Skip to main content
x
በግል ኩባንያ አማካይነት አነስተኛ የኃይል አቅርቦት መስጠት ተጀመረ

በግል ኩባንያ አማካይነት አነስተኛ የኃይል አቅርቦት መስጠት ተጀመረ

መንግሥት የሚያወጣው የሽያጭ ታሪፍ እየተጠበቀ ነው

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ከመገንባት ጀምሮ ኃይል የማሠራጨትና በሽያጭ ለተገልጋዮች እስከማዳረስ ያለውን ሥራ በብቸኝነት ይዞ የቆየው ለዚሁ ተግባር የተቋቋመው መንግሥታዊ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይሁንና በ2005 ዓ.ም. በወጣው ሕግ መሠረት የግል ባለሀብቶች ኃይል አመንጭተው መሸጥ የሚችሉበት ድንጋጌ በመቀመጡ፣ በዘርፉ ለሚሠማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀበቶች መሳተፍ የሚችሉባቸው ዕድሎች ተመቻችተዋል፡፡ የወጣውን ሕግ በተግባር ለማዋል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በግል ባለሀብት አማካይነት በመካለኛና በከፍተኛ ደረጃ ኃይል በማመንጨት በሽያጭ ወደ ተጠቃሚ ለማዳረስ ያስችላሉ የተባሉ የኃይል ማመንጫ ሥራዎች ገና በእንጥልጥል ላይ ናቸው፡፡

በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎችን ከማካሔድ ባሻገር፣ በአነስተኛ ደረጃ የሚገነቡ፣ የገጠር ቀበሌዎችን ማዕከል ያደረጉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎችም ከግል ዘርፉ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በአነስተኛ አቅም ለገጠር ቀበሌዎች በተለይም አስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ባላቸው አካባቢዎች መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ ተመራጭ የሆኑት አነስተኛ የኃይል ማመንጫዎች በጥሩ አማራጭነት ይወሰዳሉ፡፡ መልከዓ ምድራቸው አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ከዋናው የኤኬክትሪክ ኃይል ቋት አቅርቦት እንዲያገኙ ማድረግ እጅግ ፈታኝ እንደሆንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  

የአገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሽፋን ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ይገመታል፡፡ አብዛኛውና ገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደማያገኝም የታወቀ ነው፡፡ በተለይ በመልከዓ ምድራቸው አስቸጋሪነት ሳቢያ አገልግሎቱን በቀላሉ ለማግኘት ሲቸገሩ በቆዩ አካባቢዎች የሚገነቡ አነስተኛ መጠን ያላቸው የኃይል ማመንጫዎች፣ ትልቅ እፎይታ እንደሚያስገኙ ይታመናል፡፡ በአነስተኛ ወጪ አገልግሎቱን እንደሚያስገኙ ስለሚታሰብም፣ የኃይል አማራጭ ለማቅረብ ዓይተኛ መንገድ ሆነው ያገለግላሉ፡፡

በአነስተኛ ወይም በማይክሮ ደረጃ የኃይል ማመንጨትና ሽያጭ ሥራ ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ኢትዮ-ሪሶርስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ የኩባንያው ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ህላዌ ላቀው እንደሚገልጹት፣ የማይክሮ ኃይል ማመንጫዎች የኤሌክትሪክ ሽፋን እምብዛም በሌላቸው አካባቢዎች በማዳረስ የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ ኩባንያቸው ከዚሁ ሥራ ጋር በተያያዘ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር አቀማመጥ ውስጥ የሚገኙ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ፣ የኃይል አቅርቦት ለማዳረስ የሚቻለው በማይክሮ ኃይል ማመንጫዎች አማካይነት ለመሆኑ ያገኛቸው የጥናት ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡

በአገሪቱ ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት አንፃር መንግሥት አብዛኛውን ያልተዳረሰባቸውን ክፍሎች ለመሸፈን አነስተኛ የኃይል ማመንጫዎች አጋዥ ስለመሆናቸውም አቶ ህላዌ ይናገራሉ፡፡

