Skip to main content
x

በዓላት የሕዝብ ናቸው

በገነት ዓለሙ

አገራችን የምታከብራቸው የሕዝብ በዓላት በሕግ የታወጁና በዓለምም የታወቁ ናቸው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የግል ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች፣ ባንኮችም ጭምር ለሕዝብ አገልግሎት ዝግ የሚሆኑበት በመሆኑ በተለይ በውጭ ታዋቂ ያደርጋቸዋል፡፡ በአገር ውስጥም ፀንቶ በቆየውና አሁንም ሥራ ላይ ባለው የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀን ሕግ፣ እንዲሁም የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን በተካው የ1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ፣ መሠረት ‹‹በግዴታ እንዲከበሩ በሕግ የተወሰኑ›› ናቸው፡፡ እነዚህ በዓላት የዘመን መለወጫ በዓል፣ የዓደዋ ድል መታሰቢያ ቀን፣ የድል ቀን፣ የዓለም ሠራተኞች የወዛደር ቀን (ሜይዴይ)፣ ግንቦት 20፣ መስቀል፣ ጥምቀት፣ የክርስቶስ ልደት፣ ስቅለት፣ ትንሳዔ፣ እንዲሁም ኢድ አልአድሃ፣ መውሊድና ኢድ አል ፈጥር ናቸው፡፡

የዘመን መለወጫ በዓል መስከረም 1 ቀን ድርብ በዓል መሆኑ የቀረው (‹‹ኤርትራ ከእናት አገሯ ከኢትዮጵያ የተዋሀደችበት ዕለት›› ጭምር ነበር) መስከረም 2 ቀን የሕዝብ ንቅናቄ (ረቮሉሽን) መታሰቢያ ቀን ሆኖ መከበሩ የተሰረዘው፣ እንዲሁም ግንቦት 20 በዓል የሆነው በሕግ ሳይሆን በ‹‹ተግባር›› ነው፡፡   

ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፤›› የተባለው (በሕገ መንግሥት ደረጃ) 1980 ዓ.ም. የኢትዮጵያ፣ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕድሪ) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46(3) መሠረት ነው፡፡ መንግሥትና ሃይማኖትን ‹‹ክፉኛ›› ያለያዩት ግን የሕዝብ በዓላት አዋጅና ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የሕዝብ በዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣው ከመጋቢት 1967 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው አዋጅ ነው፡፡

የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጁ ዛሬ (በሕግ በግልጽ ሳይሻር) ያረጀ፣ ያፈጀና የማይተገበር ቢሆንም በወቅቱና ሥራ ላይ በነበረበት ዘመን በዓላት እያንዳንዳቸው እንደምን እንደሚከበሩ በዝርዝር ይደነግግ ነበር፡፡ አጠቃላይ ገጽታውን ለማሳየት ሃይማኖታዊ ያልሆኑትን በዓላት (ዘመን መለወጫ፣ የሕዝብ ንቅናቄ (ሪቮሉሽን) ቀን፣ የዓደዋ ድል፣ የድል ቀን፣ ሜይደይ) መንግሥት የሚመራቸው፣ ርዕስ ብሔሩ ወይም ርዕሰ መንግሥቱ በበዓሉ ዋዜማ ወይም በበዓሉ ላይ በመገኘት ንግግር የሚያደርግበት ወዘተ፣ ያደርጋቸዋል፡፡ ሠልፉ ንግግሩ የሚካተተው በአጠቃላይ መንግሥት በሚመራው ‹‹ዝርዝር ፕሮግራም›› በሚያወጣበት በዚህ ዘርፍ ውስጥ ነው፡፡

መስከረም 17 ቀን የሚውለው የመስቀል በዓልና ጥር 11 ቀን የሚውለው የጥምቀት በዓል የከተማው ማዘጋጃ ቤትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚያወጡት ፕሮግራም መሠረት ከንቲባው ወይም የማዘጋጃ ቤቱ ሹም በሚገኝበት፣ የክርስቶስ ልደት፣ የስቅለትና የትንሳዔ በዓላት ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ በምታወጣው ፕሮግራም መሠረት እንደሚከበር ሕጉ ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይም ኢድ አል አድሃ፣ መውሊድና ኢድ አል ፈጥር፣ የከተማው ማዘጋጃ ቤትና የየመስጊዱ ዒማም በሚያወጡት ፕሮግራም መሠረት ከንቲባው ወይም የማዘጋጃ ቤቱ ሹም ይከበራል ሲል ይወስናል፡፡ በደርግ የአሥራ ሰባት የሥልጣን ዓመታት ውስጥ (የኢሕዲሪ የሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ጊዜ ጨምሮ) የበዓላት አከባበር ከሞላ ጎደል በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገዛ፣ ወቅቱና ጊዜው እንዳሳደረው የሚተዳደር ነበር፡፡

