Skip to main content
x
አካባቢያዊ ስሜትና ጨዋታ ማጭበርበር የደካማው እግር ኳስ አዲሱ በሽታ

አካባቢያዊ ስሜትና ጨዋታ ማጭበርበር የደካማው እግር ኳስ አዲሱ በሽታ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ከሚወቀስበት ደካማ ብቃት ጋር የወረደ የውድድር መንፈስ እያሳየ ለዓመታት መጓዙ ሳያንስ፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደ አዲስ መንሰራፋት የጀመረው አካባቢያዊ ተኮር ‹‹የወንዜ ልጅነት›› እና ጨዋታ ማጭበርበር (ማች ፊክሲንግ) የስፖርቱን ዲሲፕሊን በመጣስ ላይ ይገኛል፡፡ የጨዋታ ማጭበርበር በሌሎች አገሮች በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

እግር ኳሱ ከገባበት የውጤት አዙሪት ቀውስ እንዲወጣ ብዙ በሚነገርበትና  መፍትሔዎች በሚቀርቡበት በአሁኑ ወቅት ብቅ ያለው በአካባቢ የመቧደንና ሲያልፍ ደግሞ በተፅዕኖ በውጤት ማጭበርበር ያልተገባ ቡድን እንዲያልፍ የሚደረገው ሽኩቻ ሥር ከሰደደ ለስፖርቱ ህልውና አደገኛነቱ ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ ከወዲሁ የሥጋት ሐሳብ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ይኼው ጉዳይ በውድድር ዓመቱ በተለይም በፕሪሚየር ሊግ፣ በከፍተኛው (ሱፐር) ሊግና በብሔራዊ ሊግ መርሐ ግብሮች ለመውጣትና ላለመውረድ በሚደረጉ ጨዋታዎች እነዚሁ አካባቢያዊ ስሜቶችና የጨዋታ ማጭበርበሮች በጉልህ የታዩበት ዓመት እንደነበረ ይወሳል፡፡

ውድድሮቹን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለጨዋታ ማጭበርበሮች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና የዲሲፕሊን ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል የዲሲፕሊን መመሪያ ቢኖረውም፣ ያንን የሚያስፈጽምበት አቅሙ በውጪያዊ ተፅዕኖ ደካማ እየሆነ መምጣቱ የሚናገሩ አሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ሊጉ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ገብረ ሥላሴ በውድድሮቹ አካባቢያዊ ስሜትና የጨዋታ ማጭበርበር ምልክቶች ካልሆኑ በተጨባጭ ማስረጃ ቀርቦበት ሕግ ፊት ሊቀርብ የሚችል ችግር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን የጨዋታ ማጭበርበሮች (ማች ፊክሲንግ) ቡድኖችን ያለ ብቃታቸው ውጤት እንዲያገኙ ሆን ተብሎ የሚፈጸም በእግር ኳሱ ቋንቋ ‹‹ወንጀል›› ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞች፣ ተጨዋቾች፣ ሚዲያውና  በአንድም ሆነ በሌላ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት ተጠቃሽ ስለመሆናቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

መንስዔዎቹን አስመልክቶ ኃላፊው፣ በአገሪቱ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች ከአንዱ ሊግ ወደ ሌላው ሊግ ለማደግና ላለመውረድ እንዲሁም ዋንጫና መሰል ጥቅሞችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ የጉዳት መጠኑ ቢለያይም ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ችግሩ እንዴትና በእነማን ይፈጸማል? የሚለው እጅግ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

‹‹ማንም ሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ወንጀል ተደርጎ የሚወሰደውን ድርጊት ማስረጃ በሚቀርብበት አግባብ አይፈጽምም፤›› የሚሉት ኃላፊው፣  ከዚህ በመነሳትም በሊጉ በተለይም በአሁኑ ወቅት በመረጃ ደረጃ ከሚነገረው ውጭ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ድርጊቱን ፈጽሟል በሚባለው አካል ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል በተጨባጭ ማስረጃ የቀረበለት ነገር እንደሌለ ነው የሚያስረዱት፡፡

