Skip to main content
x
አምባሳደር እንዲሆኑ የሚጠበቁት ሆቴሎች

አምባሳደር እንዲሆኑ የሚጠበቁት ሆቴሎች

አቶ ልዑልሰገድ መሰለ ዓለም አቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንሰልታንት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉትና እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ያለውን ትምህርት የተከታተሉት በደሴ ከተማ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ኬንያ አቅንተው እዛ በሚገኘው ኡታሊ ኮሌጅ በሆቴል ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ መንግሥት ባገኙት ነፃ የትምህርት ዕድል መሠረት በእንግሊዝ ለንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናሽናል ሆቴል ኤንድ ሬስቶራንት ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በኬንያ ሞምባሳ ከተማ ውስጥ ቱፒሺስ ሆቴል፣ ናይሮቢ ፓን አፍሪካ ሆቴል፣ እንዲሁም ለንደን በሚገኘውና በቴስኮ የምግብ መጋዘን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በአገር ውስጥ የኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሆቴሎች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አገር ቤት እንዴት ሊመለሱ ቻሉ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ለሆቴሎች ደረጃ ለማውጣት ኮንሰልታንት ይፈልግ ነበር፡፡ በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ የአሁኑ በሳዑዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አሚን አብደልቃድር በአንድ አጋጣሚ አማካይነት አገኙኝና ወደ አገር ቤት ተመልሼ እንድሠራ ጥሪ አቀረቡልኝ፡፡ ጥሪውን ተቀብዬ መጣሁ፡፡ እንደመጣሁም በኢትዮጵያ ሆቴሎች ላይ ደረጃ ለመሥራት ጨረታ ወጥቶ ነበር፡፡ ጨረታውን ለሚያኪያሂደው ግብረ ኃይል አስተባባሪ ሆኜ ሥራውን ተያያዝኩት፡፡ በወቅቱ የወጣውን ጨረታ ያሸነፉት አራት የውጭ አገር ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም ጨረታው እንዲሠረዝ ተደረገ፡፡ ምክንያቱም ኩባንያዎቹ ያቀረቡት አካሄድና ዕቅድ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጭ ያልሆነው ምኑ ላይ ነው? በምትኩስ ምን ዓይነት አካሄድ ተቀባይነት አገኘ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ኩባንያዎቹ ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት ቢኖረው ኖሮ የደረጃ አወጣጡ የጥራት ችግር ያጋጥመው ነበር፡፡ በምትኩ ያቀረብኩት ሐሳብ ደረጃ አወጣጡን የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ይሥራው የሚል ነበር፡፡ ይህም ተቀባይነት አገኘ፡፡ ሐሳቡን ያቀረብኩበት የአገሪቱ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ነው፡፡ ቱሪስቶች በሆቴሎቻችን ሙሉ በሙሉ እንዲተማመኑም ያደርጋል፡፡ ከዚህም ግንዛቤ በመነሳት ዓለም አቀፉ ድርጅት የኢትዮጵያ የሆቴሎቹን ደረጃ (ክላሲፊኬሽን) ለማውጣት የበቃ ሲሆን፣ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፉ ድርጅት ደረጃ የወጣላቸው ሆቴሎች የኢትዮጵያ ሆቴሎች ብቻ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ደረጃው በዓለም ቱሪዝም ድርጅት መስፈርት መሠረት በመከናወኑ የሚያስገኘውን ጥቅም ቢያብራሩልን?

አቶ ልዑልሰገድ፡- በዓለም አቀፉ ድርጅት ክላስፊኬሽን የወጣላቸው ሆቴሎች እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ከሠለጠኑ አገሮች ውስጥ ካሉት ሆቴሎች ጋር አንድ ዓይነት ይሆናሉ፡፡ አገሪቷም ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባትና ለቱሪስት ምቹ መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ የሆቴል ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ በር ይከፍታል፣ መንገዱንም ያመቻቻል፡፡

ሪፖርተር፡- ለታላላቅ ሆቴሎች ደረጃ የማውጣቱ አሠራር ችግር ይፈጥራል የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር፡፡ ይሄንን እንዴት ተወጣችሁት?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ችግር ይፈጥራል ተብሎ የተሠጋው ደረጃ የማውጣቱን ሥራ ኩባንያዎቹ ቢያካሂዱት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ቀርቶ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እንዲያወጣው በመደረጉ ችግሩና ሥጋቱ በሙሉ ሊወገድ ችሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ በጠቅላላው 10,000 ክፍሎችን የያዙ ሆቴሎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኛትን የባቡር ሐዲድ፣ የመኪና መንገድ ከፍታለች፣ እየከፈተችም ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ አፍሪካ አንድ ፓስፖርት ብቻ ያላት አገር ትሁን የሚል አስተሳሰብ እየመጣ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን ሆቴሎቻችን በብቃትና በብዛት መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉትና እየተገነቡ ያሉትም ተደምረው በቂ አይደሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴሎች ለአንድ ክፍል የሚጠይቁት የኪራይ ዋጋ ከ250 እስከ 350 ዶላር ወይም ከዚህም በላይ ነው፡፡ ክፍያው ከሆቴሎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንዴት ይታያል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ወደፊት የቱሪስቱ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አሁን ከሚከፈለው ዋጋ በጣም ያነሰ ማለትም ወደ 90 እና 80 ዶላር ይወርዳል፡፡ ይህም ለኪሳራ አይዳርጋቸውም፡፡ ምክንያቱም ዋጋው በጣም በተሰቀለበት ሁኔታ አንድ ክፍል የሚያዘው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ያህል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን አፍሪካ በአንድ ፓስፖርት ብቻ የሚለው አስተሳሰብ ዕውን ሲሆን ከውሮፓና ከእስያ አገሮች ከሚመጡት ቱሪስቶች ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፉት አፍሪካውያን ቁጥር ይበዛል፡፡ ገብቶም ስምንትና አሥር ቀን ሊቆይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከብዛት ትርፍ ሊገኝ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የአንዳንድ ሆቴሎች የማኔጅመንት ሥራ በውጭ አገር ሰዎች ሲመራ ይታያል፡፡ ይህንን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለመተካት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- በአገሪቱ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች በሆቴል ማኔጅመንት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶቻችን ቦታ መያዝ ይገባቸዋል፡፡ ዕድሉን ሊያገኙ ይገባል፡፡ በጄኔራል ማኔጀር ደረጃ ምናልባት ልምድን ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ልምዱ እየዳበረ ሲመጣ በኢትዮጵያውያን ሊተካ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ልምድ ያካበቱ ወገኖች ስላሉ ቦታውን መያዝ ይገባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ሆቴሎች እስከ አራትና አምስት የሚሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ማኔጅመንቱን የያዙበት ሁኔታ እንዳለ ይታያል፡፡ የሚከፈላቸው ደመወዝ ደግሞ በጣም ብዙ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ቢተኩ ወጪውም ይቀንሳል፡፡ ወገንም ይጠቀማል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ሆቴሎች በሚሰጡት አገልግሎት (ሰርቪስ) እንዴት ይገመግሟቸዋል?

አቶ ልዑልሰገድ፡- የሆቴሎቻችን አገልግሎት በጣም ደካማ ነው፡፡ ምክንያቱም በሆቴል ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ማስተማር የተጀመረው በቅርቡ በመሆኑ ነው፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት ኮሌጆችም የተሟላ አቅምና ድርጅት የላቸውም፡፡ ትምህርቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው መምህራን መሰጠቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሆቴሎች አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ኮሌጆቹ በቂና ዘመናዊ የማስተማሪያ መጻሕፍት የላቸውም፡፡ ይህም አሁን ዓለም ከደረሰችበት ቴክኖሎጂና ሥልጣኔ ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም፡፡ ይህንን ችግር ለመወጣት በሆቴል ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ ወቅታዊ መጻሕፍት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት ከኢንተርኔት በሚያገኙት መረጃ ነው፡፡ ከኢንተርኔት የሚገኘው መረጃ ደግሞ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንም ገብቶ ሊጽፍ ይችላል፡፡ በተረፈ ሆቴሎች መስፋፋት ይገባቸዋል፡፡ እየተስፋፉም ነው፡፡ በሆቴል ግንባታ ጎረቤት የሆነችውን ኬንያን በልጠናታል፡፡ በሰርቪስ ደረጃ ግን አሁንም ኋላቀር ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴሎቻችን አገልግሎት ላይ ምን መሠራት አለበት?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ሆቴሎቻችን የአገራችን አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ናቸው፡፡ ቱሪስቶች ሆኑ በሥራ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎች በየሆቴሎቹ በየአገሮቻቸው ሲመለሱ ይናገራሉ፡፡ ካልተመቻቸው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሄደን ሆቴሎቻቸው በጣም የወረዱና የሚሰጡት ሁሉ ደካማ ነው፡፡ የሚሰጡትም ከከፈልነውም ጋር የማይመጣጠንና ደረጃውን ያልጠበቀ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ሆቴሎቻችን፣ አምባሳደሮቻችን እንደመሆናቸው መጠን አገልግሎታቸውን፣ እንግዳ አቀባበላቸውን መስተንግዷቸውን በእጅጉ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ቱሪስቶች በአሁኑ ጊዜ ምርጫቸው ጤናማ በሆኑ ምግቦች ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በሳይንስ የተደገፈ፣ የተጠናና ጥራት ያለው ምግብ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኬንያ ያለው ኡታሊ ኮሌጅ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም ታስቦ  ነበር፡፡ ለምን ወደ ኬንያ እንደተሻገረ የሚያውቁት ጉዳይ አለ?

አቶ ልዑልሰገድ፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በሌላው ዓለም በእንግዳ ተቀባይነቷ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጣይቱ ሆቴል መከፈቱም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህንን ግንባር ቀደምትነታችንን ማስመለስ አለብን፡፡ ይህንንም ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ ይታያል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መንግሥት ለሆቴል ግንባታ የሚውሉ መሠረተ ልማቶችን እያስተካከለ ነው፡፡ ከመሠረተ ልማቶችም መካከል አንደኛው ለሆቴል የሚውሉ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረጉ ይገኝበታል፡፡ ከዚህ በተረፈ ኡታሊ ኮሌጅ በአፍሪካ ትልቁ የሆቴል ማኔጅመንት ኮሌጅ ነው፡፡ በደርግ ሥርዓት አዲስ አበባ ውስጥ ለማቋቋም ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም ይውደም!›› የሚል አመለካከት ይከተል ስለነበር ሊሳካ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ኬንያ ማሻገር ግድ ሆኗል፡፡