በዚህ ዘመን ‹‹ፀረ ሃይማኖት›› (‹‹እንኳን ደረሳችሁ››) ደርጉን፣ ‹‹ሃይማኖት አፍቃሪ›› ማለትም (እንኳን አደረሳችሁ) ኢሕአዴግ ተካው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ‹‹አብዮት አደባባይ››ን፣ መስቀል አደባባይ ብሎ እንደገና ሰየመ፡፡ እንደገናም አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው አለ፡፡ መንግሥት በተለይም ብቸኛ ሆነው ብቻቸውን በሚኖሩት የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሃይማኖት በዓላትን ራሱ ‹‹ማክበር›› ጀመረ፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ቀስ ብለው እንደ ቀልድና እንደ ዋዛ፣ ምናልባትም እንደ በጎ ተግባር የጀመሩት በዓል የማክበር ተግባር የመንግሥት ‹‹የሃይማኖት ጉዳዮች›› ሚኒስቴር ሚና እያጎናፀፋቸው መጣ፡፡

የመንግሥት የሬዲዮና የቴሌቪዥን የሕዝብ (በተለይም የሃይማኖት) በዓላት አከባበር ዋነኛ ፊታውራሪና ቃኚ መሆን ችግር በተወሰኑ ችግሮች ላይ የተመሠረቱና እየተለመዱ የመጡ፣ በዓል በመጣ ቁጥር በ‹‹ፍረጃ››ነት እየተመዘገቡ የሚታለፉ፣ የሁል ጊዜም ዕዳ የሆኑት ናቸው፡፡

ከእነዚህም መካከል አንዱና የታወቀው በበዓሉ ዕለት የሚቀርበው የተለመደ አንድ ዓይነት ዝግጅት፣ ከበዓሉ በፊት በቴሌቪዥን ጣቢያው አጀንዳና ካሌንደር መሠረት አስቀድሞ የሚቀረፅ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አሠራር መሠረት (ለዚያውም በሰው፣ በስፖንሰር ገንዘብና ወጪ) እሑድ የፋሲካ ዕለት ለሕዝብ የሚቀርብ ዝግጅት ከዚያ በፊት በዓብይ ፆም ውስጥ ቀሳውስት ካህናት፣ ምዕመናን በተሰበሰቡበት የቴሌቪዥን ጣቢያው ባዘጋጀው የፍስክ ፌስታ የብሉልኝ ጠጡልኝ ሆያ ሆዬ ‹‹ስክሪፕት› መሠረት ቴአትር የሚሠሩበት ትዕይንት ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ሙስሊሙም ምዕመን የኢድ አል ፈጥርን የእንኳን አደረሳችሁ የቴሌቪዥን ‹‹ፕሮግራም›› በአፍላው የረመዳን ፆም ውስጥ እንዲተውን ይገደዳል፡፡ የሌሎችም ሃይማኖታዊ በዓላት አከባበር ተመሳሳይና አቻ ማፈሪያዎች የሚመሰከርባቸው ትርዒቶች ናቸው፡፡ ቴሌቪዥን ካስፈለገ የሕዝብን የበዓል አከባበር (የሰውን የሃይማኖት ወይም የእምነት መብትና ነፃነት ሳይነካ) በመዘገብ ፋንታ፣ ሕዝብ ያለ ጊዜው ለቴሌቪዥን ‹‹ፕሮግራም›› እንዲሠራ ማስገደድ የሚጋፋው የሃይማኖት የዕምነትን መብት ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 18 የሚደነግገውን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት እንኳን የማይገደበውን ‹‹ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ›› የመጠበቅ መብት ይጋፋል፡፡ በአደባባይና በአድማጭ ያዋርዳል፡፡ ማፈሪያ ያደርጋል፡፡

ይህ ዓይነት አሠራር ከመለመዱና ሙያ ሆኖ ከመቋቋሙ የተነሳ ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. የተከበረው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ምክንያት በማድረግ በኢቢሲ የቀረበው ፕሮግራም ቀረፃ የተካሄደው፣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ሁለት ጊዜ መሆኑ የሚደንቅ ማሳያ ነው፡፡  

