ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡ ቀደምቱ አትሌቶች ተቋሙን ለማስተዳደር ኃላፊነቱን በተቀበሉ ማግስት ከውጤቱ ጎን ለጎን ለብሔራዊ አንድነት ቅድሚያ እንደሚሰጡ አበክረው ሲናገሩ መደመጣቸው አይዘነጋም፡፡

በለንደን የሚገኙት የልዑካን ቡድን መሪዎች ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ብሔራዊ ቡድኑ ባረፈበት ጉማን ሆቴል፣ የቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከውጤቱ ባልተናነሰ ብሔራዊ አንድነቱ ላይ እየተሠራና ውጤትም ማሳየቱ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንትና የልዑካን ቡድኑ መሪ ገብረ እግዚአብሔር  ገብረማርያም አብራርተዋል፡፡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው ሻምፒዮናው ከተጠናቀቀ በኋላ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከተቋማዊ አደረጃጀቱ ጀምሮ ሁሉን አቀፍ የሆነ ተሐድሶ (ሪፎርም)  እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡  በባለሙያው ለማብራራት የተሞከረውና መሬት ላይ የሚታየው ሐቅ፣ በአመራሩ እየተነገረ ካለው በተቃራኒ መሆኑ ማረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል በሥፍራው የነበረው የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ታዝቧል፡፡

ሩጫና የቡድን ሥራ በለንደን

ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ማሽቆልቆል በምክንያትነት ከሚቀርቡ ነጥቦች መካከል ቀድሞ የነበረው የቡድን ሥራ መጥፋት ይጠቀሳል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የረዥም ርቀት ዋና አሠልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የቡድን ሥራ ውጤታማ የሚሆነው ተመሳሳይ ብቃትና ችሎታ ባላቸው አትሌቶች ካልሆነ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ዋና አሠልጣኙ ለዚህ ምሳሌ ብለው ያስቀመጡት በለንደን የዓለም ሻምፒዮና በ10,000 ሜትር በሴቶችም ሆነ በወንዶች ለቀረቡት አትሌቶች የነገሯቸው አቅማቸውን ተጠቅመው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ችግር እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በአሁኑ ወቅት በተለይም በረዥም ርቀት ተስፋ ያላቸው አትሌቶች እንደ ቀደምቱ በርቀቱ ረዥም ጊዜ ወስደው ውጤታቸውን ከማስጠበቅ ይልቅ ጥቅም ወደሚያስገኙ በተለይም ፅናትን ለሚጠይቁ የጎዳና ላይ ውድድሮች ትኩረት መስጠት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ይህ ወጣ ገባ የሆነው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች አካሄድና ዝንባሌ ለእንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ውጤታማነት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም አልሸሸጉም፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበው ታምራት ቶላ በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና የተወዳደረበትን ሁኔታ በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

 ወደ ለንደን ያቀኑ የአትሌቶች የግል አሠልጣኞች፣ ለብሔራዊ ውጤት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለትን የቡድን ሥራ እንደማይስማሙበትና ‹‹ጊዜ ያለፈበት›› ሲሉ ይተቹታል፡፡ ሩጫ ቀርቶ ምግብ ለመብላት እንኳን አቅም እንደሚጠይቅ የወቅቱ የረዥም ርቀት ንግሥት አልማዝ አያና ባለቤትና አሠልጣኝ ሶሬሳ ይናገራል፡፡ እንደ አሠልጣኙ የቡድን ሥራ ቀርቶ አትሌቶች በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተሰባስበው ለረዥም ጊዜ ልምምድ መሥራት በኢትዮጵያ ካልሆነ በሌሎች አገሮች የተለመደ አይደለም፡፡ ሻምበል ቶሎሳ በበኩላቸው ‹‹የብሔራዊ ቡድን አያስፈልግም›› በሚለው አይስማሙም፡፡

ከዚህም በላይ በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡድን ከሆቴል እስከ ውድድር ዝግጅት ድባቡ ለይምሰል ካልሆነ በተቋሙ አመራሮች እንደሚነገረው እንዳልሆነ ደፍሮ ለመናገር አስረጅ አያስፈልገውም፡፡ አትሌቶች ዝግጅቶቻቸውን ሲያደርጉ የተስተዋለው በፌደሬሽኑ አሠልጣኞች ሳይሆን ወደ ሥፍራው ባቀኑ የግል አሠልጣኞቻቸው ለመሆኑ ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ አትሌቲክሱ በከባድ የጀርባ ሕመም ተይዞ እንደሚገኝ ብዙዎች የሚያንፀባርቁት ሆኗል፡፡

በመስተዋት ያልተቃጠለችው ለንደንና ዝግጅቷ

ለንደን እንደ 2012 ኦሊምፒክ ለ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትኩረት የሰጠችው አይመስልም፡፡ ምናልባትም የለንደኑን አትሌቲክስ  ሻምፒዮና ለየት እንዲል የሚያደርገው የምጊዜም የአጭር ርቀቱ ፈጣን ሯጭ ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት ከሩጫው ዓለም ራሱን ማግለሉ ብቻ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ቦልት ለዚህ ዕውቅናውና ተወዳጅነቱ ትልቁን ድርሻ ለሚይዘው መገናኛ ብዙኃን የሚሰጠው ግምት በሩጫው ዓለም ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ ምሳሌ ሊሆናቸው እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ረገድ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አናሳ ለመሆኑ ሪፖርተር በለንደን ቆይታው ታዝቧል፡፡   

 ምርትና አገልግሎታቸውን ማስተዋወቅ የሚፈልጉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን ለመገናኛ ብዙኃን ባላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ መጠቀም ያለባቸውን ያህል እየተጠቀሙ እንዳልሆነም ማናጀሮቻቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ታሪኳንና ጥንታዊነቷን ጠብቃ ያለችው ለንደን አዲስ አበባን ለመሰሉ በመስተዋት እየተቃጠሉ በማደግ ላይ ለሚገኙ ከተሞች በማስተማሪያነት ልትወሰድ የሚገባት ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በለንደን ኦሊምፒክ ስታዲየም በመከናወን ላይ ከሚገኙ ዝግጅቶች መካከል 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር የሚሸፍነው ማራቶን ውድድር ተጠቃሽ ነው፡፡ ዝግጅቱ ለንደንን ለትዝብት ከዳረጋት ይገኝበታል፡፡ በዙር መልክ በየአስር ኪሎ ሜትሩ የተደረገው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊውን ታምራት አገላለጽ ቶላን ጨምሮ ለበርካታ አትሌቶች መጎዳት ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡ እንደ ታምራት ከሆነ እንደዚህ ዓይነት የማራቶን ዝግጅት በየትኛውም አገር ተደርጎ አይታወቅም፤ በዚያ ላይ ለውድድሩ ተብሎ የተመረጠው የአስፋልት መንገድ ለንደንን እንደማይገልጻት እግሩ ላይ የደረሰበትን ጉዳት በማሳየት አዘጋጅ ኮሚቴውን ይወቅሳል፡፡ አሰለፈች መርጊያን ጨምሮ በሴቶቹ ላይም ተመሳሳይ ችግር መፈጠሩ ተነግሯል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ይህ ነው የሚባል ችግር ባይከሰትም፣ የጀርመንና የጣሊያን አትሌቶችን ለተቅማጥና ትውከት የዳረገ ሁኔታ  መፈጠሩ፣ እንዲሁም በሆቴሉ በተለይም በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ተፈጠረ የተባለው የዝርፊያ ሙከራ ተብሎ የተሰራጨው ዘገባ ለንደንን ለትዝብት ከዳረጓት ይጠቀሳሉ፡፡