Skip to main content
x
ተነካካን እንዴ?

ተነካካን እንዴ?

ሰላም! ሰላም! ‹የታሰረን አንጀት ያላሰረ አይፈታ› እያለ የሚዘፍን አልበዛባችሁም? መቼም ‹ማታ ማታ› እያሉ ምሽት ተኮር ዘፈን ከማብዛት የሚሻል ይመስላል። ካልተሸራተትን ማለቴ ነው። ብንንሸራተትም መንሸራተት በእኛ አልተጀመረም። ያዝ ለቀቅ እንደሆነ ስንፈጠር ያገኘነው ቀለም ይመስለኛል። ጥግ ጥጉን መሄድ አበዛሁ መሰለኝ። ‹‹አጥብቆ ያሰረ ዘቅዝቆ ይሸከማል›› ሲሉ እየሰማሁ ባሻዬ ይህቺ አንጀት የምትበላ የእስራት ዘመን አላስተማምነኝ ብላ እኮ ነው። ምነውማ የአድባሩ ቅኔ ያዝ ለቀቅ ስለሆነ ብያችሁ እኮ ነበር። ሰሞነኛ ሙሾና ሰሞነኛ እርሾ መቼም ኩፍ ኩፍ ሳያስብል አይረሳም። እና እኔ ምለው ሰሞነኛነት ዛሬም ያለቀቀን ወይ የማይለቀን ከሆነ አሁን ጠቁሙ የሚሉንን ሰዎች እንዴት ብለው የምናምናቸው የሚለው እያሰሰበኝ ነው። እንዴት በሉኝ?

በቀደም አንድ ወዳጄ መጣና ሰላም ሳይለኝ፣ “ቆይ ግን አንተ እስከ መቼ ነው ያን እከሌ የሚባል ደላላ የማትጠቁመው? ከአንተ በላይ የሚያውቀው የለም። ከአንተ በላይ በእሱ ደባና የሙስና ቅሌት የተደፈቀ የለም። ለእንጀራህም ለእኛም ብለህ በዚህ ሞቅ ያለ ጊዜ አግለህ ብትተኩሰው?” አይለኝ መሰላችሁ። “ስለማን ነው የምታወራው?” ስለው ስሙን ጠራውና “ቄስ ይጥራው” ብሎ ተንገሸገሸ። “ለምን አንተ አትጠቁመውም?” አልኩት። «እኔ እንዳንተ አላውቀው። አንተ ግን ተነካክተሃል?” ብሎኝ አረፈዋ። የዘንድሮ ነገርና ነገረኛ ልጥፍ ሲያደርግባችሁ እንዲህ ነው ይኼውላችሁ። ዕድሜ ለፌስቡክ አይባል ነገር። በላይክና በኮሜንት ያበደው የሦስተኛው ዓለም ሰው፣ ከሳሽና ተከሳሽ ስለሚምታቱበት ነው መሰለኝ ለወፍ የሰደደው ወንጭፍ ፍሬውን ማርገፍ ይቀናዋል። እና ዙሪያ ጥምጥም የምዞረው ምን ልላችሁ ፈልጌ ነው? በሰው ጥቆማ ጣልቃ የሚገባ ሰው በዝቷልና ጠንቀቅ እያላችሁ። አጥብቃችሁ ማሰራችሁን ሳታረጋግጡ ዘቅዝቃችሁ ለመሸከም አትቸኩሉ ነው በአጭሩ።

እናላችሁ ዛሬ በአጭር ባጭሩ የማጫውታችሁ ጉዳዮች አሉ። በረዥሙ መጫወት እንኳን ለእኛ ለቼልሲም አልሠራ ብሏል። ካላመናችሁኝ አንቶኒዮ ኮንቴን ጠይቋቸው። የአገር ቤቱን ጉዳይ ግን ከእኔ የበለጠ የሚነግራችሁ የለም። በአጭሩ ብያለሁና ስጀምር በአጭሩ ሳስቀምጠው ዘመናችን የከተፋ ሆኗል። ሐሳብ ይከተፋል፣ ኪነት ይከተፋል፣ የመንግሥት ድምፅ ይከተፋል፣ የሕዝብ ልሳን ይከተፋል፣ ኧረ ምኑ ቅጡ። ለምን ይሆን ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ፣ “ከሥጋ ጋር ባለን ለየት ያለ ቁርኝት የመጣ ዘይቤ ሳይሆን አይቀርም፤” ነበር ያለኝ። “ጥብስና ክትፎ የአምሮቱ ማሳረጊያ ለሆነ ኅብረተሰብ፣ ከሐሳብ እስከ እሴት ከታትፎ ቢያላምጥ ለውጡ አይታየውም፤” የሚለውን የጨመረበት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። “በዘመነ ኢንተርኔት ለምሁር ቅጥያ ብቻ ቢቀረውም፤” የሚለው ግን የእኔ ነው።