ይህ የጠቀስኩት ጉዳይ ከማሳያነትና ከተራ ምሳሌነት በላይ ራሱን የቻለ ዜናና ‹‹ታሪክ›› ነው፡፡ ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. የአረፋን በዓል ለማክበር ‹‹ታምሩ  ፕሮዳክሽን›› ከኢቢሲ ጋር በመተባበር ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ድረስ ያቀረቡት እንደገና የተቀረፀ ዝግጅት ነው፡፡ እንደገና የተቀረፀውም ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ እንደገና የተቀረፀበትም ምክንያት ከሳምንት በፊት ዓርብ ነሐሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቀረፀው ዝግጅት የተቀመጠበት ቋት (ዲስክ) አልከፍትም በማለቱ ነው፡፡ አሉ የተባሉ የሙያውና የመስኩ ባለሙያዎች ቢሉት ቢሠሩት እንቢ ይላል፡፡ ያን ሁሉ የዝግጅት ‹‹ትምህርት›› ቀልድ ኢንተርቪው ውኃ ይበላዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ላይ ስልክ እየተደወለ ታዳሚው ለድጋሚ ትርዒት ትዕይንት፣ ለድጋሚ ትወና (አክቲንግ) ይጠራል፡፡ የፈረደበት ታዳሚ እንደገና ይተውናል፣ የቃለ ምልልስ ቀልድ እንደገና ይሠራል፡፡ ዓርብ በበዓሉ ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓተ የቀረበው የኢቢሲ ዝግጅት ይህን የመሰለ መከራ የታየበት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሥራው እንኳንስ ከበዓሉ በፊት ስለመቀረፁ ለሁለተኛ ጊዜ ስለመቀረፁ እንኳን በዚያ ፕሮግራም አልተገለጸም፡፡ ጉዳዩን በሰማንበት መድረክ በአዘጋጆች በኩል ጎልቶ የወጣው ነገር ደግሞ፣ ‹‹ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብዓዊ የሆነው ክብርን የሚያዋርደው›› አያያዝ ሳይሆን አዘጋጆቹ የከሰሩት መቶ ሺሕ ብር ያህል ድጋሚ ወጪ የተባለው ነው፡፡ በዓልን በተለይም ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓልን እኔ አከብርልሃለሁ ማለት፣ ይህ ሕዝብን የመተካት አባዜ ገና ከዚህ የበለጠ እንዳያስከፍለን ያሠጋል፡፡   

የሃይማኖት እኩልነት መሥፈኑን ማረጋገጫ ለመስጠት ሃይማኖቶችና እምነቶች በእኩልነት የአከባበር ወግ ማዕረግ ማግኘታቸውን ለማስመስከር፣ ለዚህ ዓይነት ፖለቲካዊ ፋይዳው ሲባል የታወቁ ሃይማኖቶችና እምነቶች ዋና ዋና ሁነቶች የግድና ‹‹እኩል›› የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ያግኙ ይባላሉ፡፡ የእነዚህ መነሻ የአንዱን ሃይማኖት ከሌላው ጋር የማስተካከል በጎ ምኞት ቢሆንም፣ የአንዱን ሃይማኖት አንቀጸ እምነት የሌላው እኩልነት መለኪያ ማድረግ ሃይማኖቶችን በእኩልነት የማየት ቀና ፍላጎታችንን ሲበዛ ያበላሸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአንድን እምነት ሁነት በቀጥታ ሥርጭት ለመሸፈን የካሜራና የሥርጭት ቴክኖሎጂው ከሚጠይቀው ክህሎት በላይ የእምነቱን እሴቶችና ግዕዛን (Norms) ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማረጋገጥ ቀርቶ ስለመኖሩም በማይታወቅበት ሁኔታ ሥራው ውስጥ ዝም ብሎ ዘሎ መግባት ጣጣና ጠንቅ ያስከትላል፡፡

