Skip to main content
x

አራቱ የአማረ አረጋዊ ሽልማቶች

የዛሬ 20 ዓመት (በ1989 ዓ.ም.) በዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋካልቲ፣ በያኔው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ኢንስቲትዩት በጋዜጠኝነት ትምህርት ላይ ሳለን አንድ አሰቃቂና አስደንጋጭ አደጋ ደርሶ ነበር፡፡ በጠላፊዎች ተገዶ አቅጣጫውን እንዲቀይር ከተደረገ በኋላ ነዳጅ በመጨረሱ በኮሞሮስ ደሴት አቅራቢያ ኅዳር 14 ቀን በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ያለቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሟቾች መካከል ኮንጎ ብራዛቪል የሚገኝ ፈረንሣዊ ባለቤቷን ለመጠየቅ በጉዞ ላይ የነበረች የ24 ዓመቷ ያለምዘውድ ሽፈራው ትገኝበታለች፡፡

ኅዳር 25 ቀን 1989 ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብሯ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ከተከናወነ በኋላ፣ ግራ ባጋባ ሁኔታ ወዳጇ በነበረ አንድ የፖሊስ ባልደረባ አማካይነት ከተቀበረበት ወጥቶ በወቅቱ የት እንደደረሰ ስለማይታወቀው አስከሬኗ የከነከናት ጓደኛችን ትነግረኛለች፡፡

በአሁን ወቅት አሜሪካ የምትገኘው ጋዜጠኛ መታሰቢያ አፈወርቅና እኔ የምንተዋወቀው ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ ውስጥ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤትም ከሌሎች አራት የክበቡ ጓደኞቻችን ጋር አብረን ነው የዲፕሎማ ትምህርታችንን ለሁለት ዓመታት ተከታትለን የተመረቅነው፡፡ እዚያ ሳለን አንድ ቀን፣ ‹‹በኮሞሮስ አውሮፕላን አደጋ ከሞቱት መካከል የአንዷ አስከሬን’ኮ ከዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቆ ተወሰደ፤›› ትለኛለች፡፡ ቀጥላም፣ ‹‹መረጃውን ለዕፎይታ ጋዜጣና መጽሔት ዋና አዘጋጅ ለተስፋዬ ገብረአብ ብነግረውም ችላ አለው፤›› ስትለኝ፣ ‹‹ኧረ ለሪፖርተሮች ብንነግራቸው ይሻላል፤›› አልኳትና ካዛንቺዝ ሱፐር ማርኬት ይገኝ ከነበረው ቢሯቸው ሄድን፡፡

መረጃውን አሁን ለማላስታውሰው ባልደረባቸው ነግረን አድራሻችንን ከወሰዱ በኋላ አመስግነው አሰናበቱን፡፡ ከቀናት በኋላ ለመታሰቢያ ተደውሎ ሁለታችንም ሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ እንድንገኝ ተነገረንና ስንሄድ፣ ‹‹አቶ አማረ ነው የፈለጋችሁ›› ተብለን ገባን፡፡ አቶ አማረም መታሰቢያ መነሻ መረጃ ብቻ ለሰጠችበት ትንሽ ነገር የሁለታችንም ትልቅ ሥራ ውጤት መሆኑን አግዝፎ እያደነቀ አመሠገነን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ወስዶ በዚህ ዕድሜያችንና የትምህርት ደረጃችን ያን ለሚያህል የምርመራ ዘገባ መነሻነታችን ሠርተን ያቀረብን ያህል ማበረታቻና ከሥልጠና የማይተናነስ ሙያዊ ልምዱን አካፈለን፡፡ ይህ እንግዲህ የመጀመርያው ሽልማት ነው፡፡ በዚህ ሳይገታ ሁለተኛውን ሽልማት፣ ‹‹ወደ ፋይናንስ ክፍል ጎራ ብላችሁ ሂዱ›› ብሎ አበሰረንና 500 ብር ከፋይናንስ ክፍሉ አሳቀፈን፡፡ የዚያን ጊዜው 500 ብር ዛሬ ከመጠነኛ ግነት ጋር 5,000 ብር በሉት፡፡ ያኔ ኑሮ ርካሽ ነበረና!

(‹‹ከርዕስ ወጣህ›› አትበሉኝና ያኔ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ አንድ. . . አራት በአራት ሜትር የዘነጠ ቤት 100 ብር ባልሞላ ኪራይ ታገኙ ነበር፡፡ ዛሬ ያ በሃያ እጥፍ አድጎ 2,000 ብር ደርሷል፡፡ ‹‹ኤርትራ ውስጥ ጤፍ 1,000 ብር ገባ›› ብለን ‹‹ጉድ! ጉድ!›› ያልንበት የኛ ከ500 ብር በታች የነበረበት ጊዜ ዛሬ 2,000 እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡ በ0.25 ሳንቲም ስንሳፈርበት የነበረው አንበሳ አውቶቡስ ከሁለት ብር በላይ አድጓል)፡፡

ሦስተኛው የአቶ አማረ አረጋዊ ሽልማት፣ አቶ አማረ በስልክ ይሁን በደብዳቤ ለትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር፣ ለአቶ ፀሐዬ ደባልቀው አሳውቀው አቶ ፀሐዬ ቢሯቸው ካስጠሩን በኋላ፣ ‹‹በዚህ ዕድሜያችሁ አኮራችሁን!›› ያሉን ብዙ ሙገሳ ነው፡፡ በአቶ አማረ የተሸለምነውና እኔ በወቅቱ ባልጠቀምበትም መታሰቢያ የተቀበለችው አራተኛው ሽልማታችን ከተመረቅን በኋላ ያለውድድር (በቀጥታ) ሪፖርተር ጋዜጣና መጽሔት ላይ እንድንቀጠር መፍቀድ ነበር፡፡

እንዲህ ዓይነት ሰው መመስገን ብቻ ሳይሆን መሸለምም ያለበት ቢሆንም፣ የአቅምም ሆነ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ውለታውን በልባችን ይዘን ቆይተን ነበር፡፡ በቆይታችን ግን መታሰቢያ በሙያዋ ከእሱ ጋር ስትሠራ ከእንጀራዋና ከህሊናዋ ባሻገር ውለታውም ያስራት ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ከዚያ በፊት በትንሹ አደርግ የነበረውን በጋዜጣው ላይ ተሳትፎ አሳድጌ፣ ረዣዥምና አጫጭር ጽሑፍ ስጽፍ አንድም ቀን ክፍያ ጠይቄ አላውቅም፡፡

ሰሞኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትና ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማኅበር ለአቶ ክፍሌ ወዳጆና ለባለውለታችን ለአቶ አማረ አረጋዊ ለአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ መጠናከርና ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና መስጠቱን ስሰማና ሳነብ ልዩ ስሜት ነው ያደረብኝ፡፡ ይህን ስሜት ያሳደረብኝን የአቶ አማረ ውለታ ለብዙ ሰዎች እስካሁን እነግር የነበረ ቢሆንም፣ ሽልማቱ የበለጠ ሰፋ ላለ ሕዝብ ለማዳረስ ምክንያት ሆነኝ፡፡

እንዲህ ዓይነት ሰዎች ‹‹አደረግን›› ባይሉም ፈጣሪ ቀኑን ጠብቆ ይክሳቸዋል፡፡ በእርግጥ ያደረገ ሰው ቢዘነጋውም የተደረገለት ግን እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ አይረሳውም፡፡ እናም ውለታ የሠራልንን ሰው ከምሥጋና ጀምሮ የአቅማችንን እናድርግና ሰዎቹን ለበለጠ ቸርነት እናዘጋጃቸው፡፡ አቶ አማረም ከ‹‹እንኳን ደስ አለህ!›› ምኞቴ ባሻገር ሽልማቱ ለበለጠ ትጋትና አሳቢነት አደራ አሸክሞሃልና ፈጣሪ እንዲረዳህ እመኝልሃለሁ፡፡

እስክንድር መርሐ ጽድቅ፣ ከአዲስ አበባ