ታክሲ ላይ ተለጥፎ ካያችሁት ጠቁሙኝ ኮሚሽን እቀበልበታለሁ። ስለዘመንና ከተፋው እያወራሁ ጨዋታችንን መከታተፋችንን ትተን ለአፍታ ተቃራኒውን እናስብ። የከተፋ ወይም በአጭር ባጭሩ የመመተር ተቃራኒ ጋ ስትሄዱ በቀላሉ ረዥም የሚባል ቃል አለ። እንደ እኛ ላለ አራት ጎማ አምላኪዎች በቀላሉ ለማስረዳት በረዥሙ ማብራት የሚለውን ሐረግ መጠቀም ነው። እና መንገዱ በሙሉ በረዥሙ የሚያበሩ መኪኖች ሰበብ እያደር እንደወጣ በሚቀረው ሰው ደም ታጥቦ አርቆ ማሰብ ሲከብደን ስታዩ ምን ትላላችሁ? ባሻዬ ሰው የሚያወራው በልቡ የሞላውን ነው ይላሉ። ለወትሮው ሲባል እንሰማ የነበረው ልብ ሩቅ አዳሪ መሆኑን ነበር። የዘንድሮ ልብና ሐሳብ ምን አዚም እንደያዘው በጥናት ባይረጋገጥም፣ በአጭር ባጭሩ በተሸራረፉ ነገሮች ተሞልቶ አገር እንደ መካን እዬዬዋ በአራቱም ማዕዘን ደምቆ አረፈው። ታዲያስ? ጥልቅ ተሃድሶው ይኼን ይኼን ቢጎበኘው የሚል ሐሳብ አልጫርኩባችሁም? አይዟችሁ ስለአጫጫሩ አትጨነቁ ዋናው መንደዱ ነው!

ስናወራ ቸስተን እንደቀረነው ነገር ስለቃቅም ጎጆዬን እንዳላፈርስ ስለሰጋሁ የሆነ ‘ለጌስት ሐውስነት’ የተዘጋጀ ግቢ ቤት ለማከራየት ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመርኩ። ይቅርታ አድርጉልኝና ስንቱን የእግዜር ‘ቢዝነስ’ እንደዘጋነው ስታስቡ ግርም አይላችሁም? እንግዳ ባረፈበት አገር ሁሉ የእግዜር እንጂ የሰው አይደለምና በነፃ ሲስተናገድ እንዳልኖረ፣ ዛሬ ለእንግዳ ማረፊያ ቤቶች የሚጠየቀውን ዋጋ ሳይ እኮ ነው ይኼን የምለው። “በስንቱ እንጠየቅ ይሆን?” ይላሉ ባሻዬ ነገሩ እያስገረማቸው። እንዳልኳችሁ የሚከራይ ምርጥ የእንግዳ ማረፊያ ቤት እንዳለ እየለፈፍኩ ስዘዋወር፣ ሁለት ጥንድ በአዛውንትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች አገኘሁ። ቤቱን አሳይቻቸው ሳበቃ ለአንድ ወር በዶላር ከፍለው ወዲያው ገቡት። ያውም ሐበሻ? ያውም በዶላር? እንዴት ይሆናል? እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት ቆየሁና ኮሚሽኔ እጄ እንደገባ (መጀመርያ የመቀመጫዬን ነዋ) ልጠይቃቸው ወሰንኩ።