ኢትዮ-ሪሶርስ ግሩፕ ከዚህ ፍላጎት አንፃር ከነፋስና ከፀሐይ ኃይል አመንጭቶ ለመሸጥ የሚያስችለውን ፈቃድ ጠይቆ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኤጀንሲ የኃይል ማመንጫ ግንባታውን በመውሰድ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ኩባንያቸው የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራውን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዝ ጌራ ምድር፣ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በሚገኙ ስድስት መንደሮች የኃይል አቅርቦት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ የአካባቢ የቦታ አቀማመጥ አስቸጋሪ በመሆኑና ከዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ የሚተላለፉ መስመሮችን በመዘርጋት ኃይል ማዳረሱም አስቸጋሪና ዳጎስ ያለ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ አነስተኛ የኃይል አቅርቦት አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

የወረዳው የውኃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከፈለኝ ግረፍ እንደሚገልጹት፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ማሠራጫ ኃይል ለማግኘት የቀረበው ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ እንዲህ ያሉ አነስተኛ ማመንጫዎች ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ በሁለቱ ቀበሌዎች ውስጥ ለሚኖሩ 200 አባወራዎች ፍጆታ የሚውል ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ግንባታ ተከናውኖ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሥርጭት ሥራ በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት የአነስተኛ የኃይል መስመሮች ለአካባቢ ኅብረተሰብ ጥቅም እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ህላዌ ገለጻ፣ ይህንን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ ከወራት በፊት ፈቃድ በመውሰድ 9.5 ኪሎ ዋት ኃይል የሚያመነጩ መስመሮችን በመትከል ለ200 የአካባቢው ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበ ይገኛል፡፡

ላለፉት ሁለት ወራት ያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለነዋሪዎቹ እያቀረበ የሚገኘው ይህ ኩባንያ፣ የሚያመነጨውን ኃይል በሽያጭ ለማቅረብ የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለነዋሪዎች በነፃ እየቀረበ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደፊት የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኤጀንሲ በሚያወጣው ተመን መሠረት በሽያጭ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የዋጋ ተመኑ እስከሚወጣ ድረስም ተጠቃሚዎች ኮሚቴ በማዋቀር የአገልግሎቱ ክፍያ በኮሚቴው በኩል እንዲከናወን ለማድረግ የሚያስችል አሠራር እየዘረጉ እንደሚገኙ አቶ ከፈለኝ ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን እያገኙ ያሉት ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት እየቀረበላቸው የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ሁለት አምፖሎችን ለማብራት፣ ሬዲዮና ቴፕ ሪኮርደር ለማጫወት የሚያስችል እንዲሁም ሞባይል ስልኮችን ቻርጅ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ቴሌቪዥንና ሌሎችም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ መገልገያዎችን ለመጠቀም ካስፈለጋቸው፣ የሚቀርብላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከፍ ማለት እንደሚችል አቶ ህላዌ ጠቅሰው፣ የአገልግሎት ጊዜውንም አብሮ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለተጠቃሚዎቹ የሚቀርበው ኃይል ለአምስት ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ እንደ አትራፊ ኩባንያ ለአገልግሎቱ የሚሆን ክፍያ ለመሰብሰብ ግን የኤጀንሲውን ፈቃድ ማግኘት ግድ በመሆኑ ለሚቀርበው ኃይል የሚወጣውን ታሪፍ ኩንያው እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አቶ ህላዌ ገልጸዋል፡፡

አቶ ከፈለኝ እንደሚሉት ከሆነም ለአምስት ሰዓት እንዲያገለግል የሚለቀቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ምሽት ላይ በተለይ የተለያዩ ተጓዳኝ ሥራዎችን ለመሥራት አስችሏል፡፡ ሴቶች ጥልፍ ይጠልፋሉ፣ ሞባይል ቻርጅ ይደረግበታል፡፡ ሬዲዮና ቴፕ ማጫወት የተቻለውም በዚሁ ኃይል ነው ብለዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ያላቸው ሱቆች ለአካባቢው ነዋሪዎች ሞባይል ቻርጅ እያደረጉ በአንድ ስልክ ሁለት ብር ያስከፍላሉ ያሉት አቶ ከፈለኝ፣ እስካሁን ሞባይል ቻርጅ ማድረግ ከባድ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ለአገልግሎቱ ተመጣጣኝ ይሆናል ያለውን የታሪፍ መጠን ኩባንያው ሠርቶ ማቅረቡን የጠቀሱት አቶ ህላዌ፣ ከኤጀንሲው የሽያጭ ፈቃድ ማግኘት ከቻለ  ከመንግሥት በተጓዳኝ በኃይል ሽያጭ ላይ የሚሰማራ የግል ድርጅት ይሆናል ብለዋል፡፡