የሊጉ ዋና ጸሐፊ ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሚደመጠው ቅሬታ በማስረጃ ደረጃ የጎላ ችግር ነው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል ቢናገሩም፣ ሌሎች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ለሚገኘው የእግር ኳሱ ውጤት አካባቢያዊ ስሜትና ጨዋታ ማጭበርበር አንድ ወይም ሁለት ክለቦች ካልሆኑ የተቀሩት የችግሩ ተዋናያኖች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ከነዚህ አስተየያት ሰጪዎች መካከል ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ደጋፊ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን ተሾመ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ አቶ ሰለሞን እግር ኳስ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ስፖርቱ ከመዝናኛነቱ አልፎ ዓለም ላይ ትልቁ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በተለይ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ስፖርቱ ‹‹ነበር›› ከሚለው ታሪኩ በስተቀር የነበረውን እንኳን በነበረበት ማስቀጠል ተስኖት የንትርክና የውዝግብ መድረክ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ውድቀት በዋናነት ተጠያቂው ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሆኖ ክለቦችና የክለብ አመራሮች፣ ክልሎች፣ ሙያተኞች፣ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች ድርሻ ድርሻቸውን እንደሚወስዱም ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌሎች ሙያተኞች የአቶ ሰለሞንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ እግር ኳሱ ከዚህ ችግሩ ሳይላቀቅ በአካባቢያዊ ስሜት ጉትቻና የጨዋታ ማጭበርበር (ማች ፊክሲንግ) መጤ በሽታ የባሰ እንዲሽመደመድ መንገዱ ተመቻችቶለታል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

በ2008 የውድድር ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ጅማ አባቡና የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ነኝ ይላል፡፡ ክለቡ ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስገባው ደብዳቤ በውድድር ዓመቱ እስከ 30ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከነበረበት ሥጋት በመነሳት በተለይም የቡድኖች የነጥብ መጣጣል አሳሳቢ ሆኖበት እንደነበር ይገልጻል፡፡

እንደ ጅማ አባቡና አቤቱታ ከሆነ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከተጋጣሚዎቻቸው ‹‹በማች ፊክሲንግ›› ነጥብ ሊያሰባስቡ ይችላሉ በሚል በደብዳቤ ቁጥር አቡሰ/-372/2009 በቀን 10/10/2009 ዓ.ም. ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ብሎ ማስታወቁን ያትታል፡፡ ለጅማ አባቡና ሥጋት ከነበሩት ሁለቱ ክለቦች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ በ30ኛው የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ0 ተሸንፎ መውረዱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብን በተመለከተ ግን፣ የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ተጨዋች ለሆነው ኤፍሬም ዘካሪያስ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የነጥብ ማስለወጫ ገንዘብ መስጠቱን፣ ይህንኑ የሐዋሳ ክለብ የቦርድ አመራሮች በክትትል ደርሰውበት በፖሊሲ ቁጥጥር ሥር አውለው ጉዳዩን ካጣሩ በኋላ ተጨዋቹን 25 ሺሕ ብርና በማንኛውም የእግር ኳስ ጨዋታ እንዳይሳተፍ መወሰኑን እንዳረጋገጠ ይገልጻል፡፡

ይህንኑ አስመልክቶ የሊጉ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን፣ በፕሪሚየር ሊጉ 30ኛ የጨዋታ መርሐ ግብር በሐዋሳ፣ ሐዋሳ ከተማና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ያደረጉትን ጨዋታ ተከትሎ በማስረጃ ሳይሆን በመረጃ ደረጃ የሚነገሩ ቅሬታዎች እንዳሉ፣ ሆኖም ያንን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጦ ለፌዴሬሽኑ ያሳወቀ አካል እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኃላፊው አሁንም ቢሆን ቅሬታው በማስረጃ ተደግፎ መቅረብ ከቻለ ፌዴሬሽኑ በዲሲፕሊን መመሪያው መሠረት ዕርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይል ጭምር አስረድተዋል፡፡

የጅማ አባቡና ክለብ ግን ይህ በእግር ኳሱ እየታየ ያለው የጨዋታ ማጭበርበር ሒደት ስፖርቱን ከማቀጨጩም ባሻገር በተለይ እንደ ጅማ አባቡና የመሳሰሉ በሕዝብ እየተደገፉ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ብቅ የሚሉ ታዳጊ ክለቦችን ለማጥፋት የተነጣጠረ ዒላማ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ክለቡ ‹‹በእንደዚህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ተሰማርቶ የሚገኝ አካል›› በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ በአንቀጽ 70 እንደተጠቀሰው ከሆነ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ራሱ ወይም ሌላ ሦስተኛ ወገን በመገፋፋትና በማነሳሳት በፌዴሬሽኑ አካል (አባል)፣ ለዳኞች፣ ለታዛቢዎች፣ ለተጨዋቾች ወይም ለአመራሮች ስጦታ ወይም መደለያ ለመስጠት ቃል የገባ ወይም የሰጠ ወይም ለመስጠት የሞከረ እንደሆነ 30 ሺሕ ብር ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም ከማንኛውም እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴዎች ሦስት ዓመት ያህል እንደሚታገድ ይደነግጋል፤›› የሚለውን የዲሲፕሊን መመሪያ በአቤቱታው አካቷል፡፡ ከዚህ የዲሲፕሊን ዕርምጃ በተጨማሪ በአንቀጽ 45 በዳይ ክለቦች ውጤታቸው የሚቀነስበት ሁኔታ እንዳለ፣ የሚቀነሰውን ነጥብ በተመለከተም በዲሲፕሊን መመሪያው አንቀጽ 47 በግልጽ መቀመጡን ጭምር የጅማ አባቡና እግር ኳስ ክለብ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በዲሲፕሊን መመርያው አንቀጽ 48 መሠረትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ በ30ኛው የፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ መርሐ ግብር ያደረገው ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ግንዛቤ ተወስዶ፣ ጅማ አባቡና በ2010 የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ቆይታው ተረጋግጦለት ዝግጅት የሚጀምርበት ሁኔታ በፌዴሬሽኑ በኩል እንዲመቻችለትም ጠይቋል፡፡

በእግር ኳሱ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከጨዋታ ማጭበርበር ባልተናነሰ አካባቢያዊ ስሜት አስመልክቶ የብሔራዊ ሊግ ኮሚቴው አቶ ሰለሞን፣ ከሁለት የተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ክለቦች የየራሳቸው ደጋፊዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተቀረውም ዓለም ያለና የሚኖር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚስተዋለው ሁኔታ ትክክለኛና ስፖርታዊ ጨዋነትን የተላበሰ ለመሆኑ ጥርጣሬ ያላቸውን መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ደጋፊ አቶ ሰለሞን ተሾመም ተመሳሳይ ስሜት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ደጋፊው በተለይ ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ የሚታመኑ የጨዋታ ማጭበርበር ሁኔታዎች በአደባባይ ባይሆንም እየተፈጸሙ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ‹‹ማስረጃ›› የሚለው ማምለጫ እንጂ ችግሩ የሚመነጨው ከራሱ ከተቋሙ ባህላዊ አሠራር እንደሆነም ነው የሚያስረዱት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ፣ ከዘንድሮው ውድድሮች አንዳንዶቹ ጨዋታዎች ከመደረጋቸው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በምን ዓይነት ውጤት እንደሚጠናቀቁ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ውጤቱም በዚሁ መሠረት ሲጠናቀቅም ታይቷል ይላሉ፡፡

ይኼ ደግሞ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የሚያስተዳድሩት አካላት የሙያው ሰዎች አለመሆናቸውን ጭምር የሚያሳይ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