“ይኼን ያህል ገንዘብ ከፍሎ ‘ጌስት ሐውስ’ ከመከራየት ዘመድ ወዳጅ ጠፋ እንዴ?” አልኳቸው እያሳሳቅኩ። እንዳይሆን ሆኖ እንዳንሆን ያደረገን አብዮት ከመፈንዳቱ አንድ ወር በፊት (ተማሪ ነበሩ ያኔ) እንደተዋወቁ፣ ኋላም መረጋጋት ሲርቅ ከአገር እንደተሰደዱ፣ ዛሬ በ40 ዓመታቸው ተመልሰው የመጡት ለ40 የተሳኩ የፍቅር ዓመታት እያሰቡ አገራቸው ላይ ኬክ ለመቁረስ እንደሆነ አጫወቱኝ። ያደለውና  ብልጡ ፍቅርን ሙጥኝ ብሎ ድንበር ተሻግሮ በሰው አገር መሬት ለሚነገር ታሪክ ይበቃል። ያላደለው በእናት አገር ፍቅር ስም መሬት ለአራሹ ይሰጥ ባለበት መሬት የደም ታሪክ ጽፎ ለማስታወስ የሚከብድ ታሪክ ያሳልፋል። የሕይወት ተቃራኒ ጎዳና እያስደነቀኝ ፈዝዤ ቀረሁ። የዛሬ 40 ዓመት ለአንድ አገር ብሩህ ተስፋ አንድ መሆን ተስኖን ወደ ጀርባና ሆድነት ተለወጥን አልኩ ለራሴ። የጥላቻም ታሪክ ዕድሜው ይወሳል ለካ እናንተ? ይገርማል እኮ! ላይሳካላን መስሎን ባዶ እጅ አጨብጭበን መቅረታችንን እያሰብኩ ራሴን አመመኝ። ጥያቄው ግን ዛሬስ ነው? ዛሬስ እዚያው ነን? ወይስ ተሽሎናል? መልሱን ለእናንተው ልተወው!

ታዲያ እንደምታውቁት በጥቂቱ ዘርቶ በብዙ የሚያጭደው ሙሰኛ ብቻ በመሆኑ፣ ሌላ ሌላ ቢዝነስ አይጠፋም እያልኩ መባከኔን ቀጠልኩ። አንዴ እዚያ ስል አንዴ እዚህ ስል ዓይኔ የሚገባው ነገር ሁሉ ነገር ይፈልገኛል። ወዲያ ማዶ ታክሲ ጥበቃ የተሠለፈው ሕዝብ፣ ከተማውን በዘንዶ የተወረረ አስመስሎት ይታያል። እዚህ ማዶ ‘በኔት ወርክ’ ሊያብድ የደረሰው ብቻውን እንደ ዕብድ እያወራ ያመለጠውን ሒሳብ እያወራረደ ይጋብዛል። ውኃ የመሰለ ሊያዩት የሚያሳሳ አውቶሞቢል በአጠገቤ ሲያልፍ እያየሁ ‘አወይ ኑሮ’ ብዬ ሳልጨርስ “ስለመድኃኔዓለም?” ብሎ ምፅዋት የሚጠይቀኝ አንድ የኔብጤ (ብቻውን እንዳይመስላችሁ መላው ቤተሰቦቹ ጭምር ይዞ ነው) ይታከከኛል።

አንዱ ለእረፍት ‘ቫኬሽን’ ብሎ አገር ይለቃል፣ ሌላው ለልመና ቤተሰቡን ሰብስቦ ቀዬውን ይረሳል። ይኼን ውጥንቅጥ ሳይ ምንም ሥራ መሥራት አቃተኝ። ያለፍንበት መንገድ ወስዶ ወስዶ የት እንዳደረሰን እያየሁ ‘ማን ይሆን ተጠያቂው?’ ስል ራሴን ጠየቅኩት። እንኳን የተወለደው ገና ያልታሰበውም ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ የባሻዬ ልጅ አንዴ ያጫወተኝ ትዝ ሲለኝ፣ ነገሩን ችላ ብሎ ማለፍ ከብዶኝ እነሆ እንዲህ እላችሁ ጀመር። የመደብ ልዩነቱ እያደር መስፋቱ፣ ግንዛቤና ገንዘብ በጥቂቶች ዘንድ መገኘቱ፣ ብዙኃን በችጋር ለበቅ እየተጠበጠቡ ዘመናት መሸምጠጣቸው፣ ለውጥ ፉከራ ብቻ ሆኖ መቆየቱን፣ እንደ እኔ አደባባይ ላይ ሆናችሁ ስታስቡት ደም ያፈላል። የረሱትን እያስተወሱ የማሩትን ያስረግማል። ‹‹ማርና ወተት›› የምታፈሰው ኢትዮጵያችን ሁሌ እያጓጓችን በማይጨበጥ የተስፋ ህልም ላይ ተንጠልጥለን መኖራችን ማክተሚያው መቼ ይሆን? ኧረ እኔስ ናፈቀኝ ጎበዝ!

