Skip to main content
x
በጦርነት ቀጣና የሚገኙ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ትምህርት የማግኘት ችግር ተጋርጦባቸዋል

በጦርነት ቀጣና የሚገኙ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ትምህርት የማግኘት ችግር ተጋርጦባቸዋል

ግጭቶች በተንሰራፉባቸው አገሮች የሚገኙ 9.2 ሚሊዮን ሕፃናትን መደበኛና መደበኛ ላልሆኑ ትምህርቶች ተደራሽ ለማድረግ 932 ሚሊዮን ዶላር ቢያስፈልግም፣ የተገኘው 12 በመቶ ወይም 115 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ፣ ሕፃናቱን ለትምህርት ተደራሽነት ችግር እንዳጋለጣቸው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለትምህርት ተደራሽነት በሚያስፈልገው በጀትና በተገኘው ገንዘብ መካከል ከፍተኛ ክፍተት ታይቷል፡፡ የዚህም የክፍተት መጠን ኢራቅ ውስጥ 36 በመቶ፣ በሶሪያ 64 በመቶ፣ በየመን 74 በመቶ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ 78 በመቶ ነው፡፡ በጣልያን በሚገኙ ስደተኞች ላይ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 38 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች አውሮፓን መጠጊያቸው ያደረጉበት ዋናው ምክንያት ትምህርት ለማግኘት ሲሉ ነው፡፡ በግሪክ በሚገኙ የሕፃናት ወላጆችና ወይም አሳዳጊዎች ላይ የተካሄደው ተመሳሳይ የዳሰሳ ጥናትም፣ ከሦስቱ አንዱ ለልጆቻቸው ትምህርት ፍለጋ አውሮፓን መምረጣቸውን መግለጫው አስፍሯል፡፡ በጀርመን ሀምቡርግ በተካሄደው የቡድን 20 የመሪዎች ስብሰባ ዩኒሴፍን በመወከል የተገኙት የመልካም ምኞት አምባሳደር ሙዛን አልሚሊሃን፣ ‹‹በጦርነት ዞን ያደጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ለትምህርት ተደራሽ አለመሆናቸው ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለጉልበት ብዝበዛና ለውትድርና ምልመላ ተጋላጭ ይሆናሉ›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ እንደሆነ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ብዙ ሕፃናት ከትምህርታቸው እንደተፈናቀሉና ይህም በትምህርቱ ጥራት ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ መግለጫው አመልክቷል፡፡