ከዚህ ሁሉ የባሰው ጉዳይ ግን አሁን አሁን መደበኛ አሠራር እየሆነ የመጣው በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ የተጀመረው የሕዝብ በዓላትን ለመንግሥታዊ ድጋፍ መሸመቻነትና መነገጃነት የመጠቀም የፖለቲካ አባዜ ነው፡፡ ሲከፋም ተቀናቃኝን ለማውገዝና ከሕዝብ ለመነጠል፣ እንዲያም ሲል ለማጋጨት ሃይማኖት መሣሪያ ሲሆን ዓይተናል፡፡ ይህንን የሚዘገንንና ያለፈ ጉዳይ እናስታውስ፡፡ ድኅረ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ቅንጅት ቤት የመዋል አድማ በጠራና በሞከረ ጊዜ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ሙስሊሙ የቅንጅት መሣሪያ አይሆንም አለ፡፡ በተለይም ከጥቅምት 23 ቀን 1998 ዓ.ም. ቀውስ በኋላ ሙስሊሙ በፆም ላይ እያለ ይህን መሳይ ነውጥና ሁከት መፈጸማቸው ቅንጅቶች ለሙስሊሙ ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ የሚገልጽ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ መዝሙር ሆነ፡፡ በእስልምና ጉዳዮች ጉባዔ አንዳንድ መሪዎችም በኩል ይኼው ውንጀላ በይፋ እየተደጋጋመ ተስተጋባ፡፡ ውስጥ ውስጡንም ቅንጅት የክርስቲያንና የአማራ ድርጅት፣ የተከሰተውም ቁጣ የክርስቲያን አማራ ተደርጎ እንዲታይ ብዙ ተጣረ፡፡ ይህ በማንምና በየትኛውም ወገን ቢሆን መወገዝ ያለበት ተሞክሯችን ነው፡፡

በዓለማችን ከሚታየው አሳሳቢና አንገብጋቢ ችግር አኳያ በአገራችን ያለው የሃይማኖት ሰላም እጅግ በጣም ሲበዛ ውድና ብርቅ ሀብታችን ነው፡፡ ባለብዙ ሃይማኖት በሆነችው የአገራችን የታሪክ ጉዞ ውስጥ በገዢዎች ምንም ተደረገ ምን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉንም ችለውና ተቻችለው እያሳለፉ አብሮ በመኖር እዚህ አድርሰውናል፡፡ መንግሥትና ኢሕአዴግ ድንገት በ2009 ዓ.ም. መሰናበቻ ላይ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመከባበር፣ የአገር ፍቅር፣ የአንድነትና የኢትዮጵያ ቀን የማክበር ዘመቻ አቀጣጥለዋል፡፡ እነዚህ ቃላትና ሐረጎች ትርጉም የሚኖራቸው አባቶቻችንና እናቶቻችን ችለውና ተቻችለው፣ በተለይም በሃይማኖቱ ዘርፍ ያስጨበጡንና በሰላም አብሮ የመኖር ቅርስ በአሁኑና በወደፊቱ ትውልድ አማካይነት በዘላቂነት መቀጠሉን የምናረጋግጠው፣ ዛሬ ያለንበት የመብትና የነፃነት ንቃት ደረጃ የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ተግባር መሸከም ከቻልን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ከመንግሥት እጅግ በጣም ብዙ ይጠበቃል፡፡ ይጠበቃል ማለት ከመንግሥት በኩል ችሮታንና ወሮታን፣ ከሕዝብ በኩል ደግሞ ልመናን አያመለክትም፡፡ ከመንግሥት የሚፈለገው ለሕግ የመገዛት፣ በሕግ የመተዳደር፣ ከሕግ በታች የመሆን ጉዳይ ነው፡፡   

አሁን ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት በተለይም የሃይማኖት ሰላማችንን በሚገባ ለመንከባከብ የሚያስችል ነባራዊና ህሊናዊ ጥሪት አለን፡፡ ጉድለቶችም አሉብን፡፡ ከጥሪቶቻችን መካከል በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ነው፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ ቃል ነው፡፡ በሕግ ደረጃ ይህ ተሟልቷል፡፡

መንግሥት ሰብዓዊ ክብርንና መብቶችን የሚጠብቅ፣ የሚከለክልና የሚያከብር ከእምነቶች ገለልተኛ ሆኖ መታነፅ ግን ብዙ ይቀረዋል፡፡

ሰፋ ወዳለውና ይህንን ወደሚያብራራው ጉዳይ እንግባ፡፡ መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ ይኼ ማለት የትኛውም ዓይነት ሃይማኖት ፖለቲካ ሆኖ በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት (ስቴት) ላይ ሊወጣና መንበረ መንግሥቱን የዕምነቱ መሣሪያ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሃይማኖት ፓርቲ ሊሆን፣ ፓርቲም የሃይማኖት አቀንቃኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ከብሔርተኛነት ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ተከስቶ ነበር፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚያን ዓይነቱን ቀዳዳ ደፍኖታል፡፡ ያ ቀዳዳ ክፍት ሆኖ ቢሆን ኖሮ የመንግሥት ገለልተኛነት የሚፈርስበት ዕድልም አብሮ ይኖር ነበር፡፡ (በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ውስጥም  ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡)

