Skip to main content
x
በዶናልድ ትራምፕ ላይ ሌላ አጀንዳ ያስከፈተው የልጃቸውና የሩሲያ ግንኙነት

በዶናልድ ትራምፕ ላይ ሌላ አጀንዳ ያስከፈተው የልጃቸውና የሩሲያ ግንኙነት

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዚዳንትነት ወሳኝ ቅስቀሳ ከጀመሩበት እ.ኤ.አ 2016 አጋማሽ ጀምሮ ስለሩሲያ ያላቸው ለዘብተኛ አመለካከት፣ በአሜሪካውያኑ ባለሥልጣናት በተለይም በዴሞክራቶቹ የሚተች ነው፡፡ ሆኖም ከሳቸው በፊት በነበሩ አመራሮች ገሸሽ ከተደረገችው ሩሲያ ጋር እንደሚቀራረቡና በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩም ነበር፡፡

በዙሪያቸው ያሉ ባለሥልጣናትም ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል፣ የምርጫ ተቀናቃኛቸው ዴሞክራቷን ሒላሪ ክሊንተንን ለመጣልም ሩሲያ እጇን አስገብታለች በማለት እ.ኤ.አ. በ2017 መግቢያ ላይ የአሜሪካ ደኅንነት ኤጀንሲም አሳውቋል፡፡

 ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ ነው ቢባልም፣ የትራምፕ ሴት ልጅ ባለቤትና የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ጄርድ ኩሽነር ከሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶ ነበር ተብሏል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ ከሩሲያ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር እንደሚፈልጉ ቢናገሩም፣ ነገሮች የተያያዙት የትራምፕ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ሚስጥር የሩሲያ እጅ ነው ከሚለው ጋር ነው፡፡ ከኩሽነር በተጨማሪ  በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ወር የመጀመሪያውን ወር እንኳን ሳያገለግሉ ከሥልጣን የለቀቁት የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ፍሊን ከሥልጣን ለመልቀቃቸው ምክንያቱ፣ ትራምፕ በዓለ ሲመት ከማድረጋቸው ሳምንት አስቀድሞ በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ነው፡፡ የስልክ ንግግራቸው አሜሪካ ሩሲያ ላይ በጣለችው ማዕቀብ ዙሪያ ቢሆንም፣ ፍሊን ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ የተናገሩት ቀናንሰው ከመሆኑም ባለፈ ለመካድ ሞክረው ነበር፡፡ ይህም ከሥራ ለመሰናበታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

 ትራምፕም በወቅቱ፣ ‹‹የሩሲያና የትራምፕ ጉዳይ ጥልፍልፎሽ የበዛበት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ የተጠላለፈ የትራምፕና የሩሲያ ግንኙነት ውሉ ተገኝቶ መፈታት አልቻለም፡፡ ይልቁንም በትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት፣ የትራምፕ የመጀመሪያ ልጅ ዶናልድ ጆን ትራምፕ ጁኒየር ስለክሊንተን መረጃ ለመስጠት ቃል ከገቡለት ሩሲያዊቷ ጠበቃ ጋር ተገናኝቶ ነበር ተብሏል፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ ሰሞኑን ይዞት በወጣው ዘገባ፣ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር ከሩሲያዊቷ ጠበቃ ናታቢያ ቬስልኒትስካያ ጋር ከመገናኘቱ አስቀድሞ፣ የሒላሪ ክሊንተንን ተቀባይነት ሊያሳጣ የሚችል መረጃ በኢሜይል ደርሶት ነበር፡፡ ይህም የሩሲያ መንግሥት የትራምፕን የምረጡኝ ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ ያደረገው እገዛ ነው ብሏል፡፡

የዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር ከሩሲያዊቷ ጠበቃ ጋር መገናኘት ግልጽ መውጣቱ፣ የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ አመቻቾች ከሩሲያ ድጋፍ ለማግኘት የነበራቸውን ፍላጎት ያሳያል፣ የአሜሪካ ሴኔት በሩሲያ ጉዳይ ለመምከር ከመቀመጡ በፊትም ትራምፕ ጁኒየር በጉዳዩ ላይ ምስክርነቱን ይሰጣልም ተብሏል፡፡

ሮብ ጎልድስቶን በተባሉ አመቻቾች ለትራምፕ ጁኒየር የተላከው የኢሜይል መልዕክት በዘገባው ባይገለጽም፣ ጁኒየር ከሩሲያዊቷ ጠበቃ ጋር መገናኘቱ የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን አባላት ሒላሪ ክሊንተንን ከሥልጣን ተጋሪነት ሊያሳወጣ የሚችል መረጃ ለማግኘት ከሩሲያ ጋር ይሠሩ እንደነበር ግልጽ ነው ሲሉ የዴሞክራት ሴኔት የደኅንነት ኮሚቴ ዋና አባል መናገራቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስፍሯል፡፡

በትራምፕ ምርጫ ዙሪያ የሩሲያ ጣልቃ ገብነትን በመመርመር ላይ የሚገኘው የፕሬዚዳንት የግል ዓቃቤ ሕግ ‹ማርክ ካዞዊርዝ ቃል አቀባይ ማርክ ኮራሎ፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ስለዚህ ጉዳይ አያውቁም፣ በስብሰባውም አልተገኙም፤›› ብለዋል፡፡

ዋይት ሃውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባይሰጥም፣ የዴሞክራቲክ ናሽናል ኮሚቴ (ዲኤንሲ) ቃል አቀባይዋ፣ ‹‹ዶናልድ ጁኒየር ለአሜሪካ ጠላት የሆነችው ሩሲያ የምርጫውን አቅጣጫ እንድታስቀይር ዕርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ ነበር፤›› ሲሉ ኮንነዋል፡፡

ትራምፕ ጁኒየር ከሩሲያ ጋር የነበረውን ግንኙነት አስመልክቶ የሚካሄደውን ምርመራ ወክለው ጥብቅና የቆሙት አለን ፊውተርፋስ የኒውዮርክ ታይምስን ዘገባ፣ ‹‹ምንም በሌለበት ብዙ ችግርና ትርምስ የፈጠረ፤›› ብለውታል፡፡ ፊውተርፋስ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ግንቦትና ሰኔ 2016 ለዶናልድ ጁኒየር በጣም የውጥረት ጊዜ ነበር፡፡ ውጥረት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሮብ ጎልድስቶን፣ ዶናልድ ጁኒየር በኢሜይል አግኝቶታል፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዋ ሒላሪ ክሊንተን ሠርተውታል ስለተባለው ስህተት መረጃ ያላቸው ሰዎች አሉም ብሎታል፡፡ መረጃው ምን እንደነበረ አያውቅም፡፡ ከሩሲያዊቷ ጠበቃ ጋር ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ቢወያዩም ምንም ፍሬ ነገር አልነበረውም፤›› ብለዋል፡፡

ከዶናልድ ጁኒየር ጋር የተወያየችው የተባለችው ሩሲያዊት ጠበቃ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳልነበረች፣ ዶናልድ ጁኒየር ከየትኛም ቢሮም ሆነ ኮሚቴ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልደረሰው፣ ምንም የሠራው ስህተት እንደሌለም ፊውተርፋስ አክለዋል፡፡

የዴሞክራቲክ ደኅንነት ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ማርክ ኮርነር ግን፣ ‹‹በከፍተኛ ደረጃ የነበሩት የትራምፕ የቅስቀሳ ዘመቻ አመቻቾች ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ሕዝቡ ግልጽ መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘበት ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዶናልድ ጁኒየር በበኩሉ፣ ከሩሲያዊቷ ጠበቃ ጋር በነበረው ውይይት ከሩሲያ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ግለሰቦች ለዴሞክራቲክ ናሽናል ኮሚቴና ለክሊንተን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እንደነገረችው፣ መረጃዎቹ ግን ግልጽ እንዳልነበሩ፣ በውይይታቸው ወቅት የተነሱ ጉዳዮችን በሙሉ ለሚጠይቃቸው አካል ለመናገር ፈቃድኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ከፓርቲያቸው ይሁኝታን ባገኙ ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ በኒውዮርክ ትራምፕ ታወር ከጠበቃዋ ጋር የተወያዩት ዶናልድ ጁኒየር ብቻ ሳይሆኑ፣ ጆርጅ ኩሽነርና በወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ መሪው ፖል ጄ ማናፎርት ናቸው ተብሏል፡፡

ትራምፕ ጁኒየር፣ ጠበቃዋ ስለምታወራው ነገር በቂ መረጃ እንዳልነበራት፣ በኋላም የአሜሪካ ኮንግረስ እ.ኤ.አ. በ2012 ባሳለፈውና በሩሲያ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማትን ገንዘብ የሚያግደውን ቪዛ መከልከል የሚፈቅደውን ድንጋጌ (Masnitsky Act) ማንሳቷን፣ በኋላም አጀንዳዋ ይህ እንደነበር ተናግሯል፡፡

የሩሲያ ኢንተርኔት ጠላፊዎች ከሒላሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ ጋር የተያያዘ መረጃዎችን ጠልፈው በመልቀቅ ትራምፕ በምርጫው እንዲያሸንፉ ረድተዋል ተብለው ይተቻሉ፡፡ ሆኖም ስለእውነተኛው ጉዳይ መደምደሚያ ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡ የኮንግረሱ ኮሚቴና ልዩ ዓቃቤ ሕግም በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላትና በሩሲያ መካከል ግንኙነት እንደነበረ በመመርመር ላይ ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንትም ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ‹‹በምርጫ ከሩሲያ በተጨማሪም ሌሎች አገሮች ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ከረዥም ጊዜ አንስቶ የነበረ ነው፤›› ብለዋል፡፡