በሉ እንሰነባበት። ቀን አያወጣው አያወርደው የለም። የሚወጣው ለእናንተ አይነገርም። ይልቅ እየወረደ ያስቸገረንን ነገር ልጠቁማችሁ። በስም ሽፋን እየተድበሰበሰ እንጂ ሰሞኑን የብዙዎች እንጥል መውረዱን ልብ ብላችኋል? የምሬን እኮ ነው። ትናንትና ዓይኔን ስገልጥ ጉሮሮዬ ደህና ነበር። ማንጠግቦሽን፣ ‹‹ደህና አድረሻል?›› ካልኳት በኋላ እንጥሌ በቦታዋ የለችም። ደርሶ ጉሮሮዬ ከረከረኝ። ቁርጥማት ወረረኝ። ማንጠግቦሽ እዚያው በዚያው ሲያንዘፈዝፈኝ ስታይ ልግመት ነው ብላ እንደማኩረፍ አሰኛት። ድምፄ ሲዘጋ ግን የሚያደርጋትን አሳጣት። ወዲያው ለባሻዬ ልጅ ደወልኩ። መድኃኒት አያጣም ብዬ ነዋ። “ሃሎ” ስል ባሻዬ ስልኩን አንስተው “እንጥሉ ወርዳ ድምፁ ተዘግቷል፤” አሉኝ። “መቼ አመመው?” ስላቸው፣ “ኧረ አሁን ከእንቅልፉ ሲነሳ በደንብ አናግሮኛል። ማር በነጭ ሽንቁርት ላስልሰው ነው፤” ብለው ስልኩ ተዘጋ።

ማንጠግቦሽም የዋዛ አደለችም ምናምኑን እየደባለቀች ስትግተኝ ውላ ከቀትር በኋላ አቅሜ መለስ ሲል ባሻዬ ዘንድ ሄድኩ። “አይገርምዎትም ተነጋግረን አገር ማቅናት ያልቻልን ሰዎች እንደተመካከረ ሰው በሽታ እኩል ሲጥለን?” ስላቸው፣ “መድኃኒተኛ አይጥፋ እንጂ ደግሞ በሽታ ምንድነው አንበርብር? የዛሬ ልጆች እንደሆነ በትንሽ በትልቁ እንደ አራስ ልጅ ፍንግል ፍንግል ነው። ይልቅ ካነሳኸውስ የሚያሳስበኝ እያደር እየቀዘቀዘብን የመጣው የፍቅር ጉዳይ ነው። ፍቅር በማር አይለሰልስ። በወጌሻ አይታሽ። ምን ታደርገዋለህ?” ብለው ጋቢያቸውን መደራረብ ጀመሩ። “የት ሊሄዱ ነው ታዲያ በዚህ ዝናብ?” ስላቸው “ሽምግልና። ማታ ተፋቅሮ ሳይነጋ እየተጣላ ሰው እንደሆነ ከእኔ ትከሻ አልወርድ ብሏል፤” ብለውኝ ተያይዘን ስንወጣ በጆሮዬ፣ “የይቅርታ ልብ አጣን። አጣን! አጣን! አጣን!” እያሉ ብቻቸውን ተነጥለው ተጓዙ። ይቅርታ ኢምፖርት ወይ ኤክስፖርት የሚደረግ ጥሬ ዕቃ ቢሆን ይኼኔ ነበር የተሰበረ ልብ እንጠግናለን ብሎ ስፔርፓርት መክፈት እያልኩ በልቤ ቤቴ ደርሼ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ ተጠቅልዬ ተኛሁ። እንቅልፍ እስኪወስደኝ ነገራችንን ሳወጣና ሳወርድ ያልተነካካንበት የለም ለካ! ወይ ግሩም! መልካም ሰንበት!