መንበረ መንግሥትን ከሃይማኖት ወገናዊነት የማራቅ መነሻና መድረሻ ሃይማኖቶችን መግፋት ሳይሆን፣ የትኞቹም ሃይማኖቶች በየትኛውም ሃይማኖት የበላይነት (ጫና) ሥር እንዳይወድቁ እኩል ተከባሪነትና የህልውና መብት እንዲያገኙ መጠበቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይኼንን ጽንሰ ሐሳብ የቆነጠጠ፣ ዕምነትን በኃይልም ሆነ በማስገደድ መገደብንም ሆነ ማስቀየርን የሚከለክልና መሠረታዊ የሲቪል መብቶችን በማይሽር ሁኔታ ለባህላዊና ለሃይማኖታዊ የጋብቻ ምሥረታና የዳኝነት ሥርዓቶች ቦታ የሰጠ ሕገ መንግሥት ሊያዋቅር መቻሉ ሁነኛ ጥንካሬ ነው፡፡ እናም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን ወይም መንግሥት ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትኛውም ሃይማኖት የሌላውን ሃይማኖት ነፃነት ሳይጋፋ እምነቱን የማራመድ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የቆመለትን እምነት በተመለከተ ትክክለኛ አተረጓጎሙና አያያዙ ይኼ ነው ብሎ መስበክ፣ የምዕመናንን ግንዛቤና የእምነት አተገባበር በማስተማር ማበልፀግ መብት ነው፡፡ በግድ መጫን ግን መብት መድፈር ነው፡፡ መስበክ መብት እንደሆነ ሁሉ መሰበክም የማይገድቡት መብት ነው፡፡ የተሰበኩትን (የተቀበሉትን) እምነት ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣ ላላ አድርጎ መያዝ፣ ወይም መቀየርና አለመቀየር የግለሰቡ መብት ነው፡፡ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ልጆቻቸውን በእምነታቸው ማነፅ መብታቸው ነው፡፡ የወላጅን እምነት ይዞ ለመቆየት ግን ተወላጅ አይገደድም፡፡ እነዚህን መብቶች ለመጣስ ማንም አልተፈቀደለትም፡፡ ማንኛውም ቤተ እምነት ነባር አማኞቹን ይዞ ከመቆየት ባሻገር አዲስ ተከታዮችን ለማፍራት የማስተማር ሥራ ማካሄድም ትርጉም የሚሰጡት፣ እነዚህ የግል መብቶች በመኖራቸውና በመረጋገጣቸው ነው፡፡

እናም የእምነት ቡድናዊና የግል መብቶች እንዳይረገጡ መንከባከብ፣ በሌላው ላይ ሲጓደሉ ሲያዩ እንኳ ነገ በእኔ ብሎ መቆርቆር የራስን የእምነት ተቋምና የምዕመናንን መብት የማስጠበቅም ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መሰሎቹን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ከማስከበር ውጪ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር መወገን የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኼንን ወይም ያንን የፖለቲካ ፓርቲ ደግፉ/ተቃወሙ/አውግዙ ብሎ ለምዕመናቸው መስበክ የሃይማኖት ተቋማትን አይመለከታቸውም፡፡ ምዕመናቸው የተለያየ የፖለቲካ እምነትና ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በአንድ እምነት ውስጥ የተለያየ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የየቤተ እምነት መሪዎች ኃላፊነታቸው ከፖለቲካ ውገና ገለልተኛ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ያለአድልኦ ማገልገል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት መወጋገን ከጀመሩ ለመንግሥታዊ ሃይማኖት መንገድ ይከፈትለታል፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ቢይዝ ድጋፍ የሰጠው ሃይማኖትም ባለ ልዩ መብት ልሁን ባይ ይሆናል፡፡ ወደ ሥልጣን የሚያመራ ወይም ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ፣ ለፖለቲካ ድጋፍ የሃይማኖት መድረክን ከመጠቀም መራቁና ይኼም ቀጣይነት ማግኘቱ ሃይማኖት ፖለቲካን እንዳይፈተፍት ይከላከላል፡፡

ይኼ ማለት ግን ፖለቲካና ሃይማኖት ጭርሱኑ አይደራረሱ ማለት አይደለም፣ ቢባልም የማይቻል ነው፡፡ ከእምነት ነፃናትና ከእኩልነት ጋር የተያየዙ መሠረታዊ መብቶች ተደፍረው ይኼንን በማውገዝ መንገድ ላይ፣ የፖለቲካ ፓርቲና ሃይማኖት ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አጥፊ ቅስቀሳ አድርጎ ሃይማኖታዊ አምባጓሮ ቢከሰት አነሳሹ ፓርቲ ተወጋዥ ከመሆን አያመልጥም፡፡

መንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትንም የሚያገናኟቸው ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ወደ መንግሥት አካላት ሊወስዷቸው ይችላሉ፡፡ የሃይማኖቶች ሰላም ጉዳይ ሃይማኖቶችንና መንግሥትን ያገናኛሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚኖራቸው የበጎ ሥራና የልማት ዕቅድ ከመንግሥት የልማት ዕቅድ ጋር ተጋጭቶ ብክነት እንዳይሆንባቸው፣ የልማት ዕቅዳቸውን ከመንግሥት ጋር ቢያገናዝቡ አስተዋይነት ነው፡፡ መንግሥት ከሚያካሂዳቸው (ከሚደግፋቸው) የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥም የሃይማኖት ጉዳይ ተደርገው ሊምታቱ የሚችሉ (የሃይማኖት መሪዎችን ማብራሪያና የቅርብ ድጋፍ የሚሹ) ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በተመለከተም አብሮ መሥራት ይኖራል፡፡

ከዚህ ያለፈ መጠጋጋት ግን ለመንግሥትም ሆነ ለሃይማኖት ተቋማት ጠቃሚ አይደለም፣ ወሰንን አልፎ በማያገባ ለመግባትም ያጋልጣል፡፡ በደርግ  ዕድሜ ማብቂያ ላይ እነ ሕወሓት በሃይማኖት መሪዎች “ወንበዴ፣ የአገር ጠላት” ተብለው እንዲኮነኑ የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚያ ዓይነት ጥፋት ዛሬ ላይደገም የሚችለው በሥልጣን ላይ ያለ ገዥ ፓርቲ ለፖለቲካ ዓላማ የሃይማኖት ተቋማትን መገልገያ ከማድረግ ሲፆም፣ የሃይማኖት ተቋማትም መንግሥት የወደደውን መውደድ፣ የጠላውን መጥላት ይገባኛል/ይጠቅመኛል ከሚል የአስተሳሰብ ቅፅር ግቢ ሲወጡ ነው፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ለገዥው ፓርቲ ቅርበት አላቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች ምርጫም ውስጥ የመንግሥት ሥውር እጅ ይገባል የሚል ሐሜት መነገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም ስለመታማቱ አይክድም፡፡ ‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ›› በተሰኘ የ“ሥልጠና” ወረቀቱ ላይ “በክርስትና እምነት መንፈሳዊ አባቶች ምርጫ ላይ እጁን አስገብቷል” (ገጽ 39) “ሙስሊሙም መሪዎቹን በነፃነት እንዲመርጥ አልተደረገም” (41) ስለመባሉ ተወስቷል፡፡ ከመሪ ምርጫ ባለፈም “መንግሥት አልሃበሽ የሚባል የውጭ እምነት አምጥቶ በላያችን ላይ ሊጭንብን ነው” የሚል እንቅስቃሴ እንደነበር ተጠቅሷል (41)፡፡ “ምርጫ ውስጥ እጅን አስገባ” ከመባል የበለጠ “እምነት ሊጭንብን ነው” ተብሎ መወቀስ ከባድ ነው፡፡ “ሊጭንብን” ቃሉ ራሱ ጠጣር ነው፡፡ በግል ጋዜጣና መጽሔት፣ በሹክሹክታና በመንገድ ሁሉ ሐሜቱና ቅዋሜው ሲንፀባረቅ ነበር፡፡

 ዋናው ጉዳይ የሐሜቱ እውነት ወይም ሐሰት መሆን ወይም የሐሜቱ ባለቤቶች ማንነት አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ መንግሥት መግባት በሌለበት ጉዳይ ገባ ተብሎ መታማቱ ነው፡፡ ዛሬም ነገም በመንግሥት ላይ ሌላ የጣልቃ ገብነት ሐሜት ቢመጣ “እሱማ የታወቀ አይደል!” ባዩ እንደሚበዛ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ይኼ ተዓማኒነት መጓደሉ ለመንግሥትም ለሃይማኖት ሰላምም ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ ክፍተቱ ተደፍኖ “ሐሰት! መንግሥት ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም!” ተብሎ ሐሜት የሚሸማቀቅበት ጊዜ እንዲመጣ የብዙዎች ፍላጎት ነው፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሐሜቱን ሐሰት ማለት ወይም የሐሜቱን ባለቤቶች “ሥውር ዓላማ” መደርደር ወይም ሐሜቱን በሥልጠና “ማጥራት” የጠንካራ ሥራ አብነቶች አይሆኑም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ልፋትም የተናጋን አመኔታ መልሶ አይጠግንም፡፡ መንግሥት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለሐሜት የዳረጉትንና ያጋለጡትን ተግባሮች ምን ምን እንደሆኑ እስካልመረመረና ለሐሜት የማይመች ያልተድበሰበሰና በተግባር የሚያሳምን ግንኙነት እስካላበጀ ድረስ ከሐሜት አይርቅም፡፡ ከሐሜት አለመራቅ ደግሞ ለፅንፈኝነት ግብዣ አሰናድቶና ቄጠማ ጎዝጉዞ እንደ መጠበቅ ያለ ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ላይ ላዩን በሚታየው ደረጃ እንኳ ምን ያህል ጥንቁቅ መሆን እንደሚያሻ የሚጠቁሙ አንዳንድ ነጥቦችን እንወርውር፡፡

የሃይማኖት በዓላትን መሠረት አድርገው መንፈሳዊ መሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ በእግረ መንገድ “አገራችንን ይባርክልን፣ ሰላማችንን፣ ፍቅራችንን፣ ዕድገታችንንና ልማታችንን ያብዛልን” የሚሉ ዓይነት መልካም ምኞቶችን ከመግለጽ ወጣ ያሉ “የዴሞክራሲ ግንባታን፣ የልማት መስመርን የማስቀጠል” ወይም በመጪው ምርጫ በንቃት የመሳተፍ ጥሪዎች ሲሰነዘሩ ያጋጥማል፡፡ የዚህ ዓይነት ወጋዊ ጥሪዎች መንግሥትንም ሆነ መርሐ ግብሮቹን ከሚበጁት ይበልጥ ለሐሜት የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የዚህ ዓይነት ጥሪዎች በውስጠ ታዋቂ የሚያመላክቱት ተቃራኒ መልዕክትም አለ፡፡ ለምሳሌ በቀጣዩ ምርጫ ምዕመናን በንቃት እንዲሳተፉ እናሳስባለን ባይነት በራሱ፣ ነገ ደግሞ በምርጫው አትሳተፉ ብሎ ለሚል ጥሪ ፈቃድ የሚሰጥ ነው፡፡

በመንግሥት በኩል ሲበዛ ጥንቁቅ መሆን የሚጠይቁ ሌሎች በርካታ ‹‹የማይመስሉ›› ምናልባትም የማይጠረጠሩ ተግባሮችንና ምሳሌዎችን ልጨምር፡፡

አንደኛው አደባባይ በሚከበሩ የሃይማኖት በዓላት ላይ የመንግሥት ተወካይ መገኘትና ንግግር ማድረግ ነገር ነው፡፡ ያ መድረክ የመንግሥት መድረክ አይደለም፡፡ እዚያ መድረክ ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚገኙት ግን በምዕመንነታቸው እንጂ በመንግሥት ተወካይነታቸው፣ የመንግሥትን ተልዕኮ ይዘው፣ የመንግሥትን አቋም ሊናገሩ አይደለም፡፡ እዚያ የተገኙት በግል አማኝነታቸው ወደው ሊሰበኩ እንጂ፣ እነሱ ንግግር ሊያደርጉ የመንግሥትን አቋም ሊሰብኩ አይደለም፡፡ ‹‹ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን›› የሚያካትተው ሕገ መንግሥታዊ የሃይማኖታዊና የእምነት ነፃነት ድንጋጌ ይዘትና አፈጻጸም፣ በመንግሥት ተወካይ መገኘትና ዲስኩር አጠራጣሪና አወዛጋቢ ጉዳይ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ሐሜትና ቅሬታ ሊጭር አይገባውም፡፡

ቭላድሚር ፑቲን ቤተ ክርስቲያን፣ ረጂብ ጠይብ ኤርዶዋንን መስጊድ ሲገኙ እኮ እናያቸዋለን፡፡ ንግግር ሊያደርጉ፣ መመርያ ሊሰጡና የመንግሥትን አቋም ሊሰብኩ ግን አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ጉዳይ ከዋናው ጉዳት በላይ ደግሞ በምዕመናን ውስጥ አለመመቸትን የሚፈጥርና ከዚህም የተነሳ የደፈረሰ፣ ቀጥሎም የፈላ ስሜት የሚፈጥረው ግብታዊ ምላሽ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የመንግሥት ተወካይ ንግግር የሚያደርግበት የፕሮግራሙ አቀራረፅና የቅደም ተከተል ተራ ቅሬታ ይፈጥራል፡፡ ይኼ ሁሉ መቀየርና እርግፍ ተደርጎ መተው አለበት፡፡

ሌላው የሚያሳማና ከ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት›› ድንጋጌ (አንቀጽ 11) ጋር የሚጣላ አሠራር የሕዝብና የሃይማኖት በዓላትን መንግሥት ‹‹አሟጥጬ›› ልገልገልበት ባይነቱ ነው፡፡ የመንግሥት ሚዲያው ሃይማኖቱን ተክቼ ልምራው ይላል፡፡ የቱሪዝምና የባህል የመንግሥት ዘርፍ ከሃይማኖታዊ በዓል በነፃ መከበር መንጭቶ፣ ሊያድግና ሊመነደግ የሚችለውን ቱሪስት የመማረክና በዩኔስኮ የማስመዝገብ ጉዳይ፣ ፖለቲካ ውስጥ ይዘፍቀውና ጠረኑን ብቻ ሳይሆን ምንነቱን ይለውጠዋል፡፡ የዛሬ ዓመት የኢሬቻ በዓል አከባባር ላይ ነገር ያመጣው፣ ዓሳ ጎርጉሮ ዘንዶ ያወጣው በበዓሉ መዳረሻ ሰሞን ተቃውሞን ለማርገብ ተብሎ የተደረገው ሁሉ በራሱ ላይ ስለባረቀ ነው፡፡ ዩኔስኮ በቅርስነት እንዲመዘግበው እየተደረገ ያለውን ጥረት ማራገቡ፣ ዋዜማውን በሩጫ ውድድር አደምቃለሁ መባሉ የመንግሥትን የበዓል የፖለቲካ ንግድ ከሚያከሽፍ በላይ አደጋ ጠራ፡ ከፖለቲካ ጫና ነፃ ሆኖ መካሄዱን ማረጋገጥ የተሳነው፣ ከዚያም ይልቅ ይህ አሠራር ያተርፈኛል ያለው የመንግሥትና የተቃዋሚው ትንቅንቅ ዕልቂት አስከተለ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጠራ እሳት ጫረ፡፡

የሃይማኖት በዓል የሕዝቡ ነው፡፡ የመንግሥት አይደለም፡፡ መንግሥት ሃይማኖት የለውም፡፡  የመንግሥት ሚና ግዴታና ግዳጅ መብትን ማክበር፣ ከሌሎች ጥቃት መከላከልና ለተፈጻሚነቱም የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ የተለያዩና ዥንጉርጉር ሃይማኖቶች ባሉባት አገር የሃይማኖት መሪዎችን በመንግሥት በተዘጋጀ ሥርዓት ተሳተፉ፣ መንግሥት ያዘጋጀውን መግለጫና መፈክር አሰሙ ማለት አደገኛና አዳላጭ ነው፡፡ ከፍጥረት አመጣጥ ጀምሮ ብዙ የተወራረሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ያሏቸው የአይሁድ፣ የክርስትና የእስልምና ሃይማኖቶች ሁላችሁም ስለሙሴ፣ ስለአብርሃም፣ ስለያዕቆብ ልጆች፣ ስለሰለሞን፣ ስለክርስቶስና ስለማርያም አንድ ዜማ አውጡ ማለት አይቻልም፡፡ አንዱ ሃይማኖት ስለእነዚህ ጉዳዮቹ የሚናገረው በራሱ አተረጓጐም ነው፡፡ ስለዚህም በሌላው (በክርስትናና በእስልምና) ሃይማኖት ውስጥ መግባቱ አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህንን ማወቅና አተረጓጎሙን ለየቤተ እምነቱ መተው ከማያስፈልግ ንቁሪያ ያድናል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

“መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ መዋቅር ውስጥ የተሰጠውን ልዩ ቦታ መለስ ብሎ ማየት፣ ጉዳዩ የሚጠይቀውን ጠንቃቃነትና ልዩ እንክብካቤ ያረጋግጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት፣ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት፣ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት፣ እንዲሁም የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች (መግቢያ) ድንጋጌዎች የሚገኙት በምዕራፍ ሁለት የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎች ውስጥ ነው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ማለትን የመሰለ አደራና ግዳጅ እንኳንስ ሆን ብለው የፖለቲካ መሣሪያ አድርገውት፣ የሚቀጭ ሞሳ ልጅ ያህል ተጠንቅቀውም ብዙ አዳላጭ ድጦች አሉት፡፡ ቆቅ ሆነው ሊጠብቁትና ሊያከብሩት የሚገባ ከላይ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያን ወድና ብርቅ ሀብት (የሃይማኖት ሰላም) መንከባከቢያ መሣሪያ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