Skip to main content
x
አቢሲኒያ ባንክ ለኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰማ የተላለፈው ውሳኔ ተሻረ

አቢሲኒያ ባንክ ለኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰማ የተላለፈው ውሳኔ ተሻረ

ከአቢሲኒያ ባንክ ይዞታ ላይ ተቀንሶ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ እንዲሰጥ ተላልፎ የነበረው ውሳኔ እንደተሻረለት ተገለጸ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አካባቢ በአቢሲኒያ ባንክ ስም ከተመዘገቡ ሁለት ቦታዎች ውስጥ ከአንደኛው ተቀንሶ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የቢሮ ማስፋፊያ ግንባታ እንዲውልና ይህንንም ቦታ አቢሲኒያ ባንክ እንዲያስረክብ ተወስኖ የነበረው ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ነበር፡፡

ሆኖም ባንኩ ቦታውን በግዥ እንደተረከበና ሕንፃ ለመገንባትም እየተዘጋጀ መሆኑን አሳውቆ፣ ሕጋዊ ባለ ይዞታ መሆኑን የሚያረጋግጡለትን መረጃዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅርቧል፡፡ ባንኩ ያቀረበው ጥያቄ ከወራት በኋላ ተቀባይነት አግኝቶ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰጥ ውሳኔ የተላለፈበት ቦታ እንዳይነካበት ማድረግ መቻሉን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ከአቢሲኒያ ባንክ ይዞታ ተቀንሶ እንዲሰጠው የጠየቀው ቦታ 1,848 ካሬ ሜትር ስፋት ነበረው፡፡ በዚህ ጥያቄ መሠረት የከተማው አስተዳደር ካቢኔ አቢሲኒያ ባንክ ከይዞታው ላይ ቀንሶ እንዲያስረክብና ለፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ እንዲውል ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደነበር ይታወቃል፡፡

ፍላሚንጎ አካባቢ በባንኩ ስም ካሉ ሁለት ይዞታዎች ውስጥ 4,230 ካሬ ሜትር ስፋት ከነበረው ቦታ ላይ ቀንሶ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ተላልፎበት የነበረው አቢሲኒያ ባንክ፣ ውሳኔው እንዳይፀናበት የባንኩ አመራሮች ከአስተዳደሩ ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት መጨረሻ ላይ ተሳክቶላቸው አስረክቡ የተባሉትን ቦታ መልሰው በእጃቸው እንዲገባ ማድረግ ችለዋል፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የ2008 የሒሳብ ዓመት የሥራ ክንውኑን ኅዳር 2009 ዓ.ም. ለባለአክሲዮኖች ባቀረበበት ሪፖርቱ ከይዞታው ላይ ተቀንስ እንዲሰጥ ተብሎ የነበረውን ቦታ በማስመልከት ቦርዱ እያደረገ ያለውን ጥረት እስከማሳወቅ ደርሶ ነበር፡፡

በባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ በኩል ቀርቦ በነበረው በዚሁ ሪፖርት ከይዞታው ተቀንሶ እንዲሰጥ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም፣ አቤቱታውን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስገባቱን ጠቅሷል፡፡

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋርም ተነጋግሮ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ተላልፎ ይሰጥ የተባለው 1,848 ካሬ ሜትር ቦታ ታግዶ እንዲቆይ ጭምር  ጠይቆ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውሳኔው የተሰጠው በካቢኔ ስለሆነ ማስረከብ እንደሚኖርባቸው የተገለጸላቸው በመሆኑ ጉዳዩ እንዳሳሰበው ለባለአክሲዮኖች ተገልጾ ነበር፡፡

ባንኩ ይዞታው እንዳይነካበት የሚያስችለውን ውሳኔ እስካገኘበት ጊዜ ድረስ በቦታው ላይ ለመሥራት አቅዶት የነበረውን ሕንፃ ለመገንባት የሚያስችለውን እንቅስቃሴ አቋርጦ ቆይቷል፡፡

ባንኩ ይዞታው እንደማይነካበት ካረጋገጠ በኋላ በቦታው ላይ ያሰበውን ሕንፃ ለመገንባት ወደሚያስችለው እንቅስቃሴ ገብቷል ተብሏል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ 19 ወለሎች ያሉት ሕንፃ ግንባታ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ከሃያ ዓመታት በላይ ዕድሜ ካላቸው ሦስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በ2009 መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ የደንበኞቹንም ቁጥር 750 ሺሕ በላይ ማድረሱን ገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 801.1 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ58.1 በመቶ ብልጫ አለው፡፡