የአገልግሎት ታሪፉ ግን አሁን መንግሥት ከሚያስከፍለው ዋጋ ብልጫ እንደሚኖረው የሚጠቁሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም መንግሥት እያስከፈለ ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋጋ በድጎማ የሚቀርብ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ትናንሽ ማመንጫዎቹ በግል የሚካሄድ የኢንቨስትመንት ወጪ ስላለባቸው፣ አመንጭተው የሚሸጡት የኤሌክትሪክ ኃይል ከመደበኛው ታሪፍ ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ይገልጻሉ፡፡

አትራፊ ሆኖ ለመቀጠል የኢንቨስትመንት ወጪውንና በአካባቢው ያለውን የኤሌክትሪክ ሥርጭት በአግባቡ ለማዳረስ የሚያስችል መነሻ የታሪፍ ስሌት ለመንግሥት መቅረቡን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም የቀረበው ዋጋም ቢሆን አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀርብለት የገጠር ነዋሪ ብርሃን ለማግኘት ከዚህ ቀደም ኩራዝ ለማንደድ  ከሚጠቀምበት የነዳጅ ወጪ ጋር ተቀራራቢ ወይም ከዚያም ያነሰ እንደሚሆን ይገምታሉ፡፡

የዚህ ቢዝነስ አዋጭነት ከታየና ከታወቀ በኋላ ሌሎችም በዘርፉ እንዲገቡበት ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አቶ ህላዌ ይናገራሉ፡፡ ኩባንያቸው ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የማማከር ሥራም የሚሠራ በመሆኑ፣ መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት የማይችሉ አካባቢዎች ውስጥ አነስተኛ ኃይል ማመንጫዎችን በመትከል ገጠራማ አካባቢዎችን ማዳረስ የሚቻልባቸው አማራጮች በጥናት እንደተለዩም ጠቁመዋል፡፡

ይህ ኩባንያ በግል የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የተነሳ ጀማሪ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ወደፊት አዳዲስ አሠራሮች እንዲቀረፁ ዕድል እንደሚፈጥርም ይታመናል፡፡ ወደዚህ ሥራ ሲገቡ፣ ሥራውንም ለመጀመር በርካታ የፈቃድና  የመስፈርት መጠይቆችን እንዲሁም ደረጃዎችን ማለፍ ግድ ነበር የሚሉት አቶ ህላዌ፣ በዚህ ፕሮጀክት መነሻነት የሚገኘው ልምድ ከዚህ በኋላ ለሚመጡ ድርጅቶች ጥሩ መነሻ እንደሚሆንም ያምናሉ፡፡ በአነስተኛ ደረጃ ኃይል አመንጭተው ለሽያጭ የሚቀርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዴትና በምን መልኩ እንደሚተዳደርም መነሻ ይሆናል ብለዋል፡፡

‹‹ወደዚህ አገልግሎት ለሚገቡት ትልቅ ግብዓት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽያጭ ሥራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን ከማሳደግ በላይ ለአካባቢ ጥበቃም ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አቶ ከፈለኝ በበኩላቸው አገልግሎቱን ካገኙት መንደሮች በተጨማሪ ሌሎች 12 ቀበሌዎችም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ ቀርቧል፡፡

ሥራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በተለይ ከክልል መንግሥታት ጋር አብሮ ለመሥራት ማቀዳቸውን አቶ ህላዌ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሚያከናውኑት ሥራ የአሜሪካ የአፍሪካ ልማት ፋውንዴሽን ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ዕገዛው ለአጭር ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ የኃይል አቅርቦቱን ዘላቂ ለማድረግ በሽያጭ መሥራቱ እንደሚመረጥ ጠቅሰዋል፡፡ ለስድስት መንደሮች ሽፋን የሚሰጠውን አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ለመገንባትና የመስመር ዝርጋታዎች ጨምሮ ሌሎችም ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን 2.5 ሚሊዮን ብር ወጪ መጠየቁ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም የጀርመን መንግሥትን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ አገሮች ድጋፍ የሰጡበት፣ አነስተኛ የኃይድሮ ኃይል ማመንጫ መስመር በደቡብ ክልል ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