Skip to main content
x
በውክልና ወደ ፌዴራል የተዛወረው የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ወደ ከተማው ሊመለስ ነው

በውክልና ወደ ፌዴራል የተዛወረው የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ወደ ከተማው ሊመለስ ነው

የፌዴራል መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር በውክልና የወሰደው የገቢዎች ባለሥልጣን፣ በድጋሚ ወደ ከተማው አስተዳደር እንዲመለስ ተወሰነ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣንን በቢሮ ደረጃ ሊያዋቅር መሆኑ ታውቋል፡፡ 

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ›› በሚባል ስያሜ የሚቋቋመው ተቋም በካቢኔ አባል የሚመራ ይሆናል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሥር የነበረውና የከተማዋን ገቢ በብቃት መሰብሰበ ባለመቻሉ ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተዘዋወረው ገቢዎች ባለሥልጣን፣ በድጋሚ በአስተዳደሩ ሥር ለማዋቀር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ታውቋል፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከቢፒአር፣ ከባላንስድ ስኮር ካርድና ከካይዘን በተጨማሪ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያስችላል የተባለ ‹ዴሊቨሪ ዩኒት› የተሰኘ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ይህንን አሠራር ለከተማው ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለማስተዋወቅ በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደ ምክክር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ ገቢዎች ባለሥልጣንን ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተማው የራሱን ገቢ በበቂ ሁኔታ መሰብሰብ የሚያስችለው ቴክኖሎጂና የአመራር ሥርዓት መዘርጋቱንም አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ከፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ወጥቶ በከተማው አስተዳደር በድጋሚ እንዲደራጅ ለማድረግ፣ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሠሩ ማዘዛቸውም በምክክር መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በተጠናቀቀው 2009 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት 35.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ደግሞ 40.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር እያለ፣ የከተማውን በጀት የመሰበሰብ አቅሙ ከግማሽ በታች ነበር፡፡

ወደ ፌዴራል ተዛውሮ በቆየባቸው ስድስት ዓመታት ግን ዕቅዱን ለማሳካት የቀረበ የመሰብሰበ አቅም ላይ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በ2009 በጀት ዓመት የከተማው አስተዳደር በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አማካይነት 31.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ከዚህ ዕቅድ ውስጥ 26.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 85 በመቶ ሆኗል፡፡  ይህ የ2009 በጀት ዓመት 11 ወራት በጠቅላላ ገቢ በ2008 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተከናውኖ ከነበረው 23.89 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 11 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጪ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገና ከተማው እስከ 50 ቢሊዮን ብር ድረስ ያመነጫል ተብሎ ቢገመትም፣ አፈጻጸሙ አሁንም ደካማ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ የቴክኖሎጂና የአመራር ብቃቱ በመጎልበቱ ይህ ዕርምጃ መወሰዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ የሚመጡ ቅሬታዎችን ለመፍታት፣ ባለሥልጣኑን ወደ አዲስ አበባ መልሶ በቢሮ ደረጃ መዋቀር ማስፈለጉን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ የ2009 በጀት ዓመት ክንውንና የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ ለከተማው ምክር ቤት በሰኔ 2009 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት፣ በፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፈታት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮች በ2010 ዓ.ም. ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለው ነበር